Saturday, July 20, 2013

በረመዳን ጾም ሙስሊሙ ተቃውሞውን አጠናክሮ ቀጥሎአል

ሐምሌ ፲፪(አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስት በረመዳን ጾም ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የጀመሩት ተቃውሞ ይበርዳል የሚል እምነት የነበረው ቢሆንም፣ ተቃውሞው ከሳምንት ሳምንት እያየለ በመምጣቱ፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት በአንዳንድ አካባቢዎች የሀይል እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።

ከሀሙስ ጀምሮ በፌደራል ፖሊስ አባላት ክትትል ስር የነበሩት የወልድያ ሙስሊሞች በዛሬው እለት በመስጊዳቸው ውስጥ ታግተው መዋላቸውና አንዳንዶች መደብደባቸውን ሌሎች ደግሞ መታሰራቸው ታውቋል።

የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ሰላም መስጊድ ቅጥር ግቢ በመግባት ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ ወጣቶችን ደብድበዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወላጆች ደግሞ ከመስጊዱ እንዳይወጡ ታግተው ለሰአታት ቆይተዋል። ፖሊሶቹ ቀንደኛ ያሉዋቸውን ወደ 38 የሚጠጉ ሰዎችን አፍሰው የወሰዱዋቸው ሲሆን ከ30 ያላነሱት ሴቶች ናቸው። ከሰአት በሁዋላ የታገቱት ወላጆች ወደ ቤታቸው በሰላም እንደሚለሱ ተደርጓል።

በትናንትናው እለትም እንዲሁ 2 ወር ያልሞላት አራስ እናትን ጨምሮ ከ15 ያላነሱ ሙስሊሞች በፖሊሶች ተወስደው ታስረዋል።
ከፍተኛ ተቃውሞ በሚካሄድበት በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድም ረመዳን የሙስሊሙን ጉልበት ያዳከመው አልሆነም። በከፍተኛ ጩኸት “መሪዎቻችን ይፈቱ፣ አሸባሪዎች አይደለንም፣ መንግስት ራሱ ገዳይ፣ ራሱ ካስሽ፣ ሳይፈቱ ሰላም የለም፣ ኮሚቴው ይፈታ፣ አንድነን እኛ” የሚሉትን መፈክሮች አስምተዋል። ኢሳት ለመራጋገጥ ባይችልም በአንዋር የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ ከ10 በላይ ሰዎች ታስረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ቀስ በቀስ እየተቀጣጠለ የመጣው ተቃውሞ ያሰጋው የአውሮፓ ህብረት የልኡካን ቡድን ኢትዮጵያን መጎብኘቱ ይታወሳል። ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲዎች የጠሩዋቸው የተቃውሞ ሰልፎች በስኬት መጠናቀቃቸው ፣ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ እየተጠናከረ መሄድ እና የትጥቅ ትግል የሚያካሂዱ ድርጅቶች ጉልበት እያገኙ መምጣት ያሰጋቸው አንዳንድ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ኢህአዴግ የፖለቲካ ሜዳውን እንዲከፍት እየወተወቱት ነው። የዚህን አዲስ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በተመለከተ ኢሳት በቅርቡ እየተከታተለ መረጃውን ለህዝብ ይፋ ያደርጋል። በመንግስት በኩልም የቀድሞ የድርጅቱን ታጋዮች ለማሰባሰብ እና የፖለቲካ አንድነት ለመፍጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል።

No comments: