Monday, November 2, 2015

የፓርላማው ድራማ

November 2,2015
ይገረም ዓለሙ
ሙሉ በሙሉ በአብዮታዊ ዴሞክራቶች በመያዙ የተለየ ሀሳብ የማይሰማበት ሙት የሆነውን ፓርላማ ህይወት ያለው ለማስመሰል የተዘጋጀው ድራማ ማክሰኞ ጥቅምት 16/2008 መታየት ጀምሯል፡፡ ይህ የፓርላማ ድራማ ቤቴሌቭዥን እንደምናያቸው ድራማዎች ሰሞነኛውን ትኩሳት እየተከተለ በየሳምንቱ የሚጻፍና የሚዘጋጅ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በዚህ የመጀመሪያ ቀን ትዕይንት መሪ ተዋናይ ሆነው የቀረቡት ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከፓርላማው አባላት መካከል በተመረጡት ተዋንያን እየተጠየቁ በመመለስ ሲተውኑ ታይተዋል፡፡Hailemariam Desalegn in the TPLF parliament
ከቀደሙት ጠቅላይ ምኒስትር ጀምሮ ሲነገር እንጂ ሲተገበር የማይታየው ከተቀዋሚዎች ጋር አብሮ የመስራት ጉዳይ ለመጀመሪያው ቀን ድራማ ማድመቂያነት ከተመረጡት ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ተባብሮ መስራት ማለት እንደ ተቀዋሚዎች በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር ሀገራዊ መግባባት ከመፍጠር የሚጀምር እንደ ወያኔ ደግሞ እሱ በሚፈልገው ጉዳይ ሲፈልጋቸው ብቻ በመጥራት የሚገለጽ ነው፡፡ እንዲ ሆነናም በአምስት ዓመቱ ዕቅድ ላይ ለማወያየት ምርጫ ቦርድ መዝግቦ ለሚያውቃቸው ፓርቲዎች በሙሉ መንግጨሥታቸው ሰነድና ደብዳቤ መላኩን የገለጹት አቶ ኃይለማሪያም ብዙዎቹ በስብሰባው ላይ ሲገኙ ጥቂቶች ውኃ የማይቋጥር ምክንያት በመስጠት አልተገኙም አሉ፡፡ ያልተገኙት ፓርቲዎች ያቀረቡት ምክንያት ውኃ የማይቋጥር ነው ያሉበትን ምክንያትም ሲያረዱ በሕጋዊ መንግድ የተመረጠ መንግሥት ስላልሆነ ከእርሱ ጋር አንነጋርም ማለታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለመሆኑ ጥሪያችንን ተቀብለው ብዙዎቹ ተገኝተዋል የተባሉት ፓርቲዎች የትኞቹና እነማን ናቸው፡፡ዝቅ ብለን እናያቸዋለን፡፡
የመሳሪያ ትግል የሚያካሂዱትን ድርጅቶች አስመልክቶም ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ለራሱም መሆን ካልቻለው ሻዕቢያ ጋር ሆነው የሚያመጡት ውጤት ስለማይኖር ጊዜያቸውን በከንቱ ባያባክኑ በማለት ምክር ለመስጠት የዳዳቸው አቶ ኃይለማሪያም አንዳንዶቹ እኮ ጭራሽ የሌሉ ናቸው በማለት ኦነግን ኦብነግንና የጋምቤላ ህዝቦች ንቅናቄን ጠቀሱ፡፡ ይቺ ገለጻ የቀረበችው በደራሲውና አዘጋጁ ስህተት ይሁን ወይንም በርሳቸው የጥናት ጉደለት ባይታወቅም ሁለት መልእክት ታስተላልፋለች፡፡ አንደኛ እነዚህ የተጠቀሱት ድርጅቶች ሰሞኑን ተባብረው ለመስራት የደረሱበት ስምምነት እነ አቶ ኃይለማያም ሰፈር የፈጠረው ነገር መኖሩን እንድንጠረጥር ያሚያደርግ ፣ ሁለተኛ ደግሞ በሰሜን በኩል ድምጻቸው የሚሰማው ድርጅቶች እነዚህ ብቻ አይደሉምና ለሌሎቹ መኖሮና ጠንካራ መሆን በዘወርዋራ እውቅና የሰጠ ነው፡፡
አቶ ኃይለማሪያም የአቶ መለስ ሌጋስ አስቀጣይ እንደመሆናቸው ስለ ድርጅቶቹ የተናገሩት ከርሳቸው የወሰዱትን ነው፡፡ አቶ መለስ ብረት አንስተው መንግሥታቸውን የሚታገሉ ድርጅቶችን አስመልክቶ ሲላቸው አጥፍተናቸዋል የሉም ሲሉ ሌላ ግዜ ደግሞ በግላቸው ብዙ ርቀት ሄደው ከድርጅቶቹ መሪዎች ጋር ለመገናኘትና ለመደራደር እንደጣሩ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ሌላ ግዜ ደግሞ ወድመዋል ተደምስሰዋል የተባሉት ደርጅቶች በዚህ ቦታ እንዲህ አደረጉ ጥፋት አደረሱ የሚል ዜና ስንሰማ ኖረናል፡፡ የሉም በተባሉ ድርጅቶች ስምም ዜጎች እየተወነጀሉ ታስረዋል እየታሰሩም ነው፡፡ አቶ መለስ አይደለም የሀገር ውስጥ ተፋላሚዎችን ሶማሌ ተሻግረው አልሻባብን ድምጥማጡን አጥፍተነዋል ብለውንም ነበር፡፡
አቶ ኃይለማሪያም ባያስታውሱም እኛ አንረሳውም፡፡ አቶ መለስ ከርሳቸው ፍላጎት ውጪ ስንዝር መሄድ የማይችለውን ፓርላማ አስፍቅደው(ነግረው) እንዲህ አስታዋሽ አጥቶ የቀረውን ሰራዊት ሶማሊያ በላኩበት ወቅት የገጠማቸውን ተቃውሞ ዝም ለማሰኘት ሰራዊታችን አልሻባብን ደምስሶ አሁን የቀረው ቃርሚያ ብቻ ነው፣ ያንን አጠናቆ በቅርብ ቀን ይመለሳል ብለውን ነበር፡፡ ነገር ግን ይኸው እስካሁን አልሻባብም አልጠፋ ሰራዊቱም አልተመለሰ፡፡ እንደውም በተቃራኒው ወንድሞቻችን የአልሻባብ ጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ አቶ ኃለማሪያም እኔም አንደ መለስ ብለው በንቀት ስሜት የሉም ጠፍተዋል ስላሉዋቸው ድርጅቶች መረጃ ስለሌለኝ የምለው አይኖርም፤ የላችሁም የተባላችሁ መኖራችሁን አሳይዋቸውና አቶ ኃይለማሪም በዚህ አፋቸው ምን እንደሚሉ ለመስማት አብቁን የሚለው ግን መልእክቴ ነው፡፡
አቶ መለስ የሻዕቢያና ወያኔ ጸብና ፍቅር ለወላይታው ምኑ ነው ብለው ለአቶ ኃይለማሪያም አለነገሯቸው እንደሁ እንጂ ወያኔን አዲስ አበባ ያደረሰው ለራሱም የማይሆን ያሉት ሻዕቢያ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሌላው ኢትዮጵያዊ (የወያኔ ታጋይ ጭምር ) የማይታመን ሆኖ እስከ ተጣሉበት ግዜ ድረስ ቤተ መንግሥቱ ይጠበቅ የነበረው በሻዕቢያ ሰራዊት እንደነበረ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ስለሆነም አቶ ኃይለማሪያም ወያኔዎች ስለ ሻዕቢያ ዛሬ የሚሉትን ብቻ እየተቀበሉ መናገር ሳይሆን ትናንት ምን ይሉ ምንስ ያደርጉ እንደነበር የተጻፈ አንብበው የነበረ ጠይቀው ቢናገሩ ቢያንስ ጠቅላይ ምኒስትር ለሚለው ማዕረጋቸው( ይስሙላም ቢሆን) የሚመጥን ይሆናል፡፡
ከላይ እንደተገለጸው አቶ ኃይለማሪያም ስለ አብሮ መስራት ሲናገሩ ምርጫ ቦርድ የመዘገባቸውን ፓርቲዎች በሙሉ ጠርተን አብዛኛዎቹ ተገኝተዋል ነው ያሉት፡፡ አብዛኛው የሚለው የጥቅል መጠሪያ ለወያኔም ለፓርቲዎቹም ለምርጫ ቦርድም እያገለገለ ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በቁጥር ሲገለጹ እንጂ በስም ሲጠሩ አይሰማም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምርጫ ቦርድ መዝገብ ላይ ሰፍረው የሚገኙት አንዳንዶቹ የሌሉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ምርጫ ሲመጣ ብቻ ብቅ የሚሉና ለምርጫ የሚሰጣቸውን ገንዘብ ተቀብለው የአጃቢነት ሚናቸውን ተወጥተው ለአራት ዓመት የሚጠፉ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹም ፓርቲ ለመባል የሚያበቃ ቁመና የሌላቸው አቶ በረከት የፓርቲዎቹ ጥቅማቸው አልታይ ብሉአቸው ይሁን ስሜት ገፋፍቶአቸው ወይንም እውነት ተናንቆአቸው ባይታወቅም በመጽሀፋቸው የቤተሰብ ፓርቲ ሲሉ የገለጹዋቸው ናቸው ፡፡ በርግጥ ለመናገር አንዳንዶቹ ሊቀመንበር ተብሎ ከሚጠራው ሰው ቀጥሎ የሚጠራ ሶስትና አራት ሰው የሌላቸው በመሆኑ የቤተሰብ ፓርቲ የሚለውንም አያሟሉም፡፡ ብዙዎቹ ከተባሉት ከእነዚህ ስመ ፓርቲዎች ውስጥ ብዙዎቹን እንኳን ህብረተሰቡ ምርጫ ቦርድም አያውቃቸው፡፡ ድረ ገጹን ብትጎበኙ ቦርዱ ስለማያውቃቸው የተመዘገቡበትን ቀን መሙላት አቅቶት ቦታው ክፍት ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ፤ብቻ ብዙዎች እየተባሉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ይውላሉ፡፡እነዚህን በስም እየጠቀሱ መሪ የሚባሉትን ሰዎች ምንነትና ማንነት እያሳዩ መግለጽ የሚቻል ቢሆንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ የምርጫ ቦርድን ድረ ገጽ ከጎበኙ ሌላም ነገር ይታዘባሉ፣ ምርጫ የማስፈጸም ብቃት አለው ተብሎ ምስጋና የተዥጎደጎደለት ይህ ተቋም ድረ- ገጹን ወቅታዊ ማድረግ ተስኖት ከአስር ዓመት በፊት የነበረ መረጃ ነው የሚያገኙት፡፡
ፓርቲ ማለት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ የህጋዊነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የተሰጠው ነው ካልተባለ በስተቀር ብዙዎች የሚባሉት ከወያኔ ዳረጎት እየተቀበሉ፤ በምርጫ ቦርድ መልካም ፈቃድ ፓርቲ እየተባሉ፤ በአዳማቂነትና በአጃቢነት የሚያገለግሉ፣ እንኳን አባል የተሟላ አመራር የሌላቸው ናቸውና ፓርቲ ሊባሉ የሚበቁ አይደሉም፡፡ መሪ ለሚባሉት ሰዎች ግን የእለት እንጀራም የሕይወት መንገድም ሆኖ እየጠቀማቸው ነው፡፡ በአንጻሩ ብዙም ባይሆን ለወያኔ ዕድሜ መርዘምም እየረዱ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ኖሩም አልኖሩ “ተለበሰ ቀረ የደበሎ ቅዳጅ ”እንደሚባለው ናቸውና ምንም ፋይዳ የላቸውም፡፡ እንደውም የማይቻል ሆኖ እንጂ አለመኖራቸው ይሻል ነበር፡፡
ሙቱን ፓርላማ ህይወት ያለው ለማስመሰል የተጀመረው ድራማ ደራሲና አዘጋጁ ሰልችቶአቸው እስካላቆሙት ድረስ በጀመረው መልኩ ወቅታዊ የትኩረት አቅጣጫዎችን እየተከተለ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የእኛም ማየትና መስማት ብሎም ከምናይ ከምንሰማው ተነስተን ብዕር ከወረቀት ማገናኘት እንዲሁ ይቀጥላል፡፡እስካላቆሙት ድረስ ያልኩት አቅጣጫ ለማስቀየሻ እየተባሉ በዚህ መልኩ የሚጀመሩ ጉዳዮች ሲዘልቁ ስለማይታይ ነው፡፡ደግሞስ የማስመሰል ስራ መች ብዙ መንገድ ያስኬዳል፡፡ይህ የፓርላማ ድራማ ቀልቡን የሚስበው ሰው ኖር ይሆን!!

No comments: