Sunday, November 15, 2015

የወያኔ የጎሳ ፖለቲካ ውጤቱ ጦርነት ነዉ! (የጎንደር ሕብረት)

November 15,2015
ልዩ መግለጫ
በጎንደር ክፍለሃገር ፤ በላይ አርማጭሆ ወረዳ፤ ልዩ ቦታው ማዉራ፤ ሮቢት፤ ጫጭቁና፤ ጋባ ጋላገር እንዲሁም ሌላም ብዙ አካባቢወች እና ከዚህ ቀደም ሲል ደግሞ፤ በጭልጋ አካባቢ ወገኖቻችን ላይ የወያኔ ሰራዊት የፈጸመዉን ኢሰባዊ ጭፍጨፋ በጥብቅ እናወግዛለን። ኢትዮጵያዊ ቆዳ ለብሶ፤ በሞሶሎኒ ጭንቅላት የሚያስበው ወያኔ፤ ገና ሲፈጠር ጀምሮ፤ ለዘመናት ሃይማኖት ፤ ቋንቋ ፤ ዘር ሳይገድበዉ አብሮ የኖረ ህዝባችንን፤ ከፋፍሎ እድሜ ልኩን ለመግዛት ሲል፤ በጎሳ ነፃነት ስም አንቀጽ 39ኝን በማር የተለወሰ መርዙን ለመላ ሕዝባችን እየጋተ አገራችንን እያተራመሰ ይገኛል። ይህ የጎሳ ፖለቲካው፤ በየተኛውም አካባቢ፤ ሰላም እና መረጋጋትን እንዳላመጣ በተግባር እያየ እንኳ ከሥህተቱ የማይማረው ግትር መንግሥት፤ በመሽ ሰዓት ወደ ሰሜኗ ክፍለ ሀገራችን ጎንደር ላይ ለመተግበር እየሞከረ ባለው የክልል ጣጣ ምክንያት፤ በጋባ፤ ትክል ድንጋይና እና በጭልጋ አካባቢ በከፈተዉ ጦርነት የንጹህ ወገኖቻችንን ህይወት ማጥፋቱ እጅግ አሳዝኖናል። በጣም የሚያስቆጨውና የሚያሳዝነው ደግሞ የወያኔ መንግሥት ሆን ብሎ አስቦና ተዘጋጅቶ አርሶ አደሩ በሳለም አርሶ ከሚኖርበት ቀየው ድረስ በመሄድ የፈጸመው የግፍ ጭፍጨፋ በመሆኑ ነው።gonder-unity
ይህ መንግሥት ተብዬ የአሸባሪ ቡድን፤ እንዲህ አይነቱን ግፍ ሲፈጸም የመጀመሪያው ባይሆንም የመጨረሻው እንደማይሆን እርግጠኞች ነን። በአሁኑ ሰዓት እየተካሄደ ባለው ጦርነት ህጻናት፤ ከቤት የዋሉ አረጋዊያን፤ እሴቱች ሳይቀሩ መገደላቸውን በአካባቢው የሚኖሩ የዓይን እማኞች ገልጸዋል። አሁንም የፌደራል ወታደር ከቤት፤ ቤት እየተዘዋወረ ሰላማዊ ዜጎችን እያፈነ ነው። ሕዝቡም ቤቱን እና ንብረቱን ለማስከበር ሳይወድ በግድ ከመጣው ወራሪ ጦር ጋር እየተጋፈጠ ይገኛል። የወያኔ መንግሥት እንዲህ አይነቱን አረመኒያዊ ጭፍጨፋ በጎንደር ህዝብ ላይ የጀመረው ዛሬ ሳይሆን ሥልጣን ከመያዙ በፊት ጀምሮ በወልቃይት ጠገዴ እና በጠለምት ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የዘር ማጥፋት እርምጃን በመውሰድ ነው። አሁንም ይህንን እኩይ ተግባሩን እንደቀጠለ ነው። ወያኔ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ፤ የህዝብን ጥያቄ በሰላም እና በዴሞክራሲዊ መንገድ የሚያሰተናግድ መንግሥት አለመሆኑን በተላያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እያደረግ ያለውን ጭፍጨፋ መመልከቱ በቂ ነው። ከእባብ እንቁላል እርግብ እንደማይገኝ ሁሉ፤ ከወያኔ መንግሥትም ሰላም እና ዴሞክራሲ ይገኛል ብሎ መጠበቅ እራስን ማታለል ነው።
በመሆኑም፤ ይህ አርመኔያዊ፤ ጨፍጫፊ እና ከፋፋይ ሥራዓት በየተራ በየአካባቢያችን እየዘለቀ በልቶን ከመጨረሱ በፊት፤ የጎንደር ህዝብ ትጥቁን ሳይፈታ በአንድነት ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በመተባበር ከማስወገድ ውጪ፤ ፈጽሞ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለዉም። ይህ ካልሆነ መሬት መንጠቁን፤ በዘር እየከፋፈለ ርስ በርስ ማዋጋቱን እና መከፋፈሉን ያለማቋረጥ ይቀጥላል።
ጎንድር የአማራዉ፤ የቅማንቱ፤ የሽናሻዉ፤ የቤተ እስራኤሉ፤ የአገዉ የጋራ ርስት አገሩ ናት። ጎንደርን በጎሳ ለመከፋፈል እየተሞከር ያለው እቅድ፤ ከጥፋት ላይ ጥፋት ከመሆኑም በላይ ለቅድስት አገራችን ኢትዮጳያም የተቀነባበረ የብተና ሞሶሎኒያዊ የወያኔ አደጋ ነዉ።
ወያኔ በአሁኑ ሰዓት በጎንደር ዙሪያ እየሰራ ያለው መሰሪ ተንኮል፤ በአንድ በኩል ለቅማንት ብሄረሰብ የሰጠውን አነስተኛ ቀበሌ ለመከለል፤ ጥቂቶችን ሲያስገድድ፤ በሌላ በኩል የጠየቁትን ሙሉውን ቀበሌ ማግኘት ይገባናል? የሚሉ ካድሬወችን በብዙ ገንዘብ ቀጥሮ ወደ ህዝቡ አሰርጎ በማሥገባት ህብረተሰቡ ዕርስ በርሱ ቅራኔ ውሥጥ እንዲገባ በመገፋፋት፤ ጎንደርን የመገነጣጠል አላማውን ለማሳካት ሌተ ከቀን የጥፋት ስራዉን እየሰራ ይገኛል። የተከበርከዉ ጀግናዉ የጎንደር ህዝብ ሆይ! ከምንጊዜዉም በበለጠ አንድነትህን አጠናክረህ ትጥቅህን አጥብቀህ ታሪካዊ ጎንደርን አድን። ለሃያ ዓምስት ዓመታት የወልቃይት ጠገዴ፤ የጠለምት ሁመራ መሬትህ በትግራይ ነጻ አዉጭ ነኝ በሚሉ ባንዳወች ተወሮ ተዘርፏል፤ የዘር ማጥፋትና አፈናቅሎ የማጽዳት ጭፍጨፋ ተፈጽሞበት ጩሆቱን እያሰማ ይገኛል።
ነጻነት በልመና አይገኝምና ተባብረህ የሰባቱም አዉራጃ ህዝብ በአንድነት ዘረኛ ወራሪዉን ወያኔ ከታሪካዊ መሬትህ ጠራርገህ አስወጣ። በጎንደር የሚኖር የትግራይ ተወላጆች ሁሉ በጎንደር መሬት የመኖር ገደብ የሌለዉ የኢትዮጵያዊነት መብታቸው ነዉ። ካድሬወች፤ ሰላዮች፤ ጦረኛ ወራሪ ታጣቂወች ግን የጎንደር ህዝብ ፍጹም አይፈልጋቸዉም፤ በግፈ ትዉልድ ጨርሰዋልና፤ በአስቸኳይ መዉጣት አለባቸዉ። ዛሬ በአንድ አካባቢ ያለው ወገንህ በግፈኛው ቡድን በወያኔ ሲጨፈጨፍ፤ አሻግረህ እያየህ ተራህን ከመጠበቅ ይልቅ፤ “ሳይቃጠል፤ በቅጠል” እንዲሉ፤ እዚያው ችግሩን ከጫረበት ቦታ ድረስ በመሄድ እና ተባብረህ በመዋጋት ለአንዴና ለመጨረሻ ነፃነትክን ተጎናጸፍ። የጎንደር ሕዝብ ወራሪና ከፋፋይ ሃይልን መሸከም ይብቃው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! የጎንደር አርሶ አደር ከበደል ላይ በደል ተደራርቦበታል። ሱዳን አዝመራውን እያቃጠለ ፊት ለፊት ሲወጋዉ፤ ወያኔ ከኋላዉ ሃብቱን ይዘርፋል፤ ሚሊሻዉን ወደ ጎንደር ለም መሬቶች ያሰማራል። ይህንን አገራዊ ስሜት የሌለውን የዘረኛ መንግሥት የኢትዮጵያ ህዝብ ተከፋፍሎ ወይም ወኔ በሌለው ስሜት ከዳር ቆሞ ከንፈር መምጠጥ እና በባዶ ቁጭት እራስን ማቃጠል ሳይሆን፤ በቆራጥነት በጋራ ሆ! ብሎ በመነሳት ተባብሮ ማሥወገድ ይገባዋል።
የጎንደር ህብረት በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸዉ ወገኖቻችን መራራ ሃዘናችን እየገለጽን፤ ከርሃቡ በላይ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባችዉን ለመርዳት ከጎንደር ህዝብ ጎን እንደምንቆም እያረጋገጥን፤ እንዲሁም ለዚህ ጉዳት ዋነኛ ተጠያቂ ወያኔ የሚመራዉ መንግስት ስለሆነ፤ እጁን በአስቸኳይ ከህዝባችን ጫንቃ ላይ እንዲያነሳ እንጠይቃለን። በመጨረሻም፤ በማንኛውም በክፍለ ሀገሩ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን አሥመልክቶ መላዉ የጎንደር ህዝብ ተባብሮ እና ተመካክሮ እንደጥንቱ እንዲፈታ ጥሪያችን እናቀርባለን።
ጎንደርን በአንድነት እናድን። ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
ከጎንደር ህብረት

No comments: