Sunday, August 25, 2013

ሕወሐት በአዜብ ጉዳይ ተወጥሯል (ከኢየሩሳሌም አርአያ)

azeb Mrs. corruption
ለስድስት አመት ኤፈርትን ሲመሩ የቆዩት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከሃላፊነት መነሳት ተከትሎ በሕወሐት ውስጥ ውጥረት መንገሱን ምንጮች አመለከቱ። የኤፈርት ቦርድ ሰብሳቢ በነበሩት ባለቤታቸው አቶ መለስ አማካይነት ዳይሬክተር ተደርገው አዜብ መሾማቸውን ያስታወሱት ምንጮች፣ ከመለስ ሕልፈት በኋላ ቦታውን የተረከቡት ኤርትራዊው ቴዎድሮስ ሃጎስ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ዳይሬክተር የመሾምና የመሻር ስልጣኑ የቦርዱ መሆኑን ያስረዳሉ።

 አዜብ ከኤፈርት እንዲወገዱ የተደረገው ግን በነቴዎድሮስ ሃጎስ ሳይሆን ስብሃት ነጋ ባቀነባበሩት ጣልቃ ገብ ውሳኔ መሆኑን ምንጮቹ ገልፀዋል። በኤፈርት የተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ሰራተኞች አዜብ በመባረራቸው ደስታቸውን እየገለፁ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፣ አያይዘውም ደስታቸውን በስብሰባ ጭምር ከመግለፅ ባለፈ፥ « አዜብ ከኤፈርት ጀምሮ ለፈፀሟቸው የሙስና ወንጀሎች በሕግ መጠየቅ አለባቸው» በማለት አቋም እስከ መያዝ መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ከዚህ በስተጀርባ በበቀለኝነታቸውና የጥፋት ሴራ በማቀነባበር የሚታወቁት ስብሃት ነጋ እንዳሉበትና ከኤፈርት ስልጣናቸው ያስነሷቸውን አዜብ ከጨዋታ ውጭ ከማድረግ ባለፈ በሙስና እንዲጠየቁ በየአቅጣጫው ጫና እያሳደሩ መሆኑን ምንጮቹ አስረድተዋል።

 በአዜብ ተፈፀሙ ተብለው ከተነሱት የሙስና ወንጀሎች በኤፈርት ስም 200 ከባድ ተሽከርካሪዎች አቶ ነጋ ገ/እግዚያብሄር ቀረጥ ሳይከፍሉ እንዲያስገቡ ማድረጋቸውን፣ በሚሊዮን የሚገመት ቀረጥ ሊከፈልባቸው የሚገቡ የተለያዩ የሕክምና መሳሪያዎች፣ በኤፈርት ገንዘብ ሶስት መርከብ ስሚንቶ የፍራንኮ ቫሉታን ሕግ በመተላለፍ ቀረጥ ሳይከፈልበት አገር ውስጥ መግባቱ፣ ክሶች እንዲቋረጡ ትእዛዝ በመስጠት..የሚሉት በዋነኛነት መነሳታቸውን ምንጮቹ አመልክተዋል። ( አዜብ ከኤፈርት እንደሚነሱ ከዚህ ቀደም በወጡ ዘገባዎች ምንጮችን በመንተራስ መገለፁ ይታወሳል)
 ይህ በእንዲህ እንዳለ – በአዜብ ቦታ የተተኩት ብርሃነ ኪ/ማርያም (በቅፅል ስማቸው ብርሃነ “ማረት”) ሲሆኑ፣ ከመለስ በፊት የአዜብ ፍቅረኛ የነበሩና ከሱዳን ተያይዘው በመምጣት ሕወሐትን እንደተቀላቀሉ ምንጮች አስታውሰዋል። ድርጅቱን ከተቀላቀሉ ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለቱ (አዜብና ብርሃነ) የፍቅር ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ ከበላይ አመራር መወሰኑን፣ አዜብ ከመለስ ጋር ግንኙነት መቀጠላቸውን ይገልፃሉ። ፓርቲው ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ብርሃነ በመቀሌ ማዘጋጃ ቤት ተመድበው ሲሰሩ «ለመንገድ ስራ ከተመደበ ገንዘብ አምስት ሚሊዮን ብር ተዘርፏል» በሚል በሙስና እንዲባረሩ መደረጉን ምንጮች ጠቁመዋል።
 
 አዲስ አበባ የመጡት ብርሃነ ብዙ ጥረት አድርገው አዜብ ዘንድ (ቤተ መንግስት) የመግባት አጋጣሚ ያገኛሉ። ባቀረቡት አቤቱታና ተማፅኖ መሰረት ሲቪል ሰርቪስ እንዲገቡ አዜብ ትእዛዝ ያስተላልፋሉ። ከኰሌጁ እንደወጡ የማ.ረ.ት. ሃላፊ ተደርገው በመለስ የተሾሙት ብርሃነ፣ በተለይ ከ1993ዓ.ም በኋላ የመለስ ቀኝ እጅ በመሆን በአውሮፓና አሜሪካ ያለውን የፓርቲውን መዋቅርና ስለላ በመምራት፣ አምባሳደሮችን በማስፈራራት፣ በማዘዝና ፈላጭ ቆራጭ ውሳኔ በማሳለፍ ታማኝ አገልጋይ ሆነው እንደቆዩ ያስታወሱት ምንጮች፣ ከመለስ ሞት በኋላ ግን የስብሃት ነጋ ተከታይና አስፈፃሚ በመሆን አሰላለፋቸውን ቀይረው እንደቀጠሉ አያይዘው ገልፀዋል። ስብሃትና ብርሃነ ዝምድና እንዳላቸው የጠቆሙት ምንጮች፣ አዜብን በማስነሳት ብርሃነ እንዲቀመጡ ያደረጉት ስብሃት መሆናቸውን አመልክተዋል።

No comments:

Post a Comment