October 23, 2015
በድንገት ከያለንበት ተይዘን እንደታሰርነው አፈታታችንም ግራ የሚያጋባ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ክሶች ቀርበውብን እያለ ግማሾቻችን ‹ክስ ተቋርጦላችኋል› ተብለን ተፈታን፣ ግማሾቻችን ደግሞ ‹ነፃ ናችሁ› (ከሳሽ በነፃነታችን ላይ ይግባኝ መጠየቁ እንዳለ ሁኖ) ተብለን ይሄው ወጥተናል፡፡ ቀሪ ክስ ይዘን በዋስ ወጥተን እየተከራከርንም ያለን አለን፡፡ በዚህ ሁሉ መሃል የሁላችንም ዕምነት ግን አንድም ቀን ሊያሳስረን የሚገባ ወንጀል አለመፈፃችን ማመናችን ነው፡፡ መፈታታችን ጥሩ ሁኖ፤ መታሰር በፍፁም የማይገባን ነበርን፡፡ መፃፋችን እና ሕግ እንዲከበር መጠየቃችን ሀገሪቱ አገራችን እንድትሻሻል እና ሁላችንም ዜጎች የተሻለ ህይወት አንዲኖራቸው ከመሻት ባለፈ ሌላ ነገር አልነበረውም/የለውም፡፡ ነገር ግን ይህን በማድረጋችን ተገርፈናል፣ ተዘልፈን-ተሰድበናል፣ ታስረናል ተሰደናልም፡፡ ይህ በፍጹም አይገባንም ነበር፡፡
የእኛ መታሰር ፖለቲካዊ ንቃት የፈጠረላቸው ሰዎች እንዳሉ ሲነግሩን ደስ ይለናል፡፡ በእኛ መታሰር ምክንያት ለመጠየቅና ለመፃፍ በጣም እንደሚፈሩ የሚነግሩን ሰዎች ስናገኝ ደግሞ እናዝናለን፡፡ የመታሰራችን ጉራማይሌ ስሜት እንደዚህ ነው፡፡ ሳይገባን በመታሰራችን የነቁ መኖራቸውን በማወቃችን የምነደሰተውን ያክል፤ ሳይገባን በመታሰራችን የተሰበሩና ከተዋስኦ መድረኩ የራቁ እንዳሉ ስናውቅ እጅግ እናዝናለን፡፡
መታሰር በደል ነው፡፡ ብዙ ነገር ያጎድላል፡፡ መታሰር መልካም ነው፡፡ ብዙ ነገር ያስተምራል፡፡ እኛ በመታሰራችን ሀገራችን የበለጠ እንድናውቃት ሁነናል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ነፃነት አሁንም ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል ተረድተናል፡፡ ሕግን መከታ አድርገው የኖሩ ‹ስም የለሽ› ዜጎች ሕጉ ሲከዳቸውና እነሱ ላይ ‹በላ› ሲያመጣባቸው ታዝበናል፡፡ ከሁሉም በላይ ፍትህ የሌለባት ሀገር ለዜጎቿ የማትመችና አገር እንደሆነች አይተናል፡፡
በእስራችን ወቅት የተለያዩ በደሎች በተቋም ደረጃ ደርሰውብናል፡፡ ግን አገር ነውና ከይቅርታ የሚያልፍ አይደለም፡፡ ለበደላችሁን አካላት እናንተ ይቅርታ ባትጠይቁንም፤ እናንተ የፈለጋችሁትን ባለማድረጋችንና ሕግን መሰረት አድርገን በመኖራችን ስላስከፋናችሁ እባካችሁ ይቅር በሉን፡፡
በዚህ ሁሉ መሃል ግን እናንተ አላችሁ፡፡ ጓደኞቻችንም ናችሁ፤ ዘመቻ አድራጊዎችም ናችሁ፤ ቤተሰቦቻችንም ናችሁ፤ ጠያቂዎቻችንም ናችሁ፤ ጠበቆቻችንም ናችሁ፣ የመንፈስ አጋሮቻችንም ናችሁ ርቀት ሳይገድባች የጮሃችሁልን አለም አቀፍ የመብት ጠያቂዎችም ናችሁ … በመታሰራችን የተረዳነው አንዱ ትልቅ ነገር የናንተን መልካምነት፣ የናንተን አጋርነት እና የናንተን የማይሰለች ድካምና ፍቅር ነው፡፡ እናንተ ባትኖሩ ‹አጭሩ› የእስር ጊዜያችን ይረዝምብን ነበር፤ ‹ቀላሏ› እስር ትከብድብን ነበር፡፡ ምስጋና ለናንተ፤ እስራችን ‹አጭር› – ፈተናችን ‹ቀላል› እንዲሆን አድርጋችሁልናልና፡፡
እናንተ ወዳጆቻችን ለሁሉም ነገር – እልፍ ምስጋና
እናመሰግናለን!
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች
የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች
No comments:
Post a Comment