August 17,2015
የኢህአዴግ ስርዓት በአለፉት 24 ዐመታት ያዋቀራቸው ወታደራዊና የፀጥታ ኃይሎችን ተጠቅሞ የሰፊውን ህዝብ ነፃነት መግፈፍ፤ ውስጥ ለውስጥ የማይስማሙትን ማሰርና መግድል ካለምንም የርዕዮተ-ዓለም መሰረት የሚካሄዱ ከውጭ ኃይል ጋር በጥቅም በመተሳሰር በህዝባችን ላይ ዘመናዊ ባርነት እንዲፈጸም ሆን ብሎ እየተንቀሳቀሰ ነው።
የወያኔ ኢህአዴግ የመንግስት መከላከያ ሃይል፤ የፀጥታውና የፖሊሱ አወቃቀር ካለውጭ ዕርዳታና ምክር እንዲሁም ስልጠና በራሱ ኃይል የተደራጀ የሚል ሰው ካለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን እንደሚካሄድ አያውቅም ማለት ነው። ስለዚህም ለነፃነት የሚደረገው ትግል ብዙ የማይታሰቡ ጥያቄዎችን ይዞ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን በአንድ አገዛዝ መገርሰስ ወይም መወገድ ብቻ አንድ ህዝብ ነፃነቱን ሊቀዳጅ እንደማይችል ከብዙ አገሮች ታሪክ የምንማረው ሀቅ ነው።
በተለይም ያለፈውን የሰላሳና አርባ ዐመታት የህዝቦችን የነፃነትና የዴሞክራሲ ትግል ስንመለከትና ስናጠና በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም አገሮች የህዝብ ነፃነት ተግባራዊ ሊሆን ያልቻለው የአብዛኛው ህዝብ ጥያቄ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ በሆነ መንገድ መፈታት ስላልተቻለ ብቻ ነው።
አንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ ካፒታሊዝም ከተስፋፋና የበላይነትን ከተቀዳጀ ወዲህ ጭቆናዊ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊስፋፋና አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በወታደራዊ ሃይል ስር በመዋላቸው ምክንያት በዓለም አቀፍ የጭቆናና የአፈና ሰንሰለት ውስጥ ገብተው ለስቃይ እንዲፈረዱ ግድ ሆኗል።
የጥሬ-ሀብት ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ይህንን የተትረፈረፈ ጥሬ ሀብታቸውን እያወጡ በስርዓት ለመጠቀም፤ ህዝቦቻቸውን ከድህነት በማላቀቅ ስነ-ስርዓት ያለው ኑሮ ለመገንባትና ህዝቦቻቸውን ለማስከበር ያልቻሉት ከላይ በተዘረዘረው የወታደራዊና የስለላ የጭቆና ሰንሰለት ውስጥ ስለተካተቱና በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊዝም የብዝበዛ አስተሳሰብ ውስጥ ተቀነባብረው ሀብታቸውን በስርዓት እንዳይጠቀሙ ስለተደረጉ ነው።
በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የተዋቀረው የመንግስት አሰራር በመሰረቱ የህዝቦች አለኝታና የሀብት ፈጣሪ መሳሪያ ወይንም መንገዱን የሚቀይስ ሳይሆን ድህነት እንዲስፋፋና ሁሉም ዜጋ በስርዓቱ ስር ሆኖ እንዲገዛና አስከፊ የኑሮ ሁኔታ እንዲያሳልፍ ነው የሚደረገው።
በሳይንስና ምንም አይነት ፍልስፍና ባልተከተለ መንገድ የተዋቀሩ የመንግስታት አሰራሮች፤ ስነ-ምግባርና ሞራል የጎደላቸው ማህበራዊ ህብረተሰባዊ፤ ባህላዊና ታሪካዊ ኃላፊነት በሚያሸክም መንገድ ስላልተቀመጡ ሁሉም ነገር በተራ ታዛዥነት እንዲፈፀም ምክንያት ሁኗል።
ወደ አገራችንም ስንመጣ የስርዓቱ የአሰራርና የአወቃቀር ስርዓት ከተቀሩት የአፍሪካ አገሮች እምብዛም የሚለይ ሳይሆን የባሰ መሆኑን የሚያከራክረን አይደለም። አንድ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው ይህ ዐይነቱ እንደሰንሰለት የተያያዘ የጭቆና አገዛዝ ለዕውነተኛ ነፃነት እጦት ዋናው ምክንያት እንደሆነና የድህነትንም አፍላቂና የተስተካከለ ዕድገት እንዳይኖር የሚያግድ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ሲገባ ብቻ ለነፃነት የሚደረገው ትግል የተቃና ይሆናል።
በሌላ አነጋገር ለዕውነተኛ ነፃነት እታገላለሁ የሚል ሁሉ አገራችን ውስጥ ላለው ፀረ ህዝብ ስርዓትና የአብዛኛዎችን የአፍሪካ አገዛዞች አወቃቀር በሚገባ መገንዘብና ከዚህ በመነሳትም እስካሁን በተካሄደው የትግል መንገድ ዕውነተኛውን የህዝብ ነፃነት ማምጣት እንደማይቻል መረዳት ይኖርበታል።
ዴምህት
ዴምህት
No comments:
Post a Comment