January 4/2014
ዳዊት ሰለሞን
ግንቦት 7፣ኦብነግ፣ኦነግ፣አልሸባብና አልቃይዳ በፓርላማ ሽብርተኛ ተብለው ከተፈረጁ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ዛሬ ዶክመንተሪ ሰርቶ እነዚህ ድርጅቶች ሽብርተኛ ለምን እንደተባሉ ማብራሪያ መስጠት የጊዜ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ነው ሳናውቀው ሽብርተኛ አይደሉም የሚል ጥያቄ ተነስቷል?
ዳዊት ሰለሞን
ግንቦት 7፣ኦብነግ፣ኦነግ፣አልሸባብና አልቃይዳ በፓርላማ ሽብርተኛ ተብለው ከተፈረጁ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ዛሬ ዶክመንተሪ ሰርቶ እነዚህ ድርጅቶች ሽብርተኛ ለምን እንደተባሉ ማብራሪያ መስጠት የጊዜ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ነው ሳናውቀው ሽብርተኛ አይደሉም የሚል ጥያቄ ተነስቷል?
እርግጥ ነው ኢቴቪ ፓርቲዎቹን በጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ዙሪያ ሲያከራክር ፓርላማው ከስልጣኑ በመውጣት ድርጅቶችን፣ቡድኖችንና ግለሰቦችን ‹‹ሽብርተኛ ››በማለት መፈረጅ እንደማይገባው የአንድነቱ ተወካይ አቶ ሃብታሙ አያሌው ሞግተው ነበር፡፡የኢህአዴጉ ሽመልስ ከማል ውሳኔው ‹‹ፖለቲካዊ››ነው በማለት እቅጩን ተናግረው ነበር፡፡
በዛሬው ዶክመንተሪ ያየሁት አዲስ ነገር ፓርላማው የተለያዮ ፓርቲዎች ተወካዮች ስብስብ ስለመሆኑ መነገሩ ነው፡፡የኢቴቪ ካሜራ ፓርላማው በተለያዮ ፓርቲዎች ተወካዮች የተሞላ መሆኑን ለማሳየት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን እያቀረበና እያራቀ አሳይቶናል፡፡ግርማ ሲቀርቡና ሲርቁ ስንት ሆነው እንደሚታዮ የሚያውቀው የካሜራው ባለሞያ ብቻ ነው፡፡
መንግስት እየተከተለው የሚገኘው መንገድ በየትኛውም መመዘኛ ተገቢ ወይም ስልጡን አይመስለኝም፡፡ብረት ያነሱ ወገኖችን ሽብርተኛ በማለት ሰላማዊ አስተዳደር መገንባት አይቻልም፡፡ደርግ ጫካ የገቡትን የዛሬዎቹን የምኒሊክ ቤተ መንግስት ተቆጣጣሪዎች‹‹ሽብርተኛ፣ገንጣይ፣አስገንጣይ ወንበዴ››በማለት መፈረጁ መዘንጋት የለበትም፡፡ህወሃት ከደርግ በተጨማሪ በአሜሪካ መንግስት ‹‹ሽብርተኛ››ተብለው ከተፈረጁ ቡድኖች አንዱም መደረጉን መርሳት ተገቢ አይመስለኝም፡፡
መንግስት ሆደ ሰፊ በመሆን ሁሉም ሃይሎች በሰላማዊ መንገድ ልዮነቶቻቸውን በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን እንዲፈጥሩ በሮቹን መክፈት ይጠበቅበታል፡፡በአገር ውስጥ የሚገኙ ድርጅቶችን እንደ ጠላት መመልከቱንና ብቅ ሲሉ በሐሰት ክስ አንገታቸውን እያነቀ ወህኒ መወርወሩን በማቆም የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ይኖርበታል፡፡
በእኔ እምነት ኢሳትን የሽብርተኛ ወፍጮ በማድረግና በማለት ተአማኒነት እንዳያገኝ ማድረግ በዚህ ዘመን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ለዚህ ፍቱን መድሃኒት ኢህአዴግ የፕሮፓጋንዳ ማሽኑ ያደረገውን ኢሬቴድን ሁሉንም ድምጾች እንዲያስተናግድ መፍቀድ ነው፡፡90 ሚልዮን ህዝብን አንድ የግል (ነጻ)የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ማሳጣት በሰው መረጃ የማግኘት መብት ላይ መፍረድ ነው፡፡የታፈነ ህዝብ አማራጭ ድምጽ ለመስማት መፈለጉ አንቴና ዘርግቶና ሳህን ገዝቶ መዋተቱ አይቀሬ ነው፡፡እናንተ በረሃ እያላችሁ ቪኦኤንና ዶቼቬሌን መስማት ያስቀጣ ነበር፡፡አሁን በትረ መንግስቱን ስትጨብጡ እኛ ካልነው ውጪ ማለት መጀመራችሁ የደርግ ተጋቦሽ ከማለት ውጪ ምን ሊባል ይችላል?
ዶክመንተሪው ኢሳትን እየተጠቀሙ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ለማስፈራራት ነው፡፡መንገዱ ይህ አይመስለኝም፡፡ኢቴቪ በአገሪቱ በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ የሚገኙ ፓርቲዎችን እንደ ኢህአዴግ በእኩልነት የሚያስተናግድበትን ሁኔታ ፍጠሩ ፡፡ይህ በሌለበት ኢቴቪን ለብቻችሁ በተቆጣጠራችሁበት፣ኤፍኤሞችን ለሙዚቃ፣ለስፖርትና ለአልባሌ ነገሮች እንዲውሉ ባደረጋችሁበት አገር አማራጭ ተደርጎ የሚታይን ሚዲያ መጠቀም ሽብርተኝነት ነው ማለት ወንዝ አያሻግራችሁም፡፡
No comments:
Post a Comment