August 16, 2015
ሻለቃ አብርሃም ታከለ
በረጅሙ ዘመን ታሪካችን ኢትዮጵያዊነትንና ብሄራዊ ስሜታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች መከሰታቸዉ ተስተዉሏል። ይህ አባዜ ዛሬም ድረስ አልተወንም።
ባዕዳን ወራሪዎች ካደረሱብን መከራና በደል ይልቅ ይበልጥ አድቅቆን የነበረዉ በአገዛዝ ስም ወገኖቻችን የሚጭኑብን ኢ-ሰብአዊ የሆነ የግፍ ቀንበር መሆኑን አንስተዉም። ከእኛ በፊት የነበሩት ኢትዮጵያዉያን እንዲያ ሆነዉ አልፈዋል። በደም በአጥንታቸዉ ዋጅተዉ ባቆሙት ነፃነት ላገር እንደእንግዳ ለወገን እንደባዳ ተቆጥረዉ በነፃነትና በባርነት መካከል ባለዉ ድንበር መሃል ሲታሹ ለእፎይታ ሳይበቁ ተሰናብተዋል።”እምሽክ ድቅቅ አርጎ እኔን ከበላኝ ነጭ ጅብ ጥቁር ጅብ ምን አስመረጠኝ ” እስከማለት መድረሳቸዉም በዚህ የተነሳ ነዉ።
ይህንን እያንጎራጎሩ ኖረዉ ይኸዉ ወደ መቃብር ወርደዋል። ይህ ለመሆኑ እርግጥ ነዉ። ተረትም አይደለም የተፈፀመ እዉነት። “እናት ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የተባለዉም በአብዛኛዉ ሕዝብ ስቃይና ሞት ጥቂቱ ተንደላቃቂና ፈላጭ ቆራጭ ስለሆነ ነዉ። ይህን ያሉትም እኒያዉ ለአገር አንድነትና ሉአላዊነት ዉድና ተተኪ የማይገኝለትን ሕይወታቸዉን ቤዛ ያደረጉና አካላቸዉን ያጎደሉ ሃቀኛ ዜጎች ናቸዉ። ይህ ግፍ በሕዝቡ ላይ ተፈጽሟል። ይህ ሁሉ አበሳና መከራ በሕዝቡ ላይ ደርሷል። ይሁን እንጂ ይህች አገራችን ታላቅ ከመባል የተዛነፈበት እስከቅርብ ግዜ ድረስ የለም። ሕዝቡም ቢሆን አገሩን አሳልፎ የሰጠ የሚል አሳፋሪ ስም በታሪክ አልተፃፈበትም።ረሃብ ድርቅ ድህነት ቢፈታተነዉም የነፃነት ሸማዉን ሳያስገፍፍ የአገሪቱን ሉአላዊነት አስከብሮ ኢትዮጵያዊነትን አዉርሶ ወር ተራዉን ጨርሶ አልፏል። መቸም ቢሆን የሕዝብ ዋና ኩራት በዜግነት መተማመን ነዉ። ይህን መተማመን ያጠነከረ ሕዝብ ለማናቸዉም ምድራዊ ሃይል ተንበርካኪ አይሆንም። በኢትዮጵያዊነት የማመን ጥኑ ማተብ ነዉ።የኢትዮጵያ ሕዝብ ቋንቋ ባሕልና የተለያየ እምነት ሳይከፋፍለዉ በአንድነትና በመተሳሰብ እንዲዘልቅ ያስቻለዉ። የትግራይ ነፃ አዉጪ የነፍሰገዳዮች ቡድን አገዛዝ ይህን የተከበረ የጀግንነት ኩራት ሊነጥቀን እየዳዳ ነዉ።
በዚያ ነዲድ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ላይ በረዶ ሊሞጅርበት ሌት ተቀን እየደከመ ነዉ። ከሁሉ በፊት ኢትዮጵያዊነትን ማሰብና ማስቀደም የቀድሞ ሥርአት ናፋቂ ሽብርተኛ ትምክህተኛ እያሰኘ ነዉ። ኢትዮጵያዊነት ነፍጠኛነት ከሚል የተሳሳተ የዘረኝነት ድምዳሜ ላይ እያደረሰ ነዉ። ኢትዮጵያዊነት ሁሉም ብሄረሰቦች የሚጠለሉበት አንድ ጃንጥላቸዉ ሆኖ እንዲዘልቅ የምንመኘዉን ያህል በዜግነት የመተማመን ስሜት እንደጠላ ቂጣ እለት ከእለት እየተሸራረፈ በጊዜ ሂደት ዉስጥ ተሟጦ እንዳያልቅና ጭራሹን እንዳይጠፋ የተቆርቋሪዎች ስጋት ከሆነ ሰንብቷል።
በመናወዝ ላይ የሚገኘዉ ይህ ትዉልድ ስለኢትዮጵያዊነትና ስለብሄራዊ ስሜት ጭብጥ እንስጥህ ቢሉት “አቦ ተወን….አትደብረን! ቢል አይፈረድበትም። ይህን በማለቱ ሊወቀስም ሊነወርም አይገባም። ለእርሱ ኢትዮጵያዊነት ጦርነት ስደትና ሞት ሆኖ ነዉ የሚታየዉ። ለእርሱ ኢትዮጵያዊነት ቀይ ሽብር ነጭ ሽብር ሆኖ ነዉ የሚቆጠረዉ። ለእርሱ ኢትዮጵያዊነት የእትብት አፈር ክልል አብሮ ማደግ፣ጎሰኝነትና ይህን ሃሳብ የማይቀበለዉን ወገን ማሰደድ ማፈናቀል ማሰርና መግደል ሆኖ ነዉ የሚታሰበዉ።
በዘመናችን አገርና ትዉልድ እሳትና ጭድ ሲሆኑ ተመልክተናል። ተካፋይም ሆነናል። የሃይማኖት አባቶች የመልካም ሥነ ምግባርን ትምህርት በመስጠት ፋንታ ከአምባገኖች ጋር ወግነዉና በዘር ተደራጅተዉ በመንፈሳዊ ሳይሆን በአለማዊ ሕይወት ዉስጥ ሲዳክሩ እያየን ነዉ።
አድርባይነትንና ጎሠኝነትን ተፀይፎ እዉነትን መቀበል አለመቻል ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ሳይሆን እኔነትን ፈልጎ ለማግኘት አለመፍቀድ ይሆናል። በቅድሚያ ኢትዮጵያዊነት የዜግነት ስሜት። ከዚያ እኔነት።
የስነ ልቡና ጠቢባን ራስን ለማወቅ በጠቀሱት ቁም ነገር “አንተነትህ አንተ እስከምታዉቀዉ ድረስ ነዉ” ይላሉ እኛም እንደዚያዉ ነን። የምናዉቀዉ ይህንኑ ነዉ። የምናሳድገዉም፤ ለትዉልድ የምናስተላልፈዉም ይህንኑ ነዉ። ኢትዮጵያዊነትን።
ይህ ሳይሆን ሲቀር ዘዋሪ እንደሌለዉ ካሚዎን ነዉ የምንሆነዉ። ሁላችንም ጠፍተን አገርም ዜጋም። እና ሁላችንም ተፈላላጊ ሆነን። አገርን ወይንም ኢትዮጵያዊነትን ያየህና ወዲህ በለኝ! እንደሚባለዉ ዓይነት። መሆኑ ነዉ።
No comments:
Post a Comment