Monday, May 5, 2014

በላዛሪስት ታስረው የሚገኙ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ድብደባ ደረሰባቸው (ነገረ ኢትዮጵያ )

May 5, 2014
ሰማያዊ ፓርቲ ሚያዝያ 19/2006 ዓ.ም ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ ላይ እያሉ ፖሊስ ይዟቸው ላዛሪስ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ድብደባ ደረሰባቸው፡፡ በተለይ ‹‹አንተን የሚጠብቅ ፖሊስ የለንም ተብሎ›› ፈተና እንዳይፈተን የተደረገው ዮናስ ከድር ከፍተኛ ድብደባ የደረሰበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት ዮናስ ከድር መንቀሳቀስ እንደማይችል አብረውት ታስረው የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ገልጸውልናል፡፡
ሳምሶን የተባለና ኮድ ሁለት 16321 መኪና የሚይዝ ደህንነት ለምን አትፈታም እንዳለውና ዮናስም ‹‹የታሰርኩበት ምክንያት ህጋዊ ስላልሆነ ህጉ እስክልተከበረ ድረስ አልፈታም›› የሚል መልስ እንደሰጠው ታውቋል፡፡ ደህንነቱም ‹‹እኔ ነኝ እንዳትፈተን ያደረኩህ፡፡ ለእናትህም ደውዬ የነገርኳት እኔ ነኝ፡፡ ስትፈታም ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰህ አትገባም፡፡ ወደ ቤትህ ነው የምትመለሰው›› እንዳለው ታውቋል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙ ሌሎች የሰማያዊ ፓርቲ አባላትም ድብደባ እንደረሰባቸው የታወቀ ሲሆን ደህንነቶችና የእስር ቤቱ ኃላፊዎች ተጨማሪ ድብደባ እንደሚደርስባቸው እያስፈራሩዋቸው መሆኑን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ለአብነት ያህል በእስር ላይ የምትገኘው እየሩስ ተስፋው እዮኤል የተባለውን የእስር ቤቱ ኃላፊ ‹‹አንተ ነህ የምታስደበድበን›› ባለችው ወቅት ‹‹አሁንም ትደበደባላችሁ፡፡ ወጥታችሁ ተደብድባችሁ መመለስ ብቻ ነው ምንም አታመጡም›› እንዳላት ገልጻለች፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድ ታሳሪዎቹን ለመጠየቅና ሁኔታውን ለማጣራት ወደ እስር ቤት በሄደበት ወቅትም እስር ቤቱ ውስጥ የሚሰራ አንድ ፖሊስ ‹‹እኔ ነኝ ያስደበደብኩት፡፡ ምንም አታመጡም፡፡ ከፈለጋችሁ በደንብ እዩኝና ክሰሱኝ፡፡ አሁን ከእኔ ጋር መነጋገር አትችሉም ከግቢ ውጡ›› ብሎ እየገፈተረ እንዳስወጣቸው ገልጾአል፡፡
በላዛሪስት ታስረው የሚገኙት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላለፉት ሁለት ቀናት በረሃብ አድማ ላይ መሆናቸውና በዚህም ምክንያት መዳከማቸው የታወቀ ሲሆን ፖሊስና ደህንነት በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው እንኳ ከፍተኛ ድብደባ እያደረሱባቸው መሆኑ እንዳሳዘነው አቶ ብርሃኑ ጨምሮ ገልጸአል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የርሃብ አድማ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ 32 የሶማሊያ ስደተኞች ያለ ምንም ምግብ፣ ልብስና ውሃ መታሰራቸውን ገልጸው ችግራቸው እልባት እንዲያገኝ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይ መታሰራቸው ህገ ወጥ ሆኖ እያለ 5500 ብር ከፍላቭሁ ውጡ መባላቸውን በመቃወም ‹‹አንፈታም!›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ብርሃኑ ‹‹ደህንነትና ፖሊስ ታሳሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ድብደባ የሚያደርሱበት ምክንያትም ታሳሪዎቹ ህግን ለማስከበር በሚያደርጉት ጥረት ነው›› ብለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment