Tuesday, May 6, 2014

አንድነት ፓርቲ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረገ! (ቪዲዮ እና ፎቶዎች ይዘናል)

May5/2014
(ኢ.ኤም.ኤፍ) – ዛሬ ሜይ 4 ቀን፣ 2014 ዓ.ም. የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። የሰላማዊው ሰልፍ ጥሪ ለመጀመሪያ ግዜ በሸገር ሬድዮ የተላለፈ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ማስታወቂያውን “አላቀርብም” ብሎ የነበረው ኢቲቪ ከሰልፉ በኋላ፤ የተቃውሞውን ምስል ቆራርጦም ቢሆን በዜና እወጃው ላይ አቅርቦታል።
ሰልፉ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የተደረገ ነው። ከዚህ ቀደም በሰበብ አስባቡ ሲከለከል የነበረው “የእሪታ ቀን” ዛሬ እውን ሲሆን፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሰልፉን ተቀላቅለውታል።
"መንገድ ዘግታችኋል ቶሎ ቶሎ ሂዱ" ፖሊስ። "መንገዱ ለኛ የተፈቀደ ነው ሰዓታችንን እንዴት እንደምንጠቀም እናውቃለን" አመራሮች
“መንገድ ዘግታችኋል ቶሎ ቶሎ ሂዱ” ፖሊስ።
“መንገዱ ለኛ የተፈቀደ ነው ሰዓታችንን እንዴት እንደምንጠቀም እናውቃለን” አመራሮች
አንድ ሁኔታውን የታዘቡ ግለሰብ እንዲህ ዘግበዋል። “የዛሬውን የአንድነት ፓርቲ ህዝባዊ ተቃውሞን በቦታው ተገኝቼ እንደታዘብኩት” ብለው ነው የጀመሩት… በዛሬው እለት ከጠዋቱ ሶስት ሰዐት ጀምሮ በርካታ የከተማይቱ እና የአካባቢው ነዋሪዎች የተገኙበት ታላቁ የእሪታ ቀን በድምቀት የተካሄደ ሲሆን በሠልፉ ላይ በርካታ መፈክሮች ተሰምተዋል፡፡
በዛሬው የሰላማዊ ሰልፍ ያሬድ አማረ ወኔ የተሞላባቸውን መፈክሮች ሲያሠማ የነበረ ሲሆን ከእርሱ መፈክሮች በተደጋጋሚ ከጓደኞቼ ጋር ፈገግ ሲያደርገን የነበረው “እመነኝ” የሚላት ቃል ናት፡፡
በሰለማዊ ሰልፉ ከኢ/ር ግዛቸው እስከ ወጣቱ ሃብታሙ አያሌው  ድረስ ያሉ ፖለቲከኞች በብዛት ይታዩ ነበር፡፡ ዳዊት ሰለሞን የአንድነት መኪና ውስጥ ሆኖ መረጃዎችን በማህበራዊ ድህረ ገፆች ሲያከፋፍል…. ነበር፡፡
ሁሉም ነገር ባዶ!
ሁሉም ነገር ባዶ!
ሰልፉ በአድዋ ድልድይ አድርጎ የመከላከያ ቤተሰቦች መኖሪያ ኢካባቢ በተለምዶ ሲግናል ተብሎ ከሚጠራው የመካላከያዎች ቤት ውስጥ የሚኖሩ የስርዐቱ ደጋፊዎች በተደጋጋሚ በመሀል ጣታቸው ሰልፈኛውን በመሳደብ ስሜታዊ ለማድረግ ሲሞክሩ ነበር፡፡
ሰልፉ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ወረዳ 8 ፊት ለፊት በሚገኘው ሜዳ ላይ ኢ/ር ግዛቸው ባደረጉት ንግግር ተቋጭቷል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባል የሆነው ሃብታሙ አያሌው ሲያደርግ የነበረውን ቅስቀሳ ለማየት ከዚህ በታች ያለውን ቪድዮ ይመልከቱ። 
እኛ ስለሰላማዊ ሰልፉ ተጨማሪ ዝርዝር ከምንሰጥበት የበለጠ እነዚህ ፎቶዎች እና መፈክሮች ብዙ ይናገራሉና… የአንድነትን ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ በፎቶ የተደገፈ እንቅስቃሴ፤ ከዚህ በታች  ይመልከቱ።

No comments:

Post a Comment