Tuesday, January 7, 2014

ሕዝባዊ ብሶት – የከተማ አብዮት? – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

January 7, 2014

ባለፈው ሳምንት ኢህአዴግ በከተሞች ላይ የቋጠረውን ስር የሰደደ ጥላቻ ከነመግፍኤው ጨርፈን ከተመለክተን በኋላ፤ ለዛሬ፣ ታላላቅ ግድፈቶቹ ሕዝባዊ ተቃውሞ ለመቀስቀስ ሊኖራቸው የሚችለውን አስተዋፅኦና በአደባባዩ የሚነሱትን ዋና ዋና ጥያቄዎች ለመዘርዘር፤ እንዲሁም ‹‹ማኦኢዝም›› የሚበይነውን ከገጠር የሚነሳ ብረታዊ ትግል፣ ከሰላማዊው የከተማ አብዮት አንፃር ለመፈተሽ ቀጠሮ መያዛችን ይታወሳል፡፡ እናም እንዲህ እንቀጥላለን…
 የኢህአዴግ ግድፈቶች
ፈረንጅኛው ‘Achilles Heels’ በሚል ስያሜ የሚገልፃቸው እና አማርኛው ደካማ ጎኖች ብሎ የሚሰይማቸው የስርዓቱ ታላላቅ ግድፈቶች ከዕለት ዕለት ራሳቸውን ማብዛታቸው ፍፃሜው የሚተነበይ አድርገውታል፤ ይኸውም ብሔር ተኮር ጥያቄዎች አለመመለሳቸው፣ ውጤት አልባው የገጠር ፖሊሲ፣ የድህረ-ደርግ የዴሞክራሲ ሽግግሩ መክሸፍ (ከፖለቲካ፣ ከሰብዓዊ እና ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ አንፃር)፣ የኢኮኖሚ እድገት አለመኖር፣ ድህነት ከቀድሞውም በበረታ መልኩ መስፋፋቱ፣ የትምህርት ፖሊሲው ክስረት፣ የስራ-አጥ ቁጥር አለቅጥ ማሻቀብ፣ የራስ አስተዳደር (Self-adminstration) ሙሉ ለሙሉ አለመተግበር (ከስልጤ እስከ ቁጫ ያሉ የማንነት ጥያቄዎች መቆሚያ ማጣታቸው)፣ የመሬት ፖሊሲው የአርሶ አደሩን የነፍስ ወከፍ የይዘት መጠን ከአንድ ሄክታር ማሳነሱ፣ የከተሞች ስራ-አጥነት በወጣት ከተሜ የተማሩ ልጆች ላይ መብዛቱ፣ በልማታዊ መንግስት ትግበራ እና በብሄር ፌደራሊዝም መሀከል የማይታረቁ ቅራኔዎች መኖራቸው፣ ከተሜነት እየተስፋፋ ሲመጣ በብሔር ፖለቲካ ሞት ላይ ግለሰባዊነት እንደሚነግስና ኢህአዴግም ይህንን ተቃርኖ ተከትሎ የርዕዮተ-ዓለም መሸጋሸግ ማድረግ የማይችል መሆኑ እና መሰል ተቋማዊ ክስረቶች በቀጣይ ሊያርማቸው የማይቻለው ታላላቅ ግድፈቶች በመሆናቸው እንደተለመደው ውጤቱ ቀድሞ የሚታወቀውን የይስሙላ ምርጫ ከመጠበቅ ይልቅ የአደባባይ ተቃውሞን ለማማተር ሥረ-ምክንያት ሊሆን መቻሉ አጠራጣሪ (አከራካሪ) አይደለም፡፡
ጉዳዩን በሚገባ ለማስረገጥ ከኢህአዴግ አጠቃላይ ህልውናዊ ባህሪ አኳያ ከላይ ከጠቀስኳቸው ነጥቦች ሊፈታቸው የማይቻላቸው ‹ብሎኖች› መሀከል ሶስቱን (ዋነኞቹ ናቸው ከሚል አረዳድ) በጨረፍታ በአዲስ መስመር እንያቸው፡፡
ያ ሁሉ ነጋሪት የተጎሰመለት የድህረ-ደርግ የዲሞክራሲ ሽግግር ‹ተስፋ› ሙሉ በሙሉ ሞት የታወጀበት አሁን በምንጠራው የ97ቱ ምርጫ ማግስት ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ አቶ መለስ ‹ልማታዊ መንግስት› የሚል ሀልዮት ይዞ ብቅ ማለቱ ይታወሳል፤ በወቅቱ (1998 ዓ.ም ይመስለኛል) በማንችስተር ዩንቨርስቲ በመገኘት ቀጣዩ የስርዓቱ ማዋቀሪያ ምሶሶ አድርጎ ሃሳቡን ያብራራው የምርጫ ፖለቲካ፣ የሰብዓዊ መብቶችን እና መሰል ዲሞክራሲያዊ ዕሴቶችን ጨፍልቆ ‹በአብዮታዊ› መንገድ ልማት ማምጣትን ቀዳሚ ግቡ እንደሚያደርገው በመፎከር ጭምር ነበር፤ ይሁንና ፅንሰ-ሃሳቡን በቅርበት ስንመለከተው፣ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ አውድ፤ በተለይም ስርዓቱ ካነበረው ቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝም ጋር በማይታረቁ ቅራኔዎች መሞላቱን ለመረዳት አያዳግትም፡፡
ለዚህ ክርክር ማስረገጫ ይሆን ዘንድም ከተቃርኖዎቹ ውስጥ ሁለት ነጥቦችን ብቻ እናንሳ፤ የመጀመሪያው ልማታዊ መንግስት ‹የዜጎች የክሂል ልቀትን በመንተራስ ብቻ የተሳለጠ ቢሮክራሲን መገንባትና ተቋማዊነትን ማጎልበት ያስፈልጋል› ከሚለው መደምደሚያ አንፃር ነው፤ በርግጥ ይህ ሃሳብ ስኬታማነቱ የታየው በአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገራት ውስጥ ቢሆንም፣ በሙያ ብቻ ስርዓቱ ሲዋቀር ግን የተለየ የቡድን ጥቅሞችን ለማስፈፀም እንደማይመች ተግባራዊ ተሞክሮዎቹ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ አኳያም የገዥው ፓርቲ የፌደራሊዝም ቅርፅ በግልባጩ የብሔር ማንነቶችን ተቀዳሚና ብቸኛ ተቋማዊነትን መገንቢያ አማራጭ ማድረጉ ከተጠቀሰው የልማታዊ መንግስት ጭብጥ ጋር በቀጥታ ያላትመዋል፡፡ እናም ከላይ እስከታች ያለው የስልጣን አወቃቀሩ የላቀ ክሂልን ረግጦ የብሔር ተዋፅኦን ለመጠበቅ በማለም ብቻ የተወሰነ ስርዓታዊ መልክ መያዙን ስንመለከት፣ ገዥዎቻችን ሀልዮቱን ለመተግበር ሲንቀሳቀሱ በሁለት ምርጫዎች ቅርቃር ውስጥ እንዲወድቁ መገደዳቸው የማይቀር ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፤ እነርሱም የፌደራሊዝሙን ቅርፅ ወደ መልከአ-ምድራዊ (Geographical) መቀየር፣ አሊያም ‹‹ልማታዊ መንግስት ነን›› የሚለውን አሰልቺ ፕሮፓጋንዳ አራግፎ መጣል የሚሉ ናቸው፡፡ ይህንን ደግሞ ኢህአዴግ
ከግትረኛነት ባህሪው አንፃር ይቀበለዋል ተብሎ አለመጠበቁ አንዱ ህልውናዊ ግድፈቱ ያደርገዋል፡፡
ሌላው ተጣራሽ ርዕሰ-ጉዳይ በስልጣን ኢ-ማዕከላዊነትና በማዕከላዊ መንግስት መጠናከር መካከል ያለው ነው፤ በሁለት አስርታቱ ስርዓታዊ ሙከራ፣ የበዛው ከወረቀት ላይ ባይዘልም፣ በጥቂቱም ቢሆን ኢ-ማዕከላዊ ለማድረግ ስለመጣሩ የምናውቀው እውነት ነው፡፡ ይሁንና የልማታዊ መንግስት ፅንሰ-ሀሳብ ማዕከላዊ አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ አጠቃላይ የስልጣን ገፆችን ጠቅልሎ እንዲይዝ ያስገድደዋል፡፡ ይህንንም ስልጣን በማከፋፈል ላይ የሚመሰረት ግጭት ህልውናዊ ድክመቱ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡
ሁለተኛው አስረጂ ጭብጥ የብሔር ማንነትን ዘላለማዊ የስርዓት መልክ ማድረጉ፣ ከከተሜነትና የከተሞች መስፋፋት ጋር አብሮ እየገነገነ ከሚመጣው ግለሰብኝነት (የግለሰብ መብትን ማስቀደም) ጋር ሊኖረው የሚችለው ግጭት ነው፡፡ በስነ-ማህበረሰብና ፖለቲካል ኢኮኖሚ አስተምህሮቶች መሰረት (በዋናነት በምዕራባዊ ሥልጣኔ)፣ የከተሜነት ዕድገት መገለጫ ኢህአዴግ ቀን-ከሌሊት እንደሚለፍፈው የፎቆች መደርደርና የመንገድ መስፋፋት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ከተሜነት ማለት ከጋርዮሽ ማንነት እየተላቀቁ በመምጣት የግል የሆኑ አለማዊ ዕይታዎችን በማጎልበት፣ በመረጡት ማንነትን መተርጎሚያ ፈር ከሚተሳሰሩ ዜጎች ጋር ህብረት መፍጠር የሚለው አንድምታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም በፆታ፣ በሙያ፣ በኃይማኖት አሊያም በተመረጠ ርዕዮተ-ዓለም ስር ምክንያተኝነትን ብቻ በመንተራስ ‹መደራጀት› የከተሜነት ቀዳሚ መለዮ ነውና፡፡ ይህንን ድምዳሜ በተለይም በአዲስ አበቤዎች ዘንድ እየመጣ ካለው የከተሜነት ባህሪ እና ከብሔር ፖለቲካው ጋር ስናስተያየው ‹‹የማይታረቀው ቅራኔ›› (በካርል ማርክስ አባባል) እነበረከት ስምዖን ፊት ይቆማል፡፡ ኢህአዴግ ይህ ተፈጥሮአዊ የማህበረሰብ ዕድገት እንኳ እንደሚገታው አለማሰቡ ከህልውናዊ ግድፈቶቹ አንዱ አድርገን ልንቆጥረው እንገደዳለን፡፡
ርዕሰ-ጉዳያችንን ለመጠቅለል የምጠቅሰው የመጨረሻው ማሳያ፣ ስርዓቱ የተነሳበትን የራስ ዕድል በራስ በመወሰን መብት ላይ ትገበራው የሚያሳየውን ሀሳዊነት ነው፤ ወታደራዊው ደርግ ይከተለው የነበረው ‹አሀዳዊ አስተዳደር›፣ ቋንቋን መሰረት ባደረገው ፌዴራሊዝም ከተተካ በኋላ ስለ ጉዳዩ ያጠኑ ምሁራኖች ‹‹የስልጤ ሞዴል›› እያሉ የሚጠሩትን ይህንን ጭብጥ፣ ግንባሩ እየመረጠ መስጠቱን የሚዘክሩ በዜጎች ደም የተፃፉ የዳጎሱ ታሪኮች ያረጋግጡልናል፡፡ እንደ ምሳሌም የሲዳማንና ሰሞኑን እየታዘብን ያለውን የቁጫን የማንነት ጥያቄዎች ብቻ መጥቀስ በቂ ይመስለኛል፤ ሲዳማ በሀገሪቱ ሕገ-መንግስት መሰረት ክልል ለመሆን የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች ሁሉ ቢያሟላም የተሰጠው ምላሽ ለዓመታት ሞትና እስርን በጥያቄው አራማጆች ላይ እንደ ሐምሌ ዝናብ መዘርገፍ ሲሆን፣ ከሲዳማ ቁጥር በታች ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ በክልል ደረጃ የመዋቀር መብታቸው ሲከበር ተመልክተናል፡፡ ይህንንም የተዛነፈ የመብት ትግበራን በመሰረታዊ የስርዓቱ ክሽፈትነት ልንቆጥረው እንደምንችል ይሰማኛል፡፡ የተቃውሞ መድረኩን ከውስጥም ከውጭም የሞሉት ኃይሎች ዋነኛ ጥያቄም፣ የብሔራችን መብት አልተከበረም የሚለው መሆኑ (በመጠኑ ላይ ባንስማማም፣ ቡድኖቹ ከየብሔራቸው ደጋፊ እንዳላቸው አይካድምና) ስርዓታዊ ሽንፈቱን ያበዛዋል፡፡ በአናቱም በስልጤው ሞዴል ግፊት ወደ አደባባይ የመጡት የወለኔና የቁጫ የማንነት ጥያቄዎች የሚጠቁሙት አንዳች ነገር ቢኖር፣ የስርዓቱ ቁንጮዎች የተጠቀሰውን ስታሊኒስታዊ የራስ ዕድል በራስ የመወሰን ጉዳይ በሕገ-መንግስታቸው ውስጥ ሲከቱት፣ ኢትዮጵያን በመሰለ ባለብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች ሀገር ጥያቄው ማቆሚያ እንደማይኖረው አለማሰባቸውን ነው፡፡
በእነዚህ የኢህአዴግ ታላለቅ ግድፈቶች ህላዊነት ከተስማማን የለውጥ መንገዱንም አንስቶ መነጋገሩ የግድ አስፈላጊ ነውና ወደዚያው እንለፍ፡፡
የከተማ አብዮት ሲባል…
በዚህ ተጠይቅ የምናየው አማራጭ የለውጥ መንገድ ያለንበት ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚበይነውን ሰላማዊ የከተማ አብዮት ብቻ ሳይሆን፣ ረዥም ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዘን በአማራጭነት ይተገበሩ የነበሩትንም ጭምር ነው፤ ምክንያቱም በኢትዮጵያችን ዛሬም ከተቃውሞ ስብስቡ መካከል ሁለቱንም ስልት የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸው እውነት ነውና፡፡
ምንም እንኳ ጥያቄያቸው፣ አመሰራረታቸው እና የሚከተሉት ርዕዮተ-ዓለም ፍፁም የተለያየ ቢሆንም፣ ከኦነግ እስከ ኦብነግ፤ ከአርበኞች ግንባር እስከ ግንቦት ሰባት (ሁሉን አቀፍ የሚሉት ስልት እንደተጠበቀ ሆኖ) ድረስ የሚጠቀሱ ድርጅቶች ከከተማ አብዮት የ‹ማኦኢዝም›ን (ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ጦርነት ላይ የሚያተኩር) የትግል ስልት እንደ ብቸኛ አማራጭ መውሰዳቸው የታወቀ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ተቃውሞ መነሾ የሆነው ራሱ ኢህአዴግም ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ ሳይቀነስ ሳይጨመር ይኸው እንደነበረም አይዘነጋም፡፡
በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ መቀንቀን ከተጀመረበት 1960ዎቹ አጋማሽ አንስቶ የተመሰረቱ ግራ ዘመም ድርጅቶች በሙሉ ‹‹መንፈሳዊ አባት›› አድርገው የሚወስዱት የማኦ ዚዱንግ (Mao Zedong) የቻይና ኮምኒስት ፓርቲ (CCP) ለጥቂት ዓመታትም ቢሆን አራምዶት የነበረው የትግል ስልት ከከተማ ወደ ገጠር የሚነሳ እንደነበረ ይታወሳል፤ ይሁንና ሲሲፒ እ.ኤ.አ. በ1927 ዓ.ም. የፀደይ ወራት በሻንጋይ ሼክ (Chiang Kai-shek) ከሚመራው ‹‹Kuomintang›› (KMT)፣ የደረሰበትን ከባድ ወታደራዊ ጡጫ መቋቋም ተስኖት ከጠንካራ መሰረቶቹ ሻንጋይ እና ክንቶን (ዛሬ ስሟ ‹ጉዋንዡ› /Guangzhou/ በሚል ተቀይሯል) ከተሞች ወደ ገጠር ማፈግፈጉን ድርሳናቱ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በኋላም የእነ ማኦ ድርጅት ‹የሠራተኛ መደብ› የሚል አጀንዳውን አርቆ ሰቅሎ፣ እንደ አዲስ በገበሬ ሰራዊት በመዋቀር የትጥቅ ትግልን ከገጠር የመጀመር ጠቀሜታ ሰባኪ ብሎም የገበሬ አምባገንነት አቀንቃኝ ሆኖ ብቅ ማለቱን ከታሪክ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ ሲሲፒ የስልት ለውጥ ከማድረጉ በፊት ከ11 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍነውን ‹‹ረጅሙ-ጉዞ››ን (Long march) በፅናት መጨረሱ የዓላማ ፅናቱን ያሳያል፡፡
እነ ማኦ ለመስማት ከሚዘገንነው መስዋዕትነት በኋላ ለሥልጣን የበቁት ድርጅታቸው በተመሰረተ በሃያ ስምንተኛ አመት (እ.ኤ.አ. በ1949 ዓ.ም) ነበር፡፡ ከዚህ በኋላም በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት የሚኖሩ ሕዝቦች ‹ጭቆናን ለማስወገድ› በሚል ‹ግራ ዘመም› ድርጅት መስርተው በእምቢተኝነት ሲያምፁ፣ ማኦኢዝም የትግል ስልት የሚበይነውን በገበሬዎች በተደራጀ ሰራዊት ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ሽምቅ ውጊያን እንደሁነኛ አማራጭ መከተላቸውን ታሪክ ይነግረናል፡፡ በአናቱም የማኦ አስተምህሮ ‹በገበሬ አብዮት› የሚመሰረትን የ‹እርሻ መር ኢኮኖሚ ማህበረሰብ› (Agrarian society) መፍጠርን እና የከተሞችን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በማፈራረስ የገበሬውን ሁለንተናዊ ከፍታ ማረጋገጥ ላይ ማተኮሩ በዚህ መንገድ ወደ ሥልጣን የወጡ ገዥዎቻችንን ባህሪ ለመዳኘት ይረዳናል፡፡
እነሆም በዚህ ትውልድ መቀመጫቸውን በሀገራችን የጠረፍ ከተሞች አሊያም በአውሮፓና አሜሪካ ያደረጉ ብረት ያነሱ ድርጅቶች ከላይ በተጠቀሰው የታሪክ ንባብ ከተመዘኑ፣ አንድም የመረጡት የትግል ስልት ዘመኑን የሚዋጅ ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል፤ ሁለትም በለስ ቀንቷቸው ያሰቡት መሳካት ቢችል እንኳ፣ በእንዲህ አይነት መልኩ ባንክ ዘርፈው፣ መሰረተ ልማቶችን አውድመው፣ ንፁህን ዜጎችን ለህልፈት ዳርገው፣ የቅርብ ጓደኞቻቸውን ሰውተውና ጠብ-መንጃ ተሸክመው ወደ ቤተ-መንግስት የሚመጡበት መንገድ፣ ከዓመታት በፊት መለስና ጓዶቹ ‹ታግለናል፣ ሞተናል፣ ደምተናል… እናም ምርጥ ምርጡ ለእኛና ለቤተሰቦቻችን ብቻ› በሚል ድምዳሜ ካዘጋጁት ‹መፅሀፍ› አንድ ገፅ ገንጥለው ‹‹የሞትንም እኛ፤ ያለንም እኛ…›› ወደሚል የአምባገነኖች ጠርዝ መገፋታቸው አይቀሬ ይመስለኛል፡፡
በተጨማሪም ‹‹ጨቋኝ ጨቋኝን ሊተካው ይችላል›› እንዲል አርስቶትል ኢህአዴግ ለአስራ ሰባት ዓመታት በዱር-በገደል ወጥቶና ወርዶ፣ አስከፊ መስዋዕትነትን ከፍሎ፣ አራት ኪሎ ከደረሰ በኋላ፣ ያነበረው ስርዓት ካመፀበት የመንግስቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ጋር ያለው ልዩነት የስም ብቻ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ ሁኔታም ነው በብረት የታጠረ፣ ደም አፋሳሽና የተናጥል አሸናፊነትን በሚያውጅ ስብከት ላይ ብቻ የተገነባው የትግል ትርጓሜ ዛሬም እንደአዲስ የመከለሱ ዜና በስጋት ያነጠበን፡፡ በርግጥም የጭቆናን ሸክም ከትከሻ ለማውረድ ሲባል የተካሄዱ መራራ ትግሎች ውጤታቸው ጨቋኞችን መቀያየር መሆኑና የትንቅንቁ ወራቶች መርዘም ያስከተሉት ኪሳራዎች ከዘመኔ ቀድሞ የነበረውን የማኦን መንገድ የታሪክ መዛግብት ላይ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር በመገደብ ለአማራጭነት እንኳ እንዳይበቃ አድርገውታል፡፡ የዚያን ዘመን የጨቋኞች አገዛዝ ውርስን ለመከተል ወቅቱ አመቺ አለመሆኑንና የሥልጣን ወንበርን ለጊዜውም ለማሰንበት ዘመን-ወለዱን አመቻማች አምባገነንትን መጠመቅ ማስፈለጉም የትግሉ ስያሜ በድጋሚ ለብይን እንዲቀርብ ተጨማሪ ኃይል ሆኗል፡፡ ርዕዮተ-ዓለማዊ ልዩነቶች እስኪዘነጉ ድረስ መጥበባቸው፣ ክስተቶች ከአንድ ሀገር ድንበር መዝለላቸው እንዲሁም ወቅታዊዎቹ የለውጥ ስኬቶች በጋራ የቀድሞውን የአብዮት መስመር በጥርጣሬ እንድንመለከተው ፈርደውበታል፡፡ ዛሬ ላይ አብዮት ቃሉ ብቻ እስኪቀር ድረስ ተነቅሎ ነባር የመዳረሻ መንገዶቹ ፈራርሰዋል፤ በፍርስራሹ ላይም አዲስ ትርጓሜ ተቸክችኮበታል፡፡
እነዚህና መሰል ሁነቶች የለውጡን መንገድ ለመቃረም ፊታችንን ወደ አውሮፓውያኖቹ የ‹ብርቱካናማ› እና የ‹ፅጌረዳ› አሊያም ወደ አረቡ የ‹ፀደይ› አብዮት እንመልስ ዘንድ ያስገድዱናል፡፡ ይህ ግን እነ ሌኒን ያራምዱትና ይመክሩት ከነበረው በከተሞች ውስጥ ከሚደረገው የትጥቅ ትግል ፍፁም የተለይ ይመስለኛል፡፡ በርግጥም እንዲህ አይነቱ አማራጭ በ1966ቱ አብዮት ማግስት በራሳችን ሰዎች ተሞክሮ ከመክሸፉም በላይ ሀገሪቱን ወደ ቀለም ሽብር ከቷት መቼም ሊተካ የማይችል ዋጋ ማስከፈሉ ሁሌም በቁጭት የምናስበው ታሪካችን ነው፡፡ እናም ለእኔ ትውልድ የለውጥ ጥያቄ ከሰላማዊው የከተማ አብዮት ውጪ ያሉ አማራጮች ከጠቀሜታቸው ይልቅ ጥፋታቸው አመዝኖ ነው የሚታየኝ፡፡ በተለይም ነባሩን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል (የ‹ጦር አርበኝነት›ን በ‹ሲቪል ጀግንነት›) ለመቀየርም ሆነ፣ ከእርስ በርስ እልቂት፣ ከደም መፋሰስ፣ ከደካማው ኢኮኖሚ መንኮታኮት፣ ካለመረጋጋት… ለመታደግ ብቸኛ መፍትሄ ይኸው ነው፡፡ በተጨማሪም ከከተማ መነሳቱ ለአገዛዙ ምሰሶ፤ ለሀገሪቱ ደግሞ ስጋት የሆኑትን የሃይማኖት እና ብሔር (ቋንቋ) ልዩነቶችን ተሻግሮ፣ በአንድ ሀገር በእኩል ማንነት ላይ የሚያሰባስብ ኃይል ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ለእንዲህ አይነቱ አደገኛ ስጋት መቃረባችንን የሚያሳየው በይበልጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተቃውሞ ስብስቡ አካባቢ የሚሰማው ከሀገር ይልቅ የትውልድ መንደርን የማስቀደም ድምፅ ነው፡፡ ይሁንና ይህ መንገድ የትም ሊያደርስ ካለመቻሉም በላይ ላለፉት ሃያ ዓመታት የጭቆና ቀንበርን ትከሻችን ላይ እንዲከርር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ እናም ወደ ተናፋቂው የነፃነት ምኩራብ ሊያደርሰን የሚችለው ድምዳሜ ስርዓቱ ትግራይን ከኦሮሚያ፣ ወይም ከአማራ… የበላይ አድርጎ ያስተዳድራል ለሚሉ ከፋፋይ አሉባልታዎች ጆሮ መንፈግ ብቻ ነው፤ የአንዳንድ ብሔር ተኮር ድርጅት አፈ-ቀላጤዎችም ንጉሳዊውን ዘመን የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወኪል ለማስመሰል መሞከራቸውም ሆነ ህወሓት የተሰኘው የማፍያ ቡድን የሚፈፅመውን ግፋአዊ አገዛዝ በየትኛውም መስፈርት ከትግራይ ህዝብ ጋር ለማያያዝ የሚያደርጉትን ጥረት ማክሸፉ ከአብዮቱ ቅድመ ዝግጅቶች አንዱ ይመስለኛል፡፡
የሆነው ሆኖ ‹አብዮት የራት ግብዣ አይደለም› እንዲል ማኦ፣ አሁን እየተናገርንለት ያለው ሰላማዊው የከተማ ተቃውሞ የጠብ-መንጃውን ያህል ባይሆንም እንኳ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በየትኛውም ሀገር ያሉ አምባገነን ገዥዎች በሕዝባዊ እምቢተኝነት አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎቻቸውን ወደ ቤተ-መንግስታቸው እንዲገቡ ሲፈቅዱ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡
እንዲያውም በግልባጩ በጦር ሠራዊትና በደህንነት ኃይል ለማስፈራራት ሲሞክሩ፣ ከተቃዋሚዎቻቸው የተወሰኑትን በመቀጣጫነት በጥይት ሲያስደበድቡ፣ አስተባባሪዎቹን ሲያስሩ፣ የአገዛዛቸውን የብረት መዳፍ ይበልጥ ሲያጠነክሩ… ይስተዋላሉ፡፡ ይሁንና ይህ አይነቱ የጭካኔ እርምጃ አምባገነኖችን ከአብዮቱ ወላፈን ሊታደጋቸው አለመቻሉን ማረጋገጥ ካስፈለገ ቱኒዝያ ጥሩ ማሳያ ትመስለኛለች፡፡ አደባባዩን ከማማተር አስቀድሞ ግን አብዮቱ መያዝ ስለሚገባው ባህርያት ጥቂት ነጥቦችን ማንሳት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡
የለውጡ መስመር አንዱ መለዮ መሆን የሚኖርበት የትኞቹንም ጨቋኝ ህጎችን በአደባባይ መጣስ ነው፤ እዚህ ቦታ ለመሰለፍ ጠይቀን ተከለከልን፤ ደጋፊዎቻችንን እንዳንሰበስብ አዳራሽ አጣን… እና መሰል ቀልዶችን በመተው አዋጆቹን (እንደ ፀረ-ሽብር እና የፕሬስ አዋጅ ውስጥ ያደፈጡ ቀፍዳጅ አንቀፆችን) በግላጭ በመጣስ በገፍ ወደዘብጥያ ለመውረድ መወሰን የአብዮቱ ዋና አካሄድ መሆን የሚኖርበት ይመስለኛል (በዚህ አውድ አንድ የቢሆን ምሳሌ እናንሳ፤ አሁን ካሉት ህጋዊ ፓርቲዎች መካከል አንዱ በአንድ ክፉ ቀን የፓርቲው የህጋዊነት ማረጋገጫ በሎሌው የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ቢሰረዝና እኛም አማራጭ አካሄዶችን ስለማሰላሰላቸው ብንጠይቅ፣ ‹‹ጨዋታው ፈረሰ…›› ብለው ወደየቤታቸው ገብተው ይቀመጡ ይሆናል ከሚለው ውጪ የምናገኘው ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?)
ሌላኛው ነጥብ ቡድናዊ መሰባሰቢያ መስፈርቶችን ይመለከታል፤ በአረቡ ፀደይ እንዳስተዋልነው (ስለአረቡ ዓለም አብዮት ባህሪያት ከፍትህ ጋዜጣ እስከ ፋክት መፅሄት ድረስ በተደጋጋሚ ሊብራራ ተሞክሯልና እዚህ መድገም አያስፈልግም) የፆታን፣ የኃይማኖትን፣ የመደብን፣ የአንድ ርዕዮተ-ዓለምን አሊያም የብሄር ልዩነቶችን በመሻገር ሁለንተናዊ የዜግነት ነፃነቶችን መሻትን ብቻ ማዕከል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሁለንተናዊ የዜግነት ነፃነቶች ሲባል ደግሞ የኃይማኖት፣ የፖለቲካና የሲቪል መብቶች መከበር ማለት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የትኞቹንም የቡድንም ሆነ ግለሰብ ተኮር ጥያቄዎች ይህንን ነፃነት በማስከበር ትግል ውስጥ ማስመለስ እንደሚቻል መታወቁ የአብዮቱን መሪ ቡድኖች መልከዓ-ባህሪ በዜግነት ላይ ብቻ እንዲቆም ያደርገዋል፤ ይህ ክንውንም፣ በአንድ በኩል የስርዓቱን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ሲያከሽፍ፣ በሌላ በኩል የተሻለች ሀገር ለማቆም የማይነቃነቅ ጠንካራ መሰረት ይጥላል (በነገራችን ላይ ከዚህ ቀደም ፋክትን ጨምሮ በአራቱም የህትመት ውጤቶች ያነሳኋቸው የፈራ ይመለስ፣ ሞት የማይፈሩ ወጣቶች፣ ለምን ትፈራለህ? የታህሪር ናፍቆት፣ የዘገየው አብዮት፣ የግፉአን ዕድሜ ምን ያህል ይረዝማል? አደባባዩ ምን ያህል ይርቃል? የመሳሰሉት ቀዳሚ ድምፆች በዚህ አይነቱ ሰላማዊ የከተማ
አብዮት የሚበየኑ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል)
የአብዮቱ ግቦች…
በጥቅሉ እዚህ ድረስ ስንነጋገርበት የነበረው የከተማ አብዮት እንደ ሊቢያ ወይም ሶርያ ለእርስ በእርስ እልቂት የሚዳርግ ደም አፋሳሽ አለመሆኑ ግልፅ ይመስለኛል፡፡ በዚህ አውድ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው አንኳር ጉዳይ የአረቡን መነቃቃት ተከትሎ በሞሮኮ፣ የመን እና ኳታር እንደታየው አይነት፣ ከስር ነቀል ለውጥ ይልቅ የፖለቲካ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የአምባገነኑን አገዛዝ እጅ መጠምዘዙ ላይ ነው፤ ይህ ይሆን ዘንድም የሚከተሉት ጥያቄዎች ወደ አደባባይ መሰባሰብ የሚያስችሉን የጋራ አጀንዳ (የአብዮቱ ግቦች) ቢሆኑ ለስርዓቱ ‹‹የወንድ በር››፤ ለምንወዳት ሀገራችን ደግሞ የተስፋውን መንገድ ጠራጊ የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡
ከፊታችን ያለው የ2007ቱ አምስተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ከመደረጉ በፊት፣ ያን ጊዜ የ97ቱ ቅንጅት ፓርላማ ለመግባት በቅድመ ሁኔታነት አንስቷቸው የነበሩትን ከፊል ጥያቄዎች ጨምሮ ሌሎችም በዚህ ፅሁፍ የተካተቱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣቸው ዘንድ ከሥራ ማቆማ አድም አንስቶ ከአገዛዙ ጋር አለመተባበርን የሚያካትትና ለውጡ እስኪመጣ በተከታታይ (በብሔር አግላይ ያልሆነ) መሬት አንቀጥቅጥ የተቃውሞ ሰልፍ መሰል እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ራስን ማዘጋጀት ይጠይቃል፤ ጥያቄዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡-
1/ ሁሉንም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር መፍታት፤
2/ እስከ ዛሬ ድረስ በሀገር ጥቅም ላይ ለተፈፀመው ጥፋትም ሆነ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋ፣ እስር፣ እንግልት፣ አካል መጉደል እና ስደት ኃላፊነት ወስዶ በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅ (ካሳ የሚገባቸውን መካስ)፣ ለብሔራዊ ዕርቅ መደላድል መፍጠር፤
3/ አፋኝ የሆኑትን የፀረ-ሽብር፣ የፕሬስ፣ የመያዶች እና የፖለቲካ ማሻሻያ አዋጆችን መሻር፤
4/ ዜጎች በሚያምኑበት የፖለቲካ አስተሳሰብ የመደራጀት መብታቸውን ያለአንዳች ገደብ መልቀቅ፤
5/ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በእኩል ደረጃ መወያየትና መደራደር፤
6/ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን ነፃና ገለልተኛ መሆኑን በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንደገና ማቋቋምና የአቅም ብቃቱን መገንባት፤
7/ ፍትሐዊ የመንግስት ሚዲያ አጠቃቀም እንዲኖርና የግል የኤሌክትሮኒክስም ሆነ የህትመት ሚዲያዎች ያለ ከልካይ እንዲኖሩ መፍቀድ፤
8/ የፍ/ቤትን እና የሌሎች የፍትህ አካላትን ነፃነት ማረጋገጥ፤
9/ የፖሊስ፣ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ከፖለቲካ ገለልተኛ እንዲሆኑ ማድረግ፤
10/ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ተፈፃሚ የሚያደርግ ለየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት የማይወግን ነፃ የሆነ አካል ማቋቋም የሚሉት
ጥያቄዎች የመንደርደሪያ ነጥብ መሆን የሚችሉ ይመስለኛል፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

No comments: