በመላው አለም በሀያ ስድስት አገራት እና ታላላቅ ከተሞች ሊደረግ የታሰበው የግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ህዝባዊ ስብሰባና የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት የኖርዌይ ዋና ከተማ በሆነችው በኦስሎ ኦገስት 31, 2014 የንቅናቄው ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበበ ቦጋለ በተገኙበት በታላቅና በደማቅ ሁኔታ ተከናወነ።
ህዝባዊ ስብሰባው በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ አዘጋጅነት ከቀኑ 15፡00 ጀምሮ የተካሄደ ሲሆን በህዝባዊ ስብሰባው ቁጥራቸው በርከት ያሉ በኦስሎና በተለያዩ የኖርዌ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች ተሳታፊ ሆነዋል። በፕሮግራሙ መጀመሪያ ህዝቡ በአንድ ላይ ሆነው የግንቦት 7 ህዝባዊ ሀይል መዝሙር የዘመሩ ሲሆን ከህዝባዊ ሀይሉ መዝሙር በመቀጠልምአቶ አቢ አማረ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አጠር ያለ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈው በአለፉት ሃያ ሶስት አመታት በወያኔ የግፍ አገዛዝ ለተገደሉ ንፁሀን ዜጎች የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት አስደርገዋል።
በፕሮግራሙ ቅድመ ተከተልም የመጀመሪያውን ንግግር ያደረጉት አቶ ደባሱ መለሱ የግብረሃይሉ ዋና ሰብሳቢ ሲሆኑ በንግግራቸው ጠንከር ያሉ ሶስት ዋና ዋና መልክቶችን አስተላልፈዋል፦
አንደኛው መልእክታቸው ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሲሆን፦ መልክቱም የደከምክበትን ዓላማ ያለምንም ጥርጥር እናሳካዋለን ምንም ጥርጥር አይግባህ በአሁኑ ሰአት በወያኔ እስር ቤት ውስጥ እየደረሰብህ ያለውን ስቃይ እናውቃለን ነገር ግን አይዞህ ጠላቶችህን እንበቀላቸዋለን ብለዋል ። ሁለተኛው መልክታቸው ደግሞ ወያኔን ለመፋለም ቆርጠው ለተነሱት ታጋዮች ሲሆን ኢትዮጵያውያኖች በማንኛውም ነገር ከጎናችሁ ነን በርቱ ብዙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያኖች አብረናችሁ ነን ብለው ሶስተኛውን መልክታቸውን ደግሞ ለወያኔዎች ሲሆን መልክቱም፦ በውስጣቸው ያለውን የበታችነት ስሜት ትተው ህዝብን ማሰቃየት፣ መግረፍ ማሰርና መግደል እንዲያቆሙ መልክታቸውን አስተላልፈዋል። ከዚያም የግንቦት 7 አላማ ራእይና ተልኮ የያዘ ስለ ግንቦት 7 ምንነት የሚያስረዳ በቪዲዮ የተደገፈ ሰፋ ያለ ገለፃ ተደርጓል።
በመቀጠል ንግግር ያደረጉት አቶ ዮሐንስ አለሙ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ሊቀመንበር ሲሆኑ እሳቸውም በንግግራቸው የግንቦት 7 ህዝባዊ ስብሰባ በመላው አለም የሚደረግ መሆኑን በመጥቀስ ይህ ህዝባዊ ስብሰባ በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ አዘጋጅነት በኖርዌ ኦስሎ መደረጉ እንዳስደሰታቸው ገልፀው በኣሁኑ ሰኣት ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ የወያኔ መንግስት በሀገራችን ላይ እያደረሰ ያለውን ስቃይና መከራ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ይሄ ዘረኛው ቡድን ህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን መከራና ስቃይ ለማስቆም ዋናው አማራጭ ወያኔን ከስልጣን ማስወገድ ብቻ ነው ብለዋል ለዚህም አላማ ሁላችንም ያለማቋረጥ ትግላችንን መቀጠል አለብን ብዙ ስብሰባዎችን፣ ሰላማዊ ሰልፎችን፣ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርገናል ነገር ግን አሁን ወደተግባር የምንሸጋገርበት ጊዜ ነው መሆን ያለበት በማለት የተናገሩ ሲሆን ህዝቡ ከስሜታዊነት ወጥቶ ትግሉን በተግባር እንዲያሳይ ጥሪ በማስተላለፍ ለህዝባዊ ስብሰባው መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉትን ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል።
ከአቶ ዮሃንስ ንግግር በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ አቶ አበበ ቦጋለ ሲሆኑ እሳቸውም ይህ ስብሰባ በተለያዩ ሀገሮች እየተደረገ እንዳለ እና በሁሉም ስብሰባዎች ላይ የሚተላለፉ መልክቶች ተመሳሳይነት እንዳላቸው ጠቅሰው እኔም አንዳርጋቸው ፅጌ ነኝ ማለት ምን ማለት ነው በሚል ለተሰብሳቢው ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል። ህዝባችን በአሁኑ ሰአት በእየአረብ ሀገራትም ሆነ ወደ ሌሎች ሀገራት ለስደት እየተዳረገ ሲሆን የዚህ ሁሉ መሰረቱ የወያኔ የዘረኝነትና የጭቆና የግፍ አገዛዝ በመሆኑ ይህንን አንባገነን ስርዓት አሽቀንጥረን መጣል የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ሃላፊነት መሆን ይገባዋል በማለት ወያኔን በስልጣን ላይ እንዲቆይ ያደረጉ ነገሮች ናቸው የሚሏቸውንም በዝርዝር አቅርበዋል። አቶ አበበ ይህንንም ሲያብራሩ በአሁኑ ሰአት የወያኔ መንግስት የኢትዮዽያ ህዝብን የሴት ማህበር፣ የወጣቶች ማህበር፣ ወዘተ... በማለት በተለያዩ ጥቅሞች ጠላልፎ እድሜውን እያራዘመ እንደሆነ ገልጸው የወያኔ ቡድን ለማስወደድ በተለይም ወጣቶች ታላቅ ሃላፊነት አለብን በአሁኑ ሰአት ትግሉ በታላቅ ሁኔታ ተፋፍሞ ይገኛል በቅርብ የውህደት ስምምነት የተፈራረሙት አርበኞች ግንባር፣ የአማራ ህዝባዊ ንቅናቄ እና የግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ድርጅቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ውህደቱ ይጠናቀቃል ይህ ውህደትም ከትህዲንና ከሌሎች በትጥቅ ትግል ከሚታገሉ ድርጅቶች ጋር ይቀጥላል። ይህ በድርጅቶች መካከል የተጀመረውን የውህደት አንድነት ማገዝ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆን ይጠበቅበታል በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል።
በስብሰባው አቶ ሙላው የትህዲን ሊቀመንበር በስልክ የትህዲንን ራእይና አመሰራረት ከተናገሩ በኋላ በአሁኑ ሰአት ድርጅታቸው የወያኔን መንግስት በከፍተኛ ሁኔት እየተፋለሙትና ብዙ የትግራይ ወጣቶች ትግሉን እየተቀላቀሉ እንደሆነ አስረድተዋል። ድርጅታቸው ለምን የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲ ንቅናቄ በዚህ አይነት የስም ስያሜ መሰየሙ በአላማና በምክንያት የሆነ እንደሆነ በመናገር እየታገሉ የሚገኙት ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሆነና እኛ ብቻችንን ለውጥ እናመጣለን ብለን ስለማናምን ወያኔን ከሚፋለሙ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ለመስራት እንደ አገር አላማ ይዘን የተነሳነው እቅድ ነው ብለዋል። በተመሳሳይ የአርበኞች ግንባር እና የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይል ተወካዮችም በስልክ ለተሰብሳቢው መልክታቸውን አስተላልፈዋል።በመቀጠልም የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ስራዎች የሚዘክር አጭር የቪዲዮ ገለፃ ተላልፎ የመጀመሪያው ዙር ተጠናቆል።
ስብሰባው ለአጭር ደቂቃ እረፍት በመውሰድ የምሳና የሻይ ቡና መስተንግዶ ከተደረገ በኋላ በቀጥታ ወደ ጨረታ ስነስርአት አምርትዋል ለጨረታ የቀረበው የአርበኛው አንዳርጋቸው ፅጌን ምስል የያዘ ፎቶ ግራፍ ሲሆን ፎቶ ግራፉ ወደ ጨረታው ስፍራ በባንዲራ ታጅቦ ሲመጣ ህዝቡ ከመቀመጫው በመነሳትና በጭብጨባ ደማቅ አቀባበል አድርጓል። በጨረታውን እጅግ በርካታ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን የበርገን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት እና የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ዋና ፅ/ቤት በከፍተኛ የገንዘብ መጠን የተፎካከሩ ሲሆን ጨረታው በዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ ዋና ፅ/ቤት አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ሎተሪዎች፣ መፅሐፍቶች እና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ቁሳቁሶችም ለገቢ ማሰባሰቢያው ሽያጭ ላይ ውለው መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ገቢ ለማግኘት ተችሏል።
በመጨረሻም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ም/ሊቀመንበር የመዝግያ ንግግር ካደረጉ በኋላ ላንቺ ነው ሀገሬ ላንቺ ነው ላንቺ ነው ኢትዮጵያ ላንቺ ነው የተሰኘውን የግንቦት 7 ህዝባዊ ሃይልን መዝሙ ዘማሪዎች እና ተሰብሳቢው በጋራ በመዘመር ዝግጅቱ በተያዘለት ሰአት በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። የመድረክ መምራቱን ስራ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ በተሳካ ሁኔታ ያከናወኑልን ወ/ሪት ዙፋን አማረ እና አቶ ሳሌ አብርሃ መሆናውንም ለመግለፅ እንወዳለን።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌ
No comments:
Post a Comment