Wednesday, October 22, 2014

የህዝብ ግንኙነት ካድሬዎች በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ሊዘምቱ ነው

October 22,2014
ኢሳት ዜና :-በአቶ ሬድዋን ሁሴን የሚመራው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አሰልጥኖ በፌዴራል የመንግስት ተቋማት በህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ለመደባቸው ካድሬዎች የሁለት ቀናት የማህበራዊ ድረገጾች አጠቃቀም ስልጠና በመስጠት በተለይ በግንቦት ወር ከሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንዲሳካ የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ አደራ ተጥሎባቸዋል፡፡

የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን እንደገለጸው የኮምኒኬሽን ጽ/ቤቱ በሚኒስትሮች ምክርቤት ደንብ ቁጥር 158/2001 ሲቋቋም በመንግስትና በሕዝቡ መካከል ቀልጣፋ ውጤታማ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማስቻል አንዱና ዋና ዓላማው ያደረገ ቢሆንም በተግባር ግን የሰለጠኑና ልምድ ያካበቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን የአመለካከት ችግር አለባቸው በሚል በማባረርና በማንሳፈፍ ካድሬዎችን በለብለብ ስልጠና ሲመድብ ቆይቷል፡፡ ዘርፉ ልምድና በቂ ስልጠና በሌላቸው ካድሬዎች በመያዙ በመረጃ አሰጣጥ በኩል ያለው ችግር እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡

ጽ/ቤቱ የመደባቸው ካድሬዎች በተለይ በማህበራዊ ድረገጾች አጠቃቀም ደካማ በመሆናቸው ምክንያት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን በሰበሰቡዋቸው ቁጥር ከፍተኛ ብስጭት የኢህአዴግን አቁዋም እንኩዋን መናገር የማይችሉ በማለት እስከመዝለፍ ደርሰዋል፡፡


የዜና ምንጮቻችን እንደጠቆሙት በአዲስአበባ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው ዋሽንግተን ሆቴል ባካሄደው ስልጠና ካድሬዎቹ እንደፌስ ቡክና ቲዎተር ባሉ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉና የመ/ቤታቸውንና የመንግስትን አቋም ከማስረዳት ባለፈም ጸረ መንግስት አቋም ያላቸውን መረጃዎች በማጣጣልና በማስተባበል ረገድ የበኩላቸውን የተከላካይነት ሚና እንዴት እንደሚወጡ በመሰልጠን ላይ ናቸው። በተለይ የማህበራዊ ድረገጾች መንግስትን በሚቃወሙ ሃይሎች ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ስር እንደወደቀ የአቶ ሬድዋን ቢሮ የሚያምን ሲሆን ይህን ለመመከት የሚያስችል ብቃት ያለው የኮምኒኬሽን ባለሙያ ባለመኖሩም ካድሬዎቹ በተደጋጋሚ ወቀሳ ሲሰነዝርባቸው መቆየቱን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡


በአሁኑ ወቅት የአንዳንድ የፌዴራል መ/ቤት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ካድሬዎች በተለይ በፌስቡክ ፈራተባ እያሉ መረጃዎችን መልቀቅና በሚጻፉ የተለያዩ ጉዳዮች አስተያየት መሰንዘር በመለማመድ ላይ ናቸው፡፡

No comments: