Tuesday, August 12, 2014

ከኢህአዲግ/ወያኔ መላቀቅ ማለት ከድንቁርና ነፃ መውጣት ነው!

August 12/2014
press freedomሰሞኑን የኢህአዲግ/ወያኔ የኮምንኬሽን ሚኒስትር ዴታ የነበሩት አሁን በስደት የሚገኙት አቶ ኤርምያስ ለገሰ የሰጡትን መግለጫ  በኢሳት ቴሌቭዥን እየተከታተልኩ ነበር።አቶ ኤርምያስ ከተናገሩት ውስጥ የኢህአዲግ/ወያኔ አመራሮችም ሆኑ ቡድኑ ባጠቃላይ የተማሩ ኢትዮጵያውያንን ለምን እንደሚያሳድድ ያስረዱበት መንገድ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።አቶ ኤርምያስ ኢህአዲግ/ወያኔ በመመርያው ውስጥ የተማሩ አባላት ከ 1% እንዳይበልጡ ለምን እንደሚደረግ እና ባጠቃላይ ድርጅቱ የተማሩ ኢትዮጵያውያንን የሚጠላበትን መሰረታዊ ምክንያት ሲያስረዱ እንዲህ ነበር ያሉት (ቃል በቃል ባይሆንም ሃሳቡን እንዲህ ይገለፃል) -
  ”ማየት ያለብን ድርጅቱን የሚመሩት ሰዎች አነሳስን ነው።እነኝህ ሰዎች ገና የ 16 እና 17 ዓመት ልጆች ሆነው ከግብርና ተነስተው (ግብርና የተከበረ ሙያ መሆኑን ሳንዘነጋ) ወደ ውግያ ገቡ።ዋናውን የወጣትነት ጊዜ ማለትም እውቀት የሚቀሰምበት እና የህዝቡን ማህበራውም ሆነ ቤተሰባዊ ሕይወት በማወቅያቸው ጊዜ ሁሉ ለአስራ ምናምን ዓመት የሚያውቁት መተኮስ ነው።አሸንፈው ቤተመንግስት ሲገቡ የመማርያ ጊዜ አልፏል።እኛ ያለፍንበትን የቤተሰብ ሕይወት እና ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተውን የዕውቀት መገብየት ዘመን አያውቁትም።ትምህርት ቤት አያውቁም፣ማህበራዊ ኑሮ አያውቁም።በመሆኑም  የተማረ ሰው አዲስ ሃሳብ ይዞ ከመጣ ይገለብጠናል ብለው ይሰጋሉ።” ነበር ያለው።ሚዛን የሚደፋ አገላለፅ ነው። 
ይህንን የአቶ ኤርምያስ አባባል በሰማሁበት ሰሞን ዛሬ ደግሞ ”የአዲስ ጉዳይ” መፅሄት ባለቤት እና ሶስት አዘጋጆች የመሰደዳቸው ዜና ተሰማ።የጋዜጠኞች መሰደድ እና የግል ሕትመት ውጤቶች መዘጋት በዘመነ ኢህአዲግ/ወያኔ የተለመደ ዜና መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን የሕትመት ውጤቶችን መዝጋት ከፖለቲካዊ አንደምታው በዘለለ የኢህአዲግ/ወያኔ ትውልዱን አደንቁሮ የመግዛት እቅዱ አካል መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው።

1/ ”ትምህርት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መጠመቅ ብቻ ነው” ኢህአዲግ/ወያኔ 

ዕውቀትን በመግደል ኢህአዲግ/ወያኔን የሚተካከለው የለም።የተማረው ክፍል ከአብዮታዊ ዲሞክራሲው ጫማ ስር ተንበርክኮ የምልኮሰኮስ እንዲሆን ለማድረግ ሃያ ሶስት ዓመታት ሙሉ ስታትር ተስተውሏል።እዚህ ላይ የዩንቨርስቲ ቁጥር መጨመር ግን በጥራት የወረዱ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን የትምህርት ደረጃው ባጠቃላይ ከሳሃራ በታች ካሉት ሀገሮች ጋርም መወዳደር የማይችል ደረጃ የደረሰው በዘመነ ኢህአዲግ/ወያኔ ነው።
 የዩንቨርስቲ ቁጥር ጨመርኩ ባለበት አፉ  የትምህርት ጥራትን መግደሉን እራሱ ኢህአዲግ/ወያኔም  በተለያየ መድረክ አረጋግጧታል።
እንደ ‘እስስት’ የሚቀያየረው የትምህርት ፖሊሲ በአንድ ሀገር የምንኖር መሆናችን ግራ እስኪገባን ድረስ አንዴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እስከ 10ኛ ሆነ።ሌላ ጊዜ የለም እስከ 12ኛ ክፍል አደረግነው። መልሰው ደግሞ የሶሻል ትምህርት 30% ሆነ፣ወዘተ እየተባለ በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ የተደናገሩ ዓመታት ሰለባ የሆነው ይሄው ትውልድ ነው።
መምህራን ግራ ተጋብተው ”በአብዮታዊ ዲሞርክራሲ ማደናገርያ ተጠመቁ” ተብለው በተማሪ ካድሬ እንዲመሩ እና እንዲሸማቀቁ የተደረጉት ብቻ ሳይሆን እነኝሁ ትውልድ ቀራጮች እንባ አውጥተው ሲያለቅሱ የታዩት አሁንም በኢህአዲግ/ወያኔ ዘመን ነው።

2/ ”ጫት ቤት እና ሺሻ ቤት ይስፋፋ! መፃህፍት ቤት እና የሚነበቡ የሕትመት ውጤቶችን  ዝጋ!”

ወደ ኃላ ሄደን በ1983 ዓም አዲስ አበባ ስንት የጫት ቤቶች እና ሺሻ ቤቶች ነበሩ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ግልፅ ነው።ባለፉት 23 ዓመታት ውስጥ ከዜሮ ከሚባል ደረጃ ዛሬ የእየደጃፋችን እና የትምህርት ቤቶች መዳረሻዎች ሁሉ በጫት መቃምያ እና በሺሻ ቤቶች እንደተሞሉ እንረዳለን።ለእዚህ ማሳያ የሚሆነን ከዛሬ 23 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ በሚኖሩ ሱቆች ላይ  ”የጫት መሸጫ ሱቅ” ብሎ መለጠፍ አስነዋሪ እና በህብረተሰቡ ዘንድተቀባይነቱ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም  ነበር።
Chat trader2
በኢህአዲግ/ወያኔ ዘመን የተስፋፋው የጫት ገበያ
ብዙም አልቆየ ኢህአዲግ/ወያኔ ስልጣን በያዘ በወራት ውስጥ ”የበለጩ ጫት፣የባህር ዳር ጫት” እና ሌሎችም ማስታወቂያዎች ተኮለኮሉ።ዩንቨርስቲዎች፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወዘተ በጫት ተጥለቀለቁ።ኢህአዲግ/ወያኔ እና ካድሬዎቹ ዋና አቀባባይ እና አሰራጮች ሆኑ።የጫት ሱሱ ከፍተኛ የኢህአዲግ/ወያኔ ባለስልጣናትን ሁሉ በሱስ ተጠምዷል እና አዲሱ ትውልድንም ለማደንዘዝ እንደ አንድ መሳርያ ተጠቀመበት።
የጫት እና ሺሻ ቤቶችን በየመንደሩ ያስፋፋው ኢህአዲግ/ወያኔ በጎን በኩል ደግሞ ወጣቱ በማንበብ እራሱን በእውቀት እንዳያበለፅግ የሰራቸው ሁለት ተጨማሪ ወንጀሎች አሉ።የመጀመርያው ከተሞች መፃህፍት ቤት እንዳይኖራቸው ምንም ባለማድረግ ሲሆን ሁለተኛው የነፃ የህትመት ውጤቶችን ማፈን ነበር

 2.1 ”መፃህፍት ቤት ዝጋ ጫት እና ሺሻ ቤት ክፈት!”

ከሶስት ሚልዮን በላይ ሕዝብ ያላት አዲስ አበባ የጫት ቤት እና ሺሻ ቤቶች ተስፋፉባት እንጂ መፃህፍት ቤት እንዲኖራት ኢህአዲግ/ወያኔ አልፈቀደላትም።በ 1997 ዓም በነበረው ሃገራዊ ምርጫ ቅንጅት ለአዲስ አበባ አቅርቦት የነበረው የምርጫ መቀስቀሻ ነጥቦች ውስጥ አንዱ ”በአዲስ አበባ ውስጥ በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ውስጥ ቢያንስ አንድ መፃህፍት ቤት መክፈት” የሚል የነበረ መሆኑን የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ያስታውሳል።ለሀገር ማሰብ ትውልድን በእውቀት ማነፅ እና የማንበብ ባህልን በማዳበር ይጀመራልና ቅንጅት ከየት እንደሚጀመር ያሳየበት ጥበብ የተሞላበት የስራ ዕቅድ ነበር ያቀረበው።
ኢህአዲግ/ወያኔ ስልጣን ከያዘ ወዲህ አዲስ አበባ አንድ ደረጃውን የጠበቀ መፃህፍት ቤት አላየችም።በግል ባንድ ጊዜ ከሁለት እና ሶስት መቶ ሰው በላይ የማያስተናግዱ መፃህፍት ቤቶች በስተቀር ከተማዋ መፃህፍት ቤቶች የሏትም። ማንበብ የማይወዱት ባለሥልጣኖቻችን የኢትዮጵያን ከተሞችም በጨለማ ውስጥ ከትተው ዓመታትን አሳለፉ።እስካሁን ባሉ መረጃዎች አዲስ አበባ ከሶስት ሚልዮን በላይ ነዋሪ ቢኖራትም አሁንም ድረስ በመፃሕፍት ብዛቱም ሆነ በትልቅነቱ የሚጠቀሰው ለሕዝብ ክፍት የሆነው መፃህፍት ቤት ከአርባ ዓመታት በፊት በብላቴ ጌታ ሕሩይ ወ/ሥላሴ የተሰራው ”ብሔራዊ ቤተ መዘክር (ወመዘክር)” ተብሎ የሚጠራው እና ባህል ሚኒስቴር አጠገብ የሚገኘው ብቻ ነው።እዚህ ላይ የዩንቨርስቲዎች ወይንም የድርጅቶች መፃህፍት ቤቶች ለሁሉም ሕዝብ ክፍት ስላልሆኑ የህዝብ መፃህፍት ቤት ተብለው እንደማይወሰዱ ለማሳሰብ እወዳለሁ።
አብዛኛው ወጣት ሥራ አጥ ሆኖ ከቤት  የሚውልባቸው ከተሞች የመፃህፍት ቤቶች ቢስፋፋላቸው በርካታ ጥቅም እንደሚኖራቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።የመጀመርያው ጥቅም ጊዜን ከአልባሌ ቦታ ጠብቆ ማሳለፍ ሲሆን ሁለተኛው አዲስ የስራ መስክ ለመፍጠር ከፍተኛ የስነልቦና ልዕልና የመቀዳጀቱ ፋይዳ ነው።ኢህአዲግ/ወያኔ ግን በተቃራኒው ለወጣቱ የደገሰለት የጫት እና ሺሻ ቤቶችን በእጥፍ ማስፋፋት ነው። 

2.3 ‘‘የሕትመት ውጤቶችን ዝጋ! አደንቁረህ ግዛ!”

ኢህአዲግ/ወያኔ መፃህፍት ቤቶችን ብቻ አይደለም ያቆረቆዘው።ላለፉት ሃያ ሶስት ዓመታት እየተከታተለ ሲያጠፋ የኖረው ለትውልዱ ጭላንጭል የዕውቀት ብርሃን የሚፈነጥቁ የነበሩትን የግል የህትመት ውጤቶችን ነው።ትውልድ የማንበብ እና የማወቅ መብቱ የተዘጋው በጣት የሚቆጠሩ የነፃው ፕሬስ ውጤቶችን ነው።ቀደም ብሎ ኢህአዲግ/ወያኔ የግል ፕሬሶችን ሲወቅስ የነበረው ‘የጋዜጠኛ ሙያ የላቸውም፣ተቃዋሚዎች ናቸው’ ወዘተ እያለ ነበር።ሆኖም ግን ይህንን አባባል ገደል የሚከቱ በፖለቲካ ትንታኔ ምጥቀትም ሆነ በምርምር ላይ በተመሰረቱ ጥናታዊ ፅሁፎችን በማተም ዝናን ያተረፉትን እንደ ”አዲስ ነገር ጋዜጣ” እና  ”የአዲስ ጉዳይ” መፅሄትን ለህትመት እንዳይበቁ የጭካኔ በትሩን አሳረፈባቸው። ኢህአዲግ/ወያኔ ትውልዱን አደንቁሮ የመግዛት ደረጃውን ለመረዳት ሃገራችንን ከአሜሪካ እና አውሮፓ ህትመቶች ጋር እያወዳደርኩ አይደለም።ነፃነቷን ካገኘች ገና ግማሽ ክ/ዘመን ካስቆጠረችው  ከኬንያ ጋር ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ማመላከት ብቻ  የኢህአዴግ/ወያኔ  ”አደንቁረህ ግዛ!” ፖሊሲምን ያህል አስከፊ እንደሆነ በግልፅ ያሳየናል።
ኢህአዲግ/ወያኔ እግር በእግር እየተከታተለ የህዝቡን የዕውቀት እና የማንበብ ባህል የሚገድልበት የግል ህትመት ውጤቶች ከሰማንያ ሶስት ሚልዮን በላይ ለሆነ ሕዝብ በአንድ ሳምንት ውስጥ የሚያሰራጩት የሕትመት ብዛት 20 ሺህ የማይሞላ ሲሆን በሕዝብ ብዛቷ ከኢትዮጵያ ከግማሽ በታች የሆነችው ኬንያ በእየቀኑ ብቻ ”ዴይሊ ኔሽን” የተሰኘው ጋዜጣ ብቻ ከሩብ ሚልዮን በላይ ለሆነ ሕዝብ አዳርሳ ታድራለች።ይህንን ወደ አንድ ሳምንት ስንቀይረው በኬንያ ብቻ ወደ 1.4 ሚልዮን የሚሆን ሕዝብ የሕትመት ውጤቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ ይደርሱታል ማለት ነው።ይህ እንግዲህ በድረ-ገፅ የሚያነበውን አይጨምርም።
ኢህአዲግ/ወያኔ የማንበብ እና የማወቅ መብታችንን ማፈኑ ብቻ አይደለም ትውልዱ የማንበብ ባህሉ እንዲሞት በተለዋጭ ግን የጫት እና የሺሻ ሱሰኛ እንዲሆን ተገዷል።ይህ ታሪካዊ፣አድሏዊ እና ዘረኛ ወንጀል ነው።ምክንያቱም ይህ ተግባር በሁሉም የኢትዮጵያ ወጣት ላይ አልተደረገማ! ጫት እንዳይሸጥባቸው ሀሽሽ እንዳይዘወተርባቸው በቂ ቁጥጥር የሚያደርግ ክልል አለና! ”አደንቁሮ መግዛት” ማለት ይህ ነው።ከኢህአዲግ/ወያኔ መላቀቅ ማለት ከድንቁርና ነፃ መውጣት ማለት ነው።ይህ ደግሞ በትውልዱ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነው።ዕውቀት ወይስ ድንቁርና? ለትውልዱ የቀረቡ ሁለት ብቸኛ አማራጮች።

ጉዳያችን 

ነሐሴ 6/2006 ዓም (ኦገስት 12፣2014)

No comments: