November 13,11 2015
“ህይወት ለማትረፍ በቅድሚያ መተማመን”
* ከአገዛዝ ለውጥ በፊት ችጋር ይቀድማል?
* “በአሁኑ ጊዜ ችጋሩ እንደ 1977 ሆኗል!”
በኢትዮጵያ ላለፉት ፴ ዓመታት ያለታየ ችጋር ተከስቷል። ድርቁና ረሃቡ ከዚህም በላይ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ኢህአዴግን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይፋ እያደረጉ ነው። “የምግብ ዋስትናን አረጋግጫለሁ” በማለት ሲወተውት የኖረው ህወሃት ተገዶ ያመነው ችጋር ከ፩፱፯፯ ድርቅ በላይ የከፋ እንደሚሆን ስጋት አይሏል። ከዚህ በፊት እንደተከሰቱት ለውጦች ይህኛውም የአገዛዝ ለውጥ ሊያስከትል እንደሚችል ተነገረ። በአስቸኳይ ብሔራዊ ግብረኃይል መቋቋም እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ህወሃት ከድርቅ እና ድርቅን ተከትሎ ከሚገኝ ዕርዳታ ጋር በተያያዘ ካለው አስጸያፊ ተሞክሮ በመነሳት ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንደሚሉት ከድርቁ ጋር በተያያዘ ፍትሐዊነት ያሳስባቸዋል፡፡ ሲያብራሩም በከፍተኛ የሙስና እና የአድልዖ ወጥመድ ውስጥ መዘፈቁን ራሱ ያመነው ህወሃት የሚመራው አገዛዝ ችጋር በመታቸው ወገኖች ስም የሚመጣውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ሥራ ላይ የማዋል አቅምም ሆነ ተዓማኒነትም በጭራሽ የለውም ይላሉ፡፡ መለስ “እስከ እንጥላችን ገምተናል” ያሉትንና በቅርቡ ደግሞ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ሕዝብ ያውቀናል፤ አያምነንም፤ ቀበሌ እንኳን ስብሰባ መጥራት አንችልም” በማለት የተናገሩትን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ ራሱ “አልታመንም፤ ሌባ ነኝ” እያለ የሚለፍፍ አገዛዝ እንዴት በረሃብ ለተጠቁ በፍትሐዊነት ዕርዳታ ያደርሳል በማለት ይጠይቃሉ?
እነዚሁ ክፍሎች የሚሉትን በመደገፍ ስማቸውን ያልገለጹ የኢህአዴግ ዲፕሎማት እንዳሉት ከሆነ አንድ ከፍተኛ ብሔራዊ መነቃቃት ካልተፈጠረ ኢህአዴግና ካድሬዎቹ ሕዝብን በማነቃነቅ ችግሩን በፍትሐዊ መንገድ ሊፈቱት እንደማይቻላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዲፕሎማቱ የኢህአዴግ ሎሌ ቢሆኑም የህወሃት የበረሃ ውጤት ስላልሆኑ ህወሃት በበረሃው ተሞክሮ በዕርዳታ እህል ስም እያጭበረበረ ስለዘረፈው ገንዘብ ሲያስቡ አሁንም ይዘገንናቸዋል፡፡
ኢህአዴግ “ብሔራዊ” በሚል የሚጀምሩ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን የመውደድ ባህርይ ባይኖረውም፤ የተፈጠረውን ድርቅና ችጋር አስመልክቶ በጋራ ለመሥራት የግድ ይህንን ማድረግ እንደሚገባው የሚጠቁሙ ክፍሎች ህወሃትና ድርቅ ያላቸውን የጠነከረ መሳሳብና ግንኙነት መረጃ በማጣቀስ ያስታውሳሉ፡፡
በተገንጣይ ስም ራሱን የሚጠራውና የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) የሚገዛት ኢትዮጵያ “በልማት ተጥለቅልቃለች፣ ልማት ላይ ነን” እየተባለ ቢዘመረላትም በውል የታየው ግን ሌላ ነው። ለዝርፊያው ሽፋን የሚለፈፈው የልማት ቀረርቶ ችጋር የሚያቃጥላቸውን ህጻናትና አረጋዊያን አንድ ወር እንኳን መታደግ የሚችል አቅም አልፈጠረም። ለምርጫ ዘመቻ ሲባል ተደብቆ የነበረው ችጋር ይፋ ሲሆን የታየው እውነት የመሰከረው ሃቅ ቢኖር አገሪቱ በባዶ ቀረርቶ እየደነቆረች መሆኑን ነው።
ህወሃት ሥልጣን ላይ በቆየበት ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ችጋር ከመከሰቱ አንጻር ጉዳዩን የሚመለከቱ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ እንደታየው አስከፊው ችጋር የአገዛዝ ለውጥ ለማምጣት የራሱን የሆነ ከፍተኛ ሚና ተጫውቶ አልፏል፡፡ ይኸኛውንም ከዚሁ ጋር በመዳመር የለውጥ ማዕበል ሊያመጣ ይችል ይሆን የሚለው የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ችጋሩን በግምባር የተጋፈጡ ነዋሪዎች አሁን ያለው የጠኔ ደረጃ እንደ 1977ቱ ዓይነት ነው ይላሉ፡፡ ከዚያም የሚያስበልጡት አሉ።
ህወሃት/ኢህአዴግ ለማድበስበስና ለመሸፋፈን የሚጥረው ችጋር ዓይኑን አፍጥጦ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ እየተሰማ ነው፡፡ በመሆኑም በመጪው የአውሮጳውያን አዲስ ዓመት መጀመሪያ ላይ በችጋር የተመታው ሕዝብ ቁጥር 15 ሚሊዮን እንደሚደርስ የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቁጥር ውስጥ ግማሽ የሚያህሉት ህጻናት እንደሆኑም ይገመታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 8.2 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እንደሚስፈልገው ይኸው የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ ያስረዳል፡፡ ይህ አኻዝ ከስድስት ወር በፊት በችጋር ከተጠቃው በዕጥፍ እንዳደገ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ይህም ህወሃት/ኢህአዴግ “ልማት፣ ውዳሴ፣ ህዳሴ፣ …” በማለት እንደ ጎበዝ ተማሪ መቶ በመቶ ያመጣበት “ምርጫ” ከመደረጉበፊት ነበር፡፡ በወቅቱ የችጋርና የድርቅ ጉዳይ አልተነሳም፤ የተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንደሌላው ጉዳይ በቂ ሽፋን ሲሰጡበት አልታየም፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ “የጎበዝ ተማሪ” ሰርቲፊኬቱን ከተቀበለ፣ ከበሮውን ከደለቀ፣ ድግሱን ከደገሰ፣ መሸከም እስኪያቅተው ከበላና ከጠጣ በኋላ ከሰከረበት በቅርሻትና በግሳት ሲነቃ የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የድርቅና ረሃብ፣ የሙስና፣ … ጉዳዮችን ከዚህ በፊት እንዳልነበሩ አድርጎ ሕዝብ ሊያሳምን መሞከሩ ተቀባይነት እንደሌለው ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን የላኩ በአጽዕኖት የሚያስረዱት ነው፡፡
ሰሞኑን ከቪኦኤ ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ ቴድሮስ አድሃኖም “የህዝብ ቁጥር እጥፍ በመጨመሩ ፰ ሚሊዮን ህዝብ ቢራብ ፹ ሚሊዮኑ በአስተማማኝ ደረጃ በምግብ ራሱን ችሏል” በማለት መሳለቃቸው ይታወሳል። ከእንደ ቴድሮስ ዓይነቱ ችጋርን በቴሌቪዥን መስኮት ከመመልከት ያለፈ ዕውቀትና ርኅራኄ የሌለው ይህ መሰሉ የድንቁርና አነጋገር መሰማቱ የሚያስደንቅ እንዳልሆነ የሚናገሩ ወገኖች ቴድሮስ ለቪኦኤ የተናገሩትን ሃሳብ ሞት ካስፈነጠራቸው መለስ እንደኮረጁት ይናገራሉ፡፡ ሕዝብ በተራበ ቁጥር መለስ ዜናዊ ምክንያቱን ሲጠየቁ የሕዝብ ቁጥር በመጨመሩ እንደሆነ የመሃይም መልስ በመስጠት ተደናቁረው ሲያደናቁሩና ሎሌዎቻቸውን ሲያስጨበጭቡ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ መለስ የሥልጣኑን ኮርቻ መጋለብ እንደጀመሩም አምላካዊነት ተሰምቷቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ በቀን ሦስት ጊዜ እንመግባለን ብለው የተነበዩት ወደ ዜሮ ወርዶ በሞት መቀደማቸው የአስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የምኞትም ደሃ መሆናቸውን ያረጋገጡበት እንደሆነ በርካታዎች የሚመሰክሩት ነው፡፡
ህወሃት ቃላት በማሳመርና ቁጥሩን በመቀነስ “የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው፣ የምግብ ዕጥረት የደረሰባቸው፣ …” በማለት ንብረቱ ባደረገው ሚዲያ ጉዳዩን አቃልሎ ቢያስወራም እውነታው ግን ሕዝብና እንስሳት በችጋር እየሞቱ መሆናቸው ነው በማለት በፌስቡክ በኩል ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ የግብርና ባለሙያ ተናግረዋል፡፡ ምናልባትም በጠኔ እየተቃጠለ ያለው ሕዝብ ብዛት ከተገመተው በላይ ሊሆን እንደሚችልና ጉዳቱም እጅግ አስከፊ እንደሚሆን እኚሁ ባለሙያ አስረድተዋል፡፡ በመንግሥታቱ ድርጅት ዘገባ መሠረት በቀን ቢያንስ ሁለት ህጻናት ይሞታሉ፡፡
አበራ ወልዱ የተባሉ የ60 ዓመት አዛውንት የግብርናው ባለሙያ የተናገሩትን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ “ችጋሩ ገና ጅማሮ ቢሆንም እየከፋ ነው የሄደው፤ ገና ካሁኑ በጣም አስከፊ ሆኗል፤ ሰዎች እየሞቱ ነው፤ ሌሎች ሰዎችም (በችጋር ምክንያት) ታምመው አልጋ ላይ ወድቀዋል” በማለት አዛውንቱ ተናግረዋል፡፡ አክለውም “እንዲያውም አሁን ልክ እንደ 1977ቱ ችጋር ሆኗል” በማለት የሰጡትን ምስክርነት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ዘመን የተከሰተውን የወሎ ችጋር (የወሎ ድርቅ የሚባለውን) ለመደበቅ የተደረገው ሁኔታ ለንጉሣዊው አገዛዝ መውደቅ ክብሪት ከጫሩ ምክንያቶች እንደ ዋንኛው ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ለንጉሡ ልደት በርካታ ገንዘብ በከንቱ እንዳባከኑ ደርግ የአጼ ኃይሥላሴን አገዛዝ ሲያማበትና ሲኮንንበት የነበረ ፕሮፓጋንዳ ነበር፡፡
ከላይ አቶ አበራ ወልዱ ያወሱት የ1977ቱ ረሃብ በተከሰተበት ወቅት ደርግ ለ10ኛው ዓመት የአገዛዝ ዘመኑን አገር ምድሩን በሰሜን ኮሪያ ብልጭልጭ ማድመቂያዎች “አስውቦ” ነበር፡፡ ይኸው ችጋር ለደርግ መውደቂያ ምክንያት ሲሆን በሌላ በኩል ለህወሃት ደግሞ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የፋይናንስ “ዕድል” ከፍቶለት ነበር፡፡ በወቅቱ ለበዓሉ ድግስ የወጣው ወጪ ለተረጂ ወገኖች መዋል ነበረበት በማለት ህወሃት ከበረሃ ሲጮህ በተመሳሳይ መልኩ ለትግራይ ሕዝብ እህል መግዣነት የመጣውን ገንዘብ ህወሃት ለራሱ ማድረጉን የአሜሪካ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ማረጋገጡን ቢቢሲ ሲዘግብ የቀድሞ አባላቱም የድርጊቱን ትክክለኛነት አረጋግጠው ነበር፡፡
የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ በቢቢሲ ይፋ የተደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው በ1977 በተከሰተው አስከፊ ችጋር ምዕራባውያን ድርጅቶች እና ለጋሾች ወደ ኢትዮጵያ ለእህል መግዣነት እንዲውል የላኩት ገንዘብ የህወሃት ሹሞች ራሳቸውን በመደበቅ እህል ሻጭ መስለው በመቅረብ ከላዩ እህል ከሥሩ በአሸዋ የተሞላ ጆኒያዎችን እንዳረካከቡ በወቅቱ በሽያጩ ላይ የነበሩት የቀድሞው ከፍተኛ አመራር አባል አሁን በአውስትራሊያ የሚገኙት አቶ ገብረመድህን አርአያ አረጋግጠዋል፡፡ ቢቢሲ ባሰራጨው ፎቶግራፍ ላይ እንደሚታየው ሻጭ ሆነው የቀረቡት ገብረመድኅን ለሸጡበጥ ገንዘብ ቆጥረው ሲረከቡ የሚታዩት ራሳቸው መሆናችን ከመመስከር በተጨማሪ ሙስሊም መስለው በመቅረብ ጉዳዩን እንደፈጸሙም ተናግረዋል፡፡ የሸጡበትንም ገንዘብ ለመለስ ዜናዊና ለሌሎቹ የህወሃት አመራሮች ማስረከባቸውን ጨምረው አስረድተዋል፡፡ ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ መለስን ቢጠይቅም እርሳቸው ግን ምንም ዓይነት አስተያየት ሳይሰጡ ጥቂት ቆይተው በዚያው አልፈዋል፡፡
በወቅቱ Christian Aid ከተባለው የዕርዳታ ድርጅት 500ሺህ ዶላር በብር ይዞ እህል ለመግዛት የመጣው ማክስ ፐበርዲ እንደሚለው ገንዘቡን ለእህል መግዣ እንዳዋለውና አንዳችም የዕርዳታ ገንዘብ ለሌላ ነገር እንዳልዋለ ቢናገርም ግብይይቱን የፈጸመው ግን ከከፍተኛ የትግራይ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) አመራር ጋር እንደሆነ መናገሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ይህንን ተግባር አሁን በኔዘርላንድስ በስደት የሚገኙት የቀድሞ የህወሃት አመራር አረጋዊ በርሄም ያረጋገጡ መሆናቸው በወቅቱ የተዘገበ ጉዳይ ነበር፡፡ “የዕርዳታ ሠራተኞቹ ተሞኝተው ነበር” ያሉት አረጋዊ በርሄ እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ መገኘቱንና ከዚህ ውስጥ 95በመቶ የሚያክለው የጦር መሣሪያ ለመግዛትና ማርክሲስት ሌኒንስት ሊግ ትግራይ (ማሌሊትን) ለመገንባት ወጪ እንደተደረገ መስክረዋል፡፡
“ነጻ አወጣዋለሁ” ያለውን ሕዝብ የዕርዳታ እህል እንዳይደርሰው በማድረግ አሰቃቂ ግፍን የፈጸመው ህወሃት አሁንም ተመሳሳይ ተግባር ከማድረግ የሚቆጥበው ምንድነው በማለት የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በተለይ ችጋሩ ከበረታባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በሆነው ትግራይ የሚገኙ ነዋሪዎች በከፍተኛ ሰቆቃ ውስጥ እንዳሉና ይህንኑ ችግራቸውን ከህወሃት ይልቅ ለአረና ሰዎች እና ለሌሎች ሊሰሟቸው ለሚችሉ እየተናገሩ እንደሆነ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የችጋር ሰቆቃ በአገሪቱ መከሰቱ እየታወቀ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር – ህወሃት አገር ለማፍረስ የተመሠረተበትን 40ኛ የልደት ዓመት በዓል ሲያከብር 2 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን እንዲሁም በትግራይ የዳያስፖራ ቀን ሲያከብር 200 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን፤ “እጅግ ቅንጡ የሆኑ ዘመናዊ ቪላዎች ለስድስት የቀድሞ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በ154 ሚሊዮን ብር ተሰርተው” እየተጠናቀቁ መሆናቸውን፣ እንዲሁም “የህወሃት የአማርኛ ክፍል” የሆነው ብአዴን በህወሃት እንደ ጭቃ ተጠፍጥፎ የተሰራበትን 35ኛ ዓመት ለማክበር 300 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚሆን (ትክክለኛው ከዚህ ሊበልጥም ይችላል) በተሰማበት ሰሞን 15 ሚሊዮን ሕዝብ ለአስከፊ ችጋር መጋለጡን የዓለም ሚዲያ መዘገቡ “ችጋር ውድቀትን ይቀድማል” የሚለውን አባባል እያጠናከረው መጥቷል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ከሆነ የኢትዮጵያን ችጋር ለጊዜው ለመታደግ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል ብሏል፡፡ ችጋሩ በአገሪቱ የተወሰነ ብቻ ሳይሆን ከምስራቅ እስከ ሰሜን ዘልቋል፡፡ ሰሞኑን ከሚከሰተው ዝናብ ጋር በተያያዘ በጥቂቱም ቢሆን እየበቀለ ያለው ሰብል እንደሚወድም ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ አሁን የሚታየው ሁኔታ “የምጥ ጣዕር መጀመሪያ” የሚባለው ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ችጋሩ እየዘለቀና እየከረረ እንደሚሄድ በግልጽ የሚታየው ሁኔታና ሌሎች በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የመጨረሻውን የጠኔ ሳል ስለው ህይወታቸው የሚጠፋው ህጻናት ቁጥር በቀን ሁለት ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነ በስፋት ይገመታል፡፡
ለተረጂው ወገን በዕርዳታ ስም የሚገባ ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ለሚንፏቀቀው ኢህአዴግ ታላቅ ገጸበረከት እንደሚሆን የብዙዎች ግምት ነው፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ የማይታመን ድርጅት የሆነው በሕዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከከፍተኛ አመራሮቹ አንስቶ እስከ ቀበሌ ያለው እርስበርሱ አንዳች አመኔታ የለውም፡፡ በሙስና “መበስበሳቸውን” ደጋግመው በአደባባይ ይናገራሉ፤ ይደሰኩራሉ፤ ይመሰክራሉ፡፡ ስለዚህ “በመንግሥት ሌቦች” የተሞላው ኢህአዴግ የተረጂዎችን ገንዘብ የግሉ ከማድረጉ በፊት የዕርዳታውን አሰባሰብና ፍትሐዊ አሰረጫጨት የሚቆጣጠር፣ የሚመራና የሚያስተዳድር ብሔራዊ ግብረኃይል መቋቋም እንዳለበት በአጽዕኖት የሚያምኑ ወገኖች ሃሳባቸውን ለዝግጅት ክፍላችን ለግሰዋል፡፡ ይህ ግብረኃይል ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ፤ ህወሃት ባዋረደው “ሽምግልና” ያልቀለሉ፤ በዕድሜ ብቻ ሳይሆን በተግባራቸው “አንቱ” የተባሉ አገር ውስጥና ውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መሆን እንደሚገባው አበክረው ይማጸናሉ፡፡ የአምስት ለአንድና መሰል የህወሃት አደረጃጀቶችን ለጊዜው ወደ ጎን ተደርገው ለሕዝብ ሲባል አስቸኳይ ውሳኔ ላይ ካልተደረሰ የችጋሩ ጉዳይ በትንሹም ቢሆን የቀረውን ክብራችንን አሟጥጦ በየሄድንበት ዕድሜ ልካችንን አንገታችንን የምንደፋበት እንደሚሆን በየዕለቱ በችጋር በሚሞቱት ህጻናት ስም ተማጽነዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ስለ “ውዳሴ፣ ህዳሴ፣ ባቡር፣ መንገድ፣ ፎቅ፣ ትልቅነትና ትልቅ መሆን፣ …” ሲደሰኮር ቢዋል መቀመጫን ገልቦ ፊት ከመከናነብ የማያልፍ ግብዝነት እንደሚሆንና ይህም ጊዜውን ጠብቆ ዋጋ እንደሚያስከፍል በእርግጠኝነት ይናገራሉ፡፡
No comments:
Post a Comment