Tuesday, November 5, 2013

አዲሱ የመከላከያ አዋጅ በአንድ ብሄር የበላይነት ላይ የተመሰረተውን አደረጃጀት አይቀይረውም ተባለ

November 5/2013

ጥቅምት ፳፭(ሃያ አምስት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የውጭ መከላከያ ደህንነት እንዲሁም የህግ፣ ፍትህ እና የአስተዳደር ጉዳዩች ቋሚ ኮሜቴዎች አባላት ሰሞኑን እንዲወያዩበት በተደረገው የመከላከያ አዋጅ 98 በመቶ የሚሆኑት ወታደራዊ አዛዦች ከአንድ ብሄር የሆኑበትን አወቃቀር እንደማይለውጠው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው መኮንኖች ተናግረዋል: የመከላከያ ሚኒስቴር ሹሞች በበኩላቸው አዋጁ እስከ ዛሬ የነበሩትን ህጎች ሁሉ የሚለውጥና መከላከያን የሚያሳድግ ነው ይላሉ።

ከማእረግ እድገት፣ ከመኖሪያ ቤትና ከሞት ቅጣት አፈጸጻም ጋር በተያያዘ ትኩረት እንዲደረግባቸው የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ቢጠይቁም፣ መሰረታዊ የሆነውንና የህወሀትን የበላይነትን የሚያረጋግጠውን በዘር ላይ የተመሰረተ አደረጃጀት እንዲቀየር ለመጠየቅ ወኔ አልነበራቸው ተብሎአል።

አዋጁ መከላከያን ከአገር ይልቅ የአንድ ፓርቲ አገልጋይ ሆኖ እንዲቀር የሚያደርግ ነው የሚሉት የውስጥ ምንጮች፣ በበረሀዎችና እና በሰው አገር የሚንከራተተውን ተራውን ወታደር የሚጠቅም ምንም ነገር የለውም ሲሉም ተችተዋል።

የጦር ሀይሎች ኢታማዦር ሹም ሌ/ጀኔራል ሳሞራ የኑስ፤ የምዕራብ ዕዝ የ44ኛ ዳሎል ክፍለ ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል ዘውዱ ፤ የ44ኛ ክፍለ ጦር ሁለተኛ ሬጅመንት ዋና አዛዥ ሊተናንት  ኮሎኔል አዘዘው መኮንን፤ በሱዳን የተመድ የሰላም አስካበሪ አዛዠ ሌተናልት  ጀኔራል ዮሀንስ ገብረመስቀል ተስፋማርያም፣ የሰሜን ዕዝ አዛዥ  ሌተናልት  ጀኔራል ሳእረ መኮንን  ፣ የማእከላዊ እዝ አዛዥ ሌተናት ጀነራል አበበው ታደሰ ፣ሜጀር ጀነራል ሞላ ገብረማርያም  እና አቶ ፀጋየ በርሄ በረቂቁ ላይ ውይይት አድርገው ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

ህጎቹ ከቻይና እና ከእራኤል ተወስደው የተሻሻሉ ቢሆንም መሰረታዊ የሆነው አወቃቀር እንዳይነካ መደረጉ ታውቋል።  የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤቱ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

No comments: