Sunday, November 10, 2013

Ethiopian woman raped, men killed in Saudi Arabia ሚስት እህቶቻችን አይደፈሩ ነው

የማለዳ ወግ …ከጎደፈው ስም ላይ ሌላ ጉድፍ ! – ነቢዩ ሲራክ

በሪያድ መንፉሃ በተከሰተው ሁከት ግራም ነፈሰ ቀኝ ተጎጅዎች እኛ ነን ! እንኳንስ ሰው ተደብድቦ ፣ ሞቶባቸው ፣ እንኳንስ መኪና ተሰብሮባቸው እንዲያውም እንዲው ናቸው ።

ከማለዳ እስከ ሌሊት የዘለቀውን ሁከት መቆጣጠር ይቻል ዘንድ ገና ሲጀመር አቅጣጫውን አይተው የመንግስት ተወካዮችን የመከሩ በርካታ ነበሩ። የሰማ አካል ግን የለም !

ስልክ ተደውሎ የማይነሳበት ፣ አልፎ አልፎ መስመሩ ሲነሳ ሃላፊዎችን ማግኘት በማይቻልበት ዲፕሎማቲክ መስሪያ ቤት ድክመት ገና ከጅምሩ መላ ሊገኝበት የሚችለው ጉዳይ ወዳልተፈለገ
አቅጣጫ አምርቶ ለዚህ አሳፋሪ አሳዛኝ ቀን በቅተናል …

የቀኑን ሁከት ተከትሎ ትናንት ሌሊት በጸጥታ ሃይሎችና ” ሸባብ ” ተብሎ በሚጠሩት የአረቦች ወጣቶች ኢትዮጵያውያንን በማያዳግም እና ሊሰሙት ሊያዩት በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ንብረታቸውን
ዘርፈው ፣ ሴቶች ደፍረው፣ ደብድበው ከመቁሰልና እስከ ሞት ያደረሰ ግፍ ፈጽመውባቸዋል። ሳውዲዎችም ቢሆን በገዛ ሃገራቸው ተንቀው ንብረታቸው ወድሟል ፣ ተደብድበዋል ተገድለዋል ። ( አንድ መሞቱን ሰምቻለሁ) በሁሉም ወገን ትልቅ ጥፋት ተሰርቶ እዚህ ላይ ደርሰናል! በሁሉም ወገን ችግሩን ለመፍታት የተኬደው መንገድ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ያላስገባ ነበረና ጭፍኑ አካሔድ ለዚህ አስከፊ ቀን አድርሶናል! ያም ሆነ ይህ ጥፋቱ እና ጉዳቱ ለእኛ ይከብዳል! ድሮም ከማያምረው ከጎደፈው ስማችን ላይ ሌላ ጉድፍ ጨምረንበት ለዚህ በቅተናል !

የትናንቱ ምሽት ለእኔ ፍጹም አስቀያሚ ነበር ፣ ኢትዮጵያውያን የመንፉሃ ህገ ወጥ ነዋሪዎች ግፍና ዱላው በዝቶባቸው ትናንት ማለዳ ሳውዲ ይሰራልነተብሎ የማይገመር ስራ ሰሩ! ለአመጽ ሻንጣና ቤተሰብ ይዘው በመውጣት “ወደ ሃገራችን በሰላም ስደዱን ፣ አትዝረፉን ሴቶቻችን አትለያዩብን ፣ አትድፈሩብን! ” ብለው አደባባዩን በዋይታ አቀለጡት! እንኳንስ የውጭ ዜጋ ሳውዲው በአመጽ አደባባይ መውጣት በማይታሰብበት ሃገር የኢትዮጵያውያኑ እርምጃ ቢያስገርምና ቢያስደነግጥም ” በሌሊት ቤት እየተሰበረ ከምንዋረድ የመጣው ይምጣ!” በሚል ስሜት ለአመጹ መነሳሳታቸው እውነት ነው ።

የመንፉሃው የትናንት ማለዳው አመጽ በአብዛኛው ብሶትን በመግለጽና ውሰዱን በማለት ያተኮረ ሲሆን የአካባቢው እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ከመግታት አልፎ ወደ መኪና ማውደም እንቅስቃሴ ያመራ አልነበርም። ከቀትር በኋላ ግን ከሶስት በላይ የፖሊስ መኪና ላይ በድንጋይ ጥቃት ተፈጸመ። ብዙ ሳይቆይ አካባቢው በልዩ ሃይል ተከበበ። መንገድ ዳር የነበረው ሰው ተበተነ ። እንዲህ ሆኖ ቢያልፍ መልካም ነበር። አልሆነም! በፖሊስና በጸጥታ ሃይሎች ከበባ ቀጣይ እርምጃ ፍርሃት በነዋሪው መካከል ስጋትን ጫረ ! ኢትዮጵያውያኑ ወጣቱቶች ተመልሰው በመንፉሃ አውራ መንገድ አደባባዮች ላይ ወጡ… ሁኔታው እየከረረ ሲሄድ የሳውዲ እና የኢትዮጵያ መንግስት ሃላፊዎች ቀደም ባሉ ቀናት መስራት በነበረባቸው ዜጎችን በሰላም የመሸኘት ድርድር ላይ ተቀመጡ … ከፍተኛ የጸጥታ ሃላፊዎችን ጋር ውይይቱ በቀጠለበት ምሽት ግን መንፉሃ በከፋ ቀውስ ውስጥ ወድቃለች ! ሌላ ሁከት … ሌላ አደጋ … ሌላ አደጋ …ሌላ መከራ ተከተለ !


ምሽት ላይ የምህረት አዋጁን ተከትሎ ትምህርት ቤታቸው የተዘጋባቸውን ልጆቸን ለማናፈስ ጭምር ከቤት ስወጣ ከሰአታት በፊት በትምህርት ቤቱ ጉዳይ ካንድ ብርቱ ወዳጀ ጋር ለመመካከር ጭምር ነበር ። በሪያድ የመንፉሃ ሁከት ሲያውክን በጅዳ የኮሚኒቲ የተበለሻሸ አሰራርና በቆንስል ሃላፊዎች ክትትል ጉድለት 3000 ሶስት ሽህ ታዳጊ ትምህርት ለጊዜውም ቢሆን ተሰናክሏል። ወደ 70 ሰባ የሚጠጉ መምህራንና ሰራተኞች ስራቸውን አቁመዋል። እንደ ወላጅ በቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ መምከር ግድ ነበርና ተገናኘን… ከወዳጀ ጋር በአንድ ሻሂ ቤት ተቀምጠን ስናወራ በርከት ያሉ ባልንጀሮቻችን ከዚህም ከዚያ መጥተው ክብ ሰርተን ተቀምጠን መጨዋዎት ጀመርን ። በትምህርት ቤቱ ዙሪያ አውርተን መፍትሄው ያው ተጎልቶ ትምህርት ቤቱ እስኪዘጋ የጠበቀው ቆንስል መስሪያ ቤቱን ሃላፊዎች ድክመት ከየአቅጣጫው እያነሳን ቦጫጨቅናቸው።

ወሬው ደርቶ እየተቀባበልን ስንከካው ስልኬ ደጋግሞ ይጮሃል፣ እኔም ደጋግሜ ተነስቸ በመውጣት አውርቸ ስመጣና ከፊስ ቡክ ወዳጆቸ ጋር በወሬው መካከል መልዕክት ስለዋወጥ የተመለከተኝ አንዱ ጠርጣራ ወዳጀ “ለመሆኑ ስለ ሪያድ ባህር ሃይሎች ምን አዲስ ነገር አለ እባክህ? ” በሚለው ጥያቄ ወደ ሪያድ የመንፉሃ ጉዳይ ይዞን ሄደ ። ጨዋታው መድራት ያዘ ከመንፉሃ “ባህር ሃይሎች” እስከ ለፍቶ ግሮ አዳሪው ሰላማዊና ህጋዊ ነዋሪ ሁሉንም እያነሳን ማውራት መወያየት ጀመርን። በየመን ባህር በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ሪያድ ደርሰው በህንጻ ግንባታ የተሰማሩት “ባህር ሃይል ” በሚል ቅጽል ስም ይታወቃሉ ። “ባህር ኋይሎች” በመንፉሃ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ በተለይም ጩቤ ይዘው እርስ በርሳቸው ሳይቀር ሲጋደሉ መክረማቸው አንስተን ተወያየን። በመጨረሻም “የሳውዲ መንግስት የምህረት አዋጁ እንዳለቀ በመንፉሃ የወሰደው ከባህር ሃይሎችን የማስወገዱ ዘመቻ ትክክል ነው !” በሚለው ሁላችን ተስማማን ፣ በመካከል ላይ ከአንድ አሜሪካን ሃገር ካለ ወዳጀ ጋር በሳውዲ ጉዳይ ለመነጋገር ቀጠሮ ነበረንና ስለኬ ተንጫረረች … ስልኬን አንስቸ ውይይቱን አደርጌ ስመለስ ከሻሂ ቤቱ መግቢያ የጠበቀኝ ወዳጀ ከመንፉሃ የመጣ ሰው ላገናኝህ ብሎ አንድ ልጅ እግር ወንድም አገናኘኝ። ለ15 ደቂቃ ያህል የሆነውን እና በአይኑ ያየውን ሁሉ አጫወተኝ ። የቤት ሰበራውን ድብደባ፣ ዘረፋውን እና ግድያውን ጨምሮ ሴት እህቶች መደፈራቸውን አጥብቄ ጠየቅኩት ሞተ ላለው ሃገር ቤተሰቦችን ጠቅሶ ፣ ተደፈረች ላለት ቤተሰቦቿን ላገናኝህ ብሎ አስረግጦ ነገረኝ እና ስልኩን ተቀብየው ተለያየን ..

ተመልሸ ክቧን ጠረጴዛ ስቀላቀል ከሪያድ የመጣው እማኙን የሰጠኝን ቃል በአጭሩ አስረድቻች ውይይታችን ቀጠልን ። …የሳውዲ መንግስት የምህረት አዋጁ ሲያልቅ ያወጣው “ቤት ለቤት ፍተሻ አይደረግም! ” የሚለው መመሪያ ተጥሶ የኢትዮጵያውያን ቤት ብቻ እየተሰበረ ንብረት መዘረፉና በዋናነት ሴት እህቶች የመደፈራቸው ጉዳይ በዚህችው ጠረጴዛም ተነሳ … በዚያ የተስማማነው በዚህ ግን በሃሳብ ተለያየን ፣ የትናንቱ የመንፉሃ አመጽ በሳውዲ ለሚንገኝ ነዋሪዎች ትልቅ ጠንቅ እንደሚፈጥር ግን ሁላችንም በአንድ ድምጽ ተስማማን ! “ቀይ መኪና ሰው ገጨ” ከተባለ ቀይ መኪናን ሁሉ የሚያሳድዱት ሳውዲዎች “ሃበሻ አጠፋ ” ተብሎ ሲነገራቸው በገዛ ምድራችን አመጹብን ብለው በቀጣይ ቀናት የሚሆነውን አስቡት … ይህንና ያንን ስጋት ተነጋግረን ተለያየን!
ውጭ በቆየሁበት የሶስት ሰአት ልዩነት ሰላማዊዋ የአለም ቁንጮ ነዳጅ አምራች ሃገር ዋና ከተማ በአንድ የከተማዋ አካል ታይቶ የማይታወቅ መልኩ ተቀውጣለች … በእኛና በእነሱ በተፈጠረ ሸምጋይ የጠፋለት ሁከት መንፉሃ ጸጥ ረጭ ብላ ሰማዩ መከራ አዝሎ ፣ ሃገሬውና ኢትዮጵያዊው ተፈራርቶ ማምሸቱን ወዳጆች በተከታታይ ካደረሱኝ መረጃዎች ተረዳሁ! ሁከቱ ከማለዳ እስከ ምሽት ደምቆ ታይቷልና የነዋሪውን ትኩረት በአያሌው ስቦ መስተዋሉንም ሳውዲ ባልንጀሮቸ “ምን አደረግናችሁ! ” በሚል ቀልድ በጀመሩት ጭውውት የሁኔታውን አሳሳቢነት ገለጹልኝ … እንዲያ እያለ ምሽቱ ምሽት ተብሎ እያመመኝ ተገፋ !
እኩለ ሌሊት ላይ ደግሞ አሳዛኝና አስገራሚውን ትዕይንት ደም እያፋሰሰ ሲቀጥል ሰማሁ ፣ ተጨባጭ መረጃዎችም ደረሱኝ ።
 
አሁንም ገልጋይ ሸምጋይ አልነበረም… በሳውዲ እምብት በሪያድ መንፉሃ ድሮ በህገ ወጥ ስራ እንጠራ ነበር ። ያ ጋብ ሲል ያለ ህጋዊ የሃገራት ሰምምነት እድሜያቸውን እየቆለሉ ወደ ሳውዲ የሚላኩ ታዳጊ እህቶች ተበድለው እያለ በዳይ እየተባሉ የጥቂቶች እርምጃ ብዙሃኑን በከለው ። “እዕምሮ ህሙማን ኢትዮጵያውያን የኮንትራት የቤት ሰራተኞች የአሰሪዎቻቸውን ህጻናት እስከ መግደል ደረሱ! ” በሚል የከፋው ስማችን ዳግም ከፍቶ እንገለል ዘንድ መንፉሃ ላይ ሌላ ጥቁር ታሪክ አስመዘገብን ! ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ ዙሪያ ገቡ በተኩስ ፣ በሰው ጩኽት ፣ በፖሊስ እና የአንቡላንስ መኪናዎች ኡኡታ ሲናጥ በአካባቢው የኢትዮጵያዊ የተባለ ተፈልጎ እየታደነ ነበር …ውክበት ፣ ድብደባ እና ግድያው ጨለማውን ሽፋን ያደረገ ስለነበር ትናነት ሌሊት የሆነውን በትክክል መናገር የሚችል ከቶ ያለ አይመስለኝም !


ከእኩለ ሌሊት በኋላ ሁከቱ ባልበረደበት ሁኔታ የመሳሪያ ጩኸት በሚስተጋጋባት በሪያድ በመንፉሃ ነገሮች በፍጥነት ይቀያየሩ ይዘዋል! በደረሱኝ እና በሚለቀቁ ተንቀሳቃጨሽ ምስሎች ዋይታ ገኖ ይሰማል! ተከበው የሚገኙ ህጋዊ መኖሪያ የሌላቸውን እና ህጋዊ መኖሪያ ያላቸውን ነዋሪዎች አነጋገርኩ ! አንዱ ወዳጀ አረብ መስጊድ ደርሶ ሲመለስ አንድ ሃበሻ በነጭ ለባሽ ተተኩሶ ከተመታ በኋላ በፍጥነት መነሳቱን የአይን ምስክር እንዳረጋገጠለት አጫወተኝ። ሌላው ወዳጀ ከሁለት በላይ መገደላቸውን መስማቱን እና በአይኑ ያየውን በጋዜጣ የተሸፈነ የወገን ሬሳ ምስል ላከልኝ!

በማከታተል የነዋሪውን አስተያየት ማነፍነፍ ያዝኩ ! ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር የተፋጠጡትን በስልክ አግኝች ለምን የምህረት አዋጁ ሳያልቅ እንዳልወጡ እና የአሁኑ አመጽ ምክንያት ምን የሚል ነው በሚል ጠየቅኩ ” ሳውዲዎች ሁሌ ህግ ያወጣሉ፣ ግን አይፈጽሙትም ። ይህ አዘናግቶኛል! ምንም አይፈጠሩም እርምጃ አይወስዱም ብለን እንጅ ከዚህ መከራስ መውጣት ይሻለን ነበር! ሃገራችን አንሂድ አላልንም ፣ ቤት እየሰበሩ ወንዶችን ይወስዳሉ። የእኛን መያዝ የተመለከቱ የሳውዲ ወጣቶች (ሸባቦች) ሚስት እህቶቻችን ይደፍራሉ ፣ ንብረታችን ይዘርፋሉ! ይህ ለሶስት ቀናት ሲቀጥል የደረሰልን የለም ! ኢንባሲ ደወልን ምንም ማድረግ አንችልም ይሉናል ፣ አንተም ድንጻችን ታሰማናለህ ብለን ብንደውልልህ ፈራህ መሰል አታነሳልንም! የት እንድረስ ? ምን እናድርግ? ንብረታችን እየተዘረፍን ሴቶቻችን እየተደፈሩ ዝም ብለን ማየት ነበረብን? ይህን በመቃወም ሻንጣና ቤተሰቦቻቸር ይዘን ወደ ሃገራችን ስደዱን ነው ያልናቸው ” የሚል እየተቆጣና ድምጹን ከፍ እያደረገ መልስ የሰጠኝን አንድ ወንድም መጨረሻችሁ ምን ሊሆን ይችላል ? አልኩት “… ወደ ሃገራችን ከነሚስት እህቶቻችን ይውሰዱን ነው የምንለው! ያለበለዚያ መንፉሃን እና ሚስት እህቶቻችን አንለቅም! ገድለው ያስለቅቁን ” ሲል ክችም ያለ መልሱን ሰጥቶ ስልኩን ጀሮየ ላይ ዘጋው…

“ከኑ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ ፣ አብረህ ተወቀጥ !” እንዲሉ ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸውን ኢትዮጵያውያንም የሁከቱ ቀዳሚ ተጠቂዎች ሆነዋል ። አንዳንዶችን አነጋግሬ ነበር ። ነገሩ እየከረረ ሌላ ጦስ እንዳያመጣ ስጋታቸውን በመግለጽ በጭንቀት እያለቀሱ ያሉበትን የከፋ ሁኔታ ገልጸውልኛል። ስለ ችግሩ አነሳስ፣ሴቶች ይደፈራሉ ስለሚባለው እና ስለ መፍትሔው ጠይቄያቸው የመለሱልኝ እህት ” የእኛ ወጣቶች በጩቤ ይዋጋሉ በሚልና በህገ ወጥነት ስለሚታወቁ ስማቸው ከፍቶ እንጅ አሁን የተሰራው ስራ ትክክል አይደለም ። ቤት እየተሰበረ ዝርፊያ አለ ። ሴት ትደፈራለች ። እነሱ እውንት አላቸው ! ሚስት እህቶቻችን አይደፈሩ ነው ። አላህ ምስክሬ ነው ።እኔ ሁለት የተደፈሩ እህቶች አውቃለሁ። ኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ልዩ ልዑካንን በአስቸኳይ በመላክ መፍትሔ ካልተገኘ እዚህ ያሉት የኢንባሲ ሰወችን ተዋቸው! የሚያሳስበኝ የእንግዲሁ ኑሯችን ኑሮ ነው ! አንድ ነገር ካልተደረገ ኑሮው ኑሮ አይባልም”ብለውኛል።

የፊስ ቡክ ወዳጆቸም ጠንክረው መረጃውን ያዥጎደጉዱት ይዘዋል ። አንዳቸውንም ለጥፊ በጭንቀት ያለውን ላስበርገግ አልፈለግኩምና መረጃውን ብቻ በስሱ በጽሁፍ መልክ ማስተላለፉን መረጥኩ … አንድ የፊስ ቡክ ወዳጀ የኢትዮጵያዊ ደም የረከሰበትን ጉድ አየሁ ብለው በላኩልኝ መልዕክት ” ሰላም አመሸህ ነብዪ? የሚፈሰውን ደም እያየህ ነው?ኧረ ምንድ ነው መጨረሻችን ?” ሲሉ አጠይቀዋል ! ጥያቄው እኔ መመለስ የማልችለው ግን የብዙሃኑን የሳውዲ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ነዋሪ ነው … የተፈራው ደረሰ …እኔም መጨረሻው አልገባኝምና መጨረሻችን በማጠየቅ የማለዳ ወግ እያልኩ መብተክተኬን እዚህ ላይ ቆም አደረግኩት …

No comments: