Thursday, December 12, 2013

በፖለቲካዊ ውሳኔ የህዝብን ስነልቦና መርታት አይቻልም!!! (ድምፃችን ይሰማ)

December 12, 2013
35151fd67b1e0d781375561649
ለህዳር 23 ተቀጥሮ የነበረው በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ የተመሰረተው ክስ የውሳኔ ቀጠሮ የህግ አግባብነት በሌለው እና የፍርድ ቤቶችን ከፖለቲካዊ ተፅእኖ ነፃ በሆነ መልኩ የመንቀሳቀስ ዴሞክራሲያዊ መርህ በጣሰ አካሄድ ወደ ታህሳስ 3 መዛወሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ መረጃዎች አሁንም ቢሆን ማስተማመኛ ባይኖራቸውም ፖለቲካዊ ብይን የሚሰጥበት የፍርድ ቤት ውሎ ‹አንድ ቀን› መዋሉ አይቀርም፡፡ የሃገራችን የፍትህ ስርአት በመርህ፣ በህግ እና በእቅድ መመራቱ ቀርቶ ‹‹አንድ ቀን ይሆናል›› ወደሚባልበት ደረጃ መውረዱ ዜጎችን እንቅልፍ የሚያስወስድ ጉዳይ አይደለም፡፡Ethiopian Musilms
ፖለቲካዊ ብይን በሚሰጥበት ፍርድ ቤት በአግባቡ የተጠኑ ‹‹ህዝበ ሙስሊሙን በደስታም ሆነ በሃዘን ዝም ያሰኛሉ›› ተብለው የሚገመቱ አማራጮችን በሙሉ መንግስት በጥንቃቄ እንዳጤነ ይታመናል፡፡ እንደ ህዝብ ዝም የሚያስብል መፍትሄ ካልተገኘ ደግሞ ‹‹ህዝብን ሊከፋፍሉ ይችላሉ›› ተብለው የሚታሰቡ የውሳኔ አማራጮች በፍርድ ስርአት ሳይሆን በፖለቲከኞች ጠረጴዛ ላይ ቀርበው ሲነሱና ሲጣሉ እንደከረሙም ጥርጥር የለውም፡፡ የመረጃ ምንጮች አስተማማኝ መሆናቸውን የማጣራት ጉዳይ እንጂ ፖለቲካዊ ውሳኔው ምን መልክ እንዳለውም ፍንጭ ተገኝቷል፡፡ በየትኛውም ውሳኔ ላይ ይስማሙ የፖለቲካ ውሳኔው በህዝብ ላይ የሚሰጥ መሆኑን ግን እነሱም እኛም ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡
በውሳኔው ከ28ቱ ተከሳሾች አንዱም ነፃ ተብሎ ቢለቀቅ እስከ ዛሬ በግፍ የተሰቃየው መላው ሙስሊም ላነሳው የመብት ጥያቄ በመሆኑ ያ ሰው ጀግናችን ነው፡፡ በሰላማዊ ትግላችን የነበረው ሚና የጎላ ሆነም አልሆነም በእንደኛ አይነቱ ህዝባዊ የመብት ትግል ውስጥ መሪን ከተመሪ፣ እንዲሁም ደጋፊን የምንለይበት መስፈርት አይኖረንም፡፡ ሁሉም የትግላችን ፋኖዎች የጉዟችን ገፈት ቀማሾች ናቸው፡፡ ዛሬ በመላው ሃገሪቱ ከሰላማዊ ትግላችን ጋር በተያያዘ በእስር የሚገኙት ሁሉ ከወንጀል ነፃ መሆናቸውን ህዝብም መንግስትም ያውቃል፡፡ ከ28ቱ የሰላም አርበኞች አንዱም ነፃ ቢባል ነፃ መሆኑን የምናውቀው የትግል ጀግናችን በመሆኑ በደስታ እንቀበለዋለን፡፡ ከዚህ በተቃራኒ አንድ ሰው ላይም በፖለቲካዊ የፍርድ ሂደት የጥፋተኝነት ውሳኔ ቢሰጥበት ደግሞ አሁንም መላው ሙስሊም በመንግስት ፖለቲካዊ ፍርድ እስር ቤት እንደታጎረ ይቆጠራል፡፡ ህዝብ ደግሞ ነፃነቱን ተነፍጎ በእስር ተቀፍድዶ የሚቆይበት ታሪክ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እንደማይሳካ በተግባር እናረጋግጣለን፡፡
ሶስት ቀላል የመብት ጥያቄዎቻችንን ካነሳን እለት ጀምሮ ሙሉ የህይወታችን ክፍል በመንግስት ሽብር ፈጣሪነት ተመሰቃቅሏል፡፡ ውሎና አዳራችን በመንግስት ስራ አስፈፃሚዎች ወከባ አንድ ተራ ዜጋ ሊተነፍሰው የሚችለውን የሰላም አየር መተንፈስ እንኳን ያስቻለ አልነበረም፡፡ በይበልጥም ከኮሚቴዎቻችን መታሰር በኋላ የመኖር እና የመንቀሳቀስ መሰረታዊ መብታችን ተገድቦ ሃገር በፖሊስ እና ደህንነት የምትመራ እስኪመስል የወታደራዊውን የደርግ ስርአት ግልባጭ የሚመስሉ ክስተቶች በቀንም በሌትም፣ በአደባባይም በቤታችንም እየተፈፀሙብን ቆይተዋል፡፡ ‹‹ታሪክ እራሱን ይደግማል›› እንዲሉ ከመኖሪያ እና ከአምልኮ ቤቶቻችን እየተወሰድን ተደብድብን እና ተገድለን፣ ‹‹አስክሬን ለመውሰድ ብር ክፈሉ›› ይባል እንደነበረበት ዘመን ‹‹የተገደሉብን ቤተሰቦቻችን ሽብርተኞች ነበሩ›› ብለን በአባቶቻችን፣ በወንድምና እህቶቻችን፣ እንዲሁም በልጆቻችን ላይ ሳይቀር እንድንመሰክር ስንገደድ ኖረናል፡፡ ይህ ሁሉ ግፍ ግን ከመብት ጥያቄአችን ጥቂትም ቢሆን አላደናቀፈንም፡፡ ይልቁንም የተጠነሰሰልንን ተንኮል በተባበረ ክንዳችን ካልበጠስነው እንደማይለቀን በመረዳት በአንድነት እና በፅናት ለመቆም ደግመን ደጋግመን ቃላችንን እንድናድስ አድርጎናል፡፡
በነዚህ ሁሉ ምስቅልቅሎች መንግስት በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የሥነልቦና የበላይነት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሙሉ በሙሉ ተንኮታኩቷል፡፡ ባለፉት ጊዜያት ሙስሊሙ ላይ እንደ ህዝብ የተከፈተው የሚዲያ ጦርነት ከመንግስት የማይጠበቅ መሆኑን ችላ ብንለው እንኳን ትእግስትን የሚፈታተን፣ የህዝቦችን አብሮ የመኖር የሚያደፈርስ በመርዝ የተለወሰ እሾህን ያህል ከባድ አደጋ ነበር፡፡ እነዚያ የሚዲያ ጦርነቶች የህዝበ ሙስሊሙን ስነልቦና አንዳችም አልነኩትም፡፡ በተቃራኒው የመንግስት መረጃዎች በሃሰት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን፣ ሚዲያዎቹም የሚዲያ ስነምግባር ፈፅሞ የማያውቁ የሃሰት ማሽኖች መሆናቸውን ህዝብ እንዲያውቅ ጠንካራ ማሳያ ሆነዋል፡፡ ከዚህም አልፎ የመንግስት ባለስልጣናት በእኛና በመሪዎቻችን፣ ብሎም አለም ባደነቀው ሰላማዊ ትግላችን ላይ ሲሰጧቸው ከነበሩ ቅጥፈቶች በመነሳት መላው ኢትዮጵያዊ ‹‹በሚዲያ ሲታዩ አለባበስ እና መጠሪያ ማእረጋቸው እንጂ ለካስ የሚናገሩት ፍሬ ነገር ሚዛን የለውም›› ብሎ እንዲያስብ ገበናውን ያጋለጡ አጋጣሚዎች ሆነው አልፈዋል፡፡ ከላይ ያየናቸው ማሳያዎች ፖለቲካዊው ውሳኔ በህዝብ ስነልቦና ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ እዚህ ግባ የሚባል እንደማይሆን ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡
የፍርድ ቤቱ ፖለቲካዊ ውሳኔ በቀጣይ ለሚኖረን የትግል አቅጣጫ አንድ መሰረታዊ ግብዓት ነው፡፡ በሃሰት ክስ ተመስርቶ አንድም ታሳሪ ላይ ፖለቲካዊ ብይን መስጠትን ህዝበ ሙስሊሙ እንደማይቀበለው ደግሞ ደጋግሞ እያሳወቀ ነው፡፡ ‹‹የመንግስት ውሳኔ ምን ቢሆን ምን እናደርጋለን?›› በሚለው ላይ ህዝበ ሙስሊሙ በቂ ጥናት አድርጓል፡፡ በመሆኑም የመጨረሻ አስከፊ የሆነው ውሳኔ ቢወሰን እንኳን ሙስሊሙ ህብረተሰብ ቀድሞ ባስቀመጣቸው አማራጭ መንገዶች በአዲስ ወኔና እልህ አንድነቱን ጠብቆ ከመጓዝ በዘለለ በስሜታዊነት የሚወስደው አንዳችም እርምጃ አይኖርም፡፡
በሌላ በኩልም የምናውቀውን ንፁህነታቸውን መንግስት ዳግም መስክሮ በነፃ ካሰናበታቸውም ይህን ታሳቢ ያደረገ ቀጣይ አቅጣጫ ይፋ ለማድረግ እድሉን የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በአደጋዎች መሃል ሆኖ ሰላማዊ ትግልን በድል ለመወጣት ሁኔታዎችን እያጤኑ መጓዝ ህዝበ ሙስሊሙ ሲጠቀምበት የቆየ አርቆ አሳቢነት እና የትግል ፅናት በመሆኑ ሁሌም እንደተላበሰው ይቆያል፡፡
በእርግጥም በፖለቲካዊ ውሳኔ የህዝብን ስነ ልቦና መርታት አይቻልም!!!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

No comments: