Desember 26,2016
ዘርይሁን ሹመቴ
በለንደን የሚገኘው ሌጋተም ኢንስቲትዩት (Legatum Institute) በሚያደርገው አመታዊ የጥናትና የምርምር ፕሮግራሙ በአለማችን የሚገኙ እጅግ ሃብታምና ለኑሮ አመቺ አገሮችን እንዲሁም በተቃራኒው እጅግ አደገኛ የሆኑትንም ዝርዝር ይፋ ያደርጓል።
ይህ ተቋም ዘጠኝ (9) ቁልፍ መስፈርቶችን በመጠቀም በ2016 እኤአ የአገራትን ብልጽግና እና ለኑሮ ተሰማሚነታቸውን በጥናትና ምርምር በተደገፈ ሁኔታ አቅርቧል። እነዚህ መስፈርቶች የሚያካትቱት የኢኮኖሚ ጥራትን፣ የንግድ አከባቢን፣ አስተዳደርን፣ ትምህርትን፣ ጤናን፣ ደህንነትና ጸጥታን፣ የግለሰብ ነጻነትን፣ ማህበራዊ ሃብትን እንዲሁም ተፈጥሮአዊ አካባቢን እንደሆነ ተቋሙ አስፍሯል።
ሰሜን ኮሪያና በጦርነት የምትታመሰው ሶሪያ መረጃ ለመሰብሰብ እጅግ አስቸጋሪ ስለሆኑ ይህ ተቋም በጥናቱና ምርምሩ ለማካተት እንዳልቻለ ገልጿል። በአጠቃላይ 149 አገራት በዚህ ጥናት እንደተካተቱ ተገልጿል።
በወያኔ አስተዳደር የምትገኘው ኢትዮጵያም በዚሁ የጥናትና የምርምር ተቋም አመዳደብ መሰረት በጣም አደገኛ፣ እጅግ ደሃ፣ ደስታ የራቃትና ለጤናም አደገኛ ከሚባሉት አገሮች መካከል 19ኛውን ደረጃ ይዛ ትገኛለች። እንደ ጥናቱ ተቋም መሰረት ኢትዮጵያ በተወሰኑ መስፈርቶች መሻሻል ብታሳይም በትምህርት በኩል እጅግ ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገቧን አስፍሯል። በተጨማሪም በስራ ፈጠራና ለስራ አመቺ ሁኔታን በማቅረብም ዝቅተኛ ውጤት አስመዝግባለች።
የመን፣ አፍጋኒስታንና ሴንትራል አፍሪቃ ሪፐፕሊክ በዚሁ ጥናት ተቋም መሰረት ለመኖር እጅግ አስቸጋሪና አደገኛ ከሚባሉት አገሮች ከ1ኛ እስከ3ኛ ያለውን ደረጃ በቅደም ተከተል ይዘዋል። በ2014 እኤአ በኢቦላ በሽታ ከ5 ሺህ በላይ ህዝቧን ያጣችው ላይቤሪያ በዚሁ በሽታ ምክንያት ከኢትዮጵያ አንድ ደረጃ ዝቅ ብላ 18ኛ ላይ ትገኛለች።