Friday, January 31, 2014

ኢህአዴግ ሚኒስትሮቹን የግንባሩን ስራ እንዲያከናውኑ መደበ

January31/2014

ጥር ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ ፓርቲውን እንዲመሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና ሌሎች ሁለት ሚኒስትር ዴኤታዎችን ባለፉት ወራት መሾሙን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቆሙ፡፡

ኢህአዴግ የመንግስት መዋቅርን ከፓርቲው መዋቅር ጋር አደበላልቆ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችና ትችቶች እየቀረቡበት የቆየ ሲሆን በዚህ መልኩ ግልጽ የሆነ አደረጃጀት በመያዝ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ሲመድብ ከአቶ መለስ ሞት በሃላ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሎአል፡፡

ቀደም ሲል የግንባሩ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመናብርት የግንባሩንና የአባል ፓርቲዎችን የሚመሩበት ሁኔታ የተለመደ ሲሆን የአሁኑ አደረጃጀት ግን ለየት የሚያደርገው በሚኒስትር ዴኤታ ማእረግ ጭምር በመንግስት ሃላፊነት ላይ የተመደቡ ሹማምንት ከነጥቅሞቻቸው ወደ ፓርቲው ሃላፊነት ተመድበው የመምጣታቸው ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎቹ አብዛኛውን ጊዜያቸውን በፓርቲው ስራዎች እንደሚያጠፉ የጠቆሙት ምንጮቻችን ይህም ከመጪው ምርጫ ጋር በቀጥታ የተያዘ ነው፡፡
በዚሁ መሰረት አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠ/ሚኒስትርና የኢህአዴግ ጽ/ቤትን በበላይነት የሚመሩ ሲሆን አቶ ደስታ ተስፋው እና አቶ አማኑኤል አብርሃም በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ሆነው ግንባሩን በተለያዩ ሃላፊነቶች እንዲመሩ ተመድበዋል፡፡ እነዚህ ሹማምንት በመንግስት ገንዘብ፣ ነዳጅና ጊዜ የፓርቲ ስራዎችን ማከናወናቸው ፖለቲካዊ ሙስና መሆኑን ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው ወገኖች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢህአዴግ የተማሩ አባሎች የሉትም በሚል የሚደርስበትን ትችት አስተባብሎአል። ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ያልቻለው የተማሩ አባላትና ተሿሚዎች ስለሌሉት ነው በሚል ከተቃዋሚዎችና ከሌሎች ወገኖች የሚቀርብበትን ተደጋጋሚ ትችት ሃሰት ነው ብሎአል፡፡

በጠቅላ ሚኒስቴር ቢሮ የሕዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት ሚኒሰትር ዴኤታና የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብና የውጪ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ደስታ ተስፋው ለመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዛሬ ዕትም በሰጡት መግለጫ በአሁን ወቅት የመልካም አስተዳደር ችግር አለባቸው የሚባሉት ስላልተማሩ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አያግባባም ካሉ በሃላ በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ አባላት የትምህርት ደረጃቸውን እያሻሻሉ ነው ብለዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች አጀንዳ አድርገው የሚያቀነቅኑት በፍጹም የተሳሳተ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በአባላት መካከል ውድድር ቢካሄድ የኢህአዴግ አባላት በትምህርትና በብቃት እንደሚበልጡ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አንድ የኢህአዴግ ተሹዋሚ ሲያጠፋ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ወደሌላ ቦታ ማዛወር ሁኔታ እንዳለ ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ በኢህአዴግ ውስጥ አንድ ቦታ ብቁ ሆኖ ያልተገኘ ሌላ ቦታ ሄዶ እንዲሰራ እንደሚደረግ አምነዋል፡፡“በኢህአዴግ ድርጅት ውስጥ ባለው አሰራር መሰረት እያንዳንዱ ግለሰብ ተግባር ይሰጠዋል፡፡  የተሰጠውን ተግባር እንዴት እንደፈጸመ ይገመገማል፡፡በግምገማ ውጤቱ ስራውን በብቃት የፈጸመ አባል ተመስግኖ ለቀጣይ ስራ እንዲዘጋጅ ይደረጋል፡፡በአንጻሩ ደግሞ ድክመት የታየበት አባል እንዲያስተካክል የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ለምሳሌ ያህል ሂስ ይደረጋል፣እንደየሁኔታው በማስጠንቀቂያም ይታለፋል፡፡ የተመደበበት የስራ ቦታ ከብቃቱ ጋር የማይመጣጠን ሆኖ ከተገኘ ከቦታው ተነስቶ የሚችለው ስራ መደብ ላይ ይቀየራል ”ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ችግር አድርጎ የሚያየው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብን ነው ያሉት አቶ ደስታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየተባባሱ አለመምጣታቸውን፣እንዲያውም ወደመልካም አስተዳደር በጉዞ ላይ ነን በማለት እርስ በርሱ የተምታታ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

No comments: