Friday, November 1, 2013

በባህርዳር ከተማ ከፍተኛ ፍተሻ እየተካሄደ ነው

October 31/2013
ጥቅምት ፳፩(ሃያ አንድ )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ምክንያቱ በውል ባይታወቅም ካለፉት 4 ቀናት ጀምሮ በከተማዋ ከፍተኛ ፍተሻ እየተካሄደ እንደሆነ የዘጋብያችን መረጃ ያመለክታል። በተለይ ዛሬ በከተማዋ መውጫና መግቢያ በሮች ላይ ሰዎች ከመኪናዎች እና ባጃጆች ላይ እንዲወርዱ እየተደረገ በጥብቅ ተፈትሸዋል።
አንዳንድ ወገኖች  መንግስት ጸረ ሰላም እና አሸባሪዎች በከተማዋ ገብተዋል የሚል ወሬ እንደሚያስወራ ሲገልጹ፣ ሌሎች ነዋሪዎች ደግሞ የከተማውን ህዝብ ለማስበረገግ ሆን ብሎ መንግስት የሚያደርገው ነው ይላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ እንደደረሰው አይነት የተቀነባበረ ፍንዳታ ሊከሰት ይችላል የሚል አስተያየቶች ይቀርባሉ።
የፌደራል ፖሊሶች በሚያካሂዱት ፍተሻ ህዝቡን እያንገላቱ መሆኑንም ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በጉዳዩ ላይ የከተማውን የፖሊስ አዛዦች ለማነጋገር ብንሞክርም አልተሳካልንም።
በአዲስ አበባ በቅርቡ የከሸፈውን ፍንዳታ በተመለከተ የመስተዳድሩ ፖሊስ ኮሚሽነር ይኸደጎ ስዩም ፣  የኢትዮጵያ መንግስት በህዝቦቹ ላይ ድራማ የሚሰራበትና የሚቀልድበት ምንም ምክንያት የለውም በማለት መናገራቸው ይታወቃል።
ኮሚሽነሩ ፍንዳታው ቅንብር ነው በማለት የሚናገሩትን ፖለቲከኞችንም ወቅሰዋል።
ዊኪሊክስ ይፋ ባደረገው መረጃ የአሜሪካ ኢምባሲ የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ የሽብር አደጋ አለ ለማስባል ፣ ሆን ብሎ ፍንዳታዎችን ያቀናብራል ብሎ እንደሚያምን መግለጹ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በባህርዳር አንድ የባጃጅ ሹፌር በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሎ ተገኝቷል። የቀበሌ 7 ነዋሪ የሆነው ወጣት አይኖቹ ወጥተውና በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድቦ ከቀናት በሁዋላ ነው ሞቶ የተገኘው። የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን በግድያው ዙሪያ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።

No comments: