Sunday, October 5, 2014

ሰልጣኙንም አሰልጣኙንም ያንገሸገሻቸዉ ሥልጠና

Oktober 5,2014

አባትና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ልጁ አምርረዉ ሲጨቃጨቁ እናት ትደርስና . . . . እባክሽ ልጄ አባትሽ የሚልሽን ለምን አትሰሚም ብላ ልጇን ትቆጣታለች። ልጅት ከተቀመጠችበት ትነሳና ምነዉ እማዬ ምኑን ነዉ የምሰማዉ፤ አባዬኮ እሱ እራሱ የማያዉቀዉን ነገር ላሳይሽ እያለኝ ነዉ ብላ ንግግሯን ሳትጨርስ በቁጣዉ ብዛት ፊቱ እንደ ፊኛ ያበጠዉ አበቷ ካንቺ ማወቅ ዬኔ አለማወቅ ይሻላል፤ ይልቅ የምልሽን ስሚ ብሎ ጮኸባት። ወጣቷ ተማሪ ወላጅ አበቷ ከስምንተኛ ክፍል በላይ ዘልቀዉ እንዳልተማሩ ብታዉቅም ለግዜዉ ማድረግ የምትችለዉ ምንም ነገር አልነበረምና እሽ አባዬ ብላ አባቷን መስማት ጀመረች። ይህ የአባትና የልጅ ስሚኝ አልሰማም ጭቅጭቅ ባለፉት ሁለት ወራት መሀይሞቹ የወያኔ ካድረዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየስልጠና አዳራሹ ያደረጉትን ፍጥጫ አስታወሰኝ። ይህ አብዛኛዉን ዕድሜያቸዉን ትምህርት በመማር በሳለፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በወጉ ስምንተኛ ክፍልን ባላጠናቀቁ የወያኔ ካድሬዎች መካከል በክረምቱ ወራት ተጀምሮ አሁን ድረስ የዘለቀዉ የ”አሰለጥናለሁ አታሰለጥንም” ትንግርታዊ ድራማ ወያኔ አስካሁን ከሰራቸዉ ድራማዎች በአይነቱ ለየት ያለ ድራማ ነዉ።
የወያኔ ምርጫዎች ምንም አይነት ዉድድር የማይታይባቸዉ ማንም ተወዳደረ ማንም ወያኔ ብቻ የሚያሸንፍባቸዉና ምርጫዎቹ ከመካሄዳቸዉ በፊት የት ቦታ እነማን ማሸነፍ እንዳለበቸዉ ተወስኖ ያለቀላቸዉ የለበጣ ምርጫዎች ናቸዉ። ወያኔ ግን “ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” እንደሚባለዉ ምርጫዉ በቀረበ ቁጥር የሚያክለፈልፍ በሽታ ይይዘዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በ1997ና በ2002 ዓም የተደረጉትን ምርጫዎችና እርግጠኞች ነን አሁንም በ2007 ዓም የሚደረገዉን ምርጫ የሚለያያቸዉ ነገር ቢኖር በእያንዳንዱ ምርጫ መኸል የአምስት አመት ልዩነት መኖሩ ነዉ እንጂ የምርጫዉን ዝግጅት፤ ሂደትና ዉጤት በተመለከተ ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የሚችል ልዩነት የለም። ሁሉም ምርጫዎች የሚካሄዱት ወያኔ የምርጫ ተቋሞች፤ ሜድያዉንና ፍርድ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ዉስጥ ነዉ። በዚህ ላይ ቅድመ ምርጫዎችን የሚቆጣጠረዉ፤ በምርጫዉ ብቸኛ ተወዳዳሪ የሆነዉና ህዝብ የሰጠዉን ድምጽ የሚቆጥረዉ ወያኔ እራሱ ነዉ። ይህም ሁሉ ሆኖ ወያኔ ከሱ ዉጭ ማንም ምርጫዉን እንደማያሸንፍ በልቡ እያወቀ አምስት አመት እየቆጠረ የሚመጣዉ ምርጫ በቀረበ ቁጥር ግርግር መፍጠር ይወዳል። በ1997 በተደረገዉ ምርጫ ማንም አያሸንፈኝም ብሎ ሜድያዉንና የፖለቲካ ምህዳሩን ትንሽም ቢሆን ለቀቅ አድርጎ የነበረዉ ወያኔ በ2002 ዓም ይጋፉኛል ብሎ የጠረጠራቸዉን ሁሉ ማሰር፤ መደብደብና እንቅስቃሴያቸዉን መግታት ጀመረ። አሁን በ2007 ዓም ደግሞ ገና በግንቦት ወር ለሚካሄደዉ ምርጫ የኢትዮጵያን ወጣት ካልተቆጣጠርኩ በሚል ትልቅ ዘመቻ ጀምሮ በከፍተኛ በሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚገኙትን የአገሪቱ ወጣቶች በሥልጠና ሰበብ ወያኔያዊ የፖለቲካ ጠበል እያጠመቃቸዉ ነዉ።
ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወያኔን ዘረኛ ነዉ፤ ጎጠኛ ነዉ፤ ነብሰ ገዳይ ነዉ ይሉታል። አዎ እነዚህ ሁሉ የወያኔን ማንነትና ምንነት በትክክል የሚያሳዩ ቃላት ናቸዉ። ወያኔ ግን ከእነዚህ ዉጭ ሌሎች ብዙ መገለጫዎች አሉት፤ ለምሳሌ ወያኔ መዋሻት የማይሰለቸዉ ዉሸታም ነዉ፤ ዕኩይ ነዉ፤ ጨካኝና የለየለት መብት ረጋጭም ነዉ። እነዚህ የወያኔ ባህሪያት ሁሉ ያናድዱናል ወይም ያስቆጡናል እንጂ አይገርሙንም ወይም እየኮረኮሩ አያስቁንም። ጉደኛዉ ወያኔ የሚገርሙና የሚያስቁ ባህሪያትም አሉት። ወያኔ የቁጥር ጨዋታ ይወዳል፤ በተለይ ከቁጥርና ከቁጥርም በዛ ካለ ቁጥር ጋር ለየት ያለ ፍቅር አለዉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የአገር ዉስጥ ምርት ከዉጭም ከዉስጥም ተገፍቶ 5% ከጨመረ ወያኔ የሚነግረን 10% አደገ ብሎ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የትምህርት ጥራት ተንኮታኩቶ ከመዉደቁ የተነሳ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀዉ ወደ ስራ አለም በሚገቡ ተማሪዎችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ኮሌጅ በሚገቡ ተማሪዎች መካከል ያለዉ ልዩነት ትንሽ ነዉ፤ ወያኔ ግን በኔ ዘመነ መንግስት የዩኒቨርሲቲዉ ብዛት ብቻ ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች ብዛት ከ300% በላይ አደገ እያለ ይፏልላል። ካለፈዉ ሐምሌ ወር ጀምሮ ያለፍላጎታቸዉና ያለፈቃዳቸዉ በግድ ወደ ሥልጠና ማዕከላት እየገቡ የወያኔን ርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንዲጋቱ የሚገደዱ ወጣቶችም ጉዳይ ይህንኑ ወያኔ ከቁጥርና ከብዛት ጋር የተጠናወተዉን ፍቅር የሚያሳይ ነዉ። ይህ ወያኔ በየክልሉ ሥልጠና ብሎ የጀመረዉ ቧልት የሰልጣኛቹን እዉቀት የሚያዳብር አይደለም ወይም ለአገራችን ለኢትዮጵያም በምንም መልኩ የሚጠቅም አይደለም። የሥልጠናዉ ብቸኛ አላማና ጥቅም በወጣቱ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የወያኔን አባላት ማብዛት ነዉ። ወያኔ ድርጅታዊ የፓርቲ ስራዎችን የሚሰራዉ መንግስታዊ ተቋሞችን በመጠቀም ከመንግስት ካዝና በሚወጣ ገንዘብ ነዉና እሱን የሚያስደስተዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት አሉት ተብሎ መነገሩ ነዉ እንጂ እነዚህ አባላት ታማኝ ይሁኑ አይሁኑ ወይም ድርጅታዊ ስራ ይስሩ አይስሩ ለወያኔ ጉዳዩ አይደለም።
ወያኔ በዕረፍት ላይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከያሉበት በግድ አስመጥቶ ሥልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ የወሰዳቸዉ እርምጃዎች ሁሉ በወያኔና በተማሪዎቹ መካከል ያለዉን ሰፊ የፖለቲካ ልዩነት አጉልቶ ከማዉጣቱ ባሻገር ይህ ሳይጀመር የከሸፈዉ ስልጠና ለወያኔ ምንም የፈየደዉ ፋይዳ የለም። እንዳዉም አብዛኛዉ ተማሪ የወያኔ መሪዎችን አንገት የሚያስደፋ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሥልጠና የሚያስፈልገዉ ለተማሪዎቹ ሳይሆን ለራሳቸዉ ለአሰልጣኝ ነን ባዮቹ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በብዙዎቹ የስልጠና አዳራሾች የወያኔ ካድሬዎች ተማሪዎቹ የሚጠይቁትን ጥያቄ መመለስ አለመቻላቸዉ ብቻ ሳይሆን ካድሬዎቹ በሚጠየቁት ጥያቄ እየተበሳጩ ጥርሳቸዉን ሲነክሱ ታይተዋል። በእርግጥም ጎንደር ዉስጥ የነበረዉን ጄኔሬተር ነቅላችሁ ዬት አደረሳችሁት ከሚል አፋጣጭ ጥያቄ ጀምሮ አንዳርጋቸዉ ጽጌን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በጠየቁ ተማሪዎች ላይ አሰልጣኝ ካድሬዎች “ከእናንተ ጋር በኋላ እንገናኛለን” እያሉ ሲዝቱ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ካለ ለጋሽ አገሮች ዕርዳታ መንፈቅ መዝለቅ የማትችል ደሃ አገር ናት፤ ሆኖም የወያኔ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸዉ የሚዘርፉትን ገንዘብና አላግባብ የሚያባክኑትን የአገር ሃብት የተመለከተ ማንም ሰዉ ድርጊታቸዉ ከደሃዋ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በፍጹም እንደማይገናኝ ለመገንዘብ ግዜ አይፈጅበትም። ወያኔ ገነባሁ ብሎ የሚያፈርሳቸዉንና በየስብሰባዉና በየጉባኤዉ ከሚያባክነዉ ግዙፍ የአገር ኃብት ዉጭ ከሰሞኑ ምንም አገራዊ ጥቅም በሌለዉና ሠልጣኞቹ አንፈልግም ብለዉ ለተዉት ሥልጠና የሚያባክነዉ የህዝብና የአገር ገንዘብ እጅግ በጣም ብዙ ነዉ። ለምሳሌ ለአሰልጣኝ ካድሬዎች ከሚወጣዉ የትርንፖርትና የዉሎ አበል ዉጭ ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ ተማሪ በቀን የሚከፈለዉ ሃምሳ ብር ቁጥራቸዉ ከ600 ሺ በላይ በሆኑ ሰልጣኝ ተማሪዎች ልክ ሲሰላ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ ነዉ።
ለመሆኑ ዜጎች የሚላስና የሚቀመስ አጥተዉ በሚራቡበት አገር፤ ወጣቶች ስራ ፍለጋ ያደጉበትን መንደር ጥለዉ ባሕር እየተሻገሩ በሚሰደዱበት አገርና የገንብዘብ እጥረት እየተባለ ብዙ ፕሮጀክቶች በሚታጠፉበት አገር ወያኔ ከየት እያመጣ ነዉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየከፈለ ምንም እርባና የሌለዉ የፖለቲካ ሥልጠና ሥልጠናዉ በፍጹም ለማያስፈልገዉ የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠዉ? ደግሞስ ከዉጭ አገር ምንጮች ምንም አይነት የገንዝብ እርዳታ እንዳያገኙ በህግ የተከለከሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የስራ ማስኬጃ ወጪያቸዉን መሸፈን አቅቷቸዉ በሚንገዳገዱበት አገር ምን ቢደረግ ነዉ ወያኔ የራሱን ፓርቲ ስራዎች በመንግስትና በህዝብ ገንዘብ የሚያሰራዉ?
የወያኔና የገንዝብ ጉዳይ ከተነሳ እነዚህ ጉደኞች ቢነገር ቢነገር የማያልቅ ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ ብዙ የቆሸሸ ታረክ አላቸዉ። ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገሪቱን የአየር ሞገዶች ከዳር እስከ ዳር ያጨናነቀዉ ከዚሁ ከወያኔ የረጂም ግዜ ቆሻሻ ታሪክ ጋር የተያያዘዉ የገንዘብ ጉዳይ ነዉ። ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ባንኮች፤ ትላልቅ መደብሮችና ዘመናዊ የመገበያያ አዳራሾች በብዙ መቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ሀሰተኛ ገንዘብ ተጨናንቀዋል። ይህ ማን፤ መቼ፤ ከየትና እንዴት እንዳሰራጨዉ የማይታወቅ የሀሰተኛ ገንዝብ ዝርጭት ኢትዮጵያ ዉስጥ እያንዳንዱን ሰዉ እያነጋገረ ነዉ። የወያኔ ፖሊሶች ከየባንኩና ከየገበያ አዳራሹ በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሀሰተኛ የብር ኖቶች እየሰበሰቡ መሆናቸዉን ቢናገሩም ከዚህ ሀሰተና ገንዘብ ስርጭት በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለበት ግን ምንም የተነፈሱት ነገር የለም። እንደዚህ ብዛት ያለዉ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ደግሞ አቅምና እዉቀት በሌላቸዉ ተራ ወንጀለኞች የሚሞከር ወንጀል አይደለም። ለዚህም ይመስላል ብዙ ኢትዮጵያዉያን በዚህ ሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት ዉስጥ ያለምንም ጥርጥር የወያኔ ባለስልጣኖች እጅ አለበት ብለዉ በድፍረት አፋቸዉን ሞልተዉ የሚናገሩት። መቼም መሬት ቆፍሮ ቦምብ እየቀበረ በተቃዋሚዎች የሚያሳብበዉና በፈንጂ ህዝባዊ ተቋሞችን እያፈረሰ ሽብርተኛ ብሎ በፈረጃቸዉ ድርጅቶች ላይ ጣቱን የሚቀስረዉ ወያኔ የደረሰበትን ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት ለመሙላት ሀሰተኛ ገንዘብ አሰራጭቶ ሊያጠፋቸዉ በሚፈልጋቸዉ ሰዎችና ቡድኖች ላይ አያመካኝም ማለት አይቻልም። ለሁሉም የወያኔ ነገር አንቺዉ ታመጪዉ አንቺዉ ታሮጪዉ ነዉና ይህ የሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት የራሱ የወያኔ ስራ እንደሆነ ከራሱ ዉስጥ አዋቂ ምንጮች የምንሰማበት ግዜ ሩቅ አይደለም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዉያንን የሙጥኝ ብሎ ተጣብቆ የሚያሰቃያቸዉ የዋጋ ንረት መሠረታዊ መንስኤዉ መለስ ዜናዊ በህይወት ከነበረበት ግዜ ጀምሮ ከአገሪቱ የማምረት አቅም በላይ በሆነ መልኩ በገፍ እየታተመ ወደ ኤኮኖሚዉ ዉስጥ እንዲገባ የተደረገዉ የገንዘብ አቅርቦት ነዉ። ይህ ዘንድሮ ስሙን ቀይሮ “ሀሰተኛ የገንዝብ ስርጭት” ተብሎ አገራችንን የሚያምሳት በሽታም የዚሁ የተለመደ ወያኔ እያተመ የሚያሰራጨዉ የገንዘብ አቅርቦት ችግር አካል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለዉም። አለዚያማ ወያኔ በነጋ በጠባ ሚሊዮንና ቢሊዮን እያለ የሚያባክነዉ ገንዘብ ከዬት ይመጣል?
ስልጠና በየትኛዉም ማህበረሰብ ዉስጥ የእዉቀትና የልምድ ልዉዉጥ ለማድረግ የሚረዳ ጠቃሚ ተግባር ነዉ፤ ሆኖም ስልጠና ሲባል አላማ፤ አትኩረትና ግብ ኖሮት በተወሰነ ቡድን ወይም ቡድኖች ላይ የሚያነጣጥር የእዉቀትና ልምድ መቀባበያ መሳሪያ ነዉ እንጂ እንዳዉ በጅምላ የአንድ አገር ህዝብ እንዳለ ተመሳሳይ ስልጠና ይዉስድ እየተባለ የሚደገስ የጨረባ ተዝካር አይደለም። ደግሞም ስልጠና አሰልጣኝና ሰልጣኝ ተግባብተዉና ሁለቱም ሚናቸዉን ወድደዉና ፈቅደዉ የሚካሄድ የጋራ እንቅስቃሴ ነዉ እንጂ ሠልጣኝ አልሰልጥንም ካለና አሰልጣኝ ደግሞ ጥያቄ የጠየቀዉን ሁሉ “ቆይ ጠብቀኝ” እያለ የሚዝትበት ከሆነ ነገሩ ሥልጠና መሆኑ ቀርቶ ጦርነት ይሆናል። ለመሆኑ ወያኔ የአገሪቱን ወጣቶች ሥልጠና ብሎ ሰብስቦ ምንድነዉ የሚላቸዉ? መልሱ ቀላል ነዉ። ከብዙዎቹ ሰልጣኞች አንደበት በግልጽ እንደሰማነዉ፤ የወያኔ ካድሬዎች በየስልጠናዉ አዳራሽ የሚናገሩት በሚቀጥለዉ ምርጫ ኢህአዴግን ካልመረጣችሁ የወደፊት ዕድላችሁ ይጨልማል፤ ከሐይማኖት አክራሪዎች እራሳችሁን አጽዱ ወይም ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር እንዳትተባበሩ እያሉ ነዉ። ወያኔ በስልጣን ላይ በቆየባቸዉ አመታት ህይወቱ እንደ ሐምሌ ጨለማ የጨለመበት የኢትዮጵያ ወጣት ግን በየስልጠና አዳራሹ በተደጋጋሚ የሚጠይቀዉ እነሱ ሽብርተኛ ብለዉ ያሰሯቸዉን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ባስቸኳይ እንዲፈቱና ወያኔዎችን እራሳቸዉን በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ እያለ ነዉ።
ባለፈዉ የአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊ/መንበር ለኢትዮጵያ ወጣቶች ኑና ለነጻነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት አብረን እንታገል የሚል አገራዊ ጥሪ አድረገዋል። በየዘመኑ ለወገኖቹ መብትና ነጻነት መከበር ሽንጡን ገትሮ የታገለዉ የኢትዮጵያ ወጣት የነጻነት መሪዉ ያቀረበለትን የፍትህና የእኩልነት ትግል ጥሪ ረግጦ ከወያኔ ጋር በተላላኪነት ከሚያስተሳስረዉ ሥልጠና ጋር በፍጹም እንደማይተባበር ሁላችንም እርግጠኞች ነን። ዛሬ ዕድሜዉ ከ35 አመት በታች የሆነ ኢትዮጵያዊ ወጣት አብዛኛዉን ዕድሜዉን በወያኔ ስርዐት ዉስጥ የኖረ ወጣት ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ወጣት ወንድሙ፤ ዘመዱ ወይም የቅርብ ጓደኛዉ በወያኔ ነብሰ ገዳዮች ሲገደሉ በአይኑ እየተመለከተ ያደገ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት የወያኔ በደልና ግፍ የሚነገረዉ ወጣት ሳይሆን ይህንን በደልና ግፍ ለማቆም ቆርጦ የተነሳ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት ወያኔ ሥልጠና እያለ የሚፈጥርለትን አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀመ እራሱንና ወገኖቹን ነጻ ያወጣል እንጂ በሥልጠና ስም ከወያኔ በሚመጣለት ኮቶቶ እጅና እግሩን አስሮ የወያኔ ባሪያ ሆኖ አይኖርም። ለዚህ ቆራጥና አርቆ አስተዋይ ለሆነ ወጣት ያለን መልዕክት አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና በድል የምንገናኝበትና የአገራችን ባለቤት የምንሆንበት ቀን ቅርብ ነዉ የሚል ወገናዊ መልዕክት ነዉ።

No comments: