Wednesday, October 21, 2015

ሶማሊያ የሚገኙ የጦር ሠራዊት አባላት ሲበደሉ ያመናል !

October 21, 2015
def-thumbየተባበሩት መንግሥታት ማኅበር የሚሰጠው ገንዘብ ህሊናቸውን በሰወራቸው፤ የህወሓት አባላት በሆኑ ጄኔራሎች አዝማችነት ሶማሊያ የገባው ኢትዮጵያዊ ድሃ ወታደር እጣ ፈንታ በጣም አሳዛኝ ደረጃ ላይ ደርሷል። በየእለቱ ኢትዮጵያዊያን ወታደሮች እየተገደሉ፤ አስከሬናቸው በጎዳናዎች እየተጎተተና እየተቃጠለ ነው። ሶማሊያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ወገኖቻችን ናቸውና በእነርሱ ላይ የሚደርሰው ስቃይ ይሰማናል፤ ሲበደሉ ያመናል፤ ጭንቀታቸው ይጨንቀናል። ወገኖቻችን ናቸውና የደህንነታቸው ጉዳይ ያገባናል።
የህወሓት ጄኔራሎች ሙሉ ትኩረታቸው ያለው በእያንዳንዱ ወታደር ስም ከተባበሩት መንግሥታት በሚያገኙት ገንዘብ መጠን ላይ ነው። ለሶስት ሣምንታት ብለው የገቡበት ጦርነት እነሆ አስር ዓመታት አስቆጥሯል። አንዱ የገቢያቸው ምንጭ ነውና ጦርነቱ ለሌላ አስር ዓመታት ቢራዘም ለእነሱ ደስታቸው ነው። ኢትዮጵያዊው ምስኪን ወታደር ግን አዛዦቹ እንዲያልቅ በማይፈልጉት ጦርነት ውስጥ ገብቶ መስዋዕትነት ይከፍላል፤ ሲወድቅ የሚያነሳው የለም፤ መስዋዕት ሲሆን የክብር አሸናኘት የለውም፤ ቤተሰቦቹም ይኑር ይሙት አያውቁም። ይህ ሁላችንንም ሊያስቆጣ የሚገባ ግፍ ነው።
ኢትዮጵያን ለመታደግ ብሎ የዘመተን ወታደር ስለኢትዮጵያ ግድ በማይሰጣቸው፤ ጥቅማቸውን ብቻ በማሳደድ ላይ ያሉ አዛዦች ቸልተኝነት ምክንያት ለስቃይ፣ ሰቆቃና ውርደት መዳረግ የለበትም። በሶማሊያ በሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ የሚደርሰው በደል በሁላችም ላይ የደረሰ በደል ነው፤ በእነርሱ ስብዕና ላይ እየደረሰ ያለው ውርደት በአገራችን ላይ የደረሰ ውርደት ነው።
የጦሩ አዛዦቹ በወታደሩ ስቃይና ሞት ከብረው የከተማ ድሆችን እያፈናቀሉ ሕንፃዎችን እየገነቡ፤ የባንኩን፣ የኢንሹራንሱን፣ የገቢና ወጪ ንግዱን እያጧጧፉ ነው። የወታደር ልብስ ቢለብሱም፤ “ጄኔራል እከሌ” ተብለው ቢጠሩም በተግባር መጥፎ ነጋዴዎች እንጂ ወታደሮች አይደሉም። እነዚህ የስም ጄኔራሎች በጦርነት ውስጥም የሚታያቸው ንግድና ገበያ ነው። በእንደነዚህ ዓይነቶች አዛዦች ተመርቶ ጦርነትን ማሸነፍ አይቻልም።
አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በህወሓት የጦር አዛዦች ብቃት ማነስ፣ ስግብግብነትና ቸልተኝነት ሳቢያ በሶማሊያ እየሞቱ፣ እየቆሰሉ፣ አስከሬናቸው እየተዋረደ ስላለው ኢትዮጵታዊያን የሚሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል።
ከሶማሊያ ውጭም የኢትዮጵያ ወታደር የሚገኝበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው። በተለይም በሀገር ውስጥ የኢትዮጵያ ወታደር እንደ ስሙ “የአገር መከላከያ ሠራዊት” በመሆን ፋንታ ወገንን ማጥቂያ ሠራዊት እየሆነ ነው፤ አገርን በመከላከል ፋንታ ወገንን ማጥቃት የሠራዊቱ የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል። ለዚህ አሳፋሪ ተግባር ሠራዊቱ ራሱ መላ ሊፈልግለት ይገባል።
አርበኞች ግንቦት 7 እየታገለ ያለው ሠራዊቱን ከሚገኝበት ከዚህ አሳፋሪ ሁኔታ ለማውጣትም ጭምር ነው። ሠራዊቱ የአዛዦቹ መገልገያ መሣሪያ መሆኑ ማብቃት አለበት። ሠራዊቱ ወገንን ማጥቂያ መሆኑ ማክተም አለበት። ሠራዊቱ ወደ ውጭ አገራት ለግዳጅ ሲላክ ተገቢውን ክብር ሊሰጠው፤ ጥቅማ ጥቅሞቹም ሳይሸራረፉ ሊያገኝ ይገባል። የሠራዊቱ አባላት እየደኸዩ፣ ቤተሰቦቻቸው እየተራቡና እየታረዙ አዛዦቹ በሀብት ላይ ሀብት የሚያጋብሱበት ሁኔታ ማብቃት አለበት። ይህ አዋራጅ የሠራዊት አያያዝ መቀየር አለበት፤ መቀየር ደግሞ ይቻላል።
እያንዳንዱ የሠራዊት አባል በግል የጠራ ፀረ-ህወሓት አገዛዝ አቋም ይያዝ፤ ከሚመስሉት ወዳጆቹ ጋር ውስጥ ውስጡን ይምከር፤ አርበኞች ግንቦት 7 ጋር የምስጢር ግኑኝነት ለመመስረት ይጣር፤ ጦሩ ውስጥ እያለ ሥርዓቱን የሚዳክሙ ተግባራትን ይፈጽም። ህወሓትን ለማዳከም የሚደረግ ጥረት ትንሹም ትልቅ ዋጋ አለው። ሠራዊቱ የህወሓት መገልገያ አለመሆኑ ማስመስከሪያ ወቅት አሁን ነው። የህወሓት አምባገነን አገዛዝን ከውስጥም ከውጭም ሆነን እንፋለመዋለን፤ እንደምናሸንፍ ጥርጥር የለውም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

No comments:

Post a Comment