Sunday, January 19, 2014

የፊንላንድ ጋዜጠኞች እና የፓርላማ አባላት ከኮሚሽነሮቹ ጋር ተወያዩ

January 19/2014

ሚዲያዎች ሙስናን በብቃት እያጋለጡ አይደለም ተባለ

ሚዲያዎች ሙስናን በብቃት እያጋለጡ አይደለም ተባለ የፊንላንድ ጋዜጠኞችና የፓርላማ አባላት ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ከእንባ ጠባቂ እና ከፀረ ሙስና ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የምርጫ ጉዳይ የፀረ ሙስናን እንቅስቃሴ በተመለከተ ተወያዩ፡፡ ሚዲያዎች ሙስናን በብቃትና በተደራጀ መልኩ እያጋለጡ አለመሆኑን የጸረ ሙስና ኮሚሽን ገልጿል። 21 የልዑክ አባላት ያሉት የፊንላንዳውያኑ ቡድን ለሰብአዊ መብት ኮሚሺን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፤ የ97 ዓ.ም ምርጫን በማስታወስ፣ “ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ መሆኑን በምን ታረጋግጣላችሁ?” የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን አምባሳደሩም ምርጫዎች ከተከናወኑ በኋላ ተቋማቸው የምርጫውን ሂደት እና ውጤት እንደሚገመግምና ሰብአዊ መብትን የተመለከቱ ቅሬታዎች ሲቀርቡ እንደሚያጣራ ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ዜጐች ምርጫ የሚያካሂዱት ራሳቸው ወስነው እንጂ ተገደው አለመሆኑ የምርጫ ስርአቱን ዲሞክራሲያዊነት ያሳያል ብለዋል፡፡

ህገወጥ የሠዎች ዝውውርን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ባለው ችግር ዙሪያ የተደራጀ ጥናት ማድረጋቸውንና በቅርቡም ውጤቱ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በውይይት መድረኩ የተገኙት የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ተወካይ በበኩላቸው፤ ከህዝቡ የሚቀርቡ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምላሽ ያገኛሉ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ወዲያው ሊፈቱ የሚችሉት በአንድ ቀን መልስ የሚሰጥባቸው ሲሆን ውስብስብ የሆኑት ደግሞ ከ6 ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መልስ እንደሚያገኙ ገልፀዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ አባላት በሀገሪቱ ያለውን የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ በተመለከተ በሙስና ጉዳይ ፖለቲከኞችን ደፍረው የሚመረምሩ ሚዲያዎች ስለመኖራቸው የተጠየቁት የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ወዶ አጦ፤ ተቋማቸው ከሚዲያዎች ጋር ተቀናጅቶ ጠንካራ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ነገር ግን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሚዲያዎች የሙስና ጉዳዮችን በብቃትና በተደራጀ መልኩ እያጋለጡ ነው ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ለወደፊት ግን ከሚዲያዎች ጋር በቅርብ ለመስራት መስሪያ ቤታቸው ዝግጁ መሆኑን ም/ኮሚሽነሩ ለጋዜጠኞቹና ለፓርላማ አባላቱ ገልፀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment