July 9/2014
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገ አንድ ታዋቂ የአሜሪካ የዜና አውታር በቅርቡ ኮካኮላ በኢትዮጵያ እንዳይጠጣ በሚል ያሰራጨሁትን ጽሁፍ በማስመልከት የተሰማውን ቅሬታ አስመልክቶ አንድ የኢሜይል መልዕክት ላከልኝ፡፡ እንዲህ የሚል ጽሁፍ ጻፈ፣ “በድፍረት ልናገርና ሆኖም ግን ኮካኮላ እንዳይጠጣ ለማሳሰብ ስለተጻፈው ጽሁፍ ገቢራዊነት እምነት የለኝም፣ ይህንንም ጽሁፍ በማዘጋጀት በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ባለው ‘ሰይጣናዊ’ ገዥ አካል እና በ’ቅዱሳኑ በተባበሩት የተቃዋሚ ኃይሎች’ መካከል ባለው የፖለቲካ ውዝግብ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ በጥቂቱ አንባቢዎችህን ሊያሳስት እንዲችል የታለመ ዓላማን ያዘለ ነው“ በማለት አስተያየቱን አጠቃሏል፡፡
ለዚህ አደናጋሪ የውጭ የዜና አውታር ቃል አቀባይ የሰጠሁት ምላሽ አጭር፣ ግልጽ፣ ፈጣን እና የማያወላዉል ነበር ፡፡ እንዲህ የሚል መልስ ሰጠሁት፣ “አዎ እውነት ነው፣ የራሰህ ጉዳይ ነው! በግልጽ ለመናገር እኔ በዚህ ጉዳይ አላዝንም፣ የገዥውን አካል ህሊና ቢስ አካሄድ በመከተል እንደ ገደል ማሚቶ ብትጮህ መብትህ ነው!!!“ በኢትዮጵያ የአንድ የጋዜጠኝነት የእውቅና እና የሙሉ ክብር ህልውና በመረጠው የቃላት አጠቃቀም እና እምነተቢስ የአዘጋገብ ዘይቤ ላይ የሚወሰን ከሆነ ድፍረት ማጣት እና አስመሳይነት እንደ እውነተኛ እና ገለልተኛ የጋዜጠኝነት ባህሪ የክብር መገለጫ ጸጋ ይሆናሉ፡፡
ይህ በድህነት ጥያቄ የቀረበው የትችት ጽሁፍ በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል፣ ተባባሪዎቹን፣ ደጋፊዎቹን እና የውስጥ እና የውጭ የፍልስፍናው ጠባቂ ተከራካሪዎቹን ሊያደናግር ሊያስከፋ ይችላል፡፡ እንዲህ ይሉም ይሆናል፣ “ይሄው ደግሞ የእዚህን ጭራቅ ገዥ አካል ስም ጥላሸት ለመቀባት ተነሳ፡፡ ለገዥው አካል ምክንያታዊነት ፍትህን አይሰጥም፣ እናም እስከ አሁን ድረስ ላከናወኑት ለማንኛውም ስራ በፍጹም እውቅና አይሰጥም፡፡“ “አገሪቱ ባለፉት አስርት ዓመታት አስመዘገበችው እየተባለ በየጊዜው ስለሚደሰኮርለት ተስፈንጣሪ የኢኮኖሚክ እድገት በማቀርበው የማስተባበያ አካሄድ የሆድ ቁርጠት ይይዛቸዋል፡፡“ ሁልጊዜ ሰኞ የማቀርባቸውን ትችቶቸ ለምን እንደማልረሳ እና አንድ ቀንም እንደማላሳልፍ ያላቸውን ቅሬታ ያሰማሉ፡፡
እውነታው ግን ምንም ይሁን ምን የፈለገው ነገር ይምጣ፡፡ እራሴን በሞራል ዝቅጠት ስር አለመደበቄ እና ለእራስ ጥቅም፣ ምቾት እና የሞራል ልዕልናን ባልተላበሰ መልኩ እያገለገለ ላለ ጋዜጠኛ የማላዝን በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ሰይጣንን አንደ መላዕክት ወደ ላይ ከፍ አድርጎ በማውጣት እና በማውረድ አላምንም፡፡ ያየሁትን እንደ አየሁት አድርጌ እናገራለሁ፡፡ ስልጣናቸውን ከህግ አግባብ ውጭ ለሚጠቀሙበት ለሌሎች ትክክለኛውን ንግግር ለማያቀርቡት እውነተኛ እና ቀጥተኛ የሆነውን ነገር እነገራለሁ፡፡
እንደዚሁም ሁሉ ትክክለኛ ያልሆኑ ነገሮችን ገለልተኛ በሆነ መልኩ አጋልጣለሁ፡፡ ለሰብአዊ መብቶች መጠበቅ፣ ለህግ የበላይነት መርሆዎች እና ተግባራዊነት መቶ በመቶ ገለልተኛ ነኝ፡፡ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ገለልተኛ የሆነ አስተያየቴን እሰጣለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የሚካሄዱ ነገሮችን ሁሉ በመጀመሪያ ጊዜ እንደ ህገመንግሰት የህግ ባለሙያ እና እንደ ፖለቲካ ሳይንቲስት የህገመንግስቱን መነጽር በማድረግ እመረምራቸዋለሁ፣ አገናዝባቸዋለሁም፡፡ በየጊዜው ወንዶቸም ሆኑ ሴቶች በሚያደርጓቸው አስደንጋጭ እና ሰይጣናዊ ስራዎች ሞራልን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እመለከታለሁ፡፡ ድህነት የሁሉም ጭራቆች ሁሉ መሰረት እንደሆነ አምናለሁ፡፡ አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ለትውልድ የሚሸጋገር ጨለምተኝነትን፣ የሞራል የአካል ዝቅጠትን ትቶልን አልፏል፡፡ ሸክስፒር ጭራቃዊነትን በሚገባ በመገንዘብ በአንቶኒ በጁሊየስ ቄሳር በኩል እንዲህ በማለት ተናግሯል፣ “ሰይጣናዊ ስራ ሰሪዎቹ ሰዎች ካለፉ በኋላም ይኖራል፡፡ በጎው ነገር ከአጥንታቸው ጋር አብሮ ይቀበራል፡፡ ስለዚህ ከቄሳር ጋር ይሆናል፡፡ እንዲህ በማለትም በዚህ ላይ እጨምራለሁ፣ “ጭራቃዊነት በድል አድራጊነት ተንሰራፍቶ እንዲኖር የሚፈቅድለት ብቸኛው መንገድ ደጋግ ወንዶች እና ሴቶች ምንም ነገር አለማድረጋቸው እና አለመናገራቸው ነው፡፡ ስለሆነም ስለድህነት-ከድህነት ስለሚያተረርፉት እና ስለሚሰብኩት ሁሉ ድህነት በኢትዮጵያ ስላለው የሁሉም ጭራቃዊነቶች መሆኑን መናገር አለብኝ፡፡“
ኢትዮጵያ ከዓለም ከመጨረሻዎቹ ደሀ አገሮች ሁለተኛ እንድትሆን ያደረገሽንጡን ገትሮ የሚሰራ ጭራቃዊ ኃይል
ባለፈው ሳምንት የኦክስፎርድ የድህነት እና የሰብአዊ ልማት ተነሳሽነት ኦክስፎርድ/Human Development Initiative (OPHD) ዘርፈብዙ የድህነት መለኪያ (በቀድሞ ስሙ U.N.D.P Human Poverty Index) ለአራት ተከታታይ ዓመታት ባቀረበው ዘገባ መሰረት ኢትዮጵያ ከዓለም በድህነት ሁለተኛዋ አገር ሆናለች፡፡ ለዓመታት ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ደግሞ ከታች በድህነት አራንቋ ከተዘፈቁት አምስት የመጨረሻ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ በድህነት ተተብትባ መያዟ ብቻ ሳይሆን በሰብአዊ መብት አያያዝ እና በሌሎች መለኪያዎችም ዝቅተኛውን ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 OPHD ባቀረበው ዘገባ መሰረት “በአስከፊ ድህነት“ ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት (በቀን ከአንድ ዶላር በታች ገቢ የሚያገኘው) 72.3 በመቶ ይሸፍን ነበር፡፡ ሆኖም ግን የ2014 የOPHD አሀዛዊ መረጃ ከዚህ የበለጠ አስደንጋጭ ነው፡፡ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖረው 82 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በከተማ ከሚኖረው ከ18 በመቶው ህዝብ ጋር ሲነጻጻር የገጠሩ ህዝብ የበለጠ “በአስከፊ የድህነት“ ቀለበት ውስጥ ተተብትቦ ይገኛል፡፡ በ2014 በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ከሚገኘው ህዝብ ውስጥ አብዛኛው በሚከተሉት ክልሎች ይገኛል፡ ሶማሊ (93%)፣ ኦሮሚያ (91.2%)፣ አፋር (90.9%)፣ አማራ (90.1%)፣ እና ትግራይ (85.4%):: በOPHD የመለኪያ መስፈርት ውስጥ ድህነት ማለት በቀላል አገላለጽ የገንዘብ እጥረት ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ከዚህ በተለየ መልኩ አስከፊ የጤና፣ ትምህርት፣ ስነምግብ፣ የህጻናት ሞት እና ብልሹ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቤት እና የመጸዳጃ ቤት አቅርቦትም በጣም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በመጥፎ የድህነት ገጽታ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ለዚህም ነው ከዓለም አገሮች በድህነት ከመጨረሻዎቹ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ተሰልፋ የምትገኘው!
በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ኢትዮጵያን በስልጣኔ ከፍ ወዳለ ደረጃ በማድረስ የተሀድሶ መሪ በመሆን ኢትዮጵያን ወደ ተምኔታዊ ኢትዮጵያ ለማሸጋገር ሌት ከቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እየሰራ እንደሚገኝ ሁልጊዜ በብቸኝነት በያዛቸው የመገነኛ ዘዴዎች ይደሰኩራል፡፡ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በመለስ የቀብር ስነስርዓት ላይ በመገኘት እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ ላለፉት ስምንት ዓመታት ከሁለት አሃዝ በላይ እያስመዘገበ ላለው ኢኮኖሚያችን የሀገራችን ህዳሴ ቀያሽ መሀንዲስ ነበሩ“ በማለት ኩራትን በተላበሰ መልኩ ተናግረው ነበር፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አቶ ኃይለማርያም የአፍሪካን የኢኮኖሚ ዘገባ ባቀረቡበት ወቅት እንዲህ የሚል በኩራት የታጀበ ንግግር አሰምተው ነበር፣ “እያንዳንዱ ሰው ስለኢትዮጵያ ተሀድሶ ነው የሚያወራው“ (ይቀልዳል!?)
የወባ ትንኝ ተመራማሪው እና በብርሀን ፍጥነት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተሸጋገረው እና በ2015 የይስሙላ ምርጫ ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በመረከብ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን የሚረከበው ቴዎድሮስ አድኃኖም ባለፈው መስከረም ወደ ኒዮርክ በመሄድ ስለኢትዮጵያ እና አፍሪካ ስኬት ገለጻ አድርጓል፡፡ እንዲህም ብሎ ነበር፣ “ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ እና በፖለቲካው መስክ… ከበቂ በላይ ገስግሳለች:: በኢኮኖሚ እድገት ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ዓመታት ከ10 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች…ኢትዮጵያ በእድገት ግስጋሴ ላይ ነች…”
ኢትዮጵያ “በህዳሴ እና በእድገት ግስጋሴ” ላይ ከሆነች በምን ዓይነት መለኪያ ነው ኢትዮጵያ ከዓለም/ፕላኔት በድህነት ከመጨረሻዎቹ አገሮች በሁለተኛነት ደረጃ ላይ የምትገኘው? ለምንድንስ ነው ኢትዮጵያ በህዳሴ እና በእድገት ግስጋሴ በመዝለቅ እራሷን ከድህነት ለማላቀቅ ያልቻለችው? ለምንድን ነው እ.ኤ.አ በ2014 82 በመቶ የሚሆነው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖረው ህዝብ “በአስከፊ የድህነት” ባህር ውስጥ በመዋኘት ላይ የሚገኘው? በኢትዮጵያ ከ90 ወይም ከዚያ በላይ ከሚሆነው ህዝብ ውስጥ ወደ 60 በመቶ የሚሆነው ዜጋ ለምንድን ነው በቀን ከ1.25 ዶላር በታች የቀን ገቢ የሚያገኘው? ለምንድን ነው ወደ 60 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በአስከፊ የምግብ ወይም በየጊዜው በሚከሰት ለምግብ ዋስትና እጦት የሚዳረገው?
እውነታው ግን ድህነት፣ በሽታ፣ ድንቁርና፣ ሙስና እና የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ብቻ ናቸው በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀቡ በመሄድ ላይ ያሉት፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለ ህዳሴ የሚኖር ካለ የሙስና ተሀድሶ ነው፣ አለ የሚባል ተሀድሶ ካለ የሰብአዊ መብቶች እጦቶች እና ጥሰቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ “በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች እድገት እና እመርታ” ማሳየት ሳይሆን እንዲያውም በአስደንጋጭ ሁኔታ ወደ ኋላ ተስፈንጥራ እየሄደች ነው፡፡ ሆኖም ግን በገዥው አካል “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” እና “ልማታዊ መንግስት” (በተሻለ መልኩ ክህደታዊነት እየተባለ በሚጠራው) የገደል ማሚቶ ሰበካ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እና አጥጋቢ ነው፡፡ ከዚህ በተለየ መልኩ የሚያስብ እና የሚንቀሳቀስ እንዲሁም ስህተት ነው ብሎ የሚሞግት ከተገኘ ያ ግለሰብ የተሳሳተ ወይም ስንኩል እና ጤንነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው ተብሎ ይፈረጃል፡፡
ሊሆን በማይችለው ከነባራዊ እውነታው ውጭ በሆነ ነገር ላይ እምነታቸውን የሚጥሉት የገዥው አካል አባላት ማስተባበል በማይቻል መልኩ በተዘጋጀ ማስረጃ የቀረበውን ሰው ሰራሽ የሆነውን ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት የሙቀት መጠን እንደሚክዱት ዓይነት ቡድኖች እና ግለሰቦች ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል በሀገሪቱ ያለውን አስከፊ ድህነት ሙጥጥ አድርጎ በመካድ በዚህች አገር ለሚከሰተው ረሀብ በብቸኝነት ተጠያቂው እራሱ መሆኑን በመዘንጋት ተቃውሞውን ያሰማል፡፡ ይልቁንም ምናባዊ በሆነ መልኩ እራሳቸው ስለፈጠሩት ምናባዊ ህዳሴ ደጋግመው ይደሰኩራሉ!
እዉነታዎች በእራሳቸው ይናገራሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ/Global Financial Integrity የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “የኢትዮጵያ ህዝቦች ደማቸው ተመጧል፣ ፍጹም ከሆነ እጦት እና ድህነት ለመውጣት የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉም እንኳ በአሁኑ ጊዜ እየተደረገ ባለው የህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ባህር ውስጥ አገሪቱ ወደ ላይ በመስመጥ ላይ ትገኛለች“፡፡
እንደ ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ ዘገባ “ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 365 የኤሜሪካ ዶላር የሆነችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2000 እስከ 2009 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በህግወጥ የገንዘብ ዝውውር ከሀገር ውስጥ ወጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ህገወጥ የገንዘብ ዝውውሩ 3.26 የአሜሪካ ዶላር በመሆን ካለፉት ሁለት ዓመታት በእጥፍ ጨምሮ ታይቷል… እ.ኤ.አ በ2008 ኢትዮጵያ ከውጭ የተገኘ 829 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን ይህም በህገወጥ የገንዘብ ዝውወር ምክንያት ባክኖ ቀርቷል፡፡“ የኢትዮጵያ የካፒታል ፍሰት ሁኔታ ሲታይ በግምት 3.26 የአሜሪካን ዶላር በአመዛኙ እ.ኤ.አ በ2009 ከተገኘው 2 ቢሊዮን የኤክሰፖርት ምርት ዋጋ በእጅጉ የበለጠ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2014 ከዓለም 2ኛዋ ደኃ አገር ለምን ሆነች?
በኢትዮጵያ ሰይጣናዊው ረሀብ ድልን ሊቀዳጅ የቻለበት ዋናው ምክንያት በገዥው አካል የእውቀት ማጣት፣ የችሎታ ማነስ፣ ድንቁርና፣ እብሪ እና ሙሰኝነት እንዲሁም አሁን በህይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ ዋና መሀንዲስነት የአምባገነንነት ባህሪ ምክንያት ነው፡፡ መለስ ከሁሉም በላይ እራሱን እንደ የኢኮኖሚ ባለሙያ አድርጎ ይቆጥር ነበር፡፡ መለስ ግማሽ ብስል በነበረው የማርኪሲዝም የፖለቲካል ኢኮኖሚ በማመን ገና በወጣትነት እድሜው ወደ ጫካ በመግባት እራሱን በኢትዮጵያ “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ” እና “የልማታዊ መንግስት” “ዋና መሀንዲስ” አድርጎ ሰየመ፡፡ ሆኖም ግን መለስም ሆነ የእርሱ አሻንጉሊት ተከታዮች የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የልማታዊ መንግስት ህልዮትን እና ገቢራዊ አልሆኑም፡፡ ይልቁንም የልመና እጃቸዉን ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ለዓለም ባንክ እየዘረጉ በሌላ በኩል ደግሞ “ኒዮሊበራልን” ለማውገዝ እና ለመርገም ድምጻቸዉን ከፍ አድርገው ይጮሃሉ፡፡ በአንድ ምሁራዊ የትችት መጽሄት ላይ የጸረ ኒዮሊቨራል አቀንቃኝ በሆነው በጆሴፍ ሰትልጊዝ እርማት መሰረት አቶ መለስ እንዲህ ብሎ ነበር፣ ”የኒዮሊቨራል አካሄድ የአፍሪካን ህዳሴ ያላመጣ የሞተ ነገር ነው፣ እናም የአፍሪካን ዓላማ ለማሳካት እና አፍሪካን ወደ ዘላቂ የሆነ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡“
የመለስ መሰረታዊ ለውጥ የይስሙላ ዓላማ በአሁኑ ጊዜ እንደተረሳችው ራሽያ ማዕከላዊ የሆነ የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅድ ሳይሆን እንደ የእድገት እና ትራንስፎረሜሽን ዕቅድ ያለ ምዕናበዊ ዕቅድ ነው፡፡ ቀደም ሲል በተለያዩ አጋጣሚዎች እንዳየሁት ሁሉ መለስ የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የለውም፣ ይልቁንም ያለው ምዕናባዊ ሀሳባዊ የኢኮኖሚ እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነው፡፡
የመለስ ዜናዊ የዉሸት ምጣኔ ሀብት ዘየቤ (The Fakeonomics of Meles Zenawi) በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት እንዲህ በማለት ለማሳየት ሞክሬ ነበር፣ “የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ባዶ ሊስት ከመመዝገብ የበለጠ አይደለም፡፡“ ይህ ዕቅድ በረዥሙ ጉዞ ኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ህግ፣ መልካም አስተዳደር እና ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍኑ ለማድረግ ነበር፡፡ ዘመናዊ እና ምርታማ የሆነ የግብርና ዘርፍ ከተሟላ ቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሁም የዜጎች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ለማሳደግ እና የመካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጋር እኩል ለማድረግ የታለመ ነበር፡፡ ገዥው አካል የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማሳካት ፈጣን እና ዘላቂ እንዲሁም ፍትሀዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ምሰሶ ስልቶችን በመጠቀም ግብርናን እንደ ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር በማድረግ ለኢንዱስትሪው መዳበር ጥሩ ከባቢ አየርን ይፈጥራል በማለት ጉራ ያደርጋል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የመሰረተ ልማት እና የማህበራዊ ልማትን ማስፋፋት፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማካሄድ እና መልካም አስተዳደርን ማስፈን እንዲሁም ሴቶችን እና ወጣቶችን ማጠናከር እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማጎልበት በሚል ሀሳብ ይመራል፡፡
በባዶ የኢኮኖሚ እድገት መፈክር ታጅቦ፣ በተደጋጋሚ እየተነገረ ባለ አሰልቺ አገላለጽ ታጅሎ፣ ፋሽንነትን በተላበሱ ቃላት እየተሽሞነሞነ እና በአንድ ታዋቂ ሰው ዲስኩር እየተምነሸነሸ የመለስ የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አደናጋሪና እና ከነባራዊ እውነታው ውጭ ሆኖ ቀርቷል፡፡
