Wednesday, September 26, 2018

የነአቶ በቀለ ገርባ መግለጫ አድራሻው ለማን ነው?

September 26, 2018
ከቀሲስ መልአኩ ባወቀ ( ሎስ አንጀለስ)

እነ አቶ በቀለ ገርባ የሰጡትን መግለጫ አነበብኩ፤ የአንዳንዶችንም አስተያየት ሰማሁ። ምንም እንኳ አላማው ያነጣጠረው በኢሳትና በግንቦት ሰባት ላይ ቢሆንም እነርሱ የፈሩት፥ ግንቦት ሰባትን ወይም ኢሳትን አይደለም። የፍርሃታቸው አድራሻ ለምኒልክ ቤተ መንግሥት ለነ ዶክተር ዓቢይ ነው ።

እነ አቶ በቀለ ገርባ የፈሩት ካልጠበቁት አቅጣጫ የወጣውን የኢትዮጵያዊነት እሳት ነው። ይህ አዲሱ የለውጥ አየር፥ ለብዙ ዓመታት የተለፋበትን የዘር ፖለቲካን የዶግ አመድ እያደረገው ነው። ( የዘር ፖለቲካ የሕዝቦችን ማንነት የሚያስከብር ሳይሆን አንድን ዘር ከሌላው እያስበለጠ ጥላቻን የሚሰብክ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሃያ ሰባት ዓመት አይቶታል።)

ተቃውሞው ለግንቦት ሰባት ይምሰል እንጂ፥ ተቃውሞው ለነዶ/ር ዓቢይ ነው ብለናል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ተቃውሞ ስለፈሩ ለጊዜው ዋናውን ዒላማ ወደጎን ትተውታል። የሚቀጥለው የአመጽ አጀንዳቸው ይህ እንደሆነ በግልጥ ካሳዩን ግን ቀናት ተቆጥሯል። ለምን? መልሱ ግልጥ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ሥር እየሰደደ ነው። ኢትዮጵያዊነት፥ የኦሮሞ ልጆች በሆኑት በነ ዓቢይ አህመድና ለማ መገርሳ መሪነት በመላው ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ እየሠረጸ ነው። ሕዝባችን ባለፉት ወራት፥ እንጨት እንጨት የሚለውን የማርክሲስም ዲስኩር አሽቀንጥሮ የጣለ፥ ከጥላቻ የጸዳ፥ የቆሰለውን ልባችንን የሚያክም የይቅርታና የአንድነት ቃላት ከመሪዎቹ አድምጦአል። ንግግራቸውን በእንባ አድምጦአል። ብሔራቸውን ሳይጠይቅ በአንድ ልብ ደግፎአቸዋል። ዓቢይ፥ዓቢይ፥ ዓቢይ፥ ለማ፥ ለማ፥ ለማ ብሎ ጮዃል።

ይህ ሲባል ግን ለውጡ ፈተና የለውም ማለት አይደለም። በጎሣ ጥላቻ ላይ የፖለቲካ ቀሳቸውን የተከሉ ኃይላት፥ በመውተርተር የንጹሐን ወግኖቻችንን ደም በየአቅጣጫው በሶማሌ፥ በኦሮሚያ፥ በቤኒሻንጉል፥ በአዋሳ፥ ወዘተ . . . የኦሮሞን የአማራን፥ የጋሞን፥የወላይታን እና የሌሎችንም ወገኖቻችንን ደም አፍስሰዋል። ሚሊየኖች ከሶማሌ እና ከሌሎችም ክልሎች ተፈናቅለዋል። ወደ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉትን የኦሮሞና የጌዴዎ ወገኖቻችንን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።

ይህም ሆኖ ሳለ፥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን « ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው» በሚሉት መሪዎቹ ባየው የፍቅር መልእክት ውስጥ፥ የሞቱትን ወገኖቹን እየቀበረ፥ የተፈናቀሉትን እየረዳና እንባውን እየጠረገ፥ ከመሪዎቹ ባገኘው የመደመርና የአንድነት መንፈስ ተስፋን ሰንቋል።

ኢትዮጵያዊነት ኦሮሞነትን ወይም አማራነትን መደምሰስ አይደለም። ሁሉም ሕዝብ ክቡር ነው ። አንዱ በአንዱ አይደለዝም፥ አይሰረዝም። ኢትዮጵያዊነት ግን ኢትዮጵያዊነት፥ ተከባብሮ፥ ተሳስቦ መኖር ነው። ከመግደል ይልቅ መወያየት፥ ከመጣል ይል ማንሳትን መለማመድ ነው። ይህን የለውጥ ኃይሎቹ አሳይተውናል። ነጻ ሚዲያ፥ ነጻ አስተሳሰብ፥ ከሁሉ በላይ ፍቅር እና ይቅር ባይነትን ተመልክተናል።

ይህ ለእነ አቶ በቀለ ገርባ አልተዋጠላቸውም። ከምኒልክ ቤተ መንግሥት እየወጣ ያለው መልእክት፥ እነርሱ ከያዙት ጽንፈኛ ከሆነው የዘረኝነትና አሁን ማንሳት ከማልፈልገው አጀንዳ አንጻር፥ የትም የማያላውሳቸው ነው። ለውጡን የተደመሩት፥ የለውጡ ኃይል ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የሚወስደውን መንገድ ይጠርግልናል ብለው ነው። ታዲያ መሰናክል መስሎ የታያቸውን ኢትዮጵያዊነትንና ለኢትዮጵያዊነት አጋዥ ኃይል ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉትን ሁሉ ከመንገድ ለማስወገድ ቆርጠው ተነሥተዋል።

የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው ኃይል፥ ተቃዋሚዎቹን ተፎካካሪዎቼ ብሎ ሲጠራ አድምጠናል። የነአቶ በቀለ ገርባ ቡድን ግን የእስር ቤት ጓደኞቻቸውን፥ ለእርሳቸው መፈታት ድምጹን ከፍ አድርጎ የጮኸውን ሕዝብ ጠላቶቼ ብሎ መግለጫ አውጥቶአል። መግለጫው በግልባጭ የተላከው ለግንቦት ሰባት ይሁን እንጂ በዋናነት የተላከው ወደ ምንሊክ ቤተ መንግሥት ነው። የለውጡ ኃይል ምላሽ ምን ይሆን?

ለጊዜው ያየነውና እያየን ያለነው የሚያስፈራ እና የሚያሳፍር እየሆነ ነው። ስድብ እየተዛወር፥ ክስ እየተጣመመ ነው። የገደሉ ከመሪዎቻችን ጋር ጉባኤ ተቀምጠው ሳለ ፥ ምግብ ያቀበሉ እየታሠሩ ነው። በአደባባይ ሁለት መንግሥት እንዳለ የተናገሩት እንዳሻቸው እየሆኑ፥ ወጣቶች እየታፈሱ ነው። ገዳዮች እንደፈለጉት እየተምነሸነሹ፥ እየታሠሩ ያሉት ገዳዮችን አስቆጥተዋል የተባሉ ወጣቶች ናቸው። ሁኔታው ያስፈራል ያሳፍራልም ብለናል። የሚያስፈራው የለውጡ ኃይል ታግዷል፥ ሾፌሮቹ « ባለ ሁለት መንግሥቶቹ» ናቸው ወይ? የሚለው አሳብ በአእምሮአችን ውልብ ማለቱ ነው። የሚያሳፍረው ዓይን ያወጣውን ማስረጃ በአደባባይ ለማስተባበል የሚደረገው መንተባተብ ነው።

ይህ አንድም ከፍርሃት የመነጨ፥ ወይም ከአቅም ውሱንነት፥ ወይም ከተሳሳተ ስሌት የመነጨ ነው። ወይም ኃላፊነትን ኃላፊነት ለጎደላቸው delegate ከማድረግ የመጣ ነው።

በዚሁ ሁሉ ግን እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ነገር እናምናለን። ኢትዮጵያ እጆቿን ለእግዚአብሔር የዘረጋች ስለሆነች፥ እጣ ፈንታዋ በእርሱ እጅ ነው። ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ እንዳሉት፥ « ኢትዯጵያ በአንተ አልመጣችም። በአንተም አትጠፋም።» በመሆኑም የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በበቀለ ገርባም ወይም ከእርሳቸው ጀርባ ባለው ኃይል እጅ ውስጥ አይደለም። የኢትዮጵያ አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

ለለውጡ ኃይል ግን አንድ ሁለት ቃላትን ልናገር። አንደኛ፥ ዘር ቀለም ጎሣ ያልወሰነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ ነው። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ደግሞ በዙፋኑ ላይ ነው። ሕዝባችሁን ይዛችሁና እግዚአብሔርን ፈርታችሁ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ነገር አድርጉ። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።

Tuesday, September 25, 2018

“የአዲስ አበባ ፓሊስ” ለሉአላዊ ባለቤቱ ይመለስ!

September 25, 2018
ከኤርሚያስ ለገሰ
የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሜጄር ጄኔራል ደግፌ በዲ በወቅታው የመዲናይቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ የሰጡትን መግለጫ ሰማሁት። ኮሚሽነሩን በተሰጣቸው ሃላፊነት እና ስልጣን የማክበር የዜግነት ግዴታ አለብኝ።እንደ አንድ ዜጋ እና ድምፅ አልባ ለሆነው አዲስአበቤ( በአዲስ አበባ በፍላጐቱ የሚኖር) እንደሚቆረቆር ሰው ደግሞ ቅሬታዮን የማቅረብ መብት አለኝ።
በመግለጫው ጄኔራሉ ላለፉት 27 አመታት የሰማነውን የመነቸከ አካሄድ እንደ ምርጥ ተሞክሮ በመውሰድ የህግ የበላይነት ሳይሆን የሕጉ የበላይ መስለው ታይተዋል። ሰውየውን ያለ ዛሬ አይቼአቸው ባላውቅም ከአንደበታቸው የሚወጣው አምባገነናዊ አቋምና እብሪት በተራዘመ ሂደት ስርአቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ ሊወስደው ይችላል። በተለይም ጄኔራሉ እንደ ዛሬው በአክራሪዎቹ ተጠልፈው አይጥ በበላው ዳዋ እየፈለጉ የሚገድልና የሚያስሩ ከሆነ ለለውጥ ሀይሉ ከባድ ሸክምና እዳ መሆናቸው አይቀርም።
እዚህ ላይ የለውጡ መሪ ለሆነው ዶክተር አቢይ አንድ በጥሞና ማየት አለበት ብዮ የማስበውን ቁምነገር ላስገባ። የመጣጥፉም መዳረሻ ይሄ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው ከምርጫ 97 በኃላ ከአዲስ አበባ ፓሊስ ጋር በተያያዘ አቶ መለስ ሶስት ትላልቅ አምባገነናዊ እርምጃዎች ወስደዋል። በቅርበት ለማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሠይጣናዊ እርምጃዎች መዲናይቱን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለዋታል። በዚህ ምክንያት የተፈጠረው ችግር ፓለቲካዊ እና መዋቅራዊ በመሆኑ መፍትሔውም ፓለቲካዊ መሆኑ አይቀርም።
#የመጀመሪያው የአዲስ አበባና የአዲስ አበቤን ሉአላዊነት (በራሳቸው ህገ መንግስት አንቀፅ 49 የተጠቀሰውን) በመናድ የመዲናይቱን ፓሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለፌዴራል መንግስት አድርገዋል። በሌላ አነጋገር አዲስ አበባም ሆነ የህዝቡ ሉአላዊነት መገለጫ ተደርጐ የሚወሰደው “የከተማው ምክርቤት” የአዲስ አበባን ፓሊስ የማዘዝ መብት የለውም። በዳቦ ስም “የአዲስ አበባ ፓሊስ” ይባል እንጂ በግብር፣ በተጠሪነት እና ተጠያቂነት አዲስአበቤ አይደለም። እዚህ ላይ ሌላም አስገራሚ ነገር ልጨምር። ለነገሩ አስገራሚ ከምለው አስቂኝ ብለው እመርጣለሁ። ነብሷን ይማረው እና ወላጅ እናቴ ከአቅሟ በላይ የሆነ ነገር ሲያጋጥማት “ ወደው አይስቁ!” ትለን ነበር። ወደው አይስቁ! እናም አስቂኙ ነገር አዲስአበቤ ባለቤት ላልሆነበት፣ ተጠሪው ላልሆነ፣ ለማይጠይቀው “ የአዲስ አበባ ፓሊስ” በጀት ይመድባል። የሉአላዊነቱ አካል ያልሆነውን ፓሊስ ይቀልባል።
ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር! መቼም የአለም ሶስተኛ የዲፕሎማሲ ከተማ፣ የአፍሪካ መዲና፣ የኢትዮጵያውያን ዋና መናገሻ የምታዘው ፣ ተጠያቂ የምታደርገው ፓሊስ የላትም ብሎ እንደ መናገር የሚያሳፍር የለም። እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም እርሶም በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የፓለቲካ ቧልትና ጠላታዊ እርምጃ የሚሸማቀቁ ይመስለኛል።
በእርሶ የስልጣን ዘመን ይህን ውንብድና በማስተካከል በቀድሞው ስርአት ፓለቲካ ቁስለኛና ሰለባ የሆነውን አዲስአበቤ ከይቅርታ ጋር እንደሚክሱት ሙሉ እምነት አለኝ። በአዲስ አበባ ፓሊስና አዲስአበቤ መካከል የተጋረደውን መጋረጃ ቀዳደው ለመጪው በነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለሚመጣው የአዲስ አበባ መንግስት እንደሚያስረክቡ ጥርጥር የለኝም።
#ሁለተኛው የአቶ መለስ የውስጥ መመሪያ የፓሊስ ምልመላና ስልጠናን የተመለከተ ነው። ከምርጫ 97 ጀምሮ ለነበሩት ሶስት አመታት የአዲስ አበባ ፓሊስ ለመሆን በሚደረገው ምልመላ ለአዲስአበቤ የሚሰጠው ኮታ 10 በመቶ በታች ነበር። በሂደትም ከሃምሳ በመቶ የሚበልጥ አይደለም። የተቀረው ግማሹ በኮታ ከሌሎች አካባቢዎች ተመልምሎ የሚመጣ ነው።ከኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ…ወዘተ። ከሌላ አካባቢ የሚመጡት ፓሊሶች ደግሞ ከከተሜው ባህሪ ጋር መላመድ ስለሚያቅታቸው ነዋሪው እንደሚንቃቸው ስለሚያስቡ በበታችነት ስሜት ይሰቃያሉ። በተበቃይነት ስሜት መንፈሳቸው ይረበሻል። ፈሪና ድንጉጥ ፍጡር ይሆናሉ። ፈሪ ሰው ደግሞ ሁሉንም ሰው ጠላት ያደርጋል።
በፓሊሱና በከተማው ነዋሪ መካከል ያለው ግንኙነትም የፋራና አራዳ ፣ የተታላይና አታላይ፣ የከተማ ቀመስና ከተሜ፣ የሰገጤና ጩሉሌ መሆኑ አይቀርም። በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ፓሊስ አባላትና አዲስአበቤ መካከል ያለው ግንኙነት ከፍተኛ የመተማመን እጦት ያለበት ሆኗል። ነዋሪው እንኳን በሲነርጂ አብሮ ሊሰራ ቀርቶ በመንደሩ ያስቸገረ ሌባን ለፓሊስ አሳልፎ መስጠት አይፈልግም። ፓሊስ በፓትሮል ለአሰሳ ሲመጣ “ ዛፓው! ሰገጤው! እየመጣላችሁ ነው ወደ ቤት ግቡ!” የምትለው የአራዶች ቃል በእናቶቻችንም ዘንድ የተለመደ ሆኗል።
የምልመላ መስፈርቱም የኢህአዴግ ሊግ አባል (60 ነጥብ)፣ የወጣት ፎረም አባል (20 ነጥብ)፣ የትምህርት ዝግጅት እና ሌሎች የጤና መመዘኛዎች (20 ነጥብ) ነበሩ። በሌላ አነጋገር አዲስአበቤ የኢህአዴግ የወጣት ሊግ ውስጥ መታቀፍ ካልፈለገ ፓሊስ የመሆን የልጅነት ህልም ቢኖረው እንኳን ፓሊስ መሆን አይችልም። በዚህ እኩይ ተግባር ሁላችንም የታሪክ ተወቃሾች ነን። የታሪክ ተወቃሽነት የሚያመጣው ድርጊቱን መፈፀም አሊያም አጋዥ መሆን ብቻ አይደለም። መጥፎው ውሳኔ እንዳይተገበር ለመከላከል ቁርጠኝነት አልፎ ሔዶም ማጋለጥ አለመቻል በዚህ ፈርጅ ይመደባል።
እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከላይ የጠቀስኩት አካሄድ እንዲሁ ቢቀጥል አዲስአበቤ ለእርሶ ያለው ድጋፍ ከተወሰነ በኃላ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት ይችላሉ። የመዲናይቷን ሰላም የሚያስጠብቀው ክፍል ውስጥ ባለቤቱ ከሌለበት እና ባይተዋር ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ በሂደት እርሶንም በባላንጣነት የሚመለከትበት ሁኔታ ይፈጠራል።
በመሆኑም በእርሶ የስልጣን ዘመን ይሄን ያልተፃፈ የውስጥ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ያስቁሙ። የኦሮሚያ ክልል ፓሊስ አባላት በኦሮሚያ የሚኖሩ ዜጐች እንተደረገ ሁሉ፣ የአማራ ክልል የፓሊስ አባላት በአማራ ክልል እንደሚመለመሉ ሁሉ…ወዘተ በአዲስ አበባ ክልልም የሚመለመሉ ፓሊሶች አዲስአበቤ( በፍላጐቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ) ብቻ እንዲሆኑ አድርጉ። መመዘኛውም እንደ እርሶ ሙሉ ቁመና ያለው፣ ፓሊስ ሆኖ ማገልገል ፍላጐት ያለው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ በፀባዩ ተቀባይነት ያለው/ ያላት ያድርጉ። የፓርቲ አባልነት እንደ መመዘኛ መወሰዱ ፀያፍ እንደነበር በአደባባይ ይግለጡ።
#ሶስተኛው ከአዲስ አበባ ፓሊስ አመራር ጋር የተያያዘ ነው። አስቀድሜ እንደገለጥኩት ከምርጫ 97 በኃላ የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራር የሚመደበው ከፌዴራል ፓሊስና መከላከያ ሰራዊት ነው። በተለይም ቁልፍ ስራ የሆነውን አዛዥነት፣ ወንጀል መከላከል እና ምርመራ መምሪያ የሚያዘው ለፓርቲው ታዛዥ የሆኑ የፌዴራል ፓሊስና የመከላከያ መኮንኖች ናቸው። ይሄ በራሱ የፈጠረው ችግር አለ።
ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆንብኝ እንጂ የፓሊስ አመራር ሳይንስም ጥበብም ነው። ሳይንስ በመሆኑ ፕሮፌሽናሊዝም እና ምሁራዊ ግንዛቤ ይጠይቃል። ጥበብ በመሆኑ የሰዎችን አእምሮ የሚማርኩ ስልቶችን ማወቅ ይጠይቃል። የፓሊስ አመራር ከሌሎቹ ሙያዎች በተለየ ረቀቅ ያለ ጥበብ ይጠይቃል። በእውቀት፣ በችሎታ፣ በእምነትና ሕዝብ ለሚቀበለው መርሕ መቆምን ይጠይቃል። የሕግ የበላይነትን አምኖ መቀበል ይጠይቃል።
ስለዚህ የፓሊስ አመራር መሆን ያለበት እንደ ድሮው በፓሊስ ኮሌጅ ገብቶ በከፍተኛ መኮንንነት የሰለጠነ ፕሮፌሽናል ሰው ሊሆን ይገባል። የመከላከያ ሰራዊት ጄኔራል ተመልሶ ፓሊስ ኮሌጅ ገብቶ የአራት አመት ስልጠናውን ካልወሰደ በስተቀር ወደ ፓሊስ አመራርነት መምጣት የለበትም። አሁንም ድፍረት አይሁንብኝ እና አንድ የመከላከያ ሰራዊት መኮንን ስልጠናም ሆነ የአእምሮ ኦረንቴሽኑ ወታደርተኝነት ነው። ጠላትን የማንበርከክ ጀብደኝነት እና የጦረኝነት ዝንባሌ ነው።
ነብሱን ይማረው እና አቶ መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባ ፓሊስ አመራሮችን ከመከላከያ ሲያመጣ አዲስአበቤን እንደ ጠላት፣ አዲስ አበባን እንደ ጦርነት አውድማ ስለሚቆጥራት ነበር። የአቶ መለስ የጦረኝነት ጽንሰ ሐሳብ የሚመነጨው መዲናይቱን መቆጣጠር የሚቻለው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ በታነፀ ወታደራዊ ኃይል ነው ከሚል እምነት ነው። በጠላትነትና በአደገኛ ቦዘኔነት የፈረጀውም አዲስአበቤ ወጣት ፀጥ ረጭ ማድረግ የሚቻለው በዚህ አይነት የጦር አመራር መሆኑን ያምናል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርሶም በማወቅም ይሁን የቀድሞ አሰራር ትክክል መስሎት የፓሊስ አመራርን የቀየሩበት አሰራር ተመሳሳይ ነው። እርሶም ለአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽርነት የሾሙት የመከላከያ ሜጄር ጄኔራል ሆኗል። ሰውየው የፓሊስ አካዳሚ ገብተው ስልጠና መውሰዳቸውን ባላውቅም ከአነጋገር ለዛቸው ከወታደርተኝነት የተላቀቁ አይመስለኝም። ዶሮ ሶስት ጊዜ ሳትጮህ ጠርብ ጠርብ የሚያካክሉ ኩሸቶችን ሲያወሩ አንደበታቸው አልተደናቀፈም። መስከረም 4፣ መስከረም 5 የሰጡት መግለጫ መስከረም 14 ከሰጡት ጋር እርስ በራሱ ሲደባደብ ከመጤፍ አልቆጠሩትም( የእነዚህ ቀናት አስቂኝ ድራማ በሌላ ጽሁፍ እመጣበታለሁ።) ጆሮአቸውን በጥይት የደፈኑት እኝህ ጄኔራል ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ አይችሉም የሚለውን የህገመንግስት ቃል አንብበውት የሚያውቁም አይመስልም። በአመራር ሳይንስ ውስጥ ቅድሚ ለሚሰጥ ቅድሚያ እንስጥ በሚለው ጥበብ አጠገቡ ያለፉ አይመስልም። የጄኔራሉ አድርባይነት እና የስልጣን ብልግና ከወዲሁ ቁልጭ ብሎ ወጥቷል።
በመሆኑም እንዲህ አይነት ወታደርተኝነት ግርዶሽ የጣለባቸውን የጦር መኮንኖች ያለምንም ስልጠና ሕዝብ ውስጥ መቀላቀል ጦሱ ብዙ ነው።አዲስአበቤ በለውጡ ላይ ያሳደረው አመኔታ ይሸረሽራል። በነዋሪው አንድ “ወዴት እየሔድን ነው?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በጠቅላላው አነጋገር በዚህ ዙሪያ የሚታየው ስህተት በቀላሉ የሚታረም አይደለም። የመጀመሪያው ድንጋይ ከመወርወሩ በፊት መሰረታዊ የሆነ የአመራር ስርአት ለውጥን ይጠይቃል። መሪ መለወጥም ግድ ይላል። ከእንግዲህ በኃላ አዲስአበቤዎች በቀቢጸ ተስፋ የሚኖሩ አይደሉም። እንደ ጥቁሩ አሜሪካዊ የመብት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ህልም አላቸው። አንድ ቀን አዲስአበቤዎች በነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ራሳቸውን ያስተዳድራሉ።

Saturday, March 17, 2018

የህወሃት የደህንነት ተቋም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚን ስብሰባ መረጃዎችን “እያሾለከ” እያወጣ ነው።

17,03,2018
ፋሲል የኔአለም
የሚለቀቁት መረጃዎች ደግሞ በለማና አብይ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። ሁለቱም ሰዎች በስብሰባው ላይ የተለዬ ተቃውሞ እንዳላሰሙ የሚያሳይ ጽሁፍ አንብቤአለሁ። ። ሽፈራው ሽጉጤም ስብሰባው ያለችግር እየተካሄደ ነው የሚል መግለጫ ሰጥቷል። በጎን ደግሞ የህወሃት ድረገጾች በእነ አብይ ላይ ያሚያደርጉትን ዘመቻ አጠናክረዋል። ህወሃት ህዝብ የሚወደውን ሰው ለማስመታት ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ፣ ሰውዬው የእሱ ደጋፊ ሳይሆን ልክ የእሱ ደጋፊ እንደሆነ አድርጎ አሉባልታ በመንዛት ነው። የህወሃትን ሴራ ሳይገነዘቡ በህወሃት አሉባልታ የሚወናበዱ ሰዎች፣ “ እሱማ ከህወሃት ጋር ይሰራል” ብለው የሚወዱትን ሰው መደገፍ ሲያቆሙና ህወሃትም የሰውዬው ህዝባዊ ድጋፍ መቀነሱን ሲያይ፣ በሰውዬው ላይ የመውጊያ ጩቤውን ይመዛል። በህወሃት አሉባልታ ህዝባዊ ድጋፉ መሸርሸሩን የተረዳው ሰው፣ ህልውናውን ለማቀዬት ሲል የህወሃት ታዛዥ ሆኖ ያገለግላል፤ አልያም ዋጋ ይከፍላል።
በእነ አብይ ላይ የሚለቀቀው የፕሮፓጋንዳ አላማም ከዚህ ተለይቶ መታዬት ያለበት አይመስለኝም ፤ ሰዎቹ ከህወሃት ጋር እንደተሰለፉ አስመስሎ በማስወራት ህዝባዊ ድጋፋቸውን ለመሸርሸርና በሂደት ለመምታት ታስቦ የሚለቀቅ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ይሰማኛል። ከሚሰጡት መግለጫዎችና ጽሁፎች ተነስቼ የህወሃት የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ በጥሩ መልኩ እየሄደ እንዳልሆነ መገመት እችላለሁ። እነ ለማ የትግል ስልት ለውጥ ያደረጉም ይመስለኛል ፤ በአደባባይ ብዙ ባለማውራት “ሙያ በልብ ነው” የሚለውን አገራዊ ብሂል ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ይሰማኛል። በስራ አስፈጻሚው ስብሰባ ላይም ጠንካራ አቋም ይዘው እንደቀረቡ እገምታለሁ ። ያ ባይሆን ኖሮ “አብይ እንዲህ አለ ፣ ለማ እንዲያ ተናገረ” እየተባለ አሉባልታ መንዛት ባለስፈለገ ነበር። ህወሃቶች በራስ መተማመን ቢኖራቸውና ምንም እንዳልተፈጠረ ቢያምኑ ኖሮ የስብሰባውን ሙሉ ውይይት ቀርጸው ያቀርቡልን ነበር። አሁን “ በውስጥ አዋቂ” ስም የሚወጣው ቁንጽል መረጃ ሆን ተብሎ ከህወሃት የመረጃ ማቀነባበሪያ ቢሮ የሚወጣ ማደናገሪያና እነ አብይን ከህዝብ ነጥሎ ለመምታት የሚደረግ ሙከራ ነው ብዬ አምናለሁ።
ለማንኛውም “የበይዎች አለመስማማት ለተበይ ይጠቅመዋል” እንዲሉ፣ እነሱ ሽኩቻቸውን ሲቀጥሉ፣ የነጻነት ሃይሉም የተፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል አለበት። እውነተኛ ለውጥ በእኛ ትግል እንጅ በእነሱ መልካም ፈቃድ አይመጣም።

Tuesday, February 20, 2018

ለሕዝብ ፍላጎት መታዘዝ ያስከብራል!

February 20,2018
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መወሰናቸው ከመሰማቱ በፊት  በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ፖለቲከኞች ተፈተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲደረግ በማሰብ ራሳቸውን ለማግለል መወሰናቸው፣ አገሪቱ ያለችበትን አሳሳቢ ችግር ያመለክታል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ ከፊቱ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ተደቅነውበታል፡፡ አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሁሉንም ወገኖች በሚያግባባ ሰው መተካትና የተሻለ ምኅዳር መፍጠር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እንደካሁን ቀደሙ በነበረው ሁኔታ የሚያስቀጥል አምጥቶ ቀውሱን ማባባስ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ካለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ ጀምሮ አልበርድ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ እልባት የሚፈልግለት ከሆነ፣ በመጀመርያ በውስጡ የሚታየውን ሽኩቻ በማቆም ለሕዝብ ፍላጎት ራሱን ማስገዛት አለበት፡፡ ለአገር የሚያስብ ማንኛውም ኃይል በዚህ ወቅት ለሕዝብ ፍላጎት መንበርከክ ይኖርበታል፡፡ የአገሪቱ ሁኔታ እያደር ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነና አሳሳቢ ችግሮች ተጋርጠው፣ የፖለቲካ ቁማር ውስጥ ገብቶ ሒሳብ ለማወራረድ መሞከር የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ ይከተዋል፡፡ የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች አገርን ከቀውስ ለመታደግ ሲሉ በዚህ ቀውጢ ጊዜ በአንድነት ቢቆሙ ይበጃል፡፡ ሰላማዊና ሥልጡን የፖለቲካ ለውጥ የሚመጣው በመተናነቅ ሳይሆን፣ ለሕዝብ በሚበጅ ሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡
አሁን ግልጽ እየሆነ የመጣውና ብዙዎችን የሚያስማማው የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ነው፡፡ ይህ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ደግሞ ኢሕአዴግን ጨምሮ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚገናኙበት ሁሉን አካታች መድረክ ሲፈጠር ነው፡፡ ይህ መድረክ እንዲፈጠር የተለያዩ ተግባራት መከናወን ሲኖርባቸው፣ ከምንም ነገር በላይ ከትርምስና ከውድመት የፀዳ ከባቢ መፈጠር አለበት፡፡ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር ስለሌለ በመተማመን መንፈስ አገሪቱን ከገባችበት አረንቋ ማውጣትና የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት ምኅዳር ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ የሥልጣኑ ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ በመሆኑ፣ ሕግና ሥርዓትን ሳያዛንፉ መነጋገርና መደራደር የሚቻል ከሆነ ሥጋት ወደ ተስፋ ይለወጣል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት አገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ዕርምጃ መውሰድ እያቃተው፣ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች ተጨናግፈዋል፡፡ አገሪቱ እዚህ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ከመውደቋ በፊትም ሆነ በተከታታይ ባጋጠሙ አስከፊ ችግሮች ምክንያት፣ የሕዝብን ፍላጎት ያገናዘቡ ዕርምጃዎች ባለመወሰዳቸው ብቻ ከቀውስ ወደ ቀውስ መሸጋገር ልማድ ሆኗል፡፡ ከእንግዲህ ዓይነቱ አዘቅት ውስጥ በቶሎ አለመውጣት የአገር ህልውናን ይፈታተናል፡፡ ውጤቱም አስከፊ ይሆናል፡፡
      ያጋጣሙ ዙሪያ ገብ ችግሮችን በመሸሽ ወይም በማድበስበስ ዙሪያውን ከመዞር፣ ከእውነታው ጋር ተጋፍጦ ለሕዝብ ፍላጎት ሸብረክ ማለት ያስከብራል፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ በፖለቲካው ሠፈር ውስጥ ያሉ ወገኖች በሙሉ ሊገነዘቡት የሚገባው፣ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሆኖ የሚወጣበትን ጎዳና መምረጥ ቀውሱን ያባብሰዋል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ አገር መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማ ግራ በገባት ወቅት ሥልጣንን ብቻ ማዕከል ያደረገ ንትርክና ንዝንዝ ለማንም አይጠቅምም፡፡ አሁን የሚፈለገው አገሪቱን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ጎትቶ ማውጣት የሚችል ነው፡፡ በሐሳብ ልዩነት በማመን የተሻለ አቅምና ሐሳብ ያለውን ዕድል በመስጠት ዴሞክራሲያዊ ዓውድ መፍጠር የግድ ነው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳሩን በአስቸኳይ በመክፈትና ከአጉል ጀብደኝነት በመላቀቅ፣ በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሒደት እንዲጀመር ሁሉም ወገን ጠጠር ማቀበል እንዲችል ዕድሉ ይመቻች፡፡ ነውጥ በተነሳ ቁጥር ሕይወት እየጠፋና ንብረት እየወደመ የሚቀጠልበት ቀውስ ሳይሆን የሚያስፈልገው፣ በተቻለ መጠን ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ሊያስማማ የሚችል አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡ ለሥልጣን ከሚደረገው ሽኩቻና መራኮት የምትበልጠው አገር ናት፡፡ ከአገር በላይ ምንም የለም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላው ቢቀር በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከሠፈሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተጨማሪ፣ አስተዋዩና ጨዋው ሕዝብ ውስጥ ለዘመናት የኖሩት የጋራ መስተጋብሮች ለመነጋገርና ለመደማመጥ ትልቅ ፋይዳ ነበራቸው፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን አንዱን አሳዳጅ ሌላውን ተሳዳጅ፣ አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ የሚያደርገው አታካችና አሰልቺ የዘመናት የልሂቃን ችግር እዚህ አድርሶናል፡፡ በሕግ የበላይነትና በማኅበረሰቡ ውስጥ በዳበሩ መልካም እሴቶች አማካይነት በመታገዝ ቅራኔዎችን ከመከመር ይልቅ፣ ለጋራ መግባባት ቢሠራ ኖሮ ኢትዮጵያ የት በደረሰች ነበር፡፡ መልካም አጋጣሚዎች እንደ ዋዛ አልፈው በቀውስ ማዕበል እየተገፉ ውሳኔዎች ማስተላለፍ የተጀመረው በዚህ ምክንያት መሆኑን ከልብ መቀበል የግድ ነው፡፡ አሁን ኳሷ በዋነኝነት ያለችው በኢሕአዴግ እጅ ላይ ቢሆንም፣ በፖለቲካው ጎራ ውስጥ ያሉ ኃይሎችም የራሳቸው ሚና አላቸው፡፡ ይኼንን ሚና በአግባቡ መወጣት የሚቻለው ግን ቅድሚያ ለአገር ሰላምና ደኅንነት ማሰብ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ወጀቡን ተከትሎ በዕቅድ  የማይመራ ነውጥን ማበረታታትና ለትርምስ የሚረዱ ግብዓቶችን ማቅረብ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋትና ራስን ለቁጭት መዳረግ ነው፡፡ ፖለቲካ የሚፈልገው ብልኃትና ጥንቃቄን እንጂ መደነባበርን አይደለም፡፡
‹‹ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል፣ ሞኝ ልጅ ግን ምሳው እራቱ ይሆናል፤›› እንደሚባለው፣ ከዜሮ ድምር ፖለቲካ በመላቀቅ ለሰጥቶ መቀበል መርህ የሚረዳ ምኅዳር እንዲፈጠር ራስን ማዘጋጀት የወቅቱ ዋነኛ ጉዳይ ነው፡፡ ሕዝብን ለአመፅ የሚጋብዙ ውሳኔዎች ትርፋቸው ሞትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በሰከነ መንፈስ ማሰብ ያለባቸው፣ የሚፈለገው ነገር ሊሳካ የሚችለው አገር ስትኖር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከወቅቱ የሕዝብ ፍላጎት ጋር የሚመጣን ውሳኔ ማሳለፍ ያለበትና ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ማዘጋጀት የሚኖርበት፣ ከምንም ነገር በላይ የሆነችው አገር ሰላም እንድትሆን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠር የሚያግዙ የፖለቲካ ውሳኔዎች ታክለው ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ወደሚረዳ ምርጫ መንገድ ሲመቻች፣ የአገር ሰላምና መረጋጋት ወደነበረበት ይመለሳል፡፡ አማራጮች ሳይጠፉና ለዚህም የሚረዱ ፖለቲካዊ ማዕቀፎች ባሉበት በዚህ ዘመን፣ የኃይል ተግባር ውስጥ በመግባት አገር ማተራመስና ሕዝብን ማመሰቃቀል በታሪክ ፊት ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ አገርን አውድሞ ሙሾ ማውረድ የሞኝ እንጂ የብልህ ተግባር አይደለም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አማካይነት በነፃነት በሚደረግ ምርጫ እንጂ፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች በሚሆንበት ኢዴሞክራሲያዊ አሠራር አይደለም፡፡ የአገሪቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በእኩልነት የሚወዳደሩበት ሕጋዊ ማዕቀፍ በማበጀትና ብልሹ አሠራሮችን በማስተካከል፣ በዚህች ታሪካዊት አገር ዴሞክራሲ ነፍስ እንዲዘራ መደረግ አለበት፡፡ ባለፉት ዓመታት በስኬት ስሙ የሚነሳው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የበለጠ መመንደግ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን እንኳን ኢኮኖሚው የአገሪቱ ዕጣ ፈንታም አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ዘለቄታዊ መሆን የሚችለው በሰላማዊና በአሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ሒደት ነው፡፡ የወቅቱን ችግር ለመግታት ብቻ ዒላማ ያደረገ ውሳኔ የሚተላለፍ ከሆነ ግን ሰላም እንደ ኅብስተ መና ይርቃል፡፡ ከዚህ ቀደም አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ስትገባ የአሥር ወራት አስቸኳይ ጊዜ ቢታወጅም ዘላቂ ሰላም ግን አልመጣም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ችግሮች ተፈጥረው በርካቶች ሞቱ፣ ለአካል ጉዳት ተዳረጉ፣ ተፈናቀሉ፡፡ አሁንም ካጋጠመው ቀውስ በዘላቂነት ለመላቀቅ አስተማማኝ ሰላም ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ አገሪቱ ከገጠማት ፈተና ለመታደግ የሚቻለው ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚያግባባ ውሳኔ ላይ መድረስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ሲጣል ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ይሁንታውን ሲገልጽ ነው፡፡ ከአገር በላይ ምንም ነገር ስለሌለ ለሕዝብ ፍላጎት መታዘዝ ያስከብራል!

Saturday, February 17, 2018

የኢህአዴግ ውስጣዊ ቀውስ ተባብሷል- ስራ አስፈፃሚው አስቸኳይ ስብሰባ ይቀመጣል

Febeuary 17,2018

ዋዜማ ራዲዮ-የበረታውን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ገዥው ግንባር በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተውተረተረ ይገኛል። መሰረታዊ የፖለቲካ ማሻሻያ መደረግ አለበት የሚሉ ድምጾች በበረቱበት በአሁኑ ሰዓት ስባት ሚሊየን አባላት ያሉት ኢህአዴግ ራሱን አንድ አድርጎ መራመድ ተስኖታል። የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቷል። የመከላከያ ኤታማዦር ሹሙ ሳሞራ የኑስ መልቀቂያ ያስገባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲነሱ የቀረበው ሀሳብ ከምንግዜውም በላይ አጀንዳ ሆኖ እየተናፈሰ ነው። ከዋዜማ ራዲዮ አቅም በፈቀደ በገዥው ግንባር ሰፈር ያለውን መረጃ በግርድፉ ከተለያዩ ምንጮች አሰባስበን አቅርበናል አንብቡት።
በተቃውሞ እየተናጠ መረጋጋት የራቀው ኢህአዴግ ሰፊ የአመራር ሽግሽግ እንደሚያደርግ ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ሰዎች ግምታቸውን እየሰጡ ነው፡፡ ለዋዜማ የግል አስተያየታቸውን በስልክ ያካፈሉ አንድ የቀድሞ የፓርቲው ከፍተኛ ባለሥልጣንና አምባሳደር እንደሚሉት ብአዴንና ህወሓት በጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትላቸው ደካማ አመራር ‹‹ፍጹም ደስተኞች እንዳልሆኑ›› በይፋ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ቀደም ባለው ስብሰባ ስብሀት ነጋ ኃይለማርያም ላይ የሰላ ሂስ መስጠቱን አውቃለሁ፡፡ አልቻልክበትም ብሎታል፡፡…አሁን የቸገራቸው እሱን አንስተው ማንን እንደሚያመጡ ነው፡፡›› ይላሉ እኚሁ የቀድሞ ባለሥልጣን፡፡
በመሪዎች ደረጃ ለውጥ ይጠበቅ የነበረው ከወራት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ቢኾንም የሐዋሳው ጉባኤ የተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ላልተወሰነ ጊዜ በመገፋቱ የሥልጣን ሽግሽጉ ከተጠበቀው ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲካሄድ በአራቱም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ፍላጎት ታይቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ከትናንት በስቲያ ማምሻውን አራቱ የፓርቲ አመራሮች ስብሰባ አቋርጠው የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የተላለፈው መልዕክት ተሰርዞ በምትኩ ደኢህዴንና ብአዴን ስብሰባቸውን እንደጨረሱ አስቸኳይ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር፡፡
ትናንት ምሽቱን ደግሞ ዳግም ስብሰባው ዛሬ ሐሞስ እንደሚካሄድ እየተነገረ ነው። የስብሰባው የጊዜ ሰሌዳ መዘበራረቅ ፓርቲው በሀገሪቱ እየበረታ የመጣው ቀውስ ያስከተለው ስጋት መሆኑን ግምታቸውን የነገሩን አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ግማሽ ካቢኔያቸውን ለመፐወዝና አዳዲስ አደረጃጀቶችንና መዋቅሮችን ለማስተዋወቅ በአዲስ መንፈስ ኮሚቴ አቋቁመው እየሰሩ እንደነበር እንደሚውቁ የጠቀሱት እኚህ የቀድሞ ሹምና አምባሳደር፣ ባለፉት ሳምንታት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጀሪኖ) የሚመሩት አንድ ቡድን አዳዲስ ተሽዋሚዎችን በመመልመል ተጠምዶ እንደነበር እንደሚውቁም ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ ተሸዋሚዎችን ያስተናግዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቋማት መሐል በዶክተር ደብረጺዮን ይመራ የነበረው የመገናኛ ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ቦታ ሲሆን የብየነ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳን) ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲመሩ የቆዩት ጄኔራል ተክለብርሃን ወልደዓረጋይ ከቦታቸው ተነስተው የዶክተር ደብረጽዮንን የቀድሞ መሥሪያ ቤት እንዲመሩ መታጨታቸው ተስምቷል።፡፡ ኮሚቴው ከዚህም ባሻገር ሦስት ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶችንና ሁለት ኤጀንሲዎችን በአዲስ ለማዋቀር እየሰራ ሲሆን ዶክተር ነገሪ ሌንጮን የሚተካ እጩ አመራር በማፈላለግ ላይ እንደነበረም ተሰምቷል፡፡ ይህ የምልመላና የአዲስ መዋቅር እንቅስቃሴ የሀገሪቱ ቀውስ በመበርታቱ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል፡፡
በኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ መሰረት የመከላከያና ደህንነት ተቋማትን የመከለስና ሹም ሽር የማድረግ ስምምነት ቢደረግም የደህንነት ተቋሙ ጉዳይ ገና አልተጀመረም። የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ሳሞራ የኑስን ለመተካት ሲደረግ የቆየው ምክክርም መቋጫ አላገኘም።
ከመከላከያ አካባቢ የወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች በቀጣዮቹ ሳምንታት ዉስጥ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስ መልቀቂያቸውን እንደሚያስገቡ የሚጠበቅ ሲሆን ሲሆን ጄኔራል ሳዕረ መኮንን ይመር ቀጣዩ ጠቅላይ ኢታማዡር ሹም እንደሚሆኑና በሥራቸው የብሔር ውክልና ያላቸው ሦስት ጄኔራሎች እንዲኖሯቸው እንደሚደረግ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ጉዳዩን እናውቃለን ያሉ ምንጮች ነግረውናል። ፖለቲካዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ሲባል እንዲሁም ወቅታዊ የፖለቲካ ሚዛኑን ከግምት በማስገባት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ጄኔራል ሳሞራ ዩኑስን ሊተኩ ይችላል የሚል ግምት ከመነሻው ጀምሮ ሲናፈስ ቆይቶ የነበረ ቢኾንም ጉዳዩን የያዘው ኮሚቴ መካከል ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉም እየተነገረ ነው።
ይህ ጉዳይ በምደባ ኮሚቴው በኩል አወዛጋቢ ሆኗል። ለወቅታዊ ፖለቲካው ምላሽ ብርሀኑ ጁላ ተመራጭ ዕጩ ቢሆንም በልምድና በግዳጅ አፈፃፀም ሳዕረ ቢሆን ይሻላል ወደሚለው መደምደሚያ ተደርሷል። የዚህ ሳምንቱ የፖለቲካ ዝንባሌ ይህን ውሳኔ ሊያስቀይረው ይችላል የሚለው ግምትም እንዳለ ነው።
የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከጥር 23 ቀን ጀምሮ ስብሰባ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከደኢህዴን ቀደም ብሎ ለስብሰባ የተቀመጠው ብአዴን በሰሜን ወሎ በተፈጠሩ ግጭቶች አቋርጦት የነበረውን ስብሰባ ከጥር 27 ወዲህ እያካሄደው ይገኛል፡፡ ብአዴን ከፍተኛ አመራሮቹን ጭምር ሊቀይር ይችላል የሚሉ ግምቶች መሰማት የጀመሩት በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ሲሆን በተለይም በፓርቲው ዘንድ ፍዝ ሚና ያላቸውን ሊቀመንበሩን አቶ ደመቀ መኮንንን ሊያሰናብት እንደሚችል ሰፊ ግምት ተሰጥቷል፡፡ ከስልጣን እንዲለቁ የበረታ ግፊት አለ። በአባላት መካከል በተደረገ ግለ-ግምገማ አቶ ደመቀ መኮንን በስልጣን እንዳይቆዩ የሚያደርግ ብርቱ ትችት እንደቀረበባቸው ተሰምቷል። በተለይ የክልሉ ህዝብ ወኪል ሆነው በማዕከላዊ መንግስት ውስጥ አንዳችም ተፅዕኖ መፍጠር ያለመቻላቸው በእናት ድርጅታቸው በኩል ከፍ ያለ ቅሬታ ፈጥሯል።
በሕወሓቶች ዘንድ የክልሉ ፕሬዚደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለል እንዲሉ ከፍ ያለ ፍላጎት መኖሩም ይነገራል፡፡ ብአዴንና ደኢህዴን እንደተገመተው አመራሮቻቸውን ገምግመው የሚያሰናብቱ ከሆነ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትላቸው ስለመነሳታቸው ተጨማሪ ማረጋገጫ እንደሚሆንም ይገመታል፡፡
ፕሬዚዳንቱን በሕዝበኝነት፣ ዋና ጸሐፊዉን በሥልጣን ጥመኝነት በቅርቡ የገመገመው ኦህዴድ ያልተጠበቀ የለውጥ ኃይል ኾኖ በወጣበት በዚህ ወቅት በኢህአዴግ ደረጃ በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ የአመራር ሽግሽግ መደረጉ የሚያጠራጥር እንዳልሆነ የሚናገሩት እኚህ ባለሥልጣን ‹‹መጪዎቹ ወራት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወሳኝ ጊዜያት እንደሚሆኑ እምናለሁ›› ይላሉ፡፡