በፍሬው አበበ
ግንቦት 12 ቀን2000 ዓ.ም ከባለአደራ አስተዳደር ሥልጣኑን በመረከብ ሥራ የጀመረው ተሰናባቹ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይፈታል በሚል የበዛ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። የቀድሞ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላበተደጋጋሚ በሰጡዋቸው መግለጫዎች አውርተው የማይጠግቡት የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች በከተማዋ ሥር የመስደዱንጉዳይ ነበር። ወደሥልጣን ሲመጡም ሲሰናበቱም ይህ ወሬ ከአፋቸው አልተለየም። አንዳንዴ በከተማዋ ስለተንሰራፋው የመልካም አስተዳደርችግር፣ ሕዝቡም በዚህ ችግር የቱን ያህል እየተጎዳ፣ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን አስተዛዝነው ሲናገሩ እሳቸው በከንቲባነት ስለሚመሩትከተማ ሳይሆን ስለአንድ ራቅ ያለ አፍሪካዊ ከተማ የሚተርኩ ሁሉ ይመስሉ ነበር። እናም ይህ የመልካም አስተዳደር ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነትበእሳቸውም የሥልጣን ዘመን የሚያስታግሰው ሁነኛ መሪ ሳያገኝ እነሆ ለስንብት በቁ።
አቶ ኩማ ሰሞኑን በተካሄደውየአስተዳደሩ የመሰናበቻ ጉባዔ ላይ ባለፉት ዓመታት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት አስተዳደራቸው ያደረገው ጥረት ቢኖርም ለማሸነፍአለመቻሉን ተናዘውልናል። ንግግራቸውን እዚህ ላይ እንጠቅሳለን። “ባለፉት አምስት ዓመታት በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረው ሁሉበቀጣይ የማያቋርጥ ትግል የሚጠይቁ አራት ፈተናዎች እንደነበሩ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። አንዱና ትልቁ ችግር አሁንም ልማታዊ ዴሞክራሲያዊአቅጣጫችንን መሰረት አድርገን ርብርብ እያደረግን ቢሆንም የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ቁልፍ ማነቆ የመሆኑ ጉዳይ ነው።ይህ አስተሳሰብና ድርጊት በቁልፍ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ዘርፎቻችን መልኩን እየቀያየረ የሚከሰት በመሆኑ ምልዐተ ሕዝቡንየሚያሳትፍ የማያቋርጥ ትግል ማድረግን ይጠይቃል። በተለይ በመሬትና ግብር ጉዳዮች ላይ አተኩረን ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስወገድ ጥረትስናደርግ ብንቆይም በከተማችን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ተግባር የበላይነት የያዘበት ሁኔታ አልተፈጠረም።”
የቀድሞ ከንቲባ ኩማይቀጥላሉ። “በማስፈጸም አቅማችን ዙሪያ …በመዋቅራችን አዳዲስ ሰው ኃይል የማስገባት፣ ተከታታይ የአመለካከት ግንባታ የማካሄድ እናውጤታማ የለውጥ መሳሪያዎች አጠቃቀም የመፍጠር ሥራ ላይ አተኩረን አሠራርና አደረጃጀታችንን ለማሻሻል ጥረት ስናደርግ ብንቆይም የተደራጀየልማት ሠራዊት አልፈጠርንም።….”
አያይዘውም “የአገልግሎትአሰጣጥ የመልካም አስተዳዳር ግንባታ ማነቆ ነው። የችግሮቹ ዋንኛ ማጠንጠኛ ከላይ እስከ ያለው አመራርና ፈጻሚ የአመለካከት ፣የክህሎትእና የቁርጠኝነት መጓደል እንደሆነ ግልጽ ነው።….” በማለት ያስቀምጡታል።
በአራተኛ ደረጃ የከተማዋንሕዝብ የጎዳውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግር ሌላው ፈተና እንደነበር ይጠቅሳሉ።
እነዚህን ችግሮች ለመፍታትየአስተዳደሩ አካላት ጥረት ማድረጋቸውን ከመግለጽ ባለፈ መቼና የት ምን እንደተደረገ፣ በምን ምክንያትስ የእሳቸው ጥረት እንዳልተሳካበዝርዝር በንግግራቸው ላይ የጠቀሱት ነገር የለም። ከዚህም ባለፈ ይህ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ያንበረከኩትአመራር እንዴትስ አመኔታ አግኝቶ ሥልጣን ላይ ሊቆይ ቻለ የሚለውን ዝርዝር ምላሽን የሚሻ ነው። በእንዲህ ዓይነት ቁመና ላይ የከረመአስተዳደር ቢያንስ ለጥፋቶቹ ኃላፊነትን ለመውሰድ አለማሰቡም ያስገርማል።
አቶ ኩማ እንደከንቲባ
አቶ ኩማ ደመቅሳ አልፎአልፎ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው የሚሰጡዋቸው መግለጫዎች ያደመጠ ሁሉ የትኛውንም ዓይነት ችግር ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነትለደቂቃ ያህል አይጠራጠርም። አንደበተ ርቱዕ ናቸው። ችግሮቹን ነቅሰው ሲያስቀምጡ አድማጮችን ሁሉ አፍ ያስከፍታሉ። ችግሩ ግን አፈጻጸምላይ እሳቸውም ቢሆኑ ከባልደረቦቻቸው የተለዩ ሰው አለመሆናቸው ነው።
አንድ ሰማቸውን መግለጽያልፈለጉ ባለሃብት በአንድ ወቅት አቤቱታ ይዘው አቶ ኩማን በቢሮቸው ለማነጋገር ያዩትን ስቃይ እጅግ በማዘን ይናገራሉ። “አቶ ኩማንግግራቸውን በቴሌቪዥን ሰምቼ ቅንና አገር ወዳድ ሰው ናቸው በሚል አቤቱታዬን ለማሰማት ቢሮአቸው ሔጄ ነበር። በጣም የሚያስገርመውእንኳንስ አቤቱታ ማቅረብ ቀርቶ ቢሮአቸው አካባቢ መድረስ እንኳን አይታሰብም። ጥበቃዎች አያሳልፉም። አቤቱታ ካልዎት የጽ/ቤት ኃላፊውንያነጋግሩ ተባልኩ። እናም እንዲህ ዓይነት ራሱን ከሕዝብ ሰውሮ የተቀመጠ ከንቲባ ባለበት ከተማ ችግሮች ቢበዙ ምን ይገርማል” ሲሉይጠይቃሉ።
ሚዲያውን መሸሽ
አቶ አርከበ ዕቁባይእና የባለአደራ አስተዳደር አቶ ብርሃነ ደሬሳ በተሾሙ ማግስት በቅድሚያ ያደረጉት ከሚዲያው (ከመንግስትም ከግሉም) ጋር መተዋወቅነበር። በተለይ የአቶ አርከበ አቀራረብ “ነውጠኛ ነበሩ” በሚል መንግስት ክፉኛ ያወግዛቸው የነበሩ የግል ፕሬሶችን ሳይቀር የማረከእንደነበር የምናስታውሰው ነው። አቶ አርከበ በአጭሩ “የከተማዋ ጉዳይ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ነው። ተጋግዘን ከተማዋን እንለውጥ።የሚዲያ ባለሙያዎችም አግዙኝ” የሚል መልዕክትን ያዘለ ነበር። ይህ ከዚህ ቀደም እምብዛም ያልተሞከረ ቁርጠኝነት በእርግጥም ለአቶአርከበ ጠቅሞአቸው እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው። ከዚህ አንጻር ኩማ ሲመዘኑ ሚዲያን የሚሸሹ ሰው መሆናቸውን ቁልጭ ብሎ ይታያል።በሚጠሩዋቸው መግለጫዎች የሚጋበዙት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ብቻ ናቸው። ቢያንስ ከቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እና ከአሁኑጠ/ሚ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ትምህርት በመውሰድ ሁሉንም ሚዲያ በማሳተፍ ያሉትን የሕዝብ ችግሮች ምላሽ በመስጠት ረገድ መንቀሳቀስአለመቻላቸው ያስገርማል። በዚህ ረገድ አርአያ ሆነው ባለመገኘታቸውም በአዲስ አበባ በየእርከኑ የሚገኙ ሹመኞችና ባለሙያዎች በራቸውንለሚዲያ ለመክፈት ልዩ ትዕዛዝን ጠባቂ አድርገዋቸዋል። በዚህም ምክንያት በአስተዳደሩ መዋቅሮች ግልጽነት የሚባለው ነገር ከወሬ ማሳመሪያነትባለፈ ጥቅም ላይ መዋል አልቻለም።
ሲፈለግ ብቻ የሚጠራ ሕዝብን መፍጠራቸው
ምርጫ ሲቃረብ ወይንምየተለየ ከሕዝብ የሚፈለግ ድጋፍ ሲኖር ካልሆነ በስተቀር ሕዝብ ማሳተፍ የሚባለው ጉዳይ የወረቀት ላይ ጌጥ ነው። አቶ ኩማን ጨምሮሌሎች የአስተዳደሩ አካላት በዓመት አንዴም ቢሆን ከሕዝብ ጋር ከተሰበሰቡ ሕዝብን እንዳሳተፉ በመግለጽ ወሬውን ለሪፖርት ፍጆታ የመጠቀምነገር ጎልቶ ይታያል። ሕዝብን ማሳተፍ ሲባል ግን ስብሰባ መጥራት ብቻ አይደለም። በእያንዳንዱ የአስተዳደሩ ውሳኔ ውስጥ አሻራውእንዲኖር ማድረግ መቻል ማለት ነው። ሕዝብን በየዕለቱ ማዳመጥ ኑሮውን መኖር ማለት ነው። በዚህ ረገድ ተሰናባቹ አስተዳደር ሲመዘንእዚህ ግባ የሚባል ታሪክ ያለው አይደለም። ከምንም በላይ ደግሞ ለይስሙላ በሚጠሩ መድረኮችም ላይ ቢሆን አባል፣ደጋፊ እየተባለ ሰዎችንለያይቶ የመጥራቱ ነገር አሁንም ሰፊ የህዝብ ድጋፍና ተቀባይነትን ከማግኘት አንጻር ጉድለቱ ግዙፍ ነው።
የተዘነጋው ሰብዓዊ ልማት
የመንገድ፣ የባቡርናሌሎች የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የሚካሄዱ ግንባታዎች ለከተማዋ ዕድገት ቁልፍ ሚና ቢኖራቸውም ለከተማዋ ሕዝብ የሰብዓዊልማት የተሠጠው ቦታ አናሳ መሆን አንዳንዴ ከፈረሱ ጋሪው ማሳባሉ አልቀረም። ዛሬም የሕግ የበላይነት በመጥፋቱ ብዙ ዜጎች ፍትህፍለጋ ውድ ጊዜያቸውን በመንከራተት ያሳልፋሉ። ከአድልዎና ኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ ሲቪል ሰርቪስ ባለመኖሩ ዜጎች በየቢሮው የፍትህያለህ እያሉ ሲንከራተቱ፣ መንግስትንም ሲረግሙ የማየት ጉዳይ እምብዛም እንግዳ ነገር አለመሆኑን ለመታዘብ ለደቂቃዎች በአዲስአበባማዘጋጃ ቤት የአገልግሎት መስጫ ቢሮዎች ብቅ ማለት ብቻ ይበቃል።
ዜጎች በሕገመንገስቱበተሰጡዋቸው መብቶች መሠረት የመሰብሰብ፣ የመደራጀት መብቶቻቸው አሁንም በአስተዳደሩ ይሁንታ እስካላገኙ ድረስ የሚሞከር አይደለም።እናም ሰብዓዊ ፍላጎቱ ያልተሟላ ሕዝብ ይዞ ስለልማት እመርታ ብቻ ማውራት በአንድ እጅ እንደማጭብጨብ ይቆጠራል።
የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደርአዲሱ ካቢኔ እነዚህን የተከማቹ የህዝብ ችግሮች ወደታች ወደሕዝቡ ወርዶ የመፍታት ታሪካዊ ኃላፊነትም ጭምር ይጠብቀዋል። ይህን ኃላፊነትበብቃት መወጣት ከቻለ በርግጥም ሕዝብ የሚረካበትን ለውጥ ማስመዝገብ ይችላል። አለበለዚያም እንደነአቶ ኩማ ችግሮችን በመናገር ብቻጊዜውን በልቶ በኪሳራ መሰናበቱና ሕዝብና መንግስትንም ማራራቁ የማይቀር ይሆናል።n (ምንጭ፡-ሰንደቅጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 409 ረቡዕ ሐምሌ 03/2005)
No comments:
Post a Comment