Wednesday, March 4, 2015

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሰማያዊ ፓርቲን የቅስቀሳ መልዕክት ‹‹አላስተላልፍም›› ብሎ መለሰ

March 4 ,2015
• ‹‹ቀድሞውንም እንዳያማ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው ነው›› አቶ ስለሽ ፈይሳ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) የሰማያዊ ፓርቲን የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ‹‹እንደገና አስተካክሎ ካልላከ ለማስተላለፍ እቸገራለሁ›› በሚል መመለሱን ለፓርቲው በፃፈው ደብዳቤ አስታወቀ፡፡
ኢብኮ አላስተላልፍም ብሎ ለመመለሱ በዋነኛነት የጠቀሰው ምክንያት ‹‹ለማጀቢያነት ለተጠቀማችሁት ሙዚቃ የባለመብቶቹን ፈቃድ ስለመኖሩ ማረጋገጫ አላመጣችሁም›› የሚል ነው፡፡ ኢብኮ ሌሎች ጉድለቶችን ያልጠቀሰ ቢሆንም በጥቅሉ ‹‹የምርጫ ህጉን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ፣ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ህጎች ወይንም ማንኛውም ህግ የሚተላለፍ መሆኑን በቂ ምክንያት ካለው መልዕክቱን አላስተላልፍም የማለት መብት አለው....›› በሲል ፓርቲው የላከውን የቅስቀሳ መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሚቸገር ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል የፓርቲው የምርጫ ጉዳይ ኃላፊና ም/ሊቀመንበር አቶ ስለሽ ፈይሳ ገዥው ፓርቲ የግለሰብና የፓርቲ ስም እያጠፋ፣ የመደራጀት፣ ሀሰብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብትን በጣሰ መልኩ ቅስቀሳ እያደረገ እንደሆነ ገልጸው ሰማያዊ ፕሮግራሙ ላይ ያስቀመጣቸውን ሀሳቦች እንዲቀይር እየተጠየቀ መሆኑ ሚዲያዎቹ ለገዥው ፓርቲ ያላቸውን ወገንተኝነት በድጋሜ ያጋለጠ ነው ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
‹‹የመንግስት ሚዲያዎች ተግባር ቀድሞውንም እንዳያማ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ነው፡፡ ቢያንስ በዚህ ጊዜ እንኳን ፍትሓዊ መሆን ነበረባቸው›› ያሉት አቶ ስለሽ የመንግስት የሚባሉት ሚዲያዎች በወንጀል ሊያስከስስ የሚችለውን የኢህአዴግ ቅስቀሳ ያለ ምንም ምርመራ እያስተላለፉ ሰማያዊ ላይ ህገ ወጥ ቅድመ ምርመራቸውን ቀጥለዋል ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ኤፍ ኤም 96.3 ሰማያዊ ፓርቲ ለቅስቀሳ በላከው መልዕክት ላይ በማጀቢያነት የተጠቀመበት ሙዚቃ የባለ መብቱን ፈቃድ አላገኘም በሚልና መልዕክቱ ላይ የተጠቃለሉትን የፓርቲው አቋሞች እንዲያስተካክል በሚል የቅስቀሳ መልዕክቱን መመለሱ ይታወሳል፡፡

No comments: