August 25, 2013
ጌታቸው ሺፈራው
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ‹‹መንግስት በእምነታችን ጣልቃ እየገባ ነው!›› በሚል ከአንድ አመት በላይ እየተቃወሙ የቀጠሉት የእስልምና እምነት ተከታዮች ሀምሌ 19/2005 ዓ/ም ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ኢህአዴግ ‹‹ሰልፈኞቹ የሰንደቅ አላማውን ክብር አዋርደዋል?›› የሚል ክስ ማቅረቡ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ የተበጣጠሰውን ሰንደቅ አላማው የያዙት ሰልፈኞቹን የሚኮንን መንግስት ቅጥረኞችም ይሁን ሰልፈኞቹ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምንም እንኳ ህግ የማስከበር ሀላፊነት የነበረበት ቢሆንም ኢህአዴግ ጉዳዩን ያነሳው በእርግጥም በሰንደቅ አላማ ክብር ስለሚያምን አይደለም፡፡ የዚህ ጽሁፍ አላማም ሀምሌ 19/2005 ዓ/ም የተፈጠረው ስህተትን ማስተባበል አሊያም መክሰስ ሳይሆን በተፈጠረው ክስተት ‹‹ሌሎችን›› የሚከሰው ኢህአዴግ ራሱ ሰንደቅ አላማውን እያዋረደ መቀጠሉን የተለያዩ ክስተቶችንና የራሴን ገጠመኝ በመቃኘት ማሳየት ነው፡፡
ሰንደቅ አላማ የአንድ አገር ዋነኛ ምልክት በመሆን ያገለግላል፡፡ ለቅኝ ግዛት እጇን ያልሰጠችው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ደግሞ ከዚህም በላይ ክብር አግኝቷል፡፡ በተለይ በጸረ ቅኝ ግዛት ዘመን አፍሪካውያንና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ጭቁን ጥቁሮች የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ የነጻነት አርማ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና የደቡብ አሜሪካ አገራትም ይህን የነጻነት አርማ ቅርጽና አቀማመጡን ብቻ በመቀያየር ለአገራቸው መለያነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ከ6 ሚሊዮን በላይ ራስ ተፈሪያን ህዝቦችም የነጻዋን ኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከአምላክ የተላከ አንዳች ምልክት አድርገው እስከ ማምለክ ደርሰዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በዓለም ለበርካታ አገራትና ኢትዮጵያዊ ባልሆኑ ህዝቦች መለያነት ያገለገለ ብቸኛውና ተወዳጅ ሰንደቅ ያደርገዋል፡፡
በሌላ በኩል ይህ ዓለም አቀፍ ክብር ያለው ሰንደቅ አላማ በተለያዩ ጊዜያት አገር ውስጥ ክብሩ ተዋርዶ ተስተውሏል፡፡ የመጀመሪያው ለሰንደቁ ክብር መሰረት በሆነው አድዋ በኢትዮጵያውያን የተሸነፉት ፋሽስቶች ኢትዮጵያን ዳግመኛ ሲወሩ የፈጸሙት ነው፡፡ ጣሊያን ለአምስት አመት ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በሌሎች አፍሪካውያንና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሚገኙ ጥቁሮች ዘንድ በስፋት በመለያነት ላይ የዋለ ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በጣሊያን ሰንደቅ አላማ ተቀይሯል፡፡ ይህ ከአንድ ‹‹