Tuesday, January 21, 2014

በሃይማኖት ጭቆና ስም የሚረጩ አደገኛ መርዞች

January20/2014

ከፋሲል የኔአለም (ጋዜጠኛ)

አራተኛውን የኢቲቪ “ጥናታዊ ፊልም” አየሁት፤ ዝቅ ሲል ለምርጫ ቅስቀሳ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ከፋፍሎ ለመግዛት ተብሎ የተዘጋጀ ይመስለኛል። ፊልሙ ኢህአዴግንና የቀድሞ ስርዓቶችን ያነጻጽራል፤ ማንም ነፍስ ያለው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ጭቆና አልነበረም ብሎ አይክድም፤ ልዩነቱ የሚጀመረው “ጨቋኙ ማን ነው? ተጨቋኙስ?” የሚለውን ለመመለስ ሲሞከር ነው። በእኔ እይታ ጨቋኞቹ የኦርቶዶክስ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ መንግስታት ብቻ እንደነበሩ ተደርጎ የሚቀርበው አስተያየት ስህተት ነው፣ ተጨቋኞቹ ከኦርቶዶክስ ውጭ ያሉ ሃይማኖቶች ብቻ እንደነበሩ ተደርጎ የሚቀርበውም አስተያየት በታሪክ ያልተደገፈ፣ የስህተት ትምህርት ነው ። ታሪካችን እንደሚነግረን ከ66ቱ አብዮት በፊት፣ ሁሉም ስልጣን የያዙ ሃይሎች ስልጣናቸውን ለማቆየት ወይም ግዛታቸውን ለማደራጀት እነሱ የሚደግፉትን ሃይማኖት በሌላው ላይ ለመጫን ሙከራ አድርገዋል። የአጼ ሃይለስላሴ መንግስት የመጀመሪያውን የጽሁፍ ህገመንግስት ስላረቀቀና በህገመንግስቱ ላይ “ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት” የመንግስት ሃይማኖት መሆኑን በይፋ ስላወጀ ዛሬ እንደ ትልቅ ግኝት ተጋኖ ይቀርባል እንጅ፣ ከዚያ በፊት የነበሩት ገዢዎች ኦርቶዶክስን ብቻ ሳይሆን፣ካቶሊክንና እስልምናን የመንግስት ሃይማኖት ለማድረግ ሞክረዋል። ክርስትናን በይፋ ከተቀበለው ከመጀመሪያው ንጉስ ኢዛና ጀምሮ እስከ አክሱም ስርወ-መንግስት ውድቀት ድረስ ኦሮቶዶክስ ሃይማኖት የመንግስት ድጋፍ ነበራት፤ ዮዲት መጣችና ስርዓቱን ለማፍረስ ሞከረች። ቀደም ብሎ ክርስትናን የማያውቁት አገዎች፣ ክርስትናን ከአክሱሞች ስለተቀበሉ፣ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ያለምንም ችግር የመንግስት ሃይማኖት ሆኖ ቀጠለ። ይኩኖ አምላክ ከዛግዌዎች ስልጣኑን ከቀማበት እስከ ግራኝ አህመድ ዘመቻ ድረስ ኦሮቶዶክስ አሁንም የመንግስት ሃይማኖት ሆና ቆይታለች። ይሁን እንጅ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑት ነገስታት ከኦሮቶዶክስ ውጭ ያሉ ሃይማኖቶችን ብቻ ሳይሆን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ሆነው፣ የአስተምህሮ ልዩነት የነበራቸውን ሳይቀር፣ ሃይማኖታቸውን በነጻነት እንዳያስፋፉ ያግዱ ነበር። የደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ታሪክ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን እስከመጨረሻው ኦርቶዶክሶች ነበሩ፣ከሙስሊሙ ወይም ከቤተ-እስራኤላውያን ባላነሰ መልኩ ወከባ ደርሶባቸዋል።

ግራኝ አህመድ ዘመቻውን ወደ ሰሜን ባስፋፋበት ወቅት ደግሞ ቀድም ብሎ ክርስቲያን የነበሩት ዜጎች እስልምናን በግድ እንዲቀበሉ ተደርጓል። ግራኝ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ ቆይቲ ቢሆን ኖሮ እስልምና የመንግስት ሃይማኖት የመሆን እድሉ ሰፊ ነበር። ግራኝ በስልጣን ላይ በነበረባቸው አመታት እስልምና ዋና የአገሪቱ ሃይማኖት ነበር። ግራኝን ለመውጋት የመጣው የፖርቱጋል ጦር በበኩሉ አንዱ አላማው የካቶሊክ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ማስፋፋት ነበር። ገልውዲዎስ ፈቃደኛ ቢሆን ኖሮ ካቶሊክ የመንግስት ሃይማኖት የመሆን እድሉ ሰፊ ነበር፤ አጼ ሱስንዮስ ሲነግሱ ግን ካቶሊክ የመንግስት ሃይማኖት ሆነ ። ኦርቶዶክስ የሆኑትም ያልሆኑትም እኩል ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ተገደዱ። ካቶሊክ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የመንግስት ሃይማኖት ሆነ፣ በዚህም የተነሳ ብዙ ደም ፈሰሰ። አጼ ፋሲል ሲነግሱ ደግሞ ኦርቶዶክስ ተመልሳ ከበሬታ አገኘት- “አጼ ፋሲል ነገሱ፣ ሃይማኖትን መለሱ” ተባሉ። ይሁን እንጅ በእርሳቸውም ጊዜ “ሁለት ልደት ፣ ሶስት ልደት፣ ቅባት ፣ ተዋህዶ” በሚሉ የአስተምህሮ ልዩነቶች ኦርቶዶክስ ትናወጥ ጀመር። ከዚያ በሁዋላ በመጡ መንግስታት ቅባቶች ሲያሸንፉ ተዋህዶዎች ተሳደዱ፣ ተዋህዶዎች ሲያሸንፉ ደግሞ ቅባቶች ተሳደዱ። በዘመነ መሳፍንት ጊዜ ደግሞ ለ90 ዓመታት ገደማ ማእከላዊ መንግስት የሚባልም ነገር ስላልነበር፣ የመንግስት ሃይማኖት የሚባል ነገር አልነበረም፣ መንግስት ነበር ከተባለም የይስሙላ ነበር። ከዚያ በሁዋላ የመጡት አጼ ቴዎድሮስ በኦርቶዶክስ ውስጥ የአስተዳደር“ ተሃድሶ” ለማካሄድ ሞከሩ። አብዛኞቹ አማካሪዎቻቸው ፣ ፈረንጆቹ ማለቴ ነው፣ ፕሮቴስታንቶች ነበሩ። ንጉሱ የኦርቶዶክስ ተከታይ ቢሆኑም ሃይማኖቱን ለማስፋፋት ወይም ሌላው ሰው ሃይማኖቱን እንዲቀይር ሲያስገድዱ አልታየም፤ ከኦርቶዶክስ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መበላሸት ለውድቀታቸው አንዱ ምክንያት ሆኗል፣ ታሪክ አስተማሪዎቻችን እንደነገሩን ንጉሱ የፕሮቴስታንቱ ትምህርት እየጣማቸው ሄዶ ነበር። ከዚያ በሁዋላ የመጡት አጼ ዮሃንስ አራተኛ ደግሞ አጥባቂ ኦርቶዶክሳዊ ነበሩ። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በይፋ የመንግስት ሃይማኖት እንዲሆን ቦሩ ሜዳ ላይ ደንግገዋል። ሙስሊሙ ሃይማኖቱን እንዲቀይር አስገድደዋል፤ ከተዋህዶ ውጭ ያሉት፣ በተለይ ቅባቶች በጎጃም ( ምስራቅ ጎጃም) አካባቢ ተጠልለው እንዲቀሩ አድርገዋል። ለእርሳቸው ሃይማኖት ትልቅ ቦታ ነበረው።

እርሳቸውን የተኩዋቸው አጼ ሚኒሊክ ኦርቶዶክስ ቢሆኑም፣ ቀደም ብሎ ሃይማኖት የነበራቸው ሰዎች ፣ በተለይ ሙስሊሞች፣ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ሲያስገድዱ እምብዛም አይታይም፤ ሃይማኖት የላቸውም ተብለው የሚታሰቡት ወይም ከኦርቶዶክስና እስልምና ውጭ ያሉት ግን ኦርቶዶክስን እንዲቀበሉ ተጽእኖ ይደረግባቸው ነበር። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ግን የመንግስታቸው ሃይማኖት ነበር፡፡ ከእርሳቸው በሁዋላ የመጡት ልጅ እያሱ፣ኦርቶዶክስን የሚወዱ ሰው አልነበሩም፣ ከስልጣን የወረዱትም የመንግስትን ሃይማኖት እስልምና ለማድረግ አስበዋል በሚል ተዶልቶባቸው ነው፤ በእርሳቸው ዘመን፣ ጊዜው አጭር ቢሆንም ከኦርቶዶክሶች ይልቅ ሙስሊሞች የተሻለ ተቀባይነት ነበራቸው፤ በእርግጥ አባታቸውም ቀደም ብሎ ሙስሊም የነበሩ ናቸው። ልጅ እያሱ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ ቆይተው ቢሆን ኖሮ፣ እስልምና የመንግስት ሃይማኖት እንኳን ባይሆን፣ እንደ ኦርቶዶክስ እኩል የመንግስት ሃይማኖት የመሆን እደል ይኖረው ነበር ብየ አስባለሁ።

አጼ ሃይለስላሴ ከእያሱ ውድቀት ተምረው ኦርቶዶክስ ተዋህዶን መንግስታዊ ሃይማኖት ሆኗል ብለው በህገመንግስት ደነገጉ፤ እርሳቸውን ዘመናዊውን ትምህርት ያስተሟሩዋቸው ሰው ካቶሊክ ነበሩ። አጼ ሃለስላሴ “ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት፣ የመንግስት ሃይማኖት ነው” ቢሉም፣ ሙስሊም በሙሉ በአንድ ጊዜ ኦርቶዶክስ እንዲሆን አላዘዙም፣ በሙስሊሙ፣ በካቶሊኩና በሌላው ሃይማኖት ተከታይ ላይ አስተዳደራዊ ተጽኖዎች አልነበሩም፣ የመንግስት አድልዎ አልነበረም ማለት ግን አይደለም ። ኮሎኔል መንግስቱ ሃየለ-ማርያም መጡና “እግዚአብሄር የሚባል የለም” ብለው ሙስሊሙንም ክርስቲያኑንም ኩምሽሽ አደረጉት፤ ሙስሊሙ የአሁኑ ይባስ አለ፣ ክርስቲያኑም፣ እግዞዎ አለ። ሙስሊሞች “አላህ በኖረና በተጨቆንን ፣ ኦርቶዶክሶች ደግሞ “እግዚአብሄር በኖረና መንግስታዊ ሃይማኖት መሆኑ በቀረብን” ሳይሉ የቀሩ አይመስለኛም ። መንግስቱ በሁሉም ሃይማኖት ላይ ሳያዳላ ነው የተነሳው፤ ያም ሆኖ ግን ጓድ መንግስቱ ሰዎች በአንድ ጀንበር ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ አላስገደዱም፤ የሚከተለውን ያውቁ ነበርና። ፕሮቴስታንትን በተመለከተም ኮሎኔል መንግስቱ፣ ፕሮቴስታንት ስለሆነ ብቻ፣ የተለየ አሉታዊ ተጽእኖ አላደረጉበትም፤ እርሳቸው ፕሮቴስታንት እንዲስፋፋ ያልፈቀዱት ሌላ ራስ ምታት ላለመጨመር ነው፣ ራሳቸውን ለማዞር ኦርቶዶክስና እስልምና በቂዎች ነበሩ። መንግስቱ ኮሚኒዝምን ትተው የምእራባውያንን ዲሞክራሲ ቢከተሉ ኖሮ፣ ፕሮቴስታንት ሃይማኖት እንደልቡ እንዲንቀሳቀስ ይፈቀድለት ነበር።

በኢህአዴግ ጊዜ ደግሞ ፣ ሙሉ መብትን የማይጠይቁ ሃይማኖቶች እስካልተነሱ ድረስ፣ ማንም የፈለገውን ሃይማኖት መከተል ይችላል። ሙሉ መብትን የሚጠይቁ ሃይማኖቶች ከመጡ ግን በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው መቀመቅ ይወርዳሉ።
እንግዲህ ሳጠቃልለው፣ ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን እና ሃይማኖቱን ይከተሉ የነበሩ ነገስታትን ብቻ ጨቋኝ አድርጎ ማቅርብ ስህተት ነው። የኦርቶዶክስም ሆነ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ገዢዎች፣ ሃይማኖታቸውን በሃይል ለማስፋፋት ጥረት አድርገዋል፤ ገዢዎቹ እነሱ ከሚከተሉት ሀይማኖት ውጭ ያሉትን ዜጎች ብቻ ሳይሆን በአንድ ሃይማኖት ስር እንኳ ሆነው የተለየ አስተምህሮ ይከተሉ የነበሩትን ሳይቀር አሳደዋል። ኦርቶዶክስን ጨቋኝ ፤ ሙስሊሙንም ተጨቋኝ አድርጎ ለማሳየት የሚደረገው ሙከራ እጅግ አደገኛ ነው። ገዢው ፓርቲ ራሱን ለአንዱ የመስቀል ጦረኛ፣ ለሌላው ጂሃዲስት እያደረገ ለማቅረብ የሚያደርገው ሙከራ ከራሱ አልፎ ለአገር እንዳይተርፍ ፣ከአሁኑ እረፍ ሊባል ይገባዋል።

No comments: