Monday, July 22, 2013

በቂሊንጦ የሚገኙ እስረኞች በሞት አፋፍ ላይ እንገኛለን አሉ

ሐምሌ ፲፭(አስራ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእነ አቶ ተሻለ በካሻ መዝገብ ተከሰው ከሁለት አመታት በላይ በእስር ቤት የቆዩት እስረኞች ሰሞኑን ከፍተኛ ድብደባ ከተፈጸመባቸው በሁዋላ ለተከታታይ ቀናት ምግብ ባለመመገባቸው ህይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁን በመግለጽ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስላቸው አቤት ብለዋል።

እስረኞቹ በጻፉት ደብዳቤ ላይ  ከውጭ የመጡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በፌሮ ክፉኛ እንደደበደቡዋቸውና ህክምና በማጣታቸው ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ፍርድ ቤት በቀጠሮአቸው ቀን እንዳይቀረቡ መከልከላቸውን ለመቃወም ለበላይ አካላት ደብዳቤ በመጻፋቸው ምክንያት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የገለጹት እስረኞቹ ፣ ጉዳዩን ለቂሊንጦ ዋና አስተዳዳሪ ኦፊሰር አምባየ ስናመለክት ” እስከ መግደል ድረስ እርምጃ ለመውሰድ መብት አለን፣ አርፋችሁ ካልተቀመጣችሁ በጥይት እንቆላችሁዋለን፣ የምግብ ማቆም አድማ እናደርጋለን ብትሉም ለእኛ ደንታችን አይደለም”  በማለት እንደመለሱላቸውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እየተዛተባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። ለ4 ቀናት ምግብ ማቆማችንን ተከትሎ ማንም ስላልጠየቀን በሞት አፋፍ ላይ እንገኛለን ያሉት እስረኞቹ የኢትዮጵያ ህዝብ እና የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ እገዛ እንዲያደርግላቸውም እስረኞቹ  ተማጽነዋል።

ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው ህክምና ከተከለከሉት መካከል ቀጀላ ገላና ገቢሳ፣ በላይ ኮርሜ ባይሳ፣ መንግስቱ ግርማ አየሳ፣ ተፈራ ቀበኔ ገመቹ፣ ሙላት ሽመልስ እጀታ፣ ኢብሳ አህመድ ሙሀመድ እና ሸምሰዲን የተባሉት ሲገኙበት ፣ ድብደባ ከተፈጸመባቸው መካከል ደግሞ ሌሜሳ ዲሴሳ፣ አለሙ ተሾመ ቦኬ፣ ዘርፉ መልካ አባይ፣ ቀበታ ገቢሳ ነባራ፣ ቀበና ነጋሳ ነገራ፣ መልካሙ መገርሳ፣ አዳሙ ሽፈራው፣ ቡልቻ ሱሪሳ ጌታቸው አብራ ቶሎሳ፣ ስለሺ ሶሬሳ፣ የፓርላማ አባል የነበረው ጉቱ ወልዴሳ፣ አለማየሁ ቶሎራ፣ በርሲሳ ሊሙ፣ ብርሀኑ እምሩ፣ ኡርቄና አጀማ፣ አህመድ አብደላ ጎዳ እና ለማ በዳዳ ይገኙበታል።

በኦነግ ስም በሽብረተኝነት ወንጀል የተከሰሱት እስረኞች ያቀረቡትን ተማጽኖ ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚገኘውን ቀይ መስቀል ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግ የድርጅቱ ስልክ አይነሳም። የታራሚዎች ፍትህ አስተዳዳር ዳይሬክተር ለሆኑት አቶ ብርሀኔ ሀይለስላሴ  ስልክ ብንደውልም፣ ስልካቸው ቢጠራም አይነሳም።

ኢሳት በእስረኞች ላይ የደረሰውን ድብደባ ተከትሎ አካባቢው በደም በመበከሉ እንዲታጠብ መደረጉን መዘገቡ ይታወቃል። የቂልንጦ እስር ቤት ዋና ሃላፊ በቅጽል ስሙ ሻቢያ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በእሰረኞች ላይ መፈጸሙን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

No comments: