February 20,2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው ከመሰማቱ በፊት በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ፖለቲከኞች ተፈተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲደረግ በማሰብ ራሳቸውን ለማግለል መወሰናቸው፣ አገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢ ችግር ያመለክታል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ ከፊቱ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ተደቅነውበታል፡፡ አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሁሉንም ወገኖች በሚያግባባ ሰው መተካትና የተሻለ ምኅዳር መፍጠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እንደካሁን ቀደሙ በነበረው ሁኔታ የሚያስቀጥል አምጥቶ ቀውሱን ማባባስ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ካለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ ጀምሮ አልበርድ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ እልባት የሚፈልግለት ከሆነ፣ በመጀመርያ በውስጡ የሚታየውን ሽኩቻ በማቆም ለሕዝብ ፍላጎት ራሱን ማስገዛት አለበት፡፡ ለአገር የሚያስብ ማንኛውም ኃይል በዚህ ወቅት ለሕዝብ ፍላጎት መንበርከክ ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱ ሁኔታ እያደር ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነና አሳሳቢ ችግሮች ተጋርጠው፣ የፖለቲካ ቁማር ውስጥ ገብቶ ሒሳብ ለማወራረድ መሞከር የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ይከተዋል፡፡ የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች አገርን ከቀውስ ለመታደግ ሲሉ በዚህ ቀውጢ ጊዜ በአንድነት ቢቆሙ ይበጃል፡፡ ሰላማዊና ሥልጡን የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣው በመተናነቅ ሳይሆን፣ ለሕዝብ በሚበጅ ሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡
አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣውና ብዙዎችን የሚያስማማው የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ነው፡፡ ይህ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ደግሞ ኢሕአዴግን ጨምሮ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚገናኙበት ሁሉን አካታች መድረክ ሲፈጠር ነው፡፡ ይህ መድረክ እንዲፈጠር የተለያዩ ተግባራት መከናወን ሲኖርባቸው፣ ከምንም ነገር በላይ ከትርምስና ከውድመት የፀዳ ከባቢ መፈጠር አለበት፡፡ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር ስለሌለ በመተማመን መንፈስ አገሪቱን ከገባችበት አረንቋ ማውጣትና የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት ምኅዳር ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ በመሆኑ፣ ሕግና ሥርዓትን ሳያዛንፉ መነጋገርና መደራደር የሚቻል ከሆነ ሥጋት ወደ ተስፋ ይለወጣል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ዕርምጃ መውሰድ እያቃተው፣ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች ተጨናግፈዋል፡፡ አገሪቱ እዚህ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከመውደቋ በፊትም ሆነ በተከታታይ ባጋጠሙ አስከፊ ችግሮች ምክንያት፣ የሕዝብን ፍላጎት ያገናዘቡ ዕርምጃዎች ባለመወሰዳቸው ብቻ ከቀውስ ወደ ቀውስ መሸጋገር ልማድ ሆኗል፡፡ ከእንግዲህ ዓይነቱ አዘቅት ውስጥ በቶሎ አለመውጣት የአገር ህልውናን ይፈታተናል፡፡ ውጤቱም አስከፊ ይሆናል፡፡
ያጋጣሙ ዙሪያ ገብ ችግሮችን በመሸሽ ወይም በማድበስበስ ዙሪያውን ከመዞር፣ ከእውነታው ጋር ተጋፍጦ ለሕዝብ ፍላጎት ሸብረክ ማለት ያስከብራል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ በፖለቲካው ሠፈር ውስጥ ያሉ ወገኖች በሙሉ ሊገነዘቡት የሚገባው፣ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን ጎዳና መምረጥ ቀውሱን ያባብሰዋል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ አገር መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ግራ በገባት ወቅት ሥልጣንን ብቻ ማዕከል ያደረገ ንትርክና ንዝንዝ ለማንም አይጠቅምም፡፡ አሁን የሚፈለገው አገሪቱን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ጎትቶ ማውጣት የሚችል ነው፡፡ በሐሳብ ልዩነት በማመን የተሻለ አቅምና ሐሳብ ያለውን ዕድል በመስጠት ዴሞክራሲያዊ ዓውድ መፍጠር የግድ ነው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳሩን በአስቸኳይ በመክፈትና ከአጉል ጀብደኝነት በመላቀቅ፣ በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሒደት እንዲጀመር ሁሉም ወገን ጠጠር ማቀበል እንዲችል ዕድሉ ይመቻች፡፡ ነውጥ በተነሳ ቁጥር ሕይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ የሚቀጠልበት ቀውስ ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ በተቻለ መጠን ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ሊያስማማ የሚችል አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ ለሥልጣን ከሚደረገው ሽኩቻና መራኮት የምትበልጠው አገር ናት፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላው ቢቀር በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከሠፈሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተጨማሪ፣ አስተዋዩና ጨዋው ሕዝብ ውስጥ ለዘመናት የኖሩት የጋራ መስተጋብሮች ለመነጋገርና ለመደማመጥ ትልቅ ፋይዳ ነበራቸው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን አንዱን አሳዳጅ ሌላውን ተሳዳጅ፣ አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ የሚያደርገው አታካችና አሰልቺ የዘመናት የልሂቃን ችግር እዚህ አድርሶናል፡፡ በሕግ የበላይነትና በማኅበረሰቡ ውስጥ በዳበሩ መልካም እሴቶች አማካይነት በመታገዝ ቅራኔዎችን ከመከመር ይልቅ፣ ለጋራ መግባባት ቢሠራ ኖሮ ኢትዮጵያ የት በደረሰች ነበር፡፡ መልካም አጋጣሚዎች እንደ ዋዛ አልፈው በቀውስ ማዕበል እየተገፉ ውሳኔዎች ማስተላለፍ የተጀመረው በዚህ ምክንያት መሆኑን ከልብ መቀበል የግድ ነው፡፡ አሁን ኳሷ በዋነኝነት ያለችው በኢሕአዴግ እጅ ላይ ቢሆንም፣ በፖለቲካው ጎራ ውስጥ ያሉ ኃይሎችም የራሳቸው ሚና አላቸው፡፡ ይኼንን ሚና በአግባቡ መወጣት የሚቻለው ግን ቅድሚያ ለአገር ሰላምና ደኅንነት ማሰብ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ወጀቡን ተከትሎ በዕቅድ የማይመራ ነውጥን ማበረታታትና ለትርምስ የሚረዱ ግብዓቶችን ማቅረብ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋትና ራስን ለቁጭት መዳረግ ነው፡፡ ፖለቲካ የሚፈልገው ብልኃትና ጥንቃቄን እንጂ መደነባበርን አይደለም፡፡
‹‹ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል፣ ሞኝ ልጅ ግን ምሳው እራቱ ይሆናል፤›› እንደሚባለው፣ ከዜሮ ድምር ፖለቲካ በመላቀቅ ለሰጥቶ መቀበል መርህ የሚረዳ ምኅዳር እንዲፈጠር ራስን ማዘጋጀት የወቅቱ ዋነኛ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝብን ለአመፅ የሚጋብዙ ውሳኔዎች ትርፋቸው ሞትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በሰከነ መንፈስ ማሰብ ያለባቸው፣ የሚፈለገው ነገር ሊሳካ የሚችለው አገር ስትኖር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከወቅቱ የሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚመጣን ውሳኔ ማሳለፍ ያለበትና ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ማዘጋጀት የሚኖርበት፣ ከምንም ነገር በላይ የሆነችው አገር ሰላም እንድትሆን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠር የሚያግዙ የፖለቲካ ውሳኔዎች ታክለው ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ወደሚረዳ ምርጫ መንገድ ሲመቻች፣ የአገር ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ አማራጮች ሳይጠፉና ለዚህም የሚረዱ ፖለቲካዊ ማዕቀፎች ባሉበት በዚህ ዘመን፣ የኃይል ተግባር ውስጥ በመግባት አገር ማተራመስና ሕዝብን ማመሰቃቀል በታሪክ ፊት ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ አገርን አውድሞ ሙሾ ማውረድ የሞኝ እንጂ የብልህ ተግባር አይደለም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አማካይነት በነፃነት በሚደረግ ምርጫ እንጂ፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች በሚሆንበት ኢዴሞክራሲያዊ አሠራር አይደለም፡፡ የአገሪቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በእኩልነት የሚወዳደሩበት ሕጋዊ ማዕቀፍ በማበጀትና ብልሹ አሠራሮችን በማስተካከል፣ በዚህች ታሪካዊት አገር ዴሞክራሲ ነፍስ እንዲዘራ መደረግ አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት በስኬት ስሙ የሚነሳው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የበለጠ መመንደግ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን እንኳን ኢኮኖሚው የአገሪቱ ዕጣ ፈንታም አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ዘለቄታዊ መሆን የሚችለው በሰላማዊና በአሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ሒደት ነው፡፡ የወቅቱን ችግር ለመግታት ብቻ ዒላማ ያደረገ ውሳኔ የሚተላለፍ ከሆነ ግን ሰላም እንደ ኅብስተ መና ይርቃል፡፡ ከዚህ ቀደም አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ስትገባ የአሥር ወራት አስቸኳይ ጊዜ ቢታወጅም ዘላቂ ሰላም ግን አልመጣም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ችግሮች ተፈጥረው በርካቶች ሞቱ፣ ለአካል ጉዳት ተዳረጉ፣ ተፈናቀሉ፡፡ አሁንም ካጋጠመው ቀውስ በዘላቂነት ለመላቀቅ አስተማማኝ ሰላም ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ አገሪቱ ከገጠማት ፈተና ለመታደግ የሚቻለው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያግባባ ውሳኔ ላይ መድረስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ሲጣል ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ይሁንታውን ሲገልጽ ነው፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር ስለሌለ ለሕዝብ ፍላጎት መታዘዝ ያስከብራል!