Saturday, July 19, 2014

ለዴሞክራሲ ነፃነት በሚደረግ ትግል የሚሸበረው ማን ነው?!

July 19, 2014
ጌታቸው ፏፏቴ
መግቢያ፦ በሜዳ የሚደረገው ትግል እየጠነከረ ሲሄድና ዳሩ መሃል እየሆነ ሲመጣ ነገሮች ሁሉ አዳጋች ሲሆኑ ገዥዎች በሥልጣን ለመሰንበት የሚወስዷቸውን እርምጃዎች ከዚህ ቀደም ደርግ ይወስድ ከነበረው ርምጃ በቂ ትምህርት አግኝተናል። በጭፍን አስተሳሰብ ዐይኑ ያልወደደውን ሁሉ ወደ እስር ማጋዝና ነጻ ርምጃ በሚል ፈሊጥ በጅምላ ሕዝብ ጨፍጭፏል። «የፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት»ሳይባል የተገደሉትን ብርቅየ የኢትዮጵያ ልጆችማ ቤት ይቁጠራቸው።

ህወሃት አሁን የሚገኘበት ደረጃ የሚያሳየውም ያነውኑ ነው። በሰላማዊ መንገድ መታገል በራሱ በህወሃት ሕግ የተፈቀደ ነበር። ነገር ግን አንዲት ጠጠር ሳይወረውሩና ቅጠል ሳይበጥሱ ሕጉ በሚፈቅድላቸው መንገድ በመሄድ እየታገሉ ባሉ የተቃዋሚ ኃይሎች ላይ ህወሃት ያደረሰባቸውን እንግልት እስራትና ንብረት ዘረፋ ተመልክተናል። በአብዛኛው እኔ በመጣሁበት መንገድ ካልመጣችሁ በማለት ገፊ ሁኔታዎችን እየተነኮሰም ነው። የሰላማዊ ትግሉን እንዳይቻል አድርጐታል እንጅ ቢቻል በሰላማዊ መንገድ ታግሎ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን መረከብ ወይም ማስረከብ የ21ኛው መቶ ዓመት ሥልጡን ህዝብ ጨዋ ሥነ-ምግባር ነበር። እነዚህ የኛ ድናቁርቶች ግን በሕገ-አራዊት እየተመሩ ነገር የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም።

እነዚህ የዘረኛ ሥርዓት(አፓርታይድ)አራማጆች መንገዱ ሰለጠኝ ብላ ገበያውን አልፋ ሄደች እንዲሉ ኅሳዊ መሲኅ ለህዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል የአጼውን ሥርዓት አውግዘው ነበር።ደርግ ይፈጽማቸው የነበሩ መጠነ ሰፊ ግፎችንም አጋኖ በማቅረብ የህዝብ መቀስቀሻ በማድረግ ተጠቅመውባቸዋል። ስለ ደርግ ፋሽስታዊ ድርጊት እየሰበኩ ግን ራሳቸው ከደርግ በከፋ ሁኔታ በራሳቸው አባልና በሕዝብ ላይ አሰቃቂ ተግባሮችን ይፈጽሙ ነበር። በተለይም በገበያ ቀንና በቤተክርስቲያን እንዲሁም ሕዝብ በብዛት በሚኖርባቸው መንደሮች ሆነ ብለው ጦርነት በመጫር ያስጨረሱት ሕዝብ የሚያስከፍላቸው ዋጋ በፍጹም ሊዘነጋ የሚችል አይደለም። አሁን ደግሞ በትረ ሥልጣኑን ከጨበጡ በኋላ መደበኛ ተግባራቸው ሕዝብን ማሰቃየት መግደልና ማሰደድ በነሱ መንደር እንደ አንድ ትልቅ እድገት የሚታይ ሆኗል። በህወሃት ጋብቻ ከመፈቀዱ በፊት ግንኙነት ፈጽማችኋል ተብለው የተገደሉ፤ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ(አመለካከት) አላችሁ ተብለው በሽዎች የሚቆጠሩ የህወሃት መከላከያ ሠራዊት አባላት ደብዛቸው መጥፋቱን የማያውቅ ይኖራል ብየ አልገምትም። የራሱን አባላት እየበላ የመጣው ህወሃት ነጻነት እናገኛለን ብለው ቦንብ እንደጨበጡ ታንክ ላይ የሚወጡ ወጣቶችን ህይወት ደመ-ከልብ (የውሻ ደም) ሆኖ ጥቂቶችን በመያዝ ዘልቆ አሁን ያሉበትን ደረጃ እየተመለከትን ነው። የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር እኛ ሰዎች ለምን ካለፈው ስህተትና ውድቀታችን ተምረን ትክክለኛውን መንገድ መያዝ እንደማንችል ነው። አሁን ያለው የህወሃት የመከላከያ ሠራዊት ፤ የፖሊስ ሠራዊትና የሰላዩ ቡድን(የህወሃት ደህንነት) ደህንነቱን ደህንነት ሲሰልለውና ሲያስረው፤ፖሊሱን ፖሊሱ ሲያስረው፤የመከላከያ ሠራዊቱ በኋላውና በፊቱ በሁለት ጥይት ሲመታና ደብዛውን ሲያጠፉት ምን እየጠበቀ ነው?

በትክክለኛው አተረጓጎም ህወሃትን መግለጽ የተቻለ ባይሆንም በገደምዳሜው በቅርቡ በናይጀሪያ አዲስ ስያሜ ይዞ ብቅ ያለው«ቦኮሐራም» ሕጻናትን እያፈነ ድራሻቸውን እንዳጠፋው ህወሃት ለ23 ዓመታት ያህል በቆየበት የግዛት ዘመኑ ተኪ የማይገኝላቸው ኢትዮጵያውያንን በልቷል። አሁንም ከኢትዮጵያም አልፎ እጁን በማስረዘም የኢትዮጵያ አጎራባች በሆኑ አገሮች እየፈጸመ ያለው የጠለፋ ተግባር ኢትዮጵያውያንን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። ወራሪው የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተህዶ ቤተክርስቲያንና በአማራ ነገድ ሕዝብ ላይ ፋሽስታዊ ዘመቻ ከጀመረ አርባ ዓመት አሳልፏል።አሁንም ያን የአውሬ ፋሽስታዊ ባህሪውን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ከምርጫ 1997 ዓ/ም ወዲህ ህወሃት ያደረጋቸውን እንቅስቃሴዎች ስንመለከት ድሮ አውሬ የነበረ ቢሆንም አሁን ደግሞ አውሬነቱ ብሶበት ቀጥሏል። በቤተክርስቲያን በኩል አሁን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ህወሃት ተሳክቶለታል የሚያስብል አንድምታ አለ።ህወሃታዊ ቤተክርስቲያናት አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭው ዓለምም እንደ-አሸን ፈልተዋል።በውጭው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሥርዓቱ ያሰደደው ሆኖ ሳለ ለዚህ ስደተኛ ኢትዮጵያዊ የውጭው ስደተኛው ሲኖዶስ ወይም ህወሃታዊ ያልሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቂ ነበር።ህወሃት ግን በስደትም በሰላም እንዳንኖር እያደረገ ያለ መሆኑን ነቅቶ የጠበቀው ያለ አይመስልም።የትግሬ ቤተክርስቲያን፤ የኦሮሞ፤ የአማራ …ወዘተ እየተባለ ለሕይወቱ ዋስትና አጥቶ የተሰደደውን ኢትዮጵያዊ ሰላም እንዲያጣና ተከፋፍሎ እንዲቆም አድርጓል።

የአማራውን ነገድ ዘር ማጥፋትና ማስወገድ በተመለከተ መደረግ ያለበትን ሁሉ ህወሃት ያደረገ ቢሆንም መላውን የአማራ ህዝብ ለማጥፋት አልተቻለም።በርግጥ ሮጠው የሚቀድሙ፤ታግለው የሚጥሉትንና ተናግረው የሚያሰሙትን የክፉ ቀን ደራሽ ቁርጠኛ ትውልደ አማራዎች ቀጥፎ በልቷል።እንዴት እነማንን?የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ካለ በሕይወቱ እንዳለ አድርጎ መቁጠር ያስቸግራል።ለሆዱ ያደረውን ዐሣማ ፍጡር(ሆዳም አማራ)ሆዱን በማምለክ ከህወሃት ለሚጣልለት ፍርፋሪ ሲል የራሱን ህዝብ ማዋረዱ ማሳደዱና ነዳጅ ሆኖ ማስፈጀቱ የሚያስከፍለውን ዋጋ ይህ ነው ባይባልም መታሰብ ይኖርበታል።ከዚህ ባሻገር ያለው ትውልደ አማራ ግን ለምን ያንጎላቻል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ስለሆነ ተጠየቅን እንካችሁ እላለሁ።

ዛሬ በአብዛኛው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙት ትውልደ አማራ የሆኑ ወጣቶች ናቸው ይህን ጩኸት ህወሃት አልወደደውም ምክንያቱም የቤት ሥራውን መጨረሱን በራሱ ሚዲያ ተናግሮ ስለነበር አሁን ያለው ትውልድ የህወሃት ሰለባ አለመሆኑን በማስመስከሩና ታሪኩን የጠበቀ ሆኖ በመገኘቱ እነ አባይ በረከትና አዲሱ ለገሠ(የመለስ ራእይ አስፈጻሚዎች) ሌላ አይነት መንገድ እየተከተሉ እንደሆነ ማሳያዎችን በሰሞኑ አስመስክረዋል።

የዛሬዎቹ ዘመናዊ ፋሽስት መሪዎች በርሃ እያሉ ድሎት ጎድሎባቸው አያውቅም የቀን ሐሩር የሌሊት ቁር አቀበት ቁልቁለት አልወጡ አልወረዱም፤ አውደ ውጊያ ውስጥ ገብተው ማንነታቸው አልተፈተነም።ታጋዩንም ሆነ ህዝቡን ግራ በማጋባት የዛሬዋን ወንበር የሚጨብጡበት መንገድ ነበር ያጠኑ የነበረው።ቀኝም ነፈሰ ግራ ለአርባ ዓመት ያህል ጥርሳቸው እስኪነቃነቅ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብት ግጠው በልተዋል፤አለ የለም የሚባለውን የህዝብ ሀብት ዘርፈው በውጭው ዓለም ከፍተኛ የንግድ ቱጃሮች ሆነዋል።የሀገሪቱን ሀብት ለመጥፎ ተግባር እንዲውል በማድረግ መንገዱ ሁሉ ቀና እንዲሆንላቸው የሚቃወማቸውን የአንድነት ኃይልም ማስጠለፍ ጀምረዋል።

የህወሃት ቡድን የፀረ ሽብር ሕግ ሲያወጣ ከህዝብ የተነጠለ መሆኑን ያስመሰከረበት ወቅት ሲሆን ይህ የአሸበሪ ህግ እማን ላይ እንደሚመዘዝ አስቀድሞ ገብቶኛል።መፍትሔው ግን ያ አልነበረም የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠማው መልካም አስተዳደር፤የሕግ የበላይነትና ሰላም ነበር።ከህዝቡ መሀል የፈለቁ ሥርዓቱን የሚቃወሙ ሰላም ፤የህግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር እንዲኖር የሚታገሉትን ማጥመድ የህወሃት ዋና ተግባርእንደሚሆን እገምት ስለነበር ያ ያሰጋኝ ነገር እውን ሆነ። እውነቱን እንነጋገር ካልን አልቃይዳንም ሆነ አልሸባብን የሚቀርበው ህወሃት እንጅ የተቃዋሚ ኃይሎች ወይም የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም።ሩዋንዳ፤ ደቡብ ሱዳንና ሶማሌ የተዘመተውም የዶላር ጥማትን ለማርካት እንጅ ሰላምን ለማምጣት አለመሆኑን እርግጠኛ ነበርኩ አሁንም ነኝ።

በተደጋጋሚ ለሚዲያዎች በማቀርባቸው ጹሑፎቼ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚሰማኝን ለአንባብያን ሳቀርብ እውቀቱ ያለው የረሳውን አስታውሶ ጠንከር ያለ ጹሑፍ እንዲያወጣ ሲሆን ጥሩ ምልክቶችንም አይቸበታለሁ።በአንድ አገር የአሸባሪ ሕግ ሲወጣ ካለው ነበራዊ ሁኔታ ተነስቶ መሆን እንዳለበትና ሕዝብን የሚያሰጋ ሲሆን እንደሆነ ይገባኛል። የህወሃት የአሸባሪዎች ሕግ መሠረቱ ግን በትረ ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን አጭበርብሮ ሥልጣን የያዘ በመሆኑ እድሜውን ለማራዘም ያለመው ፈጠራ እንጅ ሕዝብን እያሸበረ ያለውማ ህወሃት ነው።ህወሃት በንግግር ከተሸበረ፤በሚፃፍ ነገር ከተሸበረ፤በተደራጀ ኃይል ከተሸበረ፤የአመጽ ትግል በጀመረ ኃይል ከተሸበረ፤የእምነት ነፃነት ይከበር ብሎ የተመመ ሕዝብ ቁጣ ካሸበረው የማን ጥፋት ነው?ጎበዝ ልብ በሉልልኝ ጅራፍ ራሷ ገርፋ እራሷ ትጮሃለች አይደለም እንዴ?

አንዳርጋቸው ጽጌ ዛሬ በራእዩ የሚገዛት የማቹ መለስ ዜናዊ የትምህርት ቤት ጓደኛ እንደነበር ሰምቻለሁ የመለስ ራእይ አስፈፃሚዎች ከየመን መንግሥት ጋር በመመሳጠር አንዳርጋቸው በጎዞ ላይ እንዳለ የመን ውስጥ ስናዐ ላይ ተጠልፎ ለወሮ በላው ህወሃት ቡድን ተላልፎ ተሰጥቶ በደህንነት ኃይሎች እንደ እባብ እየተቀጠቀጠ እንዳለ ይታወቃል።

አንዳርጋቸው ማድረግ የሚገባውን አድርጓል ቀሪውን ሂሳብ ድርጅቱ ይወጣዋል ብየ አስባለሁ።አስቂኙ ትራጀዲ ግን ወጣት የህወሃት አፓርታይድን የሚታገሉ የተቃዋሚ ድርጅት አባላትን ለቅሞ ወደ እሥር ቤት ማስገባት ምን አመጣው?የሚለው ነው።

ከሕዝብ ተነጥሎ በኃይል ሕዝብን አንበርክኮ መግዛት የማይቻል መሆኑን ህወሃቶች ከደርግ ወታደራዊ አገዛዝ መማር ካልቻሉ እዳውን መቀበል ያለበት ያው ባለእዳው እንጅ ማንም ሊሆን አይችልም።ቁም ነገሩ ግን በኢትዮጵያ በቅድመ አብዮትና ድሕረ አብዮት ተዋናኝ የነበርን መሪና ተመሪዎች በፈጸምነው ከባድ ወንጀል የነገውን አገር ተረካቢ ትልድ እጣ ፈንታ ላይ መርዝ መጨመራችን ለምን አናቋርጥም?አብርሃ ደስታ ወጣት ነው፤የሽዋስ አሰፋ ወጣት ነው፤ሀብታሙ አያሌው ወጣት ነው። ሁሉም ወደ እሥር ቤት የተጋዙት የሕሊና እሥረኞች ወጣቶች ናቸው ታዲያ ለምንና እንዴት እንዲሰቃዩ ተወሰነ? እኔ እንጃ ሂሳቡ ሲወራረድ ህወሃቶች መድረሻችሁን ሳስብ ክፉ ቀን ይታየኛል።

የነገሩን ክብደት ወደ ሚዛን ወይም ስኬል እንውሰደው ከተባለ በዚህ ሰው በላ ሥርዓት የተጠራቀመ ቡድን እኩል ይሰፈራል ብየ አላስብም ምክንያቱም አድማስ የጠበበት ፤ለሆዱ ያደረ ፤ተገዥነቱን አምኖ የተቀበለ ድብልቅ አንድ ላይ ያለ ስለሆነ ትንሽም ብትሆን የህዝቡ ብሶት ረፍት የሚነሳው ካለ በጊዜ ቦታውን እንዲፈልግ አቅጣጫ ማሳየት ይገባናል።ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት ነበረች አዎ! ኢትዮጵያ የአለም ስደተኞች መጠጊያ ነበረች አዎ! ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ የኖረችና ኃያላን የአውሮፓ ወራሪዎችን ያንበረከከች አገር ነች አዎ! ኢትዮጵያ የዓለም ትውልድ የመጀመሪያ አገር ነች አዎ! አሁንስ? ዛሬ እያየን ያለው ግን የዚያን ግልባጭ ነው።ለምን እንዴት? ችግሩ ምንድን ነው?

እንግዲህ እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች ከፊታችን ተጋርጠው እያለ ነው በጎሳ(በዘር) በሥልጣን ጥማትና በተራ ጓደኝነት ትልቁን የሀገር ጉዳይ ዘንግተን እሰጥ አገባ እያልን ህወሃትን ከዚህ ያደረስነው። ደወሉ የመጨረሻው መሆኑን ህወሃት/ኢህአዴግ የተረዳ መሆኑን በግልጽ በመናገር አቅጣጫችን ስለህወሃት አራዊታዊ ባኅሪና ጨፍጫፊነት የምንሰብክበት ጊዜ ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የተቃዋሚ ኃይሎች ወደ አንድነት እንዲመጡ ተፅዕኖ ማሳደር ፤ከምንም በላይ የሕዝቡን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ሥልጣንን መሠረት ያደረገ አተካራ ላይ የሚገኙትን የተቃዋሚ ኃይሎች ሕዝብ እንዲያገላቸው ማድረግና በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ አንድ ሁለት እያለ በመሰባሰብ ከህወሃት የሚሰነዘርበትን ማኛውም ጥቃት መመከት ከሚችልበት ደረጃ ማድረስ የህወሃትን ግብዓተ መሬት ፍጻሜ ማፋጠን አለብን። ይህ ሀገርን የማዳን ወይም ኢትዮጵያን የማቆየት ወይም ስትጠፋ ተስማምቶ እንደ ማጥፋት ስለሚቆጠር የኢትዮጵያን ሕዝብና ኢትዮጵያን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጥርሱን ነክሶ ወገቡን አጥብቆ አስሮ መታገል ያለበት አሁን በመሆኑ አብረን በጋራ እንነሳ ኢትዮጵያን እናድን።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ በክብር ትኖራለች!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!


No comments: