Sunday, January 17, 2016

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማሪያም ደሳለኝ

January 16, 2016
በዛልኝ ፀጋው ከአዲስ አበባ
ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣
ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት በአሁን ጊዜ በብዙ ኢትዮጲያዊያን ላይ የሚፈጸመውን ግድያ፣ ግፍ፣ መከራና ሰቆቃ በመመልከት ከምንም ነገር በላይ የአገራችን የኢትዮጲያ ቀጣይ  ሁኔታ ስላስጨነቀኝ ነው።
Hailemariam-PM1-300x282አቶ ኃይለማሪያም፣ እርስዎ ወደስልጣን  ሲወጡ አገራችን የተሻለ አስተዳደር ታገኛለች ብለው ብዙ ተስፋ አድርገው ከነበሩት ኢትዮጲያዊያን መካከል አንዱ ነኝ። ለዚህም ምክንያቶች ነበሩኝ። አንደኛ እርሰዎ እግዚአብሄርን የሚፈሩ ሰው ነዎት ሲባል በመስማቴ፣ ሁለተኛ በትምህርት ባገኙት ችሎታዎ በራሰዎ የሚተማመኑና የሚያምኑበትን ለመናገር ወደኋላ አይሉም ብየ በማሰቤ፣ ሶስተኛ በትምህርት ቤት በነበሩበት ዘመንዎ ያዩት የነበረው የተማሪወች እንቅስቃሴ ለአጠቃላይ ህዝብ መብት መከበር እንጅ በዘር ላይ ያልተመሰረተ ስለነበር፣ እርሰወም የዘር ፖለቲካን እንደዋና መርህ አይቀበሉም ብየ መገመቴ፣ አራተኛ እነ አቶ መለስ የሚቃወሟቸውን ሁሉ፣ የረሳቸውን ጓደኞች ሳይቀር፣ እያጠፉ ለሰው ህይወት ብዙም ሳይጨነቁ ወደ ስልጣን ሲመጡ፣ እርሰዎ ግን ወደ ስልጣን አመጣጠዎ የተለየ ነው ብየ በመገመቴ ነው። ይህ አመለካከቴ ከመጠን በላይ በጎ ነገር ከመጠበቅ የተነሳ መሆኑን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረዳሁ መጣሁ።
እኔ ተስፋ ሳደርግ፤ ብዙ ኢትዮጲያዊያን ግን የእርሰዎ ጠቅላይ ሚንስቴር መሆን፣ ስልጣኑንና፣ ጦሩን፣ የስለላ ድርጅቱንና  ኢኮኖሚውን ህውሃት እስከተቆጣጠረው ድረስ፣ ለውጥ እንደማያመጡ ሲናገሩ ነበር። በትክክልም እርሰዎ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዳሉ መገንዘብ ቻልኩ። ሆኖም ግን አሁንም አገሪቱን ወደ ከፋና የማትወጣበት ችግር ወስጥ ከመግባቷ በፊት፣ በታሪክም ተወቃሽ እንዳይሆኑ፣ ህዝቡን ይዘው ማድረግ የሚችሉትን መጠቆም እወዳለሁ።
የወያኔ መንግስት ባመጣው በዘር ከፋፍሎ አስተዳደር፣ በገዥው መንግስት መሪነት፣  በህዝቡ መካከል ይዘራ የነበረው የዘርና የጥላቻ ፖለቲካ፣  ከሃያ አራት አመታት በላይ በዘለቀው ገደብ የሌሌው የመብት ረገጣና የንጹሃን ግድያ ጋር ባንድ ላይ ሆኖ  በፈጠረው ብሶት፣ የህዝብ አመጽ ገንፍሎ እየመጣ ነው። ይህም የአገራችንን የወደፊት እጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አስቸጋሪ አድርጎታል። እርስወ በዘር ፖለቲካና ትእቢት በተሞሉና፣ የህዝብ ሃብት በሚዘርፉ ወያኔወች ተተብትበው በመታሰርዎ ኢትዮጲያን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መምራት እንደማይችሉ ኢትዮጲያዊ ሁሉ ያውቃል። ሆኖም ግን አገራችንን ከከፋ ጥፋት ለማዳን አሁንም ማድረግ የሚችሏቸው ነገሮች አሉ፣
  1. የህዝቡን ስቃይና መከራ ለማየት ህሊናዎን ይክፈቱ፣
  2. የመብት ጥያቄ የሚያነሱትን ኢትዮጲያዊያን ጠላት አድርጎ መመልከትዎን አቁመው ለአገራቸው እንደሚያሰቡና በአገራቸው ጉዳይ እኩል ባለድርሻ መሆናቸውን ይቀበሉ፣
  3. የመንግስት ሃይል በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የሚያደርገውን ዘግናኝ ግድያ ባስቸኳይ ያስቁሙ፣
  4. የታሰሩትን የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች በመፍታት፣ ሁሉንም ለአገሪቱ ባለድርሻ የሆኑትን የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት መሪወች፣ የዜጎች ወይም ማህበራዊ ድርጅቶች መሪዎችና ያአገር ሽማግሌወች የሚካፈሉበት አገር አቀፍ ጉባኤ በመጥራት፣ ጉልበት ሳይሆን የህግ የበላይነት የሚመራበት ሁሉን ኢትዮጲያዊ የሚወክል መንግስት እንዲቋቋም ይርዱ፣
  5. ይህን ማድረግ የማያስችለወት ሁኔታ ካለ ግን፣ ለኢትዮጲያ ህዝብ ችግረዎን በግልጽ አሳውቀው ስልጣንወን ይልቀቁ። ይህን በማድረግ ለእግዚአብሄር፣ ለኢትዮጲያና ለኢትዮጲያ ህዝብ መታመነዎን ያሳያሉ።
ይህን መልዕክቴን በቀና ልቦና እንደሚያዩልኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

በዛልኝ ፀጋው
አዲስ አበባ

No comments: