Wednesday, December 27, 2017

ለማ መገርሳ "አውሬውን አቁስለነዋል፤ ይህ ግን በቂ አይደለም" እያሉ ነው


December 27,2017

ክንፉ አሰፋ
  "አውሬው ቆስሏል*። ቆስሎ ስላልተኛ፣ ማቁሰሉ ብቻ በቂ አይደለም። ተመልሶ እንዳይመጣ እርግጠኞች መሆን አለብን።" የሚለው ቃል የወጣው ከ"ጽንፈኛው ዲያስፖራ" ወይንም ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አይደለም። ከአውሬው ጋር አጋር ሆኖ ከሚሰራ ድርጅት መሪ ነው። ያውም በገዥው ፓርቲ ልሳን። የ26 ዓመቱ ፖለቲካ እየተንከባለለ እዚህ ላይ ደርሷል። አንድ ሰው እውነትን በመናገሩ ጀርባው ተጠንቶ፣ ደሙ ተለክቶ፣ ግንባሩ ተገላልጦ፣  በሽብር በሚፈረጅባት ሃገር ውስጥ፣ ጥቂቶች የእድሜ-ልክ ፈራጅ ሆነው በተሰየሙበት ሃገር ይህ ተከሰት። እነ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አንዷለም አራጌ ከዚህ የባስ ነገር አልተናገሩም። በፍትህ ስም የሚቀለድባቸው እነ ፕ/ር መረራ ጉዲና እና በቀለ ገርባ ይህችን ያህል እንኳን አልተነፈሱም።
        መቀሌ ላይ በዝግ ስብሰባ፣ አዲስ አበባ ላይ በዝግ ስብሰባ፣ ፓርላማውም በዝግ ስብሰባ። ሁሉም ተዘጋግቷል። በሃገሪቱ እና በህዝቧ ላይ በዝግ ይዶለታል። ለመፍትሄ ሳይሆን ስልጣን ይዶለታል። በግልጽ ሳይሆን በድብቅ ይዶለታል።  መቶ በመቶ መርጦናል ላሉት ሕዝብ ችግሩን ለመደበቅ ይሞክሩ እንጂ፣ ምጣድ ላይ እንዳለ ቡና የሚያምሳቸው ነገር አደባባይ ላይ እንደተሰጣ እንኳ አልባነኑም። ስውር ድርጊታቸው እየገዙት ላለው ሕዝብ ባይተዋር ስለመሆናቸው ማስረገጫ ይሆናል።  
        ለ35 ቀናት መቀሌ ላይ ዘግተው የዶለቱት፣ ከዚያም አልፈው የነቀሉት እና የተከሉት ነገር፣ መስመር እንደያዘላቸው ተናግረዋል። የህልውናቸው መሰረት የሆነው የመደምሰስ እና የመቆጣጠር ፖሊሲ፣ የህወሃት ስብሰባ ላይ ሰርቶላቸው ሊሆን ይችላል። ሰሜን ላይ ያበጠውን ጎማ አተንፍሰው ሲያበቁ፣ ስንቅ እና ትጥቅ ይዘው ወደ ሸገር ነበር የዘመቱት። እነ ለማን ለማንበርከክ፣ እነ ገዱን ለመጠምዘዝ።
        የሸገሩ ዱለታ እንደታሰበው አልሄደም።   የመቀሌውን የፖለቲካ ፎርሙላ የአዲስ አበባው ኢህአዴግ ስብሰባ ላይ ለመተግበር መጣራቸው ጅል ያደረጋቸው ነው የሚመስለው። ወትሮውን  እንደሮቦት የሚታዘዙ አጋሮቻቸው ባትሪያቸውን እንደጨረሱ አላስተዋሉትም።  በሞግዚት አስተዳደሩን ቀጥሉበት-አንቀጥልም ትንቅንቅ፤  በቀድሞው የኢህአዴግኛ  ቋንቋ መግባባት አልቻሉም። እነ ለማ መገርሳን እንደ ቀድሞው ለማዘዝ የማይችሉበት ቅርቃር ውስጥ ተሸንቁረዋል።  
        የትርምሳቸው ክብደት በኪሎ ባይመዘንም፣ ከጥልቅ ተሃድሶ ወደ ጥልቅ ዝቅጠት መግባታቸውን ግን በይፋ ነግረውናል።  ትላንት በስብሰናል ብለው ነበር፣ ዛሬ ዘቅጠናል ብለዋል። ነገ ደግሞ ተልተናል ማለታቸው የሚጠበቅ ነው። የበሰበሰ ነገር የሚያዘግመው ወድዚያው ነው።
        እዚያ አካባቢ ነገሮች በፍጥነት ተቀያይረዋል።  እንደጅብ ከተሰበሰቡበት ዋሻ ለአፍታ ወጣ አሉና  በብሄራዊ ቴሌቪዥን፣ "ሰላም ነን" ለማለት ሞክረው ነበር። "ውስጡን ለቄስ" አሉ። በዚህ አባባላቸው፤ ጉልበታቸውና ፀጋቸዉእንደበግ ቆዳ ከላያቸው ተገፍፎ እንደሄደ ለማወቅ የፖለቲካ ተንባይ መሆን አያስፈልግም።
        "በመሃላችን የርስበርስ መተማመን ጠፍቷል!" ይላል በዝጉ ስብሰባ መሃል የተሰጠው መግለጫ። ይህንን መግለጫ በገለልተኛ ሜድያ ብንሰማው ኖሮ ላይደንቀን ይችላል። እንግዳ የሆነብን ይህንን መግለጫ በራሳቸው ልሳን መስማታችን ብቻ ሳይሆን፣ ስብሰባው ገና ሳያልቅ መግለጫ መልቀቃቸው ነው። አሁንም ሃገሪቱ የገባችበት ችግር ያስጨነቃቸው አይመስልም። እነሱን እንቅልፍ የነሳቸው አይበገሬ ብለው ያሰቡት የስልጣን ግንዳቸው መንገዳገዱ ነው። ይህንን ሕዝብ መቶ አመት ለመግዛት የወጣው የባለ ራዕዩ እቅድ መሃል ላይ መክሸፉ ነው ይበልጥ የሚያሳስባቸው።
        በመግለጫቸው እርስበርስ ተከፋፍለናል ማለትን በመጸየፋቸው፤ አደባባይ የወጣ ክፍፍሉን "መተማመን ጠፋ" በሚል ቃል ሊያሽሞነሙኑት ሞከሩ።  መዝቀጣቸውን ግን አልካዱትም።  ታዲያ ምን ይጠብቃሉ? የዘቀጠ እና የበሰበሰ ነገር ነብስ ስለማይዘራ መፍትሄው ልክ እንደ እንቦጭ አራሙቻ መነቀል ብቻ ነው።
        ኢትዮጵያ ዛሬ እነ ሚሚ ስብሃቱ የሚቀልዱባት ሃገር ለመሆን መብቃትዋ የመዝቀጣቸው ምልክት ለመሆኑ ቀድሞውንም ወለል ብሎ ይታይ ነበር። አንድ ሺህ ኦሮሞ ሲገደል ለነሱ ዜና አይደለም፣ አስር ሺህ አማራ ሲፈናቀልም ዜና አይደለም፣ ኮንሶ እንደባርያ ንግድ በሰንሰለት እየታሰረ ሲገረፍም የነዚህ ሰዎችን ትኩረት አይስብም። አንድ የትግራይ ተወላጅ ሲገደል ግን ሰበር ዜና ሆኖ ሃገር ይደበላለቃል። የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው ካሉን፣ ስብእናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚጨምረው ይህ ነው። ማንነታቸው ጫፍ የሚፈተነው እዚህ ላይ ነው። የሰው ዘር ደሙ በካራት እየተለካ፣ የወርቅ፣ መዳብና ነሃስ ስያሜ ካመጣብን አገዛዝ ከዚህ የተሻለ ነገር አንጠብቅም።   
        አንዱን ዘር ከፍ ሌላውን ደግሞ ዝቅ በማድረጋቸው የተወደዱ በሚመስላቸው አድርባዮችና አሽቃባጮች ታጭቀው ረጅም መዝለቅ እንደማችሉ ይመስላል አዲስ ዘመንጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ "የአገር ጠንቆችን ይዞማዝገም ለህዝብ እና ለመንግስት አደገኛ" መሆኑንየገለጸው። "አይጥ ርሃብ ሲጠናባት የራስዋን ጅራት ትበላለች" ይባል የለ።
        ለማ መገርሳ በኦሮምኛ ቋንቋ በተደረገ አንድ ዘጋቢ ፊልም ላይ ነው "አውሬውን አቁስለነዋል።" ያሉት። ምን ለማለት እና፣ ማንን ለማለትም እንደፈለጉ ግልጽ ነው። አንድን ዘር ከሌላ ዘር እያጋጨ፣ ጎሳን ከጎሳ እያተራመሰ፣ ሃይማኖትና  ከሃይማኖት እንዳይተማመን እያደረገ የነበረው አውሬ ቆስሏል። ከ26 ዓማታት ስራው በኋላ ይህ ትውልድ የባነነበት አውሬ።  የቆሰለ፣ በሞት እና በህይወት መካከል ያለ አውሬ፣  መፍጨርጨሩ የግድ ነው። መሬት ልሶም የመነሳት እድል ይኖረዋል። ጣልያናዊው ማኪያቬሊ የሚለውም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። አልጋወራሹ ላይ ከተኮስክበት ጨርሰው፤ ካልጨረስከው ይመለስብሃል። በሳል ፖለቲከኞች የማይጨርሱትን አይጀምሩትም።
        በሽፍታ የምትተዳደር ሃገር፣ በሽፍቶች የሚገዛ ሕዝብ፤ ..        ስብዕናቸውን ባዋረዱ በፖለቲካ ዘገምተኛ ምሁራን ጭምብል ውስጥ ተጠቅልለው፣ ኢትዮጵያን እንደምስጥ እየቦረቦሩ፣ እንደ መዥገርም እየመጠጡ እስካሁን ዘልቀዋል።  አሁን ግን ቆስለው እየተወራጩ ይገኛሉ። "ሌባ ተብሎ ከመፈረጅ የበለጠ ውርደት በታሪክ ሊኖር አይችልም።" ይሉናል ለማ መገርሳ።
        እስካሁን የፖለቲካ ንግድ የሸቀሉበትን የሙትራዕይም መቀሌ ላይ ቀብረውት መጥተዋል።        የሟቹን መነጽር በሮቦቱ ሰው ላይ አድርገው፣  የጀመሩት 'የመለስ ራዕይ'  ፣ 'የመለስ ቅርስ' ፣'የመለስ ሌጋሲ' ፣ 'የመለስ ሕልም' እና 'የመለስውርስ' ሁሉ ብዙ አላስኬደም። እንዲያው ያልተሳካተውኔት ሆኖ አለፏል።    ይልቁንም ሰውዬውየአዜብን ደጅ ጠንተው ያገኟት የቤተ መንግስት ወንበር ዛሬ እሾህ ሆና እየወጋቻቸው መሆኑን እየተናገሩ ነው።
        ብዙዎች ሃገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆንዋን ሲናገሩ ይሰማል። አቅጣጫው በውል የማይታወቅ ግራ የሚያጋባ መንገድ። መስቀለኛ ሚሆነው መንገዱ ሲኖር አይደል?  በ እኔ እይታ ግን መንገድ የለም። ሁሉም ተዘጋግቷል። በሁሉም አቅጣጫ የተዘጋጋ መንገድ መጓዝ ቅርቃር ውስጥ መግባት እንጂ መስቀለኛ ሊሆን አይችም። 
        ከዚህም ከዚያም ብሶት እና ሕዝባዊ ማዕበል እንሰማለን። አመጹ፣ ስርዓቱን አላፈናፍን ያለው ይመስላል። ውጥረቱ ሊላላ የማይችልበት፣ እሳቱ  ሊጠፋም የማይችልበት ደረጃ ደርሷል። ግን የህወሃት ቀብር እስከመጨረሻው የሚፈጸመው፣ አዲስ አበባ ሲያምጽ ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው። መታሰር፣ መሰቃየት እና መገደልን ለምዶታል፣ መታረዝ እና መራብ አዲስ አይደለም። ውሃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ ... ሲፈልጉ የሚሉቅቁት ሲያሻቸው ደግሞ የሚከለክሉት ሕዝብ፣ አይቶ እንዳላየ ይምሰል እንጂ ልቡ ሸፍቷል። ይህ ህዝብ ጽዋው ሞልቶ እለት የት እንደሚገቡ እናያለን።
        አመጽ በቀጠሮ አይነሳም። መምጫው ባይታወቅም፣ ምልክቶች ግን ይታያሉ።
        "መጀመሪያ ይንቁሃል። ከዚያ ቀጥሎ ይስቁብሃል። ገፋ ብለው ይጣሉሃል።... በመጨረሻ ግን ታሸንፋቸዋለህ!"  ማህተመጋንዲ።

No comments: