Tuesday, November 5, 2013

የፖለቲካው ስር ቁማርተኞች! (ተመስገን ደሳለኝ) ተመስገን ደሳለኝ

November 5/2013

በሀገራችን መንግስታዊ አስተዳደር የ‹‹ቁማር ህግ››ን ችግር መፍቻ አድርጎ መጠቀም የጀመረበትን ጊዜ ለማስላት ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ምንሊክ እንደ”ተበሉበት” ከሚነግረን የሽኩሹክታ ታሪካችን አንስቶ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት… እያልን ለመቁጠር እንገደዳለን፡፡ ይሁንና ባለሙያ (በንባብ የደረጀ) ቁማርተኛ ፖለቲከኛ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛበት ድንገቴ ክስተት የ1966ቱ አብዮት ዋዜማ ነው ቢባል ወደ እውነታው ይጠጋል፡፡ ከመንግስቱ ኃ/ማሪያም ‹‹ለምሳ ያሰቡንን፣ ቁርስ አደረግናቸው›› እና የአጥናፉ አባተ ፍፃሜን ጨምሮ የእነተስፋዬ ደበሳይና ብርሃነ መስቀል ረዳ፤ የእነኃይሌ ፊዳና አለሙ አበበ፤ የእነሌንጮ ለታና ባሮ ቱምሳ፤ የእነ አባይ ፀሀዬና አረጋዊ በርሄ፤ የእነታምራት ላይኔና ያሬድ ጥበቡ… ከትግል መድረክ መገለል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡


ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ደግሞ በእነመለስ ዜናዊና ስዬ አብርሃ፤ በእነኃይሉ ሻውልና ቀኝ አዝማች ነቅዐ ጥበብ፤ በእነብርሃኑ ነጋና ልደቱ አያሌው፤ በእነመረራ ጉዲናና አልማዝ ሰይፉ፤ በእነግዛቸውና ያዕቆብ ኃ/ማርያም… መካከል የተፈጠሩ የሃሳብ ልዩነቶች የተፈቱበት መንገድ በዚሁ የጨዋታ ህግ የተስተናገደ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ተጨባጭ ሁነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች የተቋጩት ከመተዳደሪያ ደንብ ውጪ፣ የተሻለ ዕድል ያለውን ካርታ ቀድሞ በመዘዘ ብልጣ ብልጥ አሸናፊነት ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ የምናየው ‹መልክአ ቁማር›ም ከእንዲህ አይነቱ የጥሎ ማለፉ ጨዋታ በተጨማሪ የመንፈስ ልዕልናቸውን ያረከሱትንም የሚያካትት ይሆናል፡፡
ቁማርተኞቹ…
የተለመደውን ‹‹ፖለቲካ፣ ቆሻሻ ጨዋታ ነው›› ፈረንጅኛ አባባል እንደፈጣሪ ትዕዛዝ በልባቸው ያሳደሩ ፖለቲከኞች እንደአሸን የፈሉት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ነው፤ የሀገሬንም ‹ዕድል ፈንታ› በመዳፋቸው የጨበጡ መሪዎች ከዚሁ መልክአ ምድር መብቀላቸው ይመስለኛል አስከፊ ድህነት፣ ተደጋጋሚ ድርቅ (ችጋር)፣ ሀገር ለቆ መሰደድ፣ የነፃነት እጦት፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣ… በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እንደ ምርጊት የተጣባን፡፡ ይሁንና ‹ይህ ለምን ሆነ?› የሚለው ጥያቄ የባለሙያ ጥናት የሚሻ ጉዳይ ቢሆንም በአይን የሚታየውን፣ በጆሮ የሚሰማውን አንድ ምክንያትን ግን መጥቀስ ይቻላል፡- ‹‹ባለስልጣናቱ ከሚያስተዳድሩት ህዝብ በላይ፣ ለሹመት ያበቃቸውን ድርጅት
አጥብቀው መፍራታቸው››ን፡፡

በእኔ አተያይም ይህ ስር የሰደደ ፍርሀት ከህግና መርህ ይልቅ፣ የጥቂት ወሳኝ ሰዎችን ፍላጎት እንዲያስፈፅሙ፤ ከሀገር ይልቅ ድርጅትን፣ ከድርጅት ይልቅ ሥልጣንንና የግል ጥቅምን እንዲያስቀድሙ አስገድዷቸዋል፤ ወደዚህ አይነቱ ቅጥ ያጣ ፍርሃት ለመገፋታቸውም ሁለት ምክንያት መጥቀስ ይቻላል፤ የመጀመሪያው ከብቃትና አቅም ጋር በተያያዘ (ከትምህርት ዝግጅትም ሆነ ከፖለቲካ ብስለታቸው ጋር በማይመጣጠን ከፍተኛ ሥልጣን ላይ እንዲቀመጡ መደረጉ) ሲሆን፤ ሌላኛው በሥልጣን ዘመናቸው የስግብግብ ነጋዴ ባህሪ የተጠናወታቸው ዘራፊ መሆናቸውን ነው፡፡ እነዚህ ኩነቶች ደግሞ ለከፍተኛ ስልጣን ላበቋቸው አንጋፋ ታጋዮች ለጥ-ሰጥ ብለው የሚገዙ ‹ትጉህ ባሪያ› እንዲሆኑ ተፅዕኖ አድርገውባቸዋል፤ ታማኝነታቸውን ያጎደሉ ዕለት ደግሞ ወደ ወህኒ ሊያስወረውር የሚችል ‹ጥቁር መዝገብ› (ሙስኛነታቸውን የሚያጋልጥ) መጠባበቂያ ተደርጎ መቀመጡን ማወቃቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንደ ‹የግል አዳኝ› አድርጎ ከመቀበል በቀር አማራጭ አሳጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ብሔራዊ ጥቅምንና ህዝብን የሚጎዳ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው ‹ለምን?› ብለው መከራከር አይችሉም፡፡ በርግጥ ስልቱ ቃል-በቃል የተቀዳው ጨቋኝ ገዥዎችን ምክር ይለግስ ከነበረው ኒኮሎ ማኪያቬሊ ‹‹ዘ ፕሪንስ›› ከተሰኘ መፅሀፍ ነው፡-

‹‹የሚሾማቸውን ባለሥልጣናት በሚጠቅመው መልኩ መቅረፅ የሚሻ ገዥ፣ ባለስልጣናቱን መንከባከብ፣ ለክብር ማብቃትና በሀብት ማበልፀግን መዘንጋት የለበትም፤ ከዚህም በላይ ክብሩንና ስልጣኑን ከእነርሱ ጋር በመጋራት ባለውለታው ሊያደርጋቸው ይገባል፤ ይህ ሲሆንም የገዥው ፍፁማዊ አገልጋይ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡››
በእንዲህ አይነት ሁኔታ ሰብዕናው ‹ፈርሶ የተሰራ› ተሿሚም በሥልጣን ዘመኑ ሀገር፣ ህዝብ፣ ህገ-መንግስት፣ ህሊና… እያለ የሚጨነቅበት ሁናቴ አይኖርም፡፡ ፍትህ ቢዛባ፣ ንፁሀን በጥይት ቢደበደቡ፣ ሚሊየኖች በረሀብ ቢረግፉ… አይቆረቁረውም፤ የእርሱ ጭንቀት ለሿሚዎቹ ያለውን ታማኝነት ሳያጓድል በስልጣን መቀጠሉ እና ከለታት አንድ ቀን ‹ይመጣል› ብሎ ለሚሰጋበት ክፉ ቀን ራስን አዘጋጅቶ መጠበቁን አለመዘንጋት ነው፤ የትዳር አጋር እና ልጆችም አሜሪካና አውሮፓን የሙጢኝ የማለታቸው መግፍኤ ይህ ይመስለኛል፡፡ መቼም ስንት ሚኒስትር፣ ስንት ጄነራል ያችን የቀን ጎደሎ ‹ታጥቦና ታጥኖ› እየጠበቀ መሆኑን ‹‹ጊዜ ይቁጠረው›› ከማለት ውጪ ስም ዝርዝሩ ውስጥ
መግባቱ አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም፡፡ የገዥዎችን ስነ-ልቦና ጠልቆ የተረዳው ማኪያቬሊም ቢሆን ሰዎቹ በእንዲህ አይነት ወቅት የሚወስዱትን እርምጃ ገና ድሮ እንደሚከተለው ገልፆት ነበር፡-
‹‹ህዝባዊ አመፅ በአጉረመረመበት ቅፅበት፣ መሪዎች መጀመሪያ ትዝ የሚላቸው ሀሳብ ሁሉንም ጥሎ መፈርጠጥ እንጂ፣ አደጋውን መጋፈጥ አይደለም፡፡››
አቶ መለስ ዜናዊም በአንድ ወቅት ‹‹የኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው›› በማለት ያስተላለፈውን ማስጠንቀቂያ ሹማምንቱ እንደ ‹አብሪ ጥይት› የቆጠሩት ይመስለኛል፡፡ በጥቅሉ አገዛዙ በሃያ ሁለት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ፣ ያሰባሰባቸው ባለስልጣናትም ሆኑ የጦር አዛዦቹ ‹ሎሌ› ለመሆን ራሳቸውን አሳልፈው መስጠታቸው ሀገሪቱን ለተራዘመ መከራ ማጋፈጡ አያከራክርም፡፡ በተለይም የታጠቀውን ኃይል የማንቀሳቀስ ሥልጣን በህግ የተሰጣቸው ጄነራል መኮንኖች፣ ከሲቪል ባለሥልጣናት በባሰ ፍርሃት ውስጥ መውደቃቸው አስተዛዛቢ ነው፡፡
ቁማርተኞቹ…
የአብዛኛው የኢህአዴግ ባለስልጣናት ልጆች በውጪ ሀገር ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በግልባጩ ልጅን በመንግስት ካዝና በውጪ ሀገር ማስተማር ከሙስና ጋር የሚያያዝ መሆኑን ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገና አልተረዳውም፤ ወይም መረዳት አይፈልግም፤ እነርሱም ቢሆኑ እንደ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ‹በደሞዛችን ከወር እስከ ወር መድረስ እንቸገር ነበር› ብለው ካልቀለዱ በቀር፣ እንዲህ አይነቱን ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቀውን ትምህርት ‹በሚከፈለን ደሞዝ ነው የምንሸፍነው› ብለው ሊከራከሩ አይችሉም፡፡ ሌላው የልጆቻቸው ባህር ማዶ መማር የሚያመላክተው ጉዳይ፣ የቀረፁት የትምህርት ፖሊሲ፣ የትምህርት ጥራትን ማዳከሙንና ለእነርሱ ልጆች አለመመጠኑን ነው፡፡ በርግጥ ይህ ቅስም ይሰብራል፤ ‹አስራ ሰባት ዓመት በዱር-በገደል ታግለን አሸንፈናልና፣ ለሀምሳ ዓመት ምርጥ ምርጡን ለእኛና ለልጆቻችን› የሚለው ራስ ወዳድነት ከፖለቲካ ብልሽውና በቀር ሌላ ስያሜ ሊሰጠው አይችልም፤ ለብዙሀኑ ኢትዮጵያዊ ድንጋይ ከመፍለጥ የማያስጥል ዲግሪን እንደ ፀበል መርጨቱም ቢሆን ትውልድን መግደል እንጂ ሀገርን በዕድገት ጎዳና የሚያራምድ ከቶም ሊሆን አይችልም (በነገራችን ላይ የዛሬ ሶስት ዓመት ‹‹ልጆቻችሁ ቻይና ምን ይሰራሉ?›› በሚል ርዕስ ከመለስ ዜናዊ ጋር አብረው መቃብር ባወረዷት ‹ፍትህ› ጋዜጣ ላይ በወጣ ፅሁፍ፣ ጥቂት የማይባሉ ባለስልጣናት ልጆቻቸውን ቻይና ልከው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ በአስተዳደርና መሰል ዘርፍ አሰልጥነው በወራሽነት የማስቀመጥ ዕቅድ እንዳላቸው ተገልፆ እንደነበረ ይታወሳል፤ አሁን ደግሞ አብዛኛዎቹ ልጆች ትምህርታቸውን በማጠናቀቃቸው በአፍሪካ ወጣቶች ማህበር ውስጥ ገብተው የአመራር ተሞክሮ እንዲቀስሙ እየተመቻቸላቸው መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮቼ ሰምቻለሁ፡፡ በተጨማሪም ከዚሁ ጋር ይያያዝ አይያዝ ባላረጋግጥም በዚሁ ዓመት ‹‹የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተር››ን በፓርላማ ለማፀደቅ ዝግጅቱ ተጠናቋል)

በሀገራችን ነባራዊ እውነታ አንገታችንን የምንደፋው ሚኒስትሮቻችን ባህር ማዶን፣ ቀን የከዳ ዕለት የሚወርሱት “ከናዓን” ማድረጋቸው ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የትኛውንም ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያነበሩትን ስርዓት አግልለው፣ በውጪ ሀገራት ገበያ መሸፈንን መምረጣቸውን ማወቃችንም ጭምር ነው፡፡ አቶ በረከት ስምዖን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› የሚለው መፅሀፉን ለማሳተም ኬንያ ድረስ መሄዱ የዚህ አይነተኛ ማሳያ ነው፤ ያውም በምረቃው ዕለት እንደተሰማው የህትመት ወጪውን ቱጃሩ ሼህ መሀመድ አላሙዲን ሸፍኖለትም ነው በዋጋ ውድነት ጭምር ጎረቤት ሀገርን መምረጡን አቃሎ የነገረን (አላሙዲ ግን ይህ ውለታው በምን ተካክሶለት ይሆን?)
መቼም ‹የዋጋ ንረቱን ያባባሰውን ስርዓት ማን ነው ያነበረው?› ለሚለው ጥያቄ የበረከትን ምላሽ መስማቱ ለብዙሀኑ ኢትዮጵያዊ አጓጊ ይመስለኛል፡፡

እንዲህ አይነት ጉዳዮች ናቸው የሰዎቹን ደንታ ቢስነትና የፖለቲካ ቁመራቸውን ወለል አድርገው የሚያሳዩን፡፡ ህመሙ አጥንታችን ድረስ ዘልቆ የሚሰማን ደግሞ በየቀኑ ‹‹በከፈልነው መስዋዕትነት ሀገሪቷን በዲሞክራሲ አጥለቀለቅናት፣ በኢኮኖሚም የተሻለ ደረጃ አደረስናት፣ አሁንም የታላቁ መሪያችንን ራዕይ አንግብን…›› ጂኒ ቁልቋል የሚለው ተራ ፕሮፓጋንዳቸውን ስንሰማ ነው፤ ምክንያቱም በአንደበታቸው ‹‹ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!›› እያሉ፣ በተግባር ግን ደግመው ደጋግመው ሸጠዋታልና (የመሬት ቅርምቱ /Land Grab/ አንዱ አስረጅ ነው)፤ የሆነው ሆኖ በጨነገፈ ህልም፣ በተሰበረ ቃል፣ በሸንጋይ አንደበት፣ በወረደ ሰብዕና፣ በሞተ ኢትዮጵያዊነት… ‹እንመራሀለን›
ማለታቸውን በቸልታ መመልከቱ ሀገርን ወደ ‹ተረትነት› እንዲቀይሩ የመፍቀድ ያህል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

እዚህ ጋ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ፣ የሰላምና ደህንነት ዋስትና ጥያቄ ላይ መውደቁ ነው፤ ምክንያቱም በብሔራዊ ስሜትና በሙስና የሚጠረጠር መንግስት ህዝብን ከጥቃት የመከላከል ገቱም ሆነ ንቃቱ በእጅጉ ዝቅተኛ መሆኑን ከመሰል ደካማ ሀገራት የታሪክ ድርሳናት መረዳት ይቻላል፤ ከጥቂት ሳምንት በፊት አልሸባብ በኬንያ፣ ‹‹ዌስት ጌት›› በተባለ የገበያ ማዕከል ካደረሰው ጥቃት ጋር ሙሰኞቹ የሀገሪቱ የደህንነት ኃላፊዎች እጅ እንዳለበት ከናይሮቢ ሾልከው ከሚወጡ መረጃዎች መሰማቱ ስጋታችንን ያጠናክረዋል፡፡ ‹ይህ አይነቱ ክህደት በሀገራችን ሰዎችስ ላለመደገሙ ዋስትና የሚሰጠው ማን ነው?› ለሚለው ጥያቄም በቂ መልስ ያስፈልጋል፡፡ እዚህም የአልሸባብ አባላት
ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች የኢትዮጵያና ናይጄሪያ እግር ኳስ ጨዋታ ዕለት የሽብር ጥቃት ሊፈፅሙ አቅደው እንደነበርና፣ ሆኖም ለተልዕኮአቸው ያዘጋጁት ፈንጂ በስህተት እጃቸው ላይ ፈንድቶ ማለቃቸውን መንግስት በይፋ መናገሩን እንደ ተጨባጭ ምሳሌ ወስዶ ተጨማሪ ጥያቄ ማንሳቱም አግባብ ነው፡- አሸባሪዎቹ ጅምላ ጨራሽ ፈንጂዎችን እንደታጠቁ የሀገሪቱን ድንበር አቋርጠው፣ የፍተሻ ኬላዎችን በቀላሉ አልፈው፣ ከደህንነት ሰራተኞች እይታ ተሰውረው፣ ቤት ተከራይተው ከሃያ ቀን በላይ ሴራቸውን ሲፈትሉና ሲገምዱ ማንተከታትሎ ደረሰባቸው? እንደተባለው በስህተት ራሳቸው ላይ አፈንድተው ሴራቸው ባይከሽፍስ ኖሮ? የጉዳቱ መጠን ምን ያህል ዘግናኝ ይሆን እንደነበር ማን በርግጠኝነት መናገር ይቻለዋል? ለወደፊቱስ ይህ አይነቱ እልቂት እንዳይከሰት ስለህዝቡ ደህንነት ግድ ኖሮት ‹ጋሻ መከታ› የሚሆነው ማን ነው?
ቁማርተኞቹ…
ከባለስልጣናቱ ዝቅ ስንል የምናገኛቸው ‹‹የፖለቲካው ስር ቁማርተኞች›› ደግሞ በመንፈስ ልዕልናቸው፣ በተሰጣቸው ክብር፣ በተናገሩት ቃል… የሚወራረዱ (የሚቆምሩ) ወንድም እህቶቻችንን ነው፡፡ በርግጥ ይህ በሽታ ይስተዋል የነበረው (ምንም እንኳ ‹ልንታሰር ስንል፣ ለጥቂት አመለጥን› በሚል ምክንያት ከሀገር ባይሰደዱም) በኪነት ባለሙያዎች ላይ ነበር (ሠለሞን ተካልኝ፣ ንዋይ ደበበ፣ አሊ ሚራህ፣ ቀመር የሱፍ… ከስርዓቱ ነቃፊነት ወደ አፍቃሪነት ተቀይረዋል) አሁን ደግሞ በአንድ ወቅት ‹‹ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን›› ለማስከበር ባሳዩት ቁርጠኝነት ያጀገናቸው ጋዜጠኞችም በተመሳሳይ መልኩ የኢህአዴግን ‹የለመለመ መስክ› ጥላ ከለላነት የሻቱ
ይመስላሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜው ክስተት እንኳን ብንነሳ የ‹‹አውራምባ ታይምሱ›› ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ አንዱ ማሳያ ሊሆነን ይችላል፡፡ ዳዊት ለመሰደድ የተገደደበትን ምክንያት አስመልክቶ ህዳር 23/2004 ዓ.ም ለንባብ በበቃችው ‹‹ፍትህ›› ጋዜጣ ከአሜሪካን ሀገር በስልክ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ‹‹ከሀገሬ እንድወጣ ያደረገኝ ይቅርታውን አንስተውና ሌላም ነገር አምጥተው ዕድሜ ልክ የሚያሳስር እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመራቸውን በተጨባጭ መረጃ ስላአገኘሁ ነው›› ብሎ ነበር፡፡ አሁን ታዲያ ወደ ሀገሩ የተመለሰው ምን ተአምር ተፈጥሮ፣ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ይሆን? ስር-ነቀል የአቋም ለውጥ ያደረገው ማን ነው? እሱ ራሱ ወይስ ስርዓቱ? እርግጥ ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣን ሳነብ ዳዊት የአቋም ለውጥ ማድረጉን በአርምሞ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ከአገሩ ሲሰደድ ‹‹ኢህአዴግ ይቅርታዬን አንስቶ እስር ቤት ሊከተኝ እንደሆነ መረጃ ደረሰኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት የለም፣ ስርዓቱ አፋኝ ነው…›› ሲል የኮነነውን አስተዳደር አስመልክቶ ለተጠቀሰው ጋዜጣ በሰጠው መግለጫ ‹‹በሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ የተሻሻለ መሆኑን›› ከገለፀ በኋላ፣ በዚህ ምክንያት ወደ ሀገሩ ለመመለስ መወሰኑን መግለፁ በበኩሌ እጅግ አስገራሚ የአቋም ለውጥ ሆኖብኛል፡፡ ለመሆኑ ለዳዊት የፕሬስ ነፃነት መከበር ማሳያው ምን ይሆን? እርሱ ከተሰደደ በኋላ በጉልበት እንዲዘጉ የተደረጉት ጋዜጣና መፅሄትስ? ሌላው ቀርቶ እስር ቤት ትቶት የሄደው ባልደረባው

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ እነለገሰ አስፋው እንኳ ያገኙትን ይቅርታ መነፈጉ ምን ሊባል ነው? …እነዚህና ሌሎች መሰል ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ካገኙ የዳዊት ሀገሩ መግባት ፀጉር የሚያስነጭ አይመስለኝም፡፡ በአናቱም ከሀገር ‹‹ከመሰደዱ›› በፊት ‹‹የኢህአዴግ ሰላይ ነበር›› የሚለው ውንጀላ ዘርን ያሰላ ፍረጃ ሊሆን ይችላል እንጂ እስከዛሬ ድረስ በማስረጃ የተደገፈ አይመስለኝም፡፡

ሌላው ዳዊት ቀደም ሲል ስለስርዓቱ አይረቤነትና አምባገነንነት የሰበከበትን የፖለቲካ አመለካከት በምክንያታዊነት ቀይሮ ‹የኢህአዴግ አስተዳደር ሀገሬን ይበጃል› ካለ መብቱ ነው፤ ቁማርተኛ የሚያስብለው ማዕተቡን ለባለሟልነት ከበጠሰ ነው፣ ብኩርናውን በምስር ወጥ ከለወጠ ነው፤ ያወግዘው የነበረውን የቁማር ፖለቲካ እሱም በተራው ለመተዳደሪያነት ከመረጠው ነው፤ ያቀነቅነው የነበረውን የፕሬስ ነፃነት ለ‹እህል-ውሃ› አሳልፎ ከሰጠ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ምንም እንኳ ጊዜ የሚፈታቸው ‹ምስጢረ-ዳዊት› ቢሆንም፡፡ እርግጥ ነው ‹ምስጢረ-ዳዊት› እስኪገለፅልን ድረስ በዚህ ዙርያ ብዙ ማለት አይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ክስተት ምን ጊዜም ጥያቄ ማስነሳቱ፣ ከፖለቲካም ጋር መያያዙና ግርታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ በዚህ መልኩ ከሀገር የተሰደዱ ሰዎች የደህንነት ሰራተኞች እንደጉንዳን የሚርመሰመሱበትን የቦሌ ተርሚናል አልፈው ሻንጣቸውን እየገፉ በሰላም ቤተሰቦቻቸውን ሲቀላቀሉ አይቼም ሰምቼም አላውቅም (በነገራችን ላይ በዛው ሰሞን አርከበ ዕቁባይም ወደሀገሩ መመለሱን ሰምቻለሁ፤ በአንድ አውሮፕላን አብረው ይመለሱ ወይንም ለየብቻ መሆኑን አላረጋገጥኩም) እናም ወዳጄ ዳዊት አንድም አሪዞናን ከመልቀቁ በፊት የድርጅቱን ‹ቡራኬ› ተቀብሏል፤ አሊያም አዲስ አበባ የገባው የትኛውም ባለሥልጣን ሳያውቅ እንደ ‹ነብዩ ኤልያስ› በእሳት ሰረገላ ተሳፍሮ መሆን አለበት፡፡ መቼም አበራ የማነና ታዬ ወልደሰማያት ለስራ ጉዳይ ከሀገር ወጥተው ሲመለሱ፣ ከዚሁ አውሮፕላን ማረፊያ የደህንነት ሰዎች ጆሮአቸውን አንጠልጥለው ለ15 እና 20 ዓመታት ከርቸሌ እንዲበሰብሱ ማድረጋቸውን ዳዊት አልሰማም ብዬ አላስብም፡፡ ይህ የአገዛዙ እውነተኛ ማንነት እንደሆነም ለእርሱ ይጠፋዋል ብዬ አላምንም፡፡ እናም ‹ዛሬም የሞራል ልዕልናዬን እንደጠበኩ ነው› (‹መናፍቅ አይደለሁም) ካለ፣ በአስር ሺህ ማይል ዕርቀት ላይ ሆኖ ‹የሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ ተሻሽሏል› ያለበትን አውድ አፍታቶ ማስረዳት የሚጠበቅበት ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም፡-

‹‹መንገድ ዓይኑ ይፍሰስ አይባልም ደርሶ የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ›› እንዲል አዳም ረታ፣ ዳዊት ሆይ፡- እንኳንም በሰላም ለሀገርህ አበቃህ!
እንደ መውጫ
ስርዓቱ የሚያራምደው ርዕዮተ-ዓለም የተሻለች ሀገር ሊፈጥር አለመቻሉ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት የታየ ቢሆንም፣ ዛሬም ፖሊሲዎቹንና ዕቅዶቹን የመከለስና የመፈተሽ ፍላጎት የለውም፤ የሀገርን ሀብትም ሆነ የህዝብን ጥቅም ለማስከበር ዝግጁነቱም ቁርጠኝነቱም የለውም፡፡ በርግጥ ፍርሃት ‹ሎሌ› ካደረጋቸው፣ ለሽሽት ካኮበኮቡ፣ የግል ጥቅማቸውን እያሰሉ በፖለቲካ ዥዋዥዌ ከሚያምታቱ… ‹ክቡራን› ሚንስትሮችም ሆነ ኃላፊዎች መልካም አስተዳደርን መጠበቅ ቂልነት ነው፡፡ ይህ አይነቱ እውነታም ነው በመሪዎቻችን ላይ በድፍረት ‹የፖለቲካው ስር ቁማርተኞች› የሚል ውግዘት እንድናሰማ የሚገፋን፡፡ የሆነው ሆኖ ‹የሚበላው ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል› እንዲል መረራ ጉዲና ‹ህዝብ›ን ደጋፊ ብቻ አድርጎ ማሰቡ ስህተት ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ቁልቁል ዘቅዝቆ ‹አራጋፊ› የሚሆንበት ታሪካዊ ጊዜ ይመጣልና፡፡

No comments: