Wednesday, December 27, 2017

ለማ መገርሳ "አውሬውን አቁስለነዋል፤ ይህ ግን በቂ አይደለም" እያሉ ነው


December 27,2017

ክንፉ አሰፋ
  "አውሬው ቆስሏል*። ቆስሎ ስላልተኛ፣ ማቁሰሉ ብቻ በቂ አይደለም። ተመልሶ እንዳይመጣ እርግጠኞች መሆን አለብን።" የሚለው ቃል የወጣው ከ"ጽንፈኛው ዲያስፖራ" ወይንም ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አይደለም። ከአውሬው ጋር አጋር ሆኖ ከሚሰራ ድርጅት መሪ ነው። ያውም በገዥው ፓርቲ ልሳን። የ26 ዓመቱ ፖለቲካ እየተንከባለለ እዚህ ላይ ደርሷል። አንድ ሰው እውነትን በመናገሩ ጀርባው ተጠንቶ፣ ደሙ ተለክቶ፣ ግንባሩ ተገላልጦ፣  በሽብር በሚፈረጅባት ሃገር ውስጥ፣ ጥቂቶች የእድሜ-ልክ ፈራጅ ሆነው በተሰየሙበት ሃገር ይህ ተከሰት። እነ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አንዷለም አራጌ ከዚህ የባስ ነገር አልተናገሩም። በፍትህ ስም የሚቀለድባቸው እነ ፕ/ር መረራ ጉዲና እና በቀለ ገርባ ይህችን ያህል እንኳን አልተነፈሱም።
        መቀሌ ላይ በዝግ ስብሰባ፣ አዲስ አበባ ላይ በዝግ ስብሰባ፣ ፓርላማውም በዝግ ስብሰባ። ሁሉም ተዘጋግቷል። በሃገሪቱ እና በህዝቧ ላይ በዝግ ይዶለታል። ለመፍትሄ ሳይሆን ስልጣን ይዶለታል። በግልጽ ሳይሆን በድብቅ ይዶለታል።  መቶ በመቶ መርጦናል ላሉት ሕዝብ ችግሩን ለመደበቅ ይሞክሩ እንጂ፣ ምጣድ ላይ እንዳለ ቡና የሚያምሳቸው ነገር አደባባይ ላይ እንደተሰጣ እንኳ አልባነኑም። ስውር ድርጊታቸው እየገዙት ላለው ሕዝብ ባይተዋር ስለመሆናቸው ማስረገጫ ይሆናል።  
        ለ35 ቀናት መቀሌ ላይ ዘግተው የዶለቱት፣ ከዚያም አልፈው የነቀሉት እና የተከሉት ነገር፣ መስመር እንደያዘላቸው ተናግረዋል። የህልውናቸው መሰረት የሆነው የመደምሰስ እና የመቆጣጠር ፖሊሲ፣ የህወሃት ስብሰባ ላይ ሰርቶላቸው ሊሆን ይችላል። ሰሜን ላይ ያበጠውን ጎማ አተንፍሰው ሲያበቁ፣ ስንቅ እና ትጥቅ ይዘው ወደ ሸገር ነበር የዘመቱት። እነ ለማን ለማንበርከክ፣ እነ ገዱን ለመጠምዘዝ።
        የሸገሩ ዱለታ እንደታሰበው አልሄደም።   የመቀሌውን የፖለቲካ ፎርሙላ የአዲስ አበባው ኢህአዴግ ስብሰባ ላይ ለመተግበር መጣራቸው ጅል ያደረጋቸው ነው የሚመስለው። ወትሮውን  እንደሮቦት የሚታዘዙ አጋሮቻቸው ባትሪያቸውን እንደጨረሱ አላስተዋሉትም።  በሞግዚት አስተዳደሩን ቀጥሉበት-አንቀጥልም ትንቅንቅ፤  በቀድሞው የኢህአዴግኛ  ቋንቋ መግባባት አልቻሉም። እነ ለማ መገርሳን እንደ ቀድሞው ለማዘዝ የማይችሉበት ቅርቃር ውስጥ ተሸንቁረዋል።  
        የትርምሳቸው ክብደት በኪሎ ባይመዘንም፣ ከጥልቅ ተሃድሶ ወደ ጥልቅ ዝቅጠት መግባታቸውን ግን በይፋ ነግረውናል።  ትላንት በስብሰናል ብለው ነበር፣ ዛሬ ዘቅጠናል ብለዋል። ነገ ደግሞ ተልተናል ማለታቸው የሚጠበቅ ነው። የበሰበሰ ነገር የሚያዘግመው ወድዚያው ነው።
        እዚያ አካባቢ ነገሮች በፍጥነት ተቀያይረዋል።  እንደጅብ ከተሰበሰቡበት ዋሻ ለአፍታ ወጣ አሉና  በብሄራዊ ቴሌቪዥን፣ "ሰላም ነን" ለማለት ሞክረው ነበር። "ውስጡን ለቄስ" አሉ። በዚህ አባባላቸው፤ ጉልበታቸውና ፀጋቸዉእንደበግ ቆዳ ከላያቸው ተገፍፎ እንደሄደ ለማወቅ የፖለቲካ ተንባይ መሆን አያስፈልግም።
        "በመሃላችን የርስበርስ መተማመን ጠፍቷል!" ይላል በዝጉ ስብሰባ መሃል የተሰጠው መግለጫ። ይህንን መግለጫ በገለልተኛ ሜድያ ብንሰማው ኖሮ ላይደንቀን ይችላል። እንግዳ የሆነብን ይህንን መግለጫ በራሳቸው ልሳን መስማታችን ብቻ ሳይሆን፣ ስብሰባው ገና ሳያልቅ መግለጫ መልቀቃቸው ነው። አሁንም ሃገሪቱ የገባችበት ችግር ያስጨነቃቸው አይመስልም። እነሱን እንቅልፍ የነሳቸው አይበገሬ ብለው ያሰቡት የስልጣን ግንዳቸው መንገዳገዱ ነው። ይህንን ሕዝብ መቶ አመት ለመግዛት የወጣው የባለ ራዕዩ እቅድ መሃል ላይ መክሸፉ ነው ይበልጥ የሚያሳስባቸው።
        በመግለጫቸው እርስበርስ ተከፋፍለናል ማለትን በመጸየፋቸው፤ አደባባይ የወጣ ክፍፍሉን "መተማመን ጠፋ" በሚል ቃል ሊያሽሞነሙኑት ሞከሩ።  መዝቀጣቸውን ግን አልካዱትም።  ታዲያ ምን ይጠብቃሉ? የዘቀጠ እና የበሰበሰ ነገር ነብስ ስለማይዘራ መፍትሄው ልክ እንደ እንቦጭ አራሙቻ መነቀል ብቻ ነው።
        ኢትዮጵያ ዛሬ እነ ሚሚ ስብሃቱ የሚቀልዱባት ሃገር ለመሆን መብቃትዋ የመዝቀጣቸው ምልክት ለመሆኑ ቀድሞውንም ወለል ብሎ ይታይ ነበር። አንድ ሺህ ኦሮሞ ሲገደል ለነሱ ዜና አይደለም፣ አስር ሺህ አማራ ሲፈናቀልም ዜና አይደለም፣ ኮንሶ እንደባርያ ንግድ በሰንሰለት እየታሰረ ሲገረፍም የነዚህ ሰዎችን ትኩረት አይስብም። አንድ የትግራይ ተወላጅ ሲገደል ግን ሰበር ዜና ሆኖ ሃገር ይደበላለቃል። የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው ካሉን፣ ስብእናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚጨምረው ይህ ነው። ማንነታቸው ጫፍ የሚፈተነው እዚህ ላይ ነው። የሰው ዘር ደሙ በካራት እየተለካ፣ የወርቅ፣ መዳብና ነሃስ ስያሜ ካመጣብን አገዛዝ ከዚህ የተሻለ ነገር አንጠብቅም።   
        አንዱን ዘር ከፍ ሌላውን ደግሞ ዝቅ በማድረጋቸው የተወደዱ በሚመስላቸው አድርባዮችና አሽቃባጮች ታጭቀው ረጅም መዝለቅ እንደማችሉ ይመስላል አዲስ ዘመንጋዜጣ በርዕሰ አንቀፁ "የአገር ጠንቆችን ይዞማዝገም ለህዝብ እና ለመንግስት አደገኛ" መሆኑንየገለጸው። "አይጥ ርሃብ ሲጠናባት የራስዋን ጅራት ትበላለች" ይባል የለ።
        ለማ መገርሳ በኦሮምኛ ቋንቋ በተደረገ አንድ ዘጋቢ ፊልም ላይ ነው "አውሬውን አቁስለነዋል።" ያሉት። ምን ለማለት እና፣ ማንን ለማለትም እንደፈለጉ ግልጽ ነው። አንድን ዘር ከሌላ ዘር እያጋጨ፣ ጎሳን ከጎሳ እያተራመሰ፣ ሃይማኖትና  ከሃይማኖት እንዳይተማመን እያደረገ የነበረው አውሬ ቆስሏል። ከ26 ዓማታት ስራው በኋላ ይህ ትውልድ የባነነበት አውሬ።  የቆሰለ፣ በሞት እና በህይወት መካከል ያለ አውሬ፣  መፍጨርጨሩ የግድ ነው። መሬት ልሶም የመነሳት እድል ይኖረዋል። ጣልያናዊው ማኪያቬሊ የሚለውም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። አልጋወራሹ ላይ ከተኮስክበት ጨርሰው፤ ካልጨረስከው ይመለስብሃል። በሳል ፖለቲከኞች የማይጨርሱትን አይጀምሩትም።
        በሽፍታ የምትተዳደር ሃገር፣ በሽፍቶች የሚገዛ ሕዝብ፤ ..        ስብዕናቸውን ባዋረዱ በፖለቲካ ዘገምተኛ ምሁራን ጭምብል ውስጥ ተጠቅልለው፣ ኢትዮጵያን እንደምስጥ እየቦረቦሩ፣ እንደ መዥገርም እየመጠጡ እስካሁን ዘልቀዋል።  አሁን ግን ቆስለው እየተወራጩ ይገኛሉ። "ሌባ ተብሎ ከመፈረጅ የበለጠ ውርደት በታሪክ ሊኖር አይችልም።" ይሉናል ለማ መገርሳ።
        እስካሁን የፖለቲካ ንግድ የሸቀሉበትን የሙትራዕይም መቀሌ ላይ ቀብረውት መጥተዋል።        የሟቹን መነጽር በሮቦቱ ሰው ላይ አድርገው፣  የጀመሩት 'የመለስ ራዕይ'  ፣ 'የመለስ ቅርስ' ፣'የመለስ ሌጋሲ' ፣ 'የመለስ ሕልም' እና 'የመለስውርስ' ሁሉ ብዙ አላስኬደም። እንዲያው ያልተሳካተውኔት ሆኖ አለፏል።    ይልቁንም ሰውዬውየአዜብን ደጅ ጠንተው ያገኟት የቤተ መንግስት ወንበር ዛሬ እሾህ ሆና እየወጋቻቸው መሆኑን እየተናገሩ ነው።
        ብዙዎች ሃገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆንዋን ሲናገሩ ይሰማል። አቅጣጫው በውል የማይታወቅ ግራ የሚያጋባ መንገድ። መስቀለኛ ሚሆነው መንገዱ ሲኖር አይደል?  በ እኔ እይታ ግን መንገድ የለም። ሁሉም ተዘጋግቷል። በሁሉም አቅጣጫ የተዘጋጋ መንገድ መጓዝ ቅርቃር ውስጥ መግባት እንጂ መስቀለኛ ሊሆን አይችም። 
        ከዚህም ከዚያም ብሶት እና ሕዝባዊ ማዕበል እንሰማለን። አመጹ፣ ስርዓቱን አላፈናፍን ያለው ይመስላል። ውጥረቱ ሊላላ የማይችልበት፣ እሳቱ  ሊጠፋም የማይችልበት ደረጃ ደርሷል። ግን የህወሃት ቀብር እስከመጨረሻው የሚፈጸመው፣ አዲስ አበባ ሲያምጽ ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው። መታሰር፣ መሰቃየት እና መገደልን ለምዶታል፣ መታረዝ እና መራብ አዲስ አይደለም። ውሃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ ... ሲፈልጉ የሚሉቅቁት ሲያሻቸው ደግሞ የሚከለክሉት ሕዝብ፣ አይቶ እንዳላየ ይምሰል እንጂ ልቡ ሸፍቷል። ይህ ህዝብ ጽዋው ሞልቶ እለት የት እንደሚገቡ እናያለን።
        አመጽ በቀጠሮ አይነሳም። መምጫው ባይታወቅም፣ ምልክቶች ግን ይታያሉ።
        "መጀመሪያ ይንቁሃል። ከዚያ ቀጥሎ ይስቁብሃል። ገፋ ብለው ይጣሉሃል።... በመጨረሻ ግን ታሸንፋቸዋለህ!"  ማህተመጋንዲ።

Thursday, November 2, 2017

የህውሃት የዘረኝነት ፓለቲካና መዘዙ ( ገዛኸኝ አበበ )

 November 2,2017


ወያኔ (ኢህአዲግ)የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ትልቁ የፖለቲካ አጀንዳ አድርጎ የተነሳው ሕዝብን ከሕዝብ ጎሳን ከጎሳ ሀይማኖትን ከሀይማኖት የፖለቲካ ድርጅትን ከፖለቲካ ድርጅት  በማጋጨትና በማጣላት ላይ ሲሆን ህሕዋት እያራመደ ባለው የዘርና የጎሳ ፖለቲካ የተነሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ከመቸውም ጊዜ በላቀ እና ታይቶ በመይታወቅ ሁኔታ የወያኔ መንግስት አሁን የኢትዮጵያን ህዝብ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልልና አካባቢ  ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነቱን እንዳያይ በዘር እየከፋፈለው ነው:: የህውሃ/ኢህአዴግ ገና ወደ ስልጣን ብቅ ሲል በጦርነት ከደርግ የሚረከባቸውን ቦታዎች ፣ዳገትና ቀበሌዎች ሁሉ በቤተሰብ ሳይቀር እየከፋፈለ በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች እያሰረ ልዩነታቸውን ብቻ እያሳየ ሌላ አማራጭ ያልነበረው ህዝብ ሲቀበለው ቆይቶ አሁን በክልል በዞን በወረዳ በቀበሌ እና ሰፈር ድረስ በዘርና በጎሳ ከፋፍሎ ይህ ወያኔ ከደደቤት በረሃ ይዞት የመጣው የዘረኝነት ፖለቲካ መዘዝ  ዘሬም በኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ  በየሰፈሩ አሁን የእንትን ሰፈር ልጅ ከእንትን ሰፈር ልጅ ጋር በጩቤ በድንጋይ ሲፈነካከት ሲተራረድ ማየት ምንም አዲስ ነገር አይደለም፡፡

የአንዱን ወረዳ ነዋሪ ከሌላኛው ወረዳ ነዋሪ ጋር በሆነ ባልሆነው ሲኮራረፍ ሲገዳደል ሲቀጣቀጥ ማየት ምንም አዲስ አደለም፡፡ አንዱ ዞን ከሌላኛው ዞን ጋር በስራቸው በሚያስተዳድሩት ህዝብ ስም ጥቅም እየነገዱ አንዱን ከአንዱ አባትን ከልጁ እናትን ከልጇ ወንድምን ከወንድሙ ምን አለፋችሁ በቃ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደምታዩት ጠላቶች ሆነን ስንጨራራስ ስንተራረድ እንገኛለን፡፡ሰው ከሰው ጋር ለምን ይጋጫል ለምን ይገዳደላል የሚለው እውነተ ውስጥ አልገባሁም እርሱ ራሱን የቻለ ተፈጥሯዊ ክስተት ስለሆነ፡፡በዛም አለ በዚህ የመከፋፈላችን የመጨረሻ ውጤትና ምክንያት ፍጅት ነው፡፡ ሆኖም ፍጅት ሲባል ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊነሳ የሚችለው ፍጅት እንደሁቱና ቱትሲ ይሆናል ብላችሁ ግን አታስቡት፡፡ መቸም ቢሆን ይህ ጉዳይ ሊከሰት አይችልም፡፡ በብሄር ግጭት ተነስቶ ኢትዮጵያ ሃገራችን ትጠፋለች አንድ ዘር ይጠፋል ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ ራሱን የቻሉ እውነተኛ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሌላው ዓለም ላይ የሌሉ ሃገራችን ውስጥ ግን እንደ ዕድል ብቻ ሆኖ ያሉ ነገሮች ሕዝባችን ሳይማር ተፈጥሮ ብቻ አስተምራ ያኖረችው ትውልድና ትስስር በመሆኑ ብቻ አብረውን የሚኖሩ እውነቶች አሉ፡፡

ወያኔ ኢህአዴግ ግን ከዞን እና ቀበሌ ባለፈ የመጨረሻ ሴራውን በክልል በቋንቋ፣ ዘር ፣ቀለም ወዘተ እያለ በባህል፣ በእምነት እያለ የሚታዩና የማይታንን ልዩነቶች እየፈጠረ በመካከላችን ምንም አይነት ችግርና  ሳይኖር በፍቅር የኖረን ሆነን ሳለን ህህዋት ከጅምሩ ይዞ የተነሳውን  በቋንቋና በዘር ልዩነት ላይ የተመሰረተው የፌደራል ሥርአትና ኢትዮጵያን የመሰነጣጠቅ ሴራው  አሁን ላይ ስር እየሰደደ መጥቶ በኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድን የመሳሰሉ የመሳሰሉ የወያኔ አለቅላቂዎችና  አሽከሩች ተጨምረውበት በእነዚህ የኢትዮያን ሕዝብ ደም መጣጭ ድርጅቶች በኩል እየተገበረ ያለውን ኢትዮጵያን የመሰነጣጠቅ እና ለአስተዳደር ለማመቻቸት በመሰለ ሴራና ተንኮል ህዝባችን አንድነቱ ፍርሶ አሞቱ ፈሶ ኢትዮጵያዊው ወኔ እንዲደርቅ በማድረግ ለራሳቸውየሚጠቅማቸውን ለህዝባችን እና ሃገራችን ግን ትልቅ የአንድነት ነቀርሳን ተክለውብን ምኞታቸውን እያሳኩ ይገኛሉ፡:

ይህ የወያኔ የዘረኝነት ፖለቲካ መዘዝ ስር እየሰደደ በጣም በአሳሳቢ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ አስከፊና አሳዛኝ የሆኑ የተለያዩ ችግሮች እየወለደ፤ ጸብና ግጭቶችን እያበራከተ የዜጎችን ሕይወት በቀላሉ እየቀጠፈና የሕዝቦችን ሀብት በማውደም፣ቤቶችን በማቃጠል መጥፎ ክስተት  እየተከሰተ ይገኛል። ከዚህ በፊት እንደምናስታውሰው  በምሥራቅ ኢትዮጵያ ደገሃቡርና ጅጅጋ፤ በምሥራቅ ሀረርጌ ጋራሙለታ፤ በደኖ አንስቶ በባሌና በአርሲ በሚገኙ አካባቢዎች በዘር ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችና የሰው ሕይወትና ንብረት የወደሙበት በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። በምዕራብ ኢትዮጵያም ቢሆን በተለያዩ ወቅቶች በአሶሳ በባምባሲ፤ በሰሪ፤ በጋምቤላ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ፤ ነቀምት፤ አምቦም ለዚሁ አስከፊ ሁናቴ የሚጠቀሱ ናቸው። በአርሲ ክፍለ ሀገር በአርባጉጉ አውራጃ ውስጥ በሚገኙ ጎሎልቻ፤ ጨሌ፤ ጃጁ፡ መርቂ በተሰኙ ወረዳዎችና አካባቢዎች በርካታ መኖሪያ ቤቶች የወደሙበት፤ ሕይወት የጠፋበት፤ የሰው ልጅ እንድ ከብት አንገትና ጡቶች የተቆረጡበት አሰቃቂና አሳዛኝ በድሎች ተካሂደዋል። በሌላ ቦታ ደግሞ ከነ ነፍሰሕይወታቸው ወደገደል ተውርውረው እንዲፈጠፈጡ የተደረጉም እንዳሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ እንዳየነው ለሳምንታት በዘለቀው በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት እንዲሁም በኢሊባቡር በአማራና በኦሮሞ ዜጎቻችን መካከል በተከሰተው ግጭት ለብዙ ሰዎችን መፈናቀልና ህይወት መጥፍት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለው  የእርስ በእርስ ግጭት ሆነ ተብሎ በህውሃት የበላይነት የሚመራው መንግስት በስልጣን ለመቆየት የሚጠቀምባቸው ስልቶች እንደሆኑ ሁላችንም ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል

በምንም መንገድ ከታሪካዊ አመጣጡም ቢሆን እንደተረዳነው ወያኔ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ አንድነት ሳይሆን የታገለው አሁንም የሚሮጠው ለእነዚህ አላማዎች ብቻ ነው፡፡ አንድም ታላቋ ትግራይን መመስረትና የአማራውን  ተሰሚነት አኮላሽቶ መቅበር ነው፡፡ለዚህም አማራውን ዝም ካልነው አያስቀምጠንምየሚለው የመለስ መፈክር በቂ ምስክር ሲሆን ይህንን የሚያረጋግጡም በርካታ የምስልና የድምፅ ቅጅዎች በተለያዩ ነፃነት ናፋቂ የየትኛውም ብሄር ታጋዮች እጅ ይገኛል፡ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩት መሪዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበረ ሕዝቡም አንድነቱን ጠብቆ እንዲኖር ብዙ መስዋትነትን  ከፍለዋል በወያኔ መንግስት እንደ አውሪ የሚቆጠረው ደርግ ሳይቀር ለኢትዮጵያ አንድነት ምሳሌ ናቸው ::ደርግ በርካታ አንቱ የሚያስብሉት ትግባራትን ፈፅሟል፡፡ በኋላም ለውድቀት የዳረገው በትክክል ደርግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠልቶት ሳይሆን በመካከላቸው በነበረው ተራ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት በነበራቸው የሃሳብ  መለያየት፣ ውስጣዊ ሴራ እና አማራጭ በማጣት አንድን የደርግ ወታደር በሁለት ብር ሂሳብ ለወያኔ በሰጡ ባስጨረሱ ጀኔራሎች ሴራ እንጅ በወያኔ ጥንካሬ እንዳልሆነ እውን ነው፡፡

የሚገርመው ግን የኢትዮጵያን አንድነት ለማጥፋት አላማ ይዞ የመጣው ወያኔ ስልጣን እንደያዘ የጀመረው የደርግን ጅማሮዎችን በሙሉ ከምድረ ኢትዮጵያ ማጥፋት እና ማቃጠል አንድነቷና ዳር ድንበሯ ተከብሮ የቆየውን ሀገሪቷን መሸጥና መቆራራጥ ሀገሪቷን ወደብ አልባ በማድረግ ለታሪክ መጥፎ የሆነ ጠባሳ ማስቀመጥ ነበር ይህንንም  ከሻቢያ ጋር በመሰማማት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አድርጎታል:: ወያኔ ኢህአዴግ አሁን የያዘው ስትራቴጅ ደግሞ የማያዋጣው ማጥ ውስጥ ስለከተተው የሚከተለው እንደ ትግሉ በግልፅ ራሱን በመገንጠል አላማ ማለትም የመሄድ ዓላማ ሳይሆን ተቃራኒውን ነው፡፡ ይህም ማለት አሁን በምኑም በምኑም ምንያት የከፋፈለውን ህዝብ የበለጠ በመከፋፈልና የመለያያ ታሪኮችን እንደመልካም አስተማሪ ታሪክ በመምዘዝ እና አደባባይ በማውጣት /ሆኑ አልሆኑ የሚለው ባይታወቅም ምንጭ ባይኖረውም/ አንዱን ከአንዱ በማፋጀት እራሱ መሄዱን ሳይጀምር ሌሎች በየአቅጣጫው እንዲሄዱ በማድረግ የተዳከመች ኢትዮጵያ የተፈረካከሰች ኢትዮጵያ ስትቀርበሉ እኔም የድርሻየን እናንተ ከሄዳችሁማብሎ ለመነሳት ነው ያሰበው፡፡ አንድ ልናውቀው የሚገባ  እውነት  ይህች ሃገር በፍጹም ልትበታተንና ልትጠፋ አትችልም:: ይህንም ውሃቶችና የወያኔ ተላላኪ፣ተለጣፊዎቹ ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድ ያወቁት አይመስለኝም  ፡፡ ይህ ህዝብ አንድ ሆኗል በወያኔ ተንኳልና ሴራ አሁን ላይ በተለያዩ ነገሮች ቢጋጭም የተጋባ፣ የተዋለደ፣አብሮ የበላና ፣የጠጣ አብሮ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲል የታዋጋ የደማና የቆሰለ ሕዝብ ነው :: ይህ እውነታና ሚስጥር ያልገባቸው አንዳንድ የወያኔ ኢህአዴግ ሴራ ማስፈጸሚያና መጠቀሚያ መሆናቸውን ያላወቁ በስሜት የሚነዱ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ናቸው፡፡ስለሆነም የኦሮሞው፣የአማራው፣የአፋሩ፣የትግራዩ፣የጋምቢላው ........ሕዝብ የወያኔ የዘር ፖለቲካ ማስፈጸሚያ እንዳይሆን ሊጠነቀቅ ይገባል እያልኩኝ እዚህ ላይ ላጠቃልል:: ውድቀት ለዘረኛው የወያኔ አገዛዝ !!

የኢትዮጵያ አንድነት ለዘላለም ተጠብቆ ይኖራል!!

gezapower@gmail.com