Sunday, December 15, 2013

“መድረክ”ሠላማዊ ሠልፍ ተከልክያለሁ፤ አፈናውም በርትቶብኛል አለ

December 15/2013

አመራሩ ለጠ / ሚኒስትሩ ደብዳቤ አስገብተናል ብሏል


የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ; ባልወጣ ህግ እና የባቡር ፕሮጀክቱን ሠበብ በማድረግ , በአዲስ አበባ ለማካሄድ ያቀዳቸውን ሠላማዊ ሠልፎች እንዳይካሄድ መከልከሉን አስታወቀ . ፓርቲው ; የሠላማዊ ተቃውሞን መንገድ መዝጋትና የዜጐችን ህገ - መንግስታዊ መብቶች ማፈን በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል . የመድረኩ አመራሮች በትናንትናው እለት በፓርቲው ፅ / ቤት ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ ; ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ . ም በኢህአዴግ እየተፈፀሙ ናቸው ያላቸውን ኢ - ሠብአዊና ፀረ ዲሞክራሲያዊ የመብት ጥሠቶችና ህገ - መንግስቱን የሚፃረሩ ህጎችና አዋጆች እንዲሻሻሉ ወይም እንዲቀሩ ለመጠየቅ አዘጋጅቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ , የባቡር ሃዲድ ስራን በማሳበብ መከልከሉን ገልጿል .

በተመሳሳይ ህዳር 8 ቀን 2006 ዓ . ም በሳውዲ አረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ የደረሰውን ግፍ ለመቃወም አዘጋጅቶት የነበረው ሰላማዊ ሰልፍም " ፀጥታ የሚያስከብር የፖሊስ ሃይል የለኝም " በሚል ሰበብ በመንግስት እንደተከለከለ መድረኩ ገልጿል . ለ 3 ኛ ጊዜ ያዘጋጀውና በአገሪቱ አሳሳቢ ናቸው ያላቸውን ፖለቲካዊ , ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመንግስት ለማሳሰብ , ህዳር 29 ቀን 2006 ዓ . ም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ , እውቅና ሰጪው አካል በይፋ ያልወጣና ገና በህትመት ላይ የሆነን ደንብ በመጥቀስ " የጠየቃችሁበት ስፍራ ሰላማዊ ሰልፍ የማይካሄድባቸው ቦታዎች ተብለው የተጠቀሱ በመሆናቸው , ለተጠየቀው ሰላማዊ ሰልፍ እውቅና መስጠት አንችልም " የሚል መልስ እንደሰጠ በመግለጫው አመልክቷል .

የፓርቲው የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ / ር መረራ ጉዲና በሰጡት ማብራሪያ ; ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እየታፈነ በመሆኑ , ህዝቡ ብሶቱን ማሰማት የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል ብለዋል . " ሰልፍ በምድር አይቻልም ተብለናል ; ሰማይ ላይ እናደርግ እንደሆን አናውቅም ያሉት ዶ / ር መረራ , በሳውዲ ግፍ ለተፈፀመባቸው ወገኖቻችን እንኳን ብሶታችንን እንዳናሰማ መከልከሉ ኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ግራ እንድንገባ አድርገናል ብለዋል . የመድረክ አመራር አባል አቶ አስራት ጣሴ በበኩላቸው ; በማይታወቅና ገና ባልፀደቀ ህግ መመሪያ እየተሰጠ መሆኑን አመልክተው , " ይህቺ ሃገር በአሁን ሰዓት በህገ መንግስቱ እየተመራች ነው " ብዬ አላምንም ብለዋል .

መንግስት በነዚህ እርምጃዎቹም ብዙዎችን ከሰላማዊ ትግል እንዲወጡና ወደ ጠመንጃ አማራጭ እንዲገቡ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል . ሌላው የመድረክ አመራር አባል አቶ ገብሩ ገ / ማርያም ; የሰላማዊ ሰልፉን መከልከል እንዲሁም ሃገሪቱ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የሚያሳስብ ደብዳቤ ሃሙስ እለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማድረሳቸውን ተናግረዋል . መንግስት ሰላማዊ ሰልፎቹን ከማገዱም በተጨማሪ የዜጎች እንቅስቃሴ በሙሉ ከራሱ ጋር ብቻ እንዲቆራኝ ለማድረግ 1 ለ 5 የሚባል የስለላ , የቁጥጥርና የአፈና መዋቅራዊ ወጥመድ መዘርጋቱን የመድረክ አመራሮች ገልፀዋል . በዚህ መዋቅርም በምርጫ ወቅት የዜጎችን ነፃና ሚስጥራዊ የድምፅ አሰጣጥ መብት ለማፈንና ለመጣስ እንዲሁም የእያንዳንዱን ዜጋ ፖለቲካዊ አቋምና አስተያየት , የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን ጭምር ለማፈን እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት " በዚህም ኢህአዴግ የእኛን ድምፅ እያፈነና እንዳንንቀሳቀስ እያደረገ , ለራሱ የተጠናከረ የምርጫ ቅስቀሳና ዝግጅት ከወዲሁ ጀምሯል " ብለዋል . ኢህአዴግ እንዳንቀሳቀስ አድርጎናል ካላችሁ ቀጣዩን ምርጫስ እንዴት ልትወጡት ነው የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው የመድረኩ አመራሮች ; ምንም እንኳ ጫናው ቢበረታብንም ውስጥ ለውስጥ ስራችንን እየሰራን ነው ; ነገር ግን እንደዚህ ቀደሙ የምርጫው አጃቢዎች ብቻ ሆነን ለመቅረብ አንፈልግም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል . የመድረኩ ሊቀመንበር ዶ / ር መረራ ; የ 1 ለ 5 አደረጃጀት እሳቸው በሚያስተምሩበት ዩኒቨርስቲም መግባቱን አመልክተው ; ኢህአዴግ አባይ ሣያልቅ ስልጣን አለቅም እያለ ቢሆንም , በአንድ ወር ስራ ብቻ በምርጫ ሊሸነፍ የሚችል ፓርቲ ነው ብለዋል 

No comments: