February 7/2014
ጥቂት አሳቦች በሞገደኛው ተክሌ ወሥርጉተ ሥላሴ ጽሑፎች ላይ (ክፍል-፩-) በዲ/ን ኒቆዲሞስ ዕርቅ ሁንይ
ጥቂት አሳቦች በሞገደኛው ተክሌ ወሥርጉተ ሥላሴ ጽሑፎች ላይ (ክፍል-፩-) በዲ/ን ኒቆዲሞስ ዕርቅ ሁንይ
ሥርጉተ ሥላሴ የተባሉ ጸሐፊ በተለያዩ ጊዜያት የሚጽፏቸውን በአብዛኛው ታሪካዊ የሆኑ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርስ አዘል፣ በኃይለኛው አገራዊ/ኢትዮጵያዊ ዘዬ፣ ትውፊትና ባህል የተጫነው የሚመስለውንና፤ (ይህን ለማረጋገጥ የሚወድ ጸሐፊዋ ‹‹ኢትዮጵያዊነት የሚነበብ መንፈስ ነው›› በሚል ርእስ ያስነበቡትንና ‹‹የኢትዮጵያዊነትህን መንፈስ በቅጡ ካልተረዳኸውና ካልተቀበልከው ‘ጉግ ማንጉግ’ የኾነ አንካሳ መንፈስ ይጨፍርብኻል፡፡›› እስከ ማለት የደረሱበትን፣ በኢትዮጵያዊነት ወኔ፣ ስሜትና ረቂቅ መንፈስ ፈጽሞ የሰከረውን መጣጥፋቸውን ማየቱ የሚበቃው መስለኛል፡፡) እንዲሁም ምክርና ትችት ዘመም የኾኑ፣ እንዲያም ሲል ‹‹የኢትዮጵያዊነት ወኔና ስሜት›› በእጅጉ ጎልቶ የወጣበትንና ያየለበትን መጣጥፎቻቸውን ለማንበብ ዕድሉ ገጥሞኛል፡፡
ይህችን ‹‹ዘመም›› የምትል አብዮተኛ ቃል ያለ ምክንያት አይደለም እዚህ ጋር የሰነቀርኳት፡፡ የትናንትናው ትንታግና አብዮተኛው ያ ‹‹ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪ›› የኾነው ትውልድ ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!›› ብሎ ያቀጣጠለው የለውጥ አብዮት፣ ወደ ለየለት አሰቃቂና አስፈሪ ነውጥና ፍጅት ተለውጦ፣ በሂደትም ‹‹አብዮት የገዛ ልጆቿን እንኳን ሳይቀር ትበላለች!›› ወደሚል አስፈሪ ፃረ ሞትነት ተቀይሮ ‹‹በግራና ቀኝ ዘመም›› በሚል ምድሪቱን ‹‹አኬል ዳማ/የደም ምድር›› እንድትሆን ያደረገበትን ያን የእምዬ ኢትዮጵያን የጨለማና የሰቆቃ ዘመንዋን እግር መንገዴን ለማዘከር ጭምር ነው፡፡
ያችን በማኅፀንዋ አብራክ ክፋይ፣ በገዛ ልጆቿ የአብዮት ደም ጅረት ታጥባና ተነክራ፣ በኀዘንና በብርቱ ሰቆቃ መንፈሷ ደቆና ቅስሟ ተሰብሮ፣ የኀዘን ከል ለብሳ፣ ከዘመን የተኳረፈችውን ኢትዮጵያን፣ የዛን ጊዜው የቀ.ኃ.ሥ የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበሩት አንጋፋው ምሁርና ዛሬም እንኳን በእርጅናቸው ዘመን፣ በአብዛኛው የጥላቻና የመለያየት ነጋሪት ከሚጎሰምበት ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ለመፋታት አልሆንልህ ያላቸው፣ ጉምቱው ፖለቲከኛ ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ፣ በዩኒቨርስቲ ተማሪነታቸው ዘመን በቋጠሯት ግጥማቸው/ስንኛቸው የዛን ዘመኗን እምዬ ኢትዮጵያን እንዲህ ነበር የገለጽዋት፡
-
ይኽው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣
ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ፡፡
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት፣
የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት፡፡
-
ይኽው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣
ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ፡፡
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት፣
የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት፡፡
ውድ አንባቢዎቼ ያው እንግዲህ ዘንድሮ አብዮቱ ዐርባ ዘመንም እየሞላውም አይደል እንዴ?! እስከ ጥፋቱና ልማቱም ቢሆን የዚህ የዛሬው ትውልድ አባል የኾንኩ እኔ፣ ያ ትውልድ ለውድ እናት አገሩና ለወገኑ ከነበረው ፍቅርና መቆርቆር የተነሣ በእንባው፣ በላቡና በደሙ የከፈለውን ያን ግዙፍና ታላቅ መሥዋዕትነት የማደንቅ ብቻ ሳልሆን የውለታው ባለ ዕዳ ነኝም ብዬ ነው የማስበው፡፡ እናም እንዲህ እግር መንገዴንም ቢሆን ያን ትንግረተኛ ትውልድ ላነሳሳው፣ ልዘክረው ወደድኹ፡፡
በነገራችን ላይ እናንተ በዲያስፖራ የምትገኙ የዛ ትውልድና የታሪኩ ባለቤቶች የዛን ትንታግ ትውልድ የለውጥ እንቅስቃሴውን ለመዘከር አንዳንች ነገር አላሰባችሁም እንዴ! እስቲ ከጥላቻ ፖለቲካው፣ ከመለያየቱ፣ በጎሪጥ ከመተያየቱና ከመፈራረዱ ለአፍታ ወጣ በሉና እነዛን ደማቸውን ለሕዝቦችህ ፍትሕና ዕኩልነት፣ ለሰው ልጆች መብትና ክብር መስፈን፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን መሆን ሲሉ በየጎዳናው፣ በየጋራ ሸንተረሩና ተራራው ያፈሰሱትን የትውልዳችሁን/የጓዶቻችሁን ታሪክና ውለታ ለእኔና ለትውልዴ በፍቅር፣ በቅንነትና በበጎነት መንፈስ ልታስተላልፉን/ልታሳውቁን ሞክሩ፣ እሹም፡፡
‹‹ንግባኤከ ኀበ ቅድመ ነገር/ወደቀደመው ነገር እንመለስ›› እንዲል መጽሐፉ፡፡ ለዚህ ለዛሬው መጣጥፌ ዐብይ ምክንያት የኾኑኝ በኢትዮጵያዊነት ሕያው መንፈስና ቅናት እየነደዱና እየተቃጠሉ ያሉት ጸሐፊዋ ሥርጉተ ሥላሴ፣ የትናንትናው ወይም የዛሬው የእኔው ትውልድ አባል ይሁን አይሁኑ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ስለ ጉምቱ ብዕረኛው አቶ ተክለ ሚካኤልም ቢሆን እንዲሁ፡፡’
ለማንኛውም ግን ዋና አነሳሴ እነዚህን ብዕርተኞች በትናንትናውም ሆነ በዛሬው የትውልድ ተርታ ለማሰለፍ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ታሪኩን በደሙ የጻፈውንና ያጻፈውን የትናንትናውን ትውልድ የትግል እንቅስቃሴውን ለመዘከርና ውለታውንም ለማሰብ ወይም ለማሳሰብ አይደለም፡፡ ግና በዚህ ጽሑፌ ሥርጉተ ሥላሴና አቶ ተክለ ሚካኤል በተለያዩ ጊዜያት ያስነበቧቸው መጣጥፎቻቸው አንዳንች የቅናት ስሜትን ስላጫረብኝ እኔም የበኩሌን ዕዳ ለመወጣት በማለት ነው ብዕሬን በድፍረት ያነሣሁት፡፡
የቀድሞው የኢሳት ቴሌቪዥን ባልደረባ የነበሩት ሞገደኛው አቶ ተክሌ በተለያዩ አገራዊ ፖለቲካዊ አጀንዳዎችና ክርክሮች ዙሪያ የሚያንሸርሽሯቸውን ጽሑፎች እከታተላለሁ፣ አደንቃለሁም፡፡ አቶ ተክሌ ከሰሞኑን ባስነበቡን መጣጥፋቸው በወጣቱ የፖለቲካ ተንታኝ ጀዋር መሐመድና ደጋፊዎቹ የተነሳውን የሰሞኑን ሚጢጢዬ አብዮት አስመልክቶ ኢህአዴግ ከሚያራምደው የብሔር ፖለቲካ አንፃርና በተቃራኒው ከአንድነት ኃይሎች አቋም ጋር በማዛመድ ‹‹ተወደደም ተጠላ የአንድነት ኃይሎች ለብሔር ፖለቲካ ሰፊ የመጫወቻ ሜዳ ለመስጠት ባለመቻላቸው በኢህአዴግ ተበልጠዋል፡፡
እናም እነ ጃዋርም ኾነ ለረጅም ዓመታት የኦሮሞን የመገንጠል ጥያቄ በብርቱ ሲያቀነቀኑ የነበሩ የኦሮሞ ብሔርተኞች፣ አንጋፋውን የኦነግ ታጋይ እነ ሌንጮን እንኳን ሳይቀሩ ቢያንስ ቢያንስ በመርህ ደረጃ ያን መብታቸውን በሚያከብርላቸውና በራሳቸው ቋንቋ የሚያስተዳድሩትን ክልል በሰጣቸው በኢህአዴግ ጉያ ውስጥ ለመወሸቅ እያኮበኮቡ ነው፡፡›› የሚል አንድምታ ያለው ጽሑፍን አስነብበውናል፡፡
የዲያስፖራውን ፖለቲካ በአለፍ ገደም በመተቸትና የሰሞኑን የኦሮሞ ብሔርተኞች ፀረ-ምኒልክ ዘመቻ አስመልክቶ በአንድነትና በብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች መካከል የተነሣውን፣ በአዲስ አበባውያኑ አራዳዎች የፌስ ቡክ አድማቂዎች ዘንድ ‹‹አቧራው ጨሰ›› የተተረተበትን የሰሞኑን ክስተት በማስመልከት አቶ ተክሌ ያሰፈሩትን አሳብ እህታችን ሥርጉተ ሥላሴ የሚመች ብቻ ሳይሆን የማይቀበሉትም እንደኾነ በሰፊው አትተው ጽፈዋል፣ ተጨባጭ ያሏቸውን ምክንያቶችንም በመደርደር ለመከራከር ሞክረዋል ፡፡
የዲያስፖራውን ፖለቲካ በአለፍ ገደም በመተቸትና የሰሞኑን የኦሮሞ ብሔርተኞች ፀረ-ምኒልክ ዘመቻ አስመልክቶ በአንድነትና በብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች መካከል የተነሣውን፣ በአዲስ አበባውያኑ አራዳዎች የፌስ ቡክ አድማቂዎች ዘንድ ‹‹አቧራው ጨሰ›› የተተረተበትን የሰሞኑን ክስተት በማስመልከት አቶ ተክሌ ያሰፈሩትን አሳብ እህታችን ሥርጉተ ሥላሴ የሚመች ብቻ ሳይሆን የማይቀበሉትም እንደኾነ በሰፊው አትተው ጽፈዋል፣ ተጨባጭ ያሏቸውን ምክንያቶችንም በመደርደር ለመከራከር ሞክረዋል ፡፡
የእነዚህ ብዕረኞች ፍቅር፣ ቅንነትና ጨዋነት የተሞላው የአሳብ ልውውጣቸውና በምክንያት የተደገፈ ክርክራቸውም ይበል ሚያሰኝና አልፎ አልፎ በየድረ ገጹ፣ ጋዜጣውና መጽሔቶች ላይ ባልተገራ ብዕራቸውና ሰብእናቸው ብቅ እያሉ አሳብን በአሳብ ከማሸነፍ ይልቅ ስድብና ጥላቻ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ፣ ፉከራና ቀረርቶ ለሚቀናቸውና፣ እንዲያም ሲል የስም ማጥፋት ዘመቻ (character assassination) ውስጥ ለሚዶሉ ጸሐፍቶቻችን ጥሩ ምሳሌና አርዓያዎች ናቸው ብዬ አስባለኹ፡፡
በመሠረቱ የእነዚህ ክቡራን ጸሐፊዎች የወንድማችን የአቶ ተክሌና የእህታችን የሥርጉተ ሥላሴ የሰሞኑን የአሳብ ልውውጥና ሙግት በአብዛኛው ትኩረቱን ያደረገው የብሔር ፖለቲካን በሚያራግቡና በተቃራኒው ደግሞ አንድነትን በሚያራምዱ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞቻችን ዘንድ ያለውን ክፍተት፣ ልዩነትና ርቀት ለማሳየት፣ ለመገምገምና ለመተንተን የሞከረ ነው፡፡ ለዚህ የአሳብ ሙግት ዋና መነሻና ማድመቂያ የሆነው ደግሞ ከሰሞኑን ወጣቱ ከያኒ ቴዲ አፍሮ የዓፄ ምኒልክን የግዛት ማስፋፋት ወረራ አስመልክቶ በአንድ በአገር ውስጥ በሚታተም መጽሔት ሰጠው የተባለው ቃለ መጠይቅ በበርካታ የኦሮሞ ተወላጆች/ኦሮሞ ብሔርተኞች ዘንድ የቀሰቀሰው ብርቱ ቁጣ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም የካናዳው ተክሌ ‹‹የኛ ነገር፡- የተሸነፈ ርእዮተ አገርና ገፊ ፖለቲካ›› በሚል ርእስ ባስነበቡት ጽሑፋቸው የአንድነት ኃይሉ ከተቸከለበት የአንዲት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ወጥቶ ብሔርተኝነትን ለሚያቀነቅኑ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ዕድል የሚሰጥ የፖለቲካ አጀንዳን በመቅረፅ ምቹ የመጫወቻ ሜዳ ለማዘጋጀት እስካልቻሉና እስካልደፈሩ ድረስ መጪው ጊዜ ለአንድነት አቀንቃኞች ከአሁን በበለጠ አዳጋችና ፈታኝ እንደሚሆንባቸው ምሳሌዎችን ጭምር በመጥቀስ ለመተንተን ሞክሯል፡፡
በአንፃሩም ሥርጉተ ሥላሴ ‹‹የማረተ ማጭድ ሸክም በሐቅ ጭብጥ ይረታል›› በሚል ርእስ ያስነበቡን ጽሑፋቸውን፣ በእነደ አቶ ተክሌ ያሉ ‹‹ኢትዮጵያዊነትንና የብሔር ፖለቲካን በተመለከተ›› የሚያራምዷቸው ጠንጋራ አመለካከቶች ውለው አድረው የትውልዱን ጤናማ መንፈስ እንዳይበክሉት ቀድሞ መከላከል ይገባል በሚል ጽኑና ቅን መንፈስ ተነሳስተው እንደጻፉት ይነግሩናል፡፡
ጸሐፊዋ ‹‹ኢትዮጵያዊነት የሚነበብ መንፈስ ነው›› በሚለው ጽሑፋቸውም ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ጸንቶ፣ አብርቶና ደምቆ የሚቆይ ረቂቅና ሕያው መንፈስ መሆኑን ለማስረዳት ረጅም ርቀት በመጓዝ የብሔር ፖለቲካ ያደረሰብንን ስብራትና ለወደፊቱም የተሸከመውን ክፉ አደጋ ለማሳየት ደክመዋል፡፡
ጸሐፊዋ በዚህ ስሜትም ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያዊነትን ከሚዋጋ ስሜት ያድነን!›› ዘንድም ተማፅነውልናል፡፡ በዚህ መካከል ደግሞ ኢትዮጵያዊነት የዘላላም ቅርሳችንና ቃል ኪዳናችን ነው፡፡ በሚሉና በተቃራኒው ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊነት ሳንወደውና ሳንፈቅደው እንደ ኮሶ ተበጥብጦ በግድ እያነገፈገፈን የተጋትነው፣ እየቀፈፈንና እንደ አባ ጨጓሬ እየኮሰኮሰን የተደረበብን ማንነት ብለው በሚሉ ሰዎች ዘንድ እየተካሔደ ያለው አስጥ አገባ ከሰሞኑን ዳግም በአዲስ ኃይልና ጉልበት ተጠናክሮ የኢትዮጵያንና የዲያስፖራን የፖለቲካ ሰማይ ክፉኛ እያወደው፣ እያጠነውና እየናጠው ይገኛል፡፡
የባለፈው ሰሞን በእነ ጀዋርና ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ብለው በሚያቀነቅንቱ መካከል በማኅበራዊ ድረ ገጾች፣ በመጽሔቶችና በጋዜጦች፣ በየድረ ገጾቹ፣ በየፓል ቶኩ የሰማነው ጉድ፣ የጦር አውርድ ቀረርቶና ሽለላ፣ ስድብና ዛቻ፣ ጽንፈኝነት፣ መራር የሆነ ጥላቻና ቂም የሞላባቸው ሰቅጣጭ ሙግቶች የነገይቱን ኢትዮጵያ ህልውና እንደ ሕዝብም ደግሞ በሰላምና በመቀባበል ለመኖር ተስፋችን የደበዘዘ መስሎ እንዲታየኝ ነው ያደረገኝ፡፡
ቢቻለን፣ ብንወድና ብንፈቅድ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በአንድነት ለመኖር ካልሆነም ደግሞ ተለያይተንም ቢሆን በመልካም ጉርብትና ለመቀጠል የሚያስችለን ፍቅር፣ ቅንነትና በጎነት ምን ያህል እየራቁን እንደሔዱ እንዳስተውል አስችሎኛል፡፡
የረጅም ዘመናት ታሪካችን እንደሚነግረን ትናንትናም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራው ግዛት ውስጥ ያሉ ሕዝቦች የሚያስተሳስሯቸው ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እውነታዎች በርካታ ናቸው፡፡
እስቲ ኤርትራ ሂዱ ማነው ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ ሕዝብ ያልተዋለደ፣ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም ፣ ወደ ምስራቅም ወደ ምዕራብም ተጓዙ ይሄ ሕዝብ በደምና በአጥንት የተሳሰረ ሕዝብ ነው፡፡ እስቲ ወሎን ተመልከቱ ሃይማኖቱ ሳይገድበው ተዋዶና ተዋልዶ የሚኖር ታላቅ ሕዝብ ያለበት አገር/ምድር ነው፤ ወይስ የነበረበት ልበል ይሆን እንዴ!? ‹‹መሐመድ ኤልያስ፣ ትዕግሥት ሁሴን›› ተብለው የሚጠሩ አያሌ ሰዎች ዛሬም ድረስ ያጋጥማችኋል፡፡ የሃይማኖት ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ግና ፍቅር የተባለ አንዳንች ኃያልና ጽኑ አሸናፊ መንፈስ ሰንሰለት ሆኖ ያስተሳሰራቸው ሕዝቦች!!
በቅርቡ በሀገረ አሜሪካ አገር ሕይወታቸው ያለፈው ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕ/ር ታደሰ ታምራት ለዶክትሬት ድግሪ ድርሳናቸው የሚሆናቸውን ጥናትና ምርምር ለማድረግ ከሚማሩበት የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተነስተው የውቦች አገር ወሎ ውስጥ ተገኝተው ነበር፡፡
ፕ/ር ታደሰ ለዚሁ ጥናታቸው ወደምታስፈልጋቸው አንዲት ጥንታዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያንን ለመጎብኘት እንደተዘጋጁ በዛች የገጠር ቤ/ን የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠባቂ የሆነ አንድ ግለሰብ የቤተ ክርስቲያኒቱን በር ከከፈተላቸው በኋላ፣ እኔ ሙሰሊም ነኝ እርስዎ ግን መግባት ይችላሉ ብሎ ወደ ውስጥ ይገቡ ዘንድ እንደፈቀደላቸው ተማሪያቸው የኾኑትና በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ታሪክ መምህሬ የሆኑት የአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲው ዶ/ር ውዱ ጣፈጠ ይህን የአስተማሪያቸውን አስደናቂና ልብ የሚነካ ገጠመኝ ሲናገሩ ሰምቼቸዋለኹ፡፡
እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር፣ እንዲህ ዓይነቱን መተማመን፣ እንዲህ ዓይነቱን በጎነትና ቅንነት፣ እንዲህ ዓይነቱን ዓለም ሁሉ ምሳሌ ያደረገውን አብሮነት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቅዱስ ቁርአን፣ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ነቢዮ መሐመድ፣ ከግሪክ ጸሐፊዎችና ፈላስፎች እስከ አውሮጳ አሳሾችና ተጓዦች በውብ ቀለም የከተቡለትንና የተናገሩለትን ይህን ውብ የሆነውን አንድነታችንና ውብ ፍቅራችን ዛሬ በነበር ልንዘክረው በቋፍ ላይ ያለን ነው የምንመስለው፡፡
እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር፣ እንዲህ ዓይነቱን መተማመን፣ እንዲህ ዓይነቱን በጎነትና ቅንነት፣ እንዲህ ዓይነቱን ዓለም ሁሉ ምሳሌ ያደረገውን አብሮነት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቅዱስ ቁርአን፣ ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ነቢዮ መሐመድ፣ ከግሪክ ጸሐፊዎችና ፈላስፎች እስከ አውሮጳ አሳሾችና ተጓዦች በውብ ቀለም የከተቡለትንና የተናገሩለትን ይህን ውብ የሆነውን አንድነታችንና ውብ ፍቅራችን ዛሬ በነበር ልንዘክረው በቋፍ ላይ ያለን ነው የምንመስለው፡፡
እዚህም ቤት እዛም ቤት የሚሰማው ድምፅ ደግ አይመስልም፣ የበቀል ሰይፎች በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ተመዘው እያፏጩ ያሉ ነው የሚመስለው፡፡ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነትና አብሮነት የሚሰብኩንና ወደ ዕርቅ መንገድ ይዘውን የሚጓዙ የዘመኑ ነቢያትም አድራሻቸው ወዴት እንደሆነ ጠፍቶብናል፡፡
የሕዝብ እንባ፣ ብሶት፣ ዋይታና እሮሮ እንቅልፍ፣ ዕረፍት የሚነሳቸው፣ ለፍትሕና ለእውነት ጥብቅና የቆሙ፣ በሕዝባቸው ፍቅር ፈፅመው የነደዱ፣ ‹‹ይህን ሕዝብ በምድረ በዳ በከንቱ ከምታጠፋው እኔ ከሕይወት መዝገብ እስከ ዘላለሙ ደምስሰኝ!›› የሚሉ በነፍሳቸው የተወራረዱ የዘመናችን ሙሴዎች፣ ፍቅርንና ዕርቅን የሚሰብኩ ፖለቲከኞቻችን፣ መሪዎቻችን አድራሻቸው ወዴየት ይሆን!?
የትናንትናም ሆነ ዛሬው መንገዳችን በአያሌው ፍቅርን የተራበ፣ ይቅርታን የተራቆተ፣ አንድ መሆንን የገፋና የተጠየፈ ነው፡፡ ይህ ዛሬ የደረስንበት የአገራችን የፖለቲካ የታሪክ ሒደት ውጥንቅጥና ቀውስ በአብዛኛው የትናንትና ውጤት ነው፡፡ እናም የኢትዮጵያችን የዘመናዊ ፖለቲካ ጅማሮ መንገዱ በደም የተመረቀ፣ በደም የጨቀየ፣ በደም የተፈፀመ፣ የደም መንገድ፣ የደም ጎዳና ነው፡፡ የብዙዎች ወገኖቻችን ደም እንደ ጅረት የጎረፈበትና፡-
‹‹የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፣
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ፡፡›› ተብሎ አሰቃቂ ሙሾ የተወረደበትን የታሪካችንን አብዛኛውን ምዕራፍ በደም ያስዋበ፣ በደም ያወየበ የፖለቲካ ታሪክ ነው ያለን፡፡ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራም ሆነ በወያኔ በኩል፣ በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር፣ በኢሀአፓና በመኢሶን፣ በኢህአዴግና በተቃዋሚው ስም ጎራ ለይቶ የተላለቀው ሕዝብ የአንድ ምድር ልጆች እንደሆኑ ነው የማስበው፡፡
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ፡፡›› ተብሎ አሰቃቂ ሙሾ የተወረደበትን የታሪካችንን አብዛኛውን ምዕራፍ በደም ያስዋበ፣ በደም ያወየበ የፖለቲካ ታሪክ ነው ያለን፡፡ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራም ሆነ በወያኔ በኩል፣ በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር፣ በኢሀአፓና በመኢሶን፣ በኢህአዴግና በተቃዋሚው ስም ጎራ ለይቶ የተላለቀው ሕዝብ የአንድ ምድር ልጆች እንደሆኑ ነው የማስበው፡፡
የትናንትናው እንዳይበቃን ዛሬም ደግሞ አስፈሪውና አስደንጋጩ ነገር ደግሞ እዚህም ቤት እዛም ቤት የሚጎሰመው ነጋሪት፣ የሚነፋው መለከት ሞትን የሚያውጅ፣ ጥፋትን የደገሰ መሆኑ ነው፡፡ ዛሬም በትናንትና ታሪካችን ላይ ተቸክለን ለቂም በቀል የምንፈላለግ፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከአንድነትና ኅብረት ይልቅ መለያየት፣ ከሰላም ድምፅ ይልቅ የጦርነት ነጋሪት ወኔያችን የሚያሞቀው፣ የሚቀሰቅሰው ሕዝቦች የመሆናችን ምሥጢር ነው፡፡
አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው መንግሥትም፣ በአገራችንም ሆነ በውጭ ያሉት የሚበዙት በተቃዋሚ ስም የተደራጁ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና የፖለቲከኞቻችን መንፈስ ገና ወደ ዕርቅ መንገድ ወደ ፍቅር የልዕልና ከፍታ ሊወጣ፣ ሊያድግና ሊመነደግ እንዳልተቻለው ደግመን ደጋግመን ዐይተናል፣ ታዝበናል፡፡
ከሰሞኑን በአፍቃሪ ምኒልከና በፀረ ምኒልካውያኑ መካከል የነበረው ስድብ፣ ውርጅብኝና የጦር አውርድ ዘመቻና የቃላት ጦርነት ገና በትናንትና ታሪካችን የሆኑትን መልካም ክስተቶች በምስጋና ተቀብለን፣ በአንፃሩ ደግሞ በታሪካችን የሆኑትን ስህተቶች አምነን ተቀብለን ይቅርታ ለመጠየቅ የሚሸነፍ ቅን መንፈስ እንደሌለን ያሳየን ነው ማለት ይቻላል፡፡ እናም ገና ወደ አንድነት፣ ወደ ዕርቅና ፍቅር መንገድ ለመድረስ ረጅም መንገድ በፊታችን ተዘርግቶ ይጠብቀናል፡፡ ይህን መንገድ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም ጭምር ተጉዘው ሊያሳዩን የሚችሉ ባለ ራእይና ቁርጠኛ የሆኑ ፖለቲከኞች፣ ከልባቸው የትግል ሰዎች የሆኑ፣ ሰው የሆኑ ሰዎች፣ የእውነትና የፍትሕ ጠበቃዎች በዚህ ዘመን የግድ ያስፈልጉናል፡፡
በቅርቡ በሞት የተለዩን የአፍሪካ ብርቅዬ ልጅ፣ የፀረ አፓርታይድ ታጋይና ነፃነት አርበኛ፣ የሰላምና የፍትሕ ጠበቃ፣ የይቅርታ ጀግና የሆኑት ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ/ማዲባ እ.ኤ.አ በ1990 በአይርላንድ ፓርላማ አባላት መካከል ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፡-
በቅርቡ በሞት የተለዩን የአፍሪካ ብርቅዬ ልጅ፣ የፀረ አፓርታይድ ታጋይና ነፃነት አርበኛ፣ የሰላምና የፍትሕ ጠበቃ፣ የይቅርታ ጀግና የሆኑት ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ/ማዲባ እ.ኤ.አ በ1990 በአይርላንድ ፓርላማ አባላት መካከል ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፡-
‹‹We are in struggle because we value LIFE and LOVE all humanity!›› ያው ፍቅር ለሚገባቸው፣ ፍቅር ለሚያግባባቸው የማዲባ መልእክት ግልፅ እንደሆነ አስባለሁ፡፡ ፍቅር … ሰላም … ካላግባባን፣ ካላቀራረበን እንግዲህ ምን ያግባባን እንደሆነ እኔጃ፡፡ ግን … ግን … እናንተዬ በሰላማዊም መንገድ ይሁን ነፍጥ አንስተን እንታገላለን የምንል ሰዎች የትግላችን የመጨረሻ ግቡ ምንድን ይሆን?!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
nikodimos.wise7@gmail.com