December 19/2013
-የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ ጠይቀዋል
ቀደም ሲል የኢትዮጵያንና የኤርትራን የድንበር ግጭት በቅርበት ከሚከታተሉት መካከልበአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መምርያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት፣ ሚስተር ኸርማን ሐንክ ኮኸን፣ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በማስታረቅ‹‹ጊዜው አሁን ነው›› በማለት የመፍትሔ ሐሳብ ይዘው ቀረቡ፡፡
“Time to Bring Eritrea in from the Cold” [ኤርትራን መታደግ አሁን ነው]
በሚል ርዕስ ‹አፍሪካን አርጉመንትስ› በሚባል ታዋቂ ሚዲያ ላይ በታተመው ጽሑፋቸው፣ በድንበር ግጭቱ የተነሳ ‹‹ሰላምና ጦርነት አልባ›› ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያና ኤርትራን ለማስታረቅ ትክክለኛ ጊዜው አሁን ነው ያሉበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊንና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አቀራርበው በችግሩ ላይ ለማነጋገር ሙከራ ማድረጋቸው የሚነገርላቸው ኸርማን ኮኸን፣ በአሜሪካ መንግሥት በአፍሪካ ጉዳዮች ተሰሚነት ካላቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በሁለቱም አገሮች መካከል ዕርቅ መፍጠር ትክክለኛ ጊዜው አሁን ለመሆኑ አንዳንድ መንደርደርያ ሐሳቦች ጠቁመዋል፡፡
ከአልቃይዳ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያለውንና በሶማሊያ ለሚንቀሳቀሰው አክራሪ ቡድን አልሸባብ ወታደራዊና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ታደርጋለች በማለት በኤርትራ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሁለት ጊዜ በጦር መሣሪያ ዝውውርና በአንዳንድ ባለሥልጣናት እንቅስቃሴ ላይ ማዕቀብ የጣለ መሆኑ ሲታወስ፣ ኸርማን ኮኸን ግን እ.ኤ.አ. ከ2009 ጀምሮ የኤርትራ መንግሥት ለአልሸባብ ድጋፍ ስለማድረጉ አንድም ማስረጃ የለም ብለዋል፡፡
እሳቸው ራሳቸውን እንደ እማኝ በመቁጠር፣ ‹‹እኛ ኤርትራን በደንብ የምናውቃት ሰዎች፣ የኤርትራ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ እስላማዊ አክራሪነት እንዳይስፋፋ ከሚፈሩ አገሮች እኩል ሥጋት ያለው እንደሆነ እንገነዘባለን፤›› ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ‹‹አስመራ ድረስ በመሄድ መደራደር እፈልጋለሁ፤›› ማለታቸውንና በቅርቡም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ‹‹ኤርትራ ያለ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታዋ ጨለማ ነው፤›› መናገራቸውን አውስተው፣ በድንበር ግጭቱ ሳቢያ የተካሄደው ጦርነት ሁለቱ አገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ እንዲቀጥሉ ምንም ምክንያት እንደሌለ ጽፈዋል፡፡
ቀደም ሲል በቀረበው ምክንያት ከኤርትራ ጋር መልካም ግንኙነቱን ጠብቆ ቆይቷል ያሉት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነው የአውሮፓ ኅብረት አባል አገር ጥያቄ አቅራቢነት፣ በኤርትራ ላይ የተጣለው ‹‹ሪዞሉሽን 1907›› በመባል የሚታወቀው ማዕቀብ እንዲነሳ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል፡፡
በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ በአሜሪካ አነሳሽነት መሆኑን በጽሑፋቸው ያሰፈሩት ኸርማ ኮኸን፣ አሜሪካ ማዕቀቡ እንዲነሳ ለሚቀርብ ጥያቄ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ከማድረግ ይልቅ የመፍትሔ ሐሳቡ ተባባሪ እንድትሆን ጠይቀዋል፡፡
ቀጥለውም የሁለቱም አገሮች የድንበር ውዝግብ አጣብቂኝ ያበቃ ዘንድ ኢትዮጵያ በድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት ለኤርትራ የተወሰነውን ግዛት ለመስጠት ፈቃደኛ እንድትሆን፣ ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸው ቀድሞ ወደነበረበት እንዲመለስ አጠቃላይና ግልጽ ውይይት እንዲያደርጉ መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ አንድ ገለልተኛ የሆነ አውሮፓዊ አገር ይህንን ዕርቅ እንዲጀምር በመጠየቅ፡፡
የዕርቁ ውጤት በሁለቱም አገሮች መካከል ተቋርጦ የነበረው ንግድ እንዲቀጥል፣ ኢትዮጵያ የኤርትራን የባህር ወደቦች እንድትጠቀም፣ ሁለቱም አገሮች ከዚህ ግንኙነት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መስማማቱ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡ ይህም በሁለቱ አገሮች ይፈጸማል በሚባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ለመነጋገር እንደሚያመችና በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በአሜሪካና በኤርትራ መካከል ወታደራዊ ትስስር ለማድረግ በር ይከፍታል ሲሉ አማራጭ ሐሳባቸውን ይደመድማሉ፡፡
ኸርማን ሐንክ ኮኸን የዛሬ 23 ዓመት ገደማ በደርግ መንግሥትና በኢሕአዴግ መካከል በለንደን ሊደረግ ታስቦ የከሸፈው ውይይት አደራዳሪ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ድርድሩ የከሸፈው ኢሕአዴግ በፍጥነት እየገፋ አዲስ አበባ በመቃረቡ ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment