Sunday, November 10, 2013

ወያኔ ዉስጥ “እርቅ አስፈላጊ ነው” ነዉ የሚሉ ድምጾች እያየሉ መምጣታቸዉ ተሰማ

November 9/2013

ሀያ ሁለት አመት ሙሉ ልባቸዉ በትዕቢትና በጥላቻ ተሞልቶ የተቃወማቸዉን እያሰሩና ለሚቀርብላቸዉ የእንተባበር ጥያቄ ሁሉ ጆሮ ዳባ ልብስ ሲሉ የሰነበቱት የህወሀት ጀብደኞች ዛሬ ኢትዮጵያን ግራ የሚያጋባና በአፍ ሊነገር የማይችል የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ መክተታቸዉን አምነዉ የእርቅ ሃሳብ ላይ ማተኮር መጀመራቸዉን ጎልጉል የተባላ ድረ ገጽ ላይ የሚታተም ጋዜጣ የወያኔንና የኢህአዴግን ዉስጥ አዋቂ ምንጮች ጠቅሶ ዘገበ።ህወሀትም ሆነ ኢህአዴግ ዉስጥ አፈና፤ ስለላና አለመተማመን እየተባባሱ መምጣታቸዉንና በእነዚህ ሁለት ድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመተማመን ሳቢያ ስጋት የገባቸው የህወሀት ሰዎች በእርቁ ሃሳብ እየገፉበት መምጣታቸዉን ዉስጥ አዋቂ ምንጮቹ ተናግረዋል።
ቀድሞዉንም ቢሆን በዋና ዋናዎቹ የህወሀት መሪዎች ገመድ ታስሮ የቆየዉ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ዉስጥ ያለዉ መተባበርና መግባባት ዛሬ ያ ገመድ ተበጥሶ በመካከላቸዉ አለመተማመን መንገሱ በስፋት እየተነገረ ነዉ። ዛሬ በተለይ ከመለስ ሞት በኋላ በህወሃትና ህወሃት በሚያዛቸው በሦስቱ አቻ ፓርቲዎች መካከል ያለው የመከባበርና የመገዛት ስሜት ተበላሽቶ፣ በኢህአዴግም ሆነ በህወሃት ዉስጥ የተፈጠረዉ ከፍተኛ ልዩነትና በሙስና ስም የተጀመረውን ዘመቻ ፓርቲዎቹን መዉጣት የማይችሉበት አዘቅት ዉስጥ እየከተተ መሆኑን ብዙዎች በመናገር ላይ ናቸዉ። አንደ ጎልጉል ጋዜጣ የመረጃ ምንጭች አባባል ህወሀትና ኢህአዴግ ዉስጥ በጣት ከሚቆጠሩ እጅግ በጣም ጥቂት ግለሰቦች ዉጭ የሁሉም ሰዉ እጅ በሙስና የተጨማለቀ በመሆኑ ዛሬ አንዱ ሌላዉ ላይ ጣቱን እየቀሰረ “ማን ንጹህ ሆኖ ማንን ይጠይቃል?” እየተባባሉ የእርስ በርስ ጦርነት ዉስጥ መግባታቸዉ ታዉቋል።
ህወሀት ባለፉት ሀያ ሁለት አመታት በተጓዘባቸዉ መንገዶች በተለይም በሁሉም ነገር ከሁሉም በላይ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይችል በራሱ በህወሀት ዉስጥን በየድርጅቶቹ ዉስጥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ በስፋት እየተነገረ ሲሆን፤ ይህ ከሰሞኑ ይፋ ባልሆነ መንገድ የቀረበው “ታርቀን አገራችንን እንምራ” የሚለዉ የእርቅ ጥያቄ የቀረበዉ በያዝነዉ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የተሳመዉን ከፍተኛ የተቃዉሞና አገራችንን አበላሻችኋት የሚለዉን ድምጽ ተከትሎ እንደሆነ ከብዙ የፖለቲካ ተንታኞች አካባቢ እየተደመጠ ነዉ። ከዚህ ቀደም ተደርጎና ተሰምቶ በማይታው መልኩ የሃይማኖት አባቶች ወያኔን በግልጽ ማውገዛቸውና “አገሪቷን ገደላችኋት” ብለዉ መኮነናቸው በወያኔ/ኢህአዴግ ዉስጥ ከፍተኛ መደናገጥ እንደተፈጠረ ለማወቅ ተችሏል። ወያኔ እራሱ በሾማቸዉ በቀድሞው ፓትሪያርክ አማካኝነት የቤተክርሲቲያን ተቋማትን እንደተቆጣጠረ የሚታወቅ ሲሆን ፈቃድና አሁን ግን አንደለመደዉ ቤተክርስቲያኒቱን መቆጣጠርና አመራሮቹን አንደበታቸውን ማፈን የማይችልበት ደረጃ መድረሱን በቅርብ ግዜ ከተደረገዉ የሲኖዶሱ ጉባኤ የተገነዘበ ይመስላል። ከዚህ በጨማሪ ከእስልምና እምነት ተከታዮች አካባቢ ከሁለት አመት በላይ የተካሄደዉን መልስ ያላገኘዉ የድምጻችን ይሰማ ጉዳይ ወያኔን የማይወጣበት አዘቅት ዉስጥ ከትተዉታል።
ባለፉዉ የቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ የተነሱት ሀሳቦች ወያኔ ነገሮች ቀስ በቀስ ከእጁ እንደወጡበት የሚያሳይ እንደሆነ ያመለከቱት አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የኢህአዴግ አባላት እግራቸዉ አንጅ ልባቸዉ ከድርጅቱ ጋር እንዳልሆነ ተናግረዋል ። አብዛኛው የኢህአዴግ አባልና ደጋፊ ድርጅታቸዉ ዉስጥ ሰላማዊ ለውጥ ተካሂዶ ኢህአዴግን ወደ እርቅ ለመገፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት አንዳላቸዉ እየተነገረ ነዉ።
እርቅ ከተፈለገ ለምን በግልጽ አይቀርብም በሚል ለቀረበላቸው ሃሳብ ባለስልጣኑ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም “ከማን ጋር ነው የምንታረቀው? እነማንን ነው ለእርቅ የምንጋብዘው? እርቅ ጠያቂ መሆን ያለበትስ ማን ነው?” የሚሉት ጥያቄዎች ዉስጥ ለዉስጥ እንደሚንሸራሸሩ አልሸሸጉም። በቅንጅት ጊዜም በተመሳሳይ የዕርቅ ፍላጎትና “ሥልጣን እናስረክብ” የሚል አቋም ተነስቶ እንደነበር ያስታወሱት እኚሁ ባለስልጣን፤ በወቅቱ ሃሳቡ ተግባራዊ ያልሆነው “ወያኔዎችን ወደመጡበት ጠራርገን እንመልሳቸዋለን” በማለት አንድ የቅንጅት አመራር ለሕዝብ መፈክር ሲያወርዱ ከተሰማ በኋላ ነበር የሚልና ብዙም አመኔታ የሌለዉ አስተያየት ሰንዝረዋል።

No comments:

Post a Comment