ከዚህ ቀደም “የመለስ ምዕናባዊ ኢኮኖሚከስ“ (The Voddo Economics of Meles Zenawi) በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት መለስ ግልጽ በሆነ መልኩ በፍብረካ ላይ በተመሰረተ ስታቲስቲካዊ አሀዝ በመጠቀም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚክ እድገት ተመዝግቧል ይለው የነበረውን ተራ ማደናገሪያ የሆነ ውሸት በማጋለጥ አቅርቤ ነበር፡፡ ለበርካታ ዓመታት መለስ እና የእርሱ ገዥ አካል የማተለያ የህዝብ ግንኙነትን በመፍጠር እና በማታለል የዓለም የገንዘብ ድርጅትን ከፊት በማድረግ የእርሱን የሸፍጥ የኢኮኖሚ እድገት ዓለም አቀፉን ድርጅት ባስረጅነት ድጋፍ እንዲያደርግ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት እንዳስመዘገበች እና ውጤታማ እንደሆነች አድርገው የዓለምን ህዝብ በማደናገር ላይ ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን ገዥ አካል የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እውቀት አናሳነት፣ የብቃት የለሽ እና በሙስና ስርዓት በመዘርጋት የሀገሪቱን ሀብት እጠቀራመተ ያለ መሆኑን በማጋለጡ እረገድ እኔ የመጀመሪያው አይደለሁም፡፡ እ.ኤ.አ በሴፕቴምበር 7/2006 እትሙ የኢኮኖሚክ መጽሄቱ/Economic Magazine “የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ስልጣኔ በተስፋፋበት ዘመን አንዱ የኢኮኖሚክስ ማይም“ በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት ገልጾት ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ኖቬምበር 3/2007 የኢኮኖሚስት መጽሄት/the Economist Magazine እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር፣ “እውነታው ተግልጦ ሲታይ በእርዳታ የሚገኝ ገንዘብ እና ከቻይና የሚመጣ ብድር ቢኖርም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት ማደግም ሆነ በቂ የስራ እድል መፍጠር አልቻለም፡፡ የአበባ ምርት እየተባለ ብዙ በሚወራለት አዲስ የኢኮኖሚ ዘርፍ የተፈጠሩት አዲስ የስራ መስኮች በየዓመቱ በ2 ሚሊዮን እጨመረ ከመጣው የህዝብ እድገት በአፍሪካ ፈጣኑ የህዝብ እድገት ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ብዙም አይደሉም… ገዥው አካል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚከ2003-2004 በሚያስደምም ሁኔታ 10 በመቶ እድገት አሳይቶ ነበር፡፡ሆኖም ግን እውነተኛው እና ትክክለኛው የእድገት አሀዝ ከ5-6 በመቶ ማለትምከሰሀራ በታች ካሉ አገሮች አማካይ የእድገት ምጣኔ በላይ ይሆናል ተብሎይገመታል፡፡ እናም ያ መጠነኛ የተሻሻለ የእድገት ምጣኔ ለምሳሌም በአዲስ አበባ ከተማ እየተሰሩ ባሉ ጥቂት ህንጻዎች ሰበብ ኢኮኖሚው ከመጠን በላይ እየጋለ ሄዶ መንግስት በዚያው ዓመት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የዋጋ ንረቱ 19 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ ኢኮኖሚው ለምን በእንደዚህ ያለ ሁኔታ እየዳኸ እንደሚሄድ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው፡፡ በአብዛኛው በውጭ እርዳታ የተንጠለጠለ ሆኖ ከመንግስት ትእዛዘዝ ውጭ – ለአፍሪካ ብቻ ልዩ የሆነ በእርግጠኝነት በንግድ ስራ ላይ የተሰማራ የንግድ ማህበረሰብ የለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2009 ከፍተኛ የሆኑ የምእራቡ ዓለም ለጋሽ ድርጅቶች እና ፖሊሲ አውጭዎች በበርሊን ከተማ ባካሄዱት ጉባኤ አንድ የጀርመን ዲፕሎማት በመለስ ደካማ የኢኮኖሚክስ አረዳድ መሰረት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር በውል ሊታወቅ እና ሊደረስበት አይችልም“ ብለው ነበር፡፡
ጥቂቶችን ብቻ የማበልጸግ አባዜ የተጠናወተው የኢትዮጵያ ድህነት ገፊምክንያት፣
በኢትዮጵያ ለድህነት መሰረታዊ ምክንያቱ “ኒዮሊበራሊዝም” አይደለም፡፡ ይልቁንም ዋናው የድህነት መሰረቱ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀያሽ መሀንዲሶች እና በኢትዮጵያ ልማታዊ መንግስት እየተባለ ኢኮኖሚውን በብቸኝነት ይዘው ጥቂቶችን በማበልጸግ ሰፊውን ህዝብ የበይ ተመልካች የማድረግ አባዜ ነው፡፡ ጥቂቶችን የማበልጸግ ስስታዊ አካሄድ የኢኮኖሚ ተግባራትን እና የውጤታማነት መስፈርትን በማየት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በፖለቲካ ትስስር የሚከናወን የጥቂቶች የመዝረፊያ አካሄድ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ በሀገሪቱ የአንበሳውን ድርሻ ለማግኘት ማንም ሰው ቢሆን በፖለቲካ እና በጎሳ ትስስር እና መስተጋብር አንድ በመሆን የኢኮኖሚ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ በኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ሙያዊ የቃላት ድርደራ መሰረት እንደዚህ ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ “ኪራይ ሰብሳቢነት“ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የግል ወይም የቡድን ግምገማዎች ለግብር ጉዳይ መንግስትን መለማመጥ፣ የወጭ እና የቁጥጥር ፖሊሲዎችን በመንደፍ የገንዘብ ጥቅሞችን ወይም ደግሞ በሌሎች ግብር ከፋዮች ጉዳት ሌሎች ልዩ ጥቅሞችን የማግኘት ወይም ደግሞ የተጠቃሚዎች ወይም ሌሎች ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ጋር ውድድር እንዲያደርጉ ይገዳዳሉ፡፡
የመለስ ጥቂቶችን ብቻ የማበልጸግ አባዜ የመለስ ደጋፊ እና የእርሱ ህወሀት ፓርቲ ሎሌዎች (የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ የጋራ መደጋገፍ ስርዓት በመዘርጋት የተለያዩ ጥቅሞችን የማሳደድ እንዲሁም ለእነርሱ የሚመች ከባቢያዊ ሁኔታ የመፍጠር እና የህዝብ ግዥ ሲፈጸም እና በመሳሰሉት ሁሉ ለጥቅመኛው ቡድን ተጠቃሚ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ የውስጦቹ በውጮቹ ጉዳት መሰረት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ እናም እየንዳንዱ ለገንዘቡ ሲል ሎሌ ይሆናል፡፡ የኢንተርፕሪነር/ስራ ፈጣሪ ግለሰቦች እንኳ ለመኖር ሲሉ ለአዳኙ ግለሰብ/ቡድን ሎሌ መሆን ይፈልጋሉ፡፡
በመለስ ጥቂቶችን የማበልጸግ መርህ መሰረት መንግስት ኢኮኖሚውን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ ለእርሱ ደጋፊዎች እና ሎሌዎች ትርፋማ የሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ይይዛል፡፡ የመለስ ገዥ አካል በቁጥጥር፣ በግብር፣ በጠቅላላ ለወጭ እና ለኢኮኖሚያዊ ተግባራት እንቅስቃሴ በበላይነት ይዞ ይመራል፡፡ ታማኞቻቸውን እና ሎሌዎቻቸውን ለመጥቀም ሲሉ በልጓም የማይታዘዝ ስልጣን አላቸው፡፡ በውጤቱም ኢኮኖሚያዊው እንቅስቃሴ፣ የኢንተርፕሪነር ህልውና እና ሌሎችም የፖለቲካ ስልጣኑን በተቆጣጠረው ኃይል የሚወሰን ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነው የሀብት ፈጠራ እና ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግበን እያሉ ህዝቡን ጧት ማታ የሚያሰለቹት፡፡
በመለስ ጥቂቶችን የማበልጸግ ስራ በጣም ጥቂት የሚባሉ ነጻ የስራ ፈጣሪዎች ተሳክቶላቸዋል፡፡ ጥቂቶቹ የተሳካላቸውም ቢሆኑ በእርግጠኝነት በመለስ ሎሌዎች ተውጠው ይቀራሉ፡፡ የኢኮኖሚ ስኬታማነት በአመዛኙ የሚወሰነው በፖለቲካ እንቅስቃሴው እና ገዥውን አካል ከመደገፍ አንጻር ባለው አቋም ነው፡፡ ነጻ የሆኑ የስራ ፈጣሪዎች ህልውናቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ከተፈለገ ድርጊቱን ቢጠሉትም እንኳ ጥቂቶችን በማበልጸግ ስራ ላይ መሳተፍ ይኖርባቸዋል፡፡ የመለስ ገዥ አካል የቁጥጥር ኃሉን፣ የግብር ስብሳቢ ባለስልጣኑን፣ እና ወጭዎችን እና ድጎማዎችን ለሚደግፉት ሲሰጥ በተቃራኒው ላሉት ግን አይሰጥም፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ሁሉም ስራ ፈጣሪዎች የመንግስትን ልዩ አያያዝ ለማግኘት ሲባል እና እራሳቸውን ከህጎች፣ ወጭዎች እና እነርሱን ከውድድር ጉዳት ለሚከላከሉ ነገሮች አበርትተው ይሰራሉ፡፡
በመለስ ገዥ አካል ጥቂቶችን የማበልጸግ ስርዓት ውድድር የሌለበት እና በግልጽ ለተወሰነ ቡድን ተብሎ የተቀመጠ ነው፡፡ የሰብአዊ መብተ ቡድኖች፣ ተንታኞች እና ትችት እቅራቢዎች የመለስ ገዥው አካል በእርዳታ ስም ለህዝብ እንዲደርስ የሚላከውን እርዳታ ማለትም ምግብን፣ ማዳበሪያን፣ ስልጠናን፣ ወዘተ ጨምሮ ለፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ ለሚታወቁ ተቃዋሚ ቡድኖች አብዛኛውን ጊዜ እንደሚከለክል ዘገባ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ በማወጣቸው ሳምንታዊ ትችቶቸ ላይ ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ እንደ ዓለም ባንክ ዘገባ የኢትዮጵያ ግማሽ አካባቢ የሚሆነው ብሄራዊ ኢኮኖሚ የተያዘው ለስርዓቱ ደጋፊ በሆኑ የንግድ ቡድኖች ማለትም በትግራይ ህዝብ መልሶ ማቋቋሚያፈንድ/Endowment Fund for the Rehabilitation of Tigray (EFFORT) በሚባሉ መንግስታዊ በሆኑ የንግድ ድርጅቶች ነው፡፡ የኢፈርት የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት፣ ኮንስትራክሽን፣ የመድሀኒት፣ እና የስሚንቶ የንግድ ተቋሞች ትርፋማ የሆኑ የውጭ የእርዳታ ስምምነቶችን እና ከመንግስት ባንኮች የብድር አገልግሎት ያለምንም ውጣውረድ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 በተሟላ መልኩ በሳራህ ቫውግሀን እና መስፍን ገብረሚካኤል አማካይነት “Rethiniking business and politics in Ethiopia: The role of EFFORT, the Endowment Fund for the Rehabilitation of Tigray“ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ዘገባ ገዥው አካል ከንግድ ድርጅቶች ጋር ቅርብ እና የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው ከበቂ በላይ ማስረጃ እና ትንታኔ ይሰጣል፡፡ የዓለም ባንክ በ2012 “Diagnosing Corruption in Ethiopia“ በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ሰፊ ዘገባ እና በዚያ ዘገባ ውጤት ላይ እኔ እራሴ በመለየት በሰጠሁት ትችት ጥቂቶችን የማበልጸግ ወያኒያዊ ተውኔት ምን ያህል በፍትሀዊነት ላይ ድልን እንደተቀዳጀ የሚያሳይ እኩይ ኢመንግሰታዊ ምግባር መሆኑን መግለጼ የሚታወስ ነው፡፡(እነዚህ ትችቶች Al Mariam Commentaries በሚል የእራሴ ድረ ገጽ ላይ ይገኛሉ፡፡) በኢትዮጵያ ጥቂቶችን ማበልጸግ የሚለው ወያኒያዊ መርህ ምናልባትም በማዕድኑ ዘርፍ በይበልጥ ጎልቶ ይታያል፡፡ የዓለም ባንክ ጥናት የመለስን ጥቂቶችን የማበልጸግ መርህ በግልጽ አሳይቷል፡፡
የማዕድን ኩባንያ የማዕድን ፈቃድ ለማግኘት ብዙ ፕሪሚየም/ከተገቢው በላይ እንዲከፍል ይጠየቃል፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች እና የማዕድን ኩባንያው ይህንን ክፍያ በሚስጥር እንዲያዝ ሊያደርጉ ይችላሉ፣ በቀጣይነትም ከአገር ውጭ ባሉ የባንክ ሂሳቦቻቸው ገንዘብ ገቢ እንዲያደርጉላቸው ያደርጋሉ፡፡አንድ የማዕድን ኩባንያ የማዕድን ፈቃዱን በአስቸኳይ ለማግኘት የሚፈልግ ከሆነ ለበጎ ነገር እርዳታ በሚል ብዙ ገንዘብ እንዲሰጥ በመንግስት ባለስልጣኑ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ የበጎ ነገር እርዳታው ለመልካም ነገር የታሰበ ቢሆንም ይህ ገንዘብ በትክክል ለፖለቲካ ፓርቲው ወይም ለባለስልጣኑ የግል ወይም ደግሞ ለቤተሰቡ መጠቀሚያ እንዲውል ሊደረግ ይችላል፡፡ባለስልጣኖች ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ከማዕድን ኩባንያው ጋር በመስማማት የተወሰነ ኮንትራት ለዘመዶቻቸው እንዲሰጥ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ የማዕድን ፈቃዱን የሚሰጠው ባለስልጣን ለማህበራዊ ልማት ዕቅድ በሚል ከሚጠየቀው ትክክለኛው የገንዘብ መጠን በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ኩባንያው በእራሱ ወጭ እንዲሰራ ሊጠየቅ ይችላል፡፡የማዕድን ኩባንያው የማዕድን ፈቃድ ለመውሰድ ሲፈልግ የአካባቢ ስነምህዳር አያያዝ ዕቅድ እንዲያቀርብ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ይህም ጎጂ የሆኑ መርዛማ ኬሚካሎች ወደ ውኃ አካላት በመግባት ብክለትን እንዳያስከትሉ በሚል ምክንያት ነው፡፡ ትክክለኛ ቁጥጥር ከፍተኛ የሆነ ወጭን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ የማዕድን ኩባንያው የማዕድን ፈቃዱን ለማግኘት ሲል የሚፈጠሩ ድክመቶችን ለመሸፈን በሚል ተጨማሪ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍል እንዳይጠየቅ ፈቃዱን ለሚያጸድቀው ባለስልጣን ጉቦ ሊሰጥ ይችላል፡፡ባለስጣኖች ከማዕድን ኩባንያው ትርፍ ድርሻ/share ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ የማዕድን ኩባንያ ከጥቅም ጋር በተያያዘ መልኩ ከማዕድን ትርፍ ለባለስልጣን ዘመድ ነጻ ድርሻ/share ሊሰጥ ይችላል፡፡ባለስልጣኖች በድብቅ በእራሳቸው በተያዙት ኩባንያዎች የማዕድን ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ባለስልጣኖች የፈቃድ ማመልከቻ የቀረበበትን መሬት በድብቅ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ባለስልጣን የማዕድን ስራው ይካሄድበታል ብሎ የሚያስበውን መሬት አስቀድሞ የማዕድን ፈቃዱ ከመሰጠቱ በፊት ሊያከራየው ይችላል፡፡ አንዴ ፈቃዱ ከተሰጠ የመሬቱ ጥሬ ዋጋ ሊጨምር ይችላል፡፡ ባለስልጣኑ ከውስጥ ባለው እውቀት መሰረት በመሸጥ ወይም ደግሞ ፈቃዱን በማከራየት ከኩባንያው ትርፍ ሊያገኝ ይችላል፡፡ባለስልጣኖች የፈቃድ ምዝገባን ሊያዛቡ ይችላሉ፡፡የማዕድን ፈቃድ መስጠት የሚችል በመምሪያ ደረጃ ያለ ባለስልጣን የማዕድን ኩባንያ የማዕድን ፈቃድ ለመጠየቅ የሚፈልግ መሆኑን ሊያውቅ ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻር ባለስልጣኑ መረጃውን በመገንዘብ ሌላ ከዚህ ስራ ጋር ግንኙነት ያለውን ሰው አስቀድሞ እንዲያውቅ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በዚህም መሰረት የንግድ ሰው በዚያው በአንድ ዓይነቱ መሬት ላይ ሊያመለክት ይችላል፡፡ ባለስልጣኑ ይህንን መሬት ለዚህ የንግድ ሰው ሊሰጠው ይችላል፡፡ ከዚያም የማዕድን ኩባንያው ይህንን ቀደም ሲል እራሱ እንዲሰጠው አመልክቶ የነበረበትን መሬት ከንግዱ ሰው እንዲገዛው ይደረግ እና የንግዱ ሰው ትርፉን ከባለስልጣኑ ጋር ይካፈላል፡፡አንድ ማዕድን ፈላጊ ማዕድን ሊያገኝ ይችላል፣ ያገኘበትን አካባቢም ምልክት ሊያደርግበት ይችላል፡፡ በዚህም መሰረት የግኝት ሰርቲፊኬት እንዲሰጠው ጉዳዩን ለሚመለከተው የፈቃድ ሰጭ ባለስልጣን ሊያመለክት ይችላል፡፡ ሙስና የሚያካሂድ ባለስልጣን ግኝቱን ባገኘው ሰው ስም ላይመዘግበው ይችላል፣ ከዚህ ይልቅ የቢዝነስ ጓደኛውን እንዲያውቅ በማድረግ በጓደኛው ስም እንዲመዘገብ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሙሰኛው ባለስልጣን ከዚህ በኋላ ማዕድኑ በመጀመሪያ የተገኘው በሌላው ሰው እንደሆነ ይነግረዋል፡፡
ኮንትራክተሮች እና አምራቾች በጨረታ፣ የባለቤትነት ጥያቄን በማቅረብ እና እንከን ያለባቸውን ስራዎች በመደበቅ ወይም በማጽደቅ ተግባር ላይ ሊሰማሩ ይችላሉ፡፡
የማዕድን ኩባንያዎች ስለ ማዕድናት ምንነት እና ጥራት የሀሰት መግለጫዎችን በመስጠት ወይም ደግሞ ፈቃድን ለሚያጸድቁት ኃላፊዎች ጉቦ በመስጠት የሙስና ወንጀል ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛዋ ደኃ አገር ከሆነችበት የውርደት ቦታ የምትላቀቀውመቸ ነው?
ከፖለቲካ ትስስር ጋር የተያያዙ ስራዎች ከስራ ፈጠራ ችሎታ እና ከተነሳሽነት የበለጠ ትኩረት እስከተሰጣቸው ድረስ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛዋ ደኃ አገር ሆና ትቀጥላለች፡፡
በቁጥር ጥቂት የሆኑ ከላይ የተቀመጡ የተማሩ ዜጎች በህግ ስርዓቱ የተለየ ድጋፍ የሚደረግላቸው እስከሆነ ድረስ እና በጎሳ ዝርያቸው ምክንያት እና በጣም ምርታማ በሆነው የምጣኔ ሀብት ዘርፍ እየተሰማሩ እንዲበለጽጉ በማድረግ የመጀመሪያ ደረጃ ዜግነት እስከተሰጣቸው ድረስ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛዋ ደኃ አገር ሆና ትቀጥላለች፡፡
ግለሰቦች እና ቡድኖች በስራ፣ በላብ እና በድካማቸው ከሚያገኙት አንጡራ ሀብታቸው ውጭ በፖለቲካ ትስስር ብቻ ያለፉበትን እና የላባቸው ዋጋ ያልሆነውን የሌሎችን ዜጎች አንጡራ ሀብት መዝረፍ እስካላቆሙ ድረስ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛዋ ደኃ አገር ሆና ትቀጥላለች፡፡
ይህ ሰው አዳኝ መንግስት ደካማ እና ንጹሀን ዜጎችን እያሳደደ አቅማቸውን እያዳከመ ማደኑን እና የስራ ፈጠራ ክህሎታቸውን በማጥፋት እረፍትየለሾቹን ወጣቶች እንዳይሰሩ እና ለሀገሪቱ ዘለቄታዊ ለውጥ እንዲያመጡ እስካላደረገ ድረስ ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛዋ ደኃ አገር ሆና ትቀጥላለች፡፡
ድህነት በኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍተው ለሚገኙ ጭራቆች ሁሉ ዋና መሰረት ነው፡፡ ሆኖም ግን ማን (ምንድን) ነው በኢትዮጵያ ውስጥ የድህነት መሰረቱ?
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ሰኔ 27ቀን 2006 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment