Sunday, January 19, 2014

አዲሱ የግብጽ ህገመንግስት ኢትዮጵያ በአባይ እንዳትጠቀም ይከለክላል

January19/2014

ግብፃዊያን ሰሞኑን በሰጡት ድምጽ እንደሚፀድቅ በተነገረለት አዲሱ የግብጽ ህገ መንግስት ውስጥ፣ የአባይ ወንዝ አጠቃቀም እንደበፊቱ መቀጠል አለበት የሚል አንቀጽ የተካተተ ሲሆን፤ አንቀፁ ተቀባይነት እንደሌለው የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ አድማስ ገለፀ


ከስልጣን ተባርረው በታሰሩት መሐመድ ሙርሲ አማካኝነት ተዘጋጅቶ ከነበረው ህገመንግስት በተለየ ሁኔታ አዲሱ ህገ መንግስት በርካታ የሃይማኖት አክራሪነት አንቀፆችን ያስወገደ ሲሆን፤ የአባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ደግሞ በርካታ ነጥቦችን በማስገባት ዘርዝሯል፡፡ አወዛጋቢ ከማይመስሉት ነጥቦች መካከል የውሃ ብክለትንና ብክነትን መከላከል ይገባል የሚለው አንዱ ሲሆን፤ በወንዙ ዙሪያ ለሚካሄዱ ሳይንሳዊ ምርምሮች መንግስት ድጋፍ ይሰጣል የሚልም በዚሁ አንቀጽ ተካቷል፡፡

መንግስት በናይል (አባይ) ወንዝ ለመጠቀም ቁርጠኛ ነው፤ የግብጽ ታሪካዊ ወይም ነባር መብቶችንም ያስጠብቃል የሚለው አንቀጽ ግን ኢትዮጵያና ሌሎች የአካባቢው አገራት ከሚከራከሩበት ፍትሃዊ አጠቃቀም ጋር ይጋጫል፡፡ “የግብጽን ህዝብ የራሱን ህገ መንግስት የማውጣት መብት አናከብራለን” ያሉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ “ነገር ግን የአንድ አገር ህገ መንግስት የሌሎች አገራትን ጥቅም መጉዳት የለበትም” ብለዋል፡፡ ታሪካዊ ወይም ነባር ተብለው የሚጠቀሱት “መብቶች” እኛ ያልተስማማንባቸውና ያልፈረምንባቸው ፍትሀዊ ያልሆኑ የቅኝ ግዛት ውሎች ናቸው በማለትም አምባሳደር ዲና የአንቀፁን ምንነት ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያንና ሌሎቹን በርካታ የአካባቢ አገራት ያገለሉ ኢፍትሃዊ የቅኝ ግዛት ውሎች፤ “ነባር ወይም ታሪካዊ መብቶች” በሚል መቀጠል እንደሌለበት፣ የአባይ ወንዝ ተዋሳኝ አገራት ተስማምተው መፈራረማቸውን አምባሳደሩ አስታውሰዋል፡፡

ከአሥር አመት በፊት በዩጋንዳ በተደረገ ስብሰባ፣ የድሮ ኢፍትሃዊ ውሎችን የሚተካ አዲስ ህግ ይፋ ተደርጐ ስድስት አገሮች ፈርመዋል ያሉት አምባሳደር ዲና፤ “ግብጽ ስምምነቱን አልፈረመችም፤ በህገ መንግስትም ይሁን በምንም መልክ፤ የሌሎቹን አገራት መብት የሚጻረር አንቀጽ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡ አባይን በሚመለከት ከቀድሞዎቹ የግብጽ ህገ መንግስቶች ይልቅ አዲሱ ህገ መንግስት የከፋ አቋም እንደሚንፀባረቅበት የተናገሩት አምባሳደር ዲና፤ በቅርቡ ካርቱም ላይ የተደረገው የግብጽ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ የውሃ ሚኒስቴሮች ስብሰባ ያለ ውጤትና ያለ ቀጠሮ የተበተነው በግብጽ አቋም ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አልፈው የግብጽ ተወካዮች ኢትዮጵያ ግድቡን መሥራት አትችልም በሚል እያሰራጩት ባለው መልእክት፤ ኢትዮዽያ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ፣ የዲኘሎማሲ እና የፖለቲካ ዘመቻ እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ አፍራሽ አዝማሚያ እየተከተሉ ነው፤ በህገ መንግስቱ የተካተተው አንቀጽም ከዚህ ጋር የሚያያዝ ነው ብለዋል አምባሳደሩ፡፡ የናይል ወንዝ ድንበር ዘለል የሆነ የተፋሰሱ አገሮች ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ሊጠቀሙበት የሚገባ ሀብት ሆኖ እያለ እንደ አንድ አገር ሀብት በአዲሱ ህገ መንግስት ላይ መቀመጡ ትክክል አይደለም፤ የያዙት መንገድ አፍራሽ ነው ብለዋል፤ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፡፡

No comments:

Post a Comment