Saturday, December 28, 2013

በሳውድ አረቢያ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ ዘረኝነትና ሙስና ተስፋፍቷል ተባለ

December 27/2013

ታህሳስ ፲፰( አስራ ስምንት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢሳት ከቆንስላው ባገኘው የውስጥ መረጃ በሃላፊነት ላይ የተመደቡት አምስቱ ዲፕሎማቶች በዘረኝነትና በሙስና ከመዘፈቃቸው ም በተጨማሪ ሊሴ ፓሴ ለማውጣት ወደ ቆንስላው የሚደውሉትን ስደተኞች በስብሰባ ሰበብ የሉም በማስባል ጉዳያቸውን እያስፈጸሙ እንደልሆነ ተመልክቷል። ከአንድ ወር በፊት ከ160 ሺ በላይ ህዝብ የተፈናቀለበትን ችግር ለማወቅ በቆንስላው የተገኙትና ከዲፕሎማቶች ውጭ ያሉ ሰራተኞችን ብቻ በመሰብሰብ ” የችግሩ ምንጭ ምንድነው በማለት?” የተወያዩት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ለዚህ ሁሉ ችግር መፈጠር መንስኤ በሆኑት ዲፕሎማቶች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረው የነበረ ቢሆንም እስካሁን የወሰዱት እርምጃ አለመኖሩ ታውቋል።

“የመኖሪያ ፈቃድ የላችሁም” በሚል ምክንያት ኢትዮጵያውያን ከሳውድ አረቢያ እንዲወጡ ሲታዘዙ፣ ከዚህ ቀደም በቋሚነት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ 24 የቆንስላው ሰራተኞችን የሚያግዙ በአገሪቱ የሚኖሩ 40 ድጋፍ ሰጪ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ህዳር 12 ቀን 2006 ዓም ለ3 ወራት በሚቆይ የኮንትራት ጊዜ ተቀጥረዋል። ከተቀጠሩት 40 ሰራተኞች መካከል 30 ዎቹ  ሰራተኞች የተቀጠሩት የዲፕሎማቶች የቅርብ ቤተሰቦችና ዘመዶች ናቸው። አብዛኞቹ ሰራተኞችም የተቀጠሩት የዘር ማንነታቸው እየታየ ሲሆን ከተቀጣሪዎቹ መካከል እንግሊዝኛ፣ አማርኛና አርበኛ ከማይናገሩት ጀምሮ ማስተርስ እና የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ይገኙበታል።

ከተቀጣሪዎቹ መካከል የተሻለ የትምህርት ደረጃና ብቃት ያላቸው 10 ሰዎች ከአንድ ወር በሁዋላ ታህሳስ 14 ቀን  ተመርጠው እንዲባረሩ ሲደረግ 30 ዎቹ የዲፕሎማቶች ቤተሰቦች እንዲቆዩ ተደርጓል። አስሩ ሰዎች እንዲባረሩ የተደረጉት ከመባረራቸው ከአንድ ሳምንት በፊት  ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰባቱበቋሚነት እንዲቀጠሩ ደብዳቤ መላኩን ተከትሎ ፣ በትምህርት ደረጃና በችሎታቸው የተቀጠሩትን አስቀድሞ በማባረር እና ውድድር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ የዲፕሎማቶችን ቤተሰቦች  እድሉን እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። በቆንስላው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ከ1 ሺ 300 እስከ 1 ሺ 500 ሪያድ የሚከፈላቸው ሲሆን፣ ለአዲሶቹ የሚከፈላቸው 2000 ሪያድ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ የቆንስላውን ዲፕሎማቶች በማግለል ሰራተኞችን በዝግ ስብሰባ ያነጋገሩ ሲሆን፣ ሰራተኞችም የሳውድ አረቢያ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ችግር አንድ ባንድ ዘርዝረው በድፍረት ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስዱ ለሰራተኞች ቃል ገብተው የሄዱ ቢሆንም እስካሁን ምንም እርምጃ ባለመውሰዳቸው ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል።

አንደኛው ዲፕሎማት 9 ዘመዶቹን ሲያስቀጥር፣ ሌላዋ ደግሞ 8 ቤተሰቦቿንና የብሄሩዋን ልጆች ብቻ በመምረጥ አስቀጥራለች። ቀሪዎቹ 13 ሰዎች ደግሞ የሌሎች ዲፕሎማቶች ዘመዶችና ወዳጆች ናቸው።

ዲፕሎማቶቹ በሳውድ አረቢያ የሚኖራቸው ቆይታ ከ4 አመት የማይዘል በመሆኑንም ጊዜያቸውን ሀብት በማከማቸት እንደሚያጠፉ ታውቋል። ምንም እንኳ መንግስት ወደ ሳውድ አረቢያ የሚደረገው ህገወጥ ጉዞ እንዲቆም ቀደም ብሎ መመሪያ ቢያስተላልፍም፣ በሳውዲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሊቀመንበር አማካኝነት የህገወጥ የሰዎች ዝውውር በዲፐሎማቶች አማካኝነት ሲካሄድ መቆየቱን መረጃው ያሳያል።

በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሊሴ ፓሴ እንዲሰራላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ፣ ዲፕሎማቶቹ ” ስብሰባ ላይ ናቸው” በሚል ለጥያቄያቸው መልስ እንደማይሰጡ መረጃው ያመለክታል።  የሳውዲው ችግር እንደተፈጠረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለዲፕሎማቶቹ በሰጡት ጥብቅ ትእዛዝ ለአንድ ወር ያክል ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ከ130 ሺ በላይ ሰዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ቢችሉም፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው መመለሳቸው ታውቋል። በእስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሁንም ሊሴ ፓሴ እንዲሰራላቸው በተደጋጋሚ ወደ ቆንስላው ስልክ እንደሚደውሉ ቢታወቅም፣ አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑ ግን ታውቋል።

No comments: