Friday, August 1, 2014

የህወሃት ሽብር መቆም አለበት!

August1/2014
ዛሬ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ያለ አሸባሪ ወያኔና ወያኔ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ መንግስት በመተቸታቸው በግልጽ በመጻፋቸውና በአደባባይ በመናገራቸው ከዚህም አልፎ በጥርጣሬ በተለይም በብሄረሰብ ማንነታቸው እያሳደደ የሚያፍን የሚያሰቃይና የሚገል የሽብር ተቋም ካለ ወያኔ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ መሬት ላይ ሰላማዊ ዜጎችን ኢላማ ያደረገ የተቃውሞ ሃይል በተግባርም ሆነ በአስተሳሰብ ከወያኔ ውጪ አንዳች ሃይል የለም።
አፋኙ የወያኔ ስርአት በተለየም የህዝቡን ሀብትና ንብረት እየዘረፉ የሚቀማጠሉት የህወሃት መሪዎችና ሎሌዎቻቸው የተቃውሞ ድምጽ በሰሙ ቁጥር እንደሚሸበሩና እንቅልፍ አጥተው እንደሚያድሩ ይታወቃል። አፍነውና ዘርፈው ገለው የሚገዙት ህዝብ ግፍ በዛብኝ ብሎ በተናገረ ቁጥር የሚሸበሩት እነሱ ብቻ እንጂ ህዝቡ አይደለም።
በኢትዮጵያ ምድር ያለው አሸባሪ ወያኔ ብቻ መሆኑን ሺ ምሳሌዎችን ጠቅሶ ማስረዳት ይቻላል። ሶስት አመት ሙሉ የሰላም እጃቸውን እየዘረጉ ከልመና ባልተለየ ሁኔታ መብታቸውን የጠየቁና ድምጻችን ይሰማ ያሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ማንንም ዜጋ አላሸበሩም። የተገላቢጦሽ እነሱ አሸባሪ ተብለው የግፍ ሰቆቃ ይፈጸምባቸዋል። ጋዜጠኞችና ጦማሪዎቹ መንግስት ያወጣውን ህግ እንዲያከብር ስለጠየቁ በአደባባይ ስለጻፉ ግፍ ይፈጸምባቸዋል። እነሱ ያሸበሩት ሀገርና ህዝብ የለም። ከመንገድ ላይ ጎትተው እንደ እባብ ቀጥቅጠውና ፈነካክተው በማግስቱ ፍርድ ቤት ያቀረቧት ወየንሸት ሞላ የተባለች ባለ ተስፋ ወጣት የወያኔ አረመኔዎች በሙስሊሙ ህዝብ ላይ የሚሰሩትን ጭፍጨፋ እግር ጥሏት ከማየትና ከመታዘብ ውጪ ያሸበረችው ሰው፣ ሀገር የለም። በየወህኒ ቤቱ እና አፈና ጣቢያው ታስረው የሚቀጠቀጡት የኦሮሞ ልጆች ለጥያቄያቸው መልስ ሲጠብቁ ከመጨፍጨፍ ያለፈ የፈጸሙት እብሪት የለም። በየክልሉ ቀና ብለህ ባለስልጣን ተናገርክ፣ ጥያቄ ጠየቅክ፣ ባለስልጣን ደፈርክ፣ ተሰብስበህ አየንህ ወዘተ እየተባለ የሚገረፈው እንደ እንስሳ እየተገደለ የሚጣለው ገበሬ የሰራው ወንጀል የለም። አሸባሪም አይደለም! በየቦታው ቦንብ እየቀበረ አፈንድቶ ንጹሃንን ገድሎ ሊያፈነዱ ሲሉ ፈንድቶባቸው ራሳቸውን ገደሉ ብሎ በአደባባይ የሚሳለቀው አሸባሪው ህወሃት እንጂ ንጹሃኑ አይደለም።
የኛ መሪ አንዳርጋቸው ከልጅነት እድሜው ጀምሮ ራሱን ለህዝብ ነጻነት የሰጠ አርበኛ እንጂ አሸባሪ አይደለም። በተመሳሳይ ውንብድና ከጎረቤት ሀገር ድረስ በአለም አቀፍ የወረበሎች ውንብድና መንገድ ወያኔ እያፈነ የገደላቸው አሮሞዎችና፣ ሱማሌዎች፣ አኙዋኮች፣ አማሮችና ሌሎችም ነጻነት ከመፈለግ ውጪ ያሸበሩት ህዝብና ሀገር የለም።
በኢትዮጵያ ምድር የነጻነት ድምጽና ኮሽታ በሰማ ቁጥር የሚሸበረው ህወሃትና በለሟሎች ብቻ ናቸው። ይህ የነጻነት ድምጽ ደግሞ እየጎላ መሄዱ የማይቀር ነውና ወያኔ ሰፈር ሽብር ይሆናል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ወጣት፣ ሴት፣ ሽማግሌ፣ ገበሬ እና በየቦታው ያላችሁ የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ! አሸባሪህ ወያኔና ወያኔ ብቻ መሆኑን አውቀህ በገዛ ሀገርህ ላይ ነጻነት በተመኘህና በጠየቅህ ጊዜ ሁሉ ለሽብር ጥቃቱ ኢላማ ያደረጉህን ወያኔ ተባብረን ከላያችን ለማውረድ ተነስ! በያለህበት እምቢ በል! ለወያኔ የሚጠቅም የመሰለህን ነገር ሁሉ አታድርግ! አትተባበር! ሸቀጣቸውን አትግዛ! ወያኔዎችን ከማህበራዊ ሂወትህ አግል! የቻልክ ሁሉ ደግሞ የነጻነት አርበኞችን ዛሬ ነገ ሳትል አሁን ተቀላቀል!!! ነጻነታችን ያለው በእጃችን ላይ መሆኑን አትዘንጋ። ግንቦት 7 ሁልጊዜም ከመቼውም ጠንክሮ ከጎንህ ነው።
የወያኔን ሽብር በተባበረ ሃይል እናቁመው!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!

No comments: