Monday, October 16, 2017

አቶ በረከት ስምኦን ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ።


October 16,2017

በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሪ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ።
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት አቶ በረከት የሥራ መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አስገብተዋል።
አቶ በረከት ስምኦን ለበርካታ ዓመታት በቦርድ ሰብሳቢነት ሲመሩት ከነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሊለቁ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ተነግሯል።
አቶ በረከት ባለፈው ሳምንት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስገባታቸው የተነገረ ሲሆን፤ ለመጨረሻ ጊዜ በቢሮአቸው ተገኝተው የነበሩት ሀሙስ ዕለት ነበር።
አቶ በረከት በተመሳሳይ ጊዜ ከሁለት የሃላፊነት ቦታቸው የተነሱ ሲሆን ለሥራ መልቀቃቸው ግልፅ ያለ ምክንያት አልቀረበም።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ብዙም ደስታኛ እንዳልነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ።
በተለይ ማዕከሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚያቀርባቸው ሃገር አቀፍ የፖሊሲና የአስተዳደር ጥናቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩና በመንግሥት ከፍተኛ ሃላፊዎች ዘንድ ብዙም ተቀባይነት አግኝተው ተግባራዊ አለመደረጋቸው ለቅሬታቸው ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
ቢሆንም ግን በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ያላቸውን ሃላፊነት ለመልቀቅ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት እንዳላቸው ማረጋገጥ አልተቻለም።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል በአቶ አባይ ፀሐዬ ዋና ዳይሬክተርነት የሚመራ ተቋም ነው።
አቶ በረከት ስምኦን ከቀደምት የኢህአዴግ አመራሮች መካከል የሚመደቡ ሲሆን የገዢው ፓርቲ አንድ አካል የሆነው የብአዴን አመራር አባል ናቸው።
አቶ በረከት ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊነቶች ላይ የቆዩ ሲሆን፤ የማስታወቂያ ሚኒስትርና የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል