Wednesday, September 21, 2016

ጥልቅ ተሃድሶ “በመበስበስ” ጀመረ!

September 21,2016
opdo-new

የኢህአዴግ አካል የሆነው ኦህዴድ “ጥልቅ ተሃድሶውን” “በመበስበስ” መጀመሩን የኢህአዴግ ንብረትና የንግድ ተቋም የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ያሰራጨው ዜና አመልክቷል፡፡ ዜናውን ተከትሎ “በጥልቀት የመታደሱ” ጉዳይ “በመበስበስ” መጀመሩ አመላካች ነው ተብሏል፡፡ በሌሎች ክልሎችም የመበስበስ መጠናቸው የጠለቀና ለህወሃት ከመታመን ውጪ ተስፋ በሌላቸው ታማኞች በመተካት ሹምሽር እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡
የኦህዴድ ምክትል ሆነው የተሾሙት ጄኔራል፣ ዶክተር፣ አቶ፣ አሁን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ብቅ ያሉት የኦሮሞን ብሔር የማይወክሉ የትግራይ ተወላጅ እንዶኑ በስፋት የሚነገርላቸው ሻሸመኔ ያደጉት ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “ወርቅነህ ገበየሁ ለምን ወደ ትራንስፖርት ሚኒስትርነት?” በሚል ርዕስ (July 6, 2013) ስለ ወርቅነህ ገበየሁ “ነገዎ” መጠነኛ ዘገባ ባቀረበበት ወቅት የሚከተለው ሪፖርት አድርጎ ነበር፤

“የወርቅነህ ገበየሁ “ነገዎ” ሹመት

የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ የትራንስፖርት ሚኒስትር ስለመደረጋቸው ከሚቀርቡት ምክንያቶች መካከል ቀደም ሲል ለረዥም ዓመታት ከደህንነቱና ከሽብር መከላለከል ግብረ ሃይል ጋር የነበራቸው ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑ በግንባር ቀደም ይገለጻል። ለጎልጉል አስተያየት የሰጡ እንደሚሉት ኢህአዴግ የትራንስፖርቱን ዘርፍ በቅርብ መቆጣጠር ይፈልጋል።
በምርጫ 97 ወቅት ለታየው ህዝባዊ መነቃቃት የትራንስፖርቱ ዘርፍ፣ በተለይም የታክሲና የግል ማመላለሻዎች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ ያስታውሳሉ። ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች እስከወዲያኛው እንዳይታሰቡ ለማድረግ ዘርፉን ከደህንነቱ ጋር በቅርብ ማጠላለፍ፣ ኢህአዴግ በከፍተኛ ደረጃ እየገነባሁ ነው የሚላቸውን መንገዶች፣ የስልክና የብሮድ ባንድ መስመሮች፣ የባቡር ትራንስፖርት በቅርብ ለመቆጣጠርና የቁጥጥሩ ሰንሰለት ውስጥ ለማስገባት አቶ ወርቅነህ ሁነኛ ሰው ሆነው መገኘታቸውን እነዚሁ ክፍሎች ይናገራሉ።
አዲሱ ቴሌን ጨምሮ የትራንስፖርት ዘርፉን ከደህንነቱ መዋቅር ጋር በቀላሉ ለማያያዝ ልምዳቸውና የመረቡ አባል ሆነው መቆየታቸው የትራንስፖርት ሚኒስትር ያደረጋቸው አቶ ወርቅነህ፣ የጄኔራልነት ማዕረጋቸው ከሳቸው ጋር ይቆይ ወይም ይነሳ የተገለጸ ነገር እንደሌለ የጠቆሙት ክፍሎች፣ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የህወሃት አመራሮች አቶ ወርቅነህን በታማኝነት መድበው የተቀበሏቸው ሰው ስለመሆናቸው ጥርጥር የላቸውም።
አቶ ወርቅነህ ታማኝ ስለመሆናቸው፣ በዚሁ ታማኝነታቸው ስልጣናቸውን ሳይጠቀሙ በፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተርነት ለረዥም ጊዜ መቆታቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው አቶ ወርቅነህ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሰባት ሚኒስትር መስሪያቤቶች ተውጣጥቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው የ”ደህንነት ኮር” ውስጥ አባል እንደነበሩ ይናገራሉ። ይህንን ኮር በአዲስ እየተዋቀረ ስለሆነ አቶ ወርቅነህ ወደ ትራንስፖርት ሚኒስትርነት የተዛወሩት ከደህንነቱ የኮር መዋቅር ውስጥ እንዲወጡ ስለተፈለገ መሆኑን ይገልጻሉ።”
ቀደም ሲል ከተዘረዘሩት የሥልጣን መጠሪያዎች ወርቅነህ ገበየሁ “ነገዎ” አሁን የኦህዴድ ሊቀመንበር ከሆኑት ለማ መገርሳ ጋር በአንድነት በማታው የትምህርት ክፍለጊዜ የዶ/ር መረራ ጉዲና ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ከዚህም በላይ ወርቅነህ ገበየሁ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር (የጄኔራል ማዕረግ በህወሃት ተሰጥቷቸው እንደ ሲቪል “አቶ” ተብለው) በሚሠሩበት ወቅት ለማ መገርሣ የኦሮሚያን ደኅንነት በመምራት አብረዋቸው ይሠሩ ነበር፡፡
ከህወሃት የተሰጣቸውን የሚኒስትርነት ሥራ ሳይለቁ፤ ከፓርቲና ደኅንነት ሥራቸውም ሳይነቃነቁ ትምህርት ተምረው “ዶክተር” ለመባል እንደበቁ የሚነገርላቸው ወርቅነህ ገበየሁ “ነገዎ” ተማሩበት በተባለው የትምህርት ተቋም ስማቸው “ወርቅነህ ገበየሁ ወልደኪዳን” ተብሎ ከነፎቷቸው ተመዝግቧል፡፡
ከግራ ወደቀኝ ፓስተር ገመቺስ ቡባ፣ ጌታቸው ረዳ፣ የኦሮሞዎች መገደል ትክክል ነው ያለ አዲሱ ገብረእግዚአብሔር እና ለማ መገርሳ
ከግራ ወደቀኝ ፓስተር ገመቺስ ቡባ፣ ጌታቸው ረዳ፣ የኦሮሞዎች መገደል ትክክል ነው ያለ አዲሱ ገብረእግዚአብሔር እና ለማ መገርሳ
በኢህአዴግ አሠራር የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት የሚሆኑት ዛሬ ፋና ይፋ ያደረጋቸው አዲሱ የኦህዴድ ሊቀመንበር (የኦሮሚያ ምክርቤት አፈጉባዔ) ለማ መገርሣ በደኅንነት ውስጥ ከፍተኛ ታማኝነት ያተረፉና በሚያቋቸው ሰዎችና የሥራ ባልደረቦች “ተንበርካኪ የመቀሌ ልጅ” እየተባሉ የሚጠሩ መሆናቸውን በቅርብ የሚያቋቸው ይመሰክራሉ፡፡
ተሰናባቾቹ ሙክታር ከዲርና አስቴር ማሞ ራሳቸውን ከኃላፊነት አንስተዋል በሚል በሁለቱ የደኅንነት ማሽኖች መተካታቸው ያፈነገጠውን ኦህዴድ ወደ ሃዲዱ ስለመመለሱ ማረጋገጫ አይሰጥም፡፡
በሼህ መሃመድ አላሙዲን ባልደረቦችና ታዛዦች አማካኝነት አባዱላን ገልብጠው የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት የሆኑት ሙክታር ዛሬ ራሳቸውን ከሥልጣን አነሱ ቢባልም ከመሾማቸው ጊዜ ጀምሮ ካድሬው ሙሉ በሙሉ የሚቀበላቸው ሰው አልነበሩም፡፡
በጅማ ንጹሃን በታረዱነበት የህወሃት ወንጀል እጃቸው እንዳለበት በሥፋት የሚነገርላቸው ሙክታር እጅግ ውብ የሆኑት ባለቤታቸው ሚሊዮኔር መሆናቸው የኢህአዴግ ወፍጮ ሊቀረጥፋቸው ታሳቢ ካደረጋቸው መካከል የቅድሚያ ተሰላፊ እንደሚሆኑ ይነገራል፡፡
በባለቤታቸው የህወሃት አባል የሆኑት አስቴር ማሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ azeb and asterሚኒስትር የሚል ረጅም ሥልጣን ከተሰጣቸው ጊዜ ጀምሮ ብቃት የላቸውም፣ ዓቅም ያንሳቸዋል፣ ለቦታው አይመጥኑም፣ ወዘተ በሚል ተቃውሞ በግምገማ ላይ ሲቀርብባቸው ህወሃት/ኢህአዴግ “ጥሪ አይቀበልም” ሲል ሰንብቷል፡፡ ይልቁንም ዕድገት እየሰጠ የኦህዴድ መሪ አድረጋቸው፡፡ በሰባራ ጋሪ “ሽምጥ እየጋለብኩኝ” ነው ሲል የነበረው ኦህዴድ ራሱ አንኮታኩቶ ያጠፋውን የመልካም አስተዳደር፤ መሠረታዊ የችግር ቁልፍ አድርጎ በመውሰድ የአስቴር ማሞን ከሥልጣን መውረድ በ11ኛው ሰዓት ላይ ተቀብሎታል፡፡
የአስቴር ማሞን ከኃላፊነት መነሳት የተቀበለው ህወሃት “በጥልቅ ተሃድሶ” ምሎ ጥልቅ ተሃድሶውን በግፍ ከሸተተው መጋዘኑ ውስጥ ታማኞቹ አውጥቶ በመሾም የመታደሱን ቁርጠኝነት አሳይቷል፡፡ በዚህ የሥልጣን ሹም ሽር የቀለዱ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሉት የኢህአዴግ የጥልቅ ተሃድሶ “ዳግም መበስበስ” ነው ብለውታል፡፡ አክለውም በመበስበስ የተጀመረው ይህ “ጥልቅ ተሃድሶ” ህወሃትን ወደ ትክክለኛ ጥልቅ ተወርውሮ የሚገባበትን ፍጥነት ቁልቁል የሚያዳልጥ አድርጎ ያፋጥነዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የተወሰደ

No comments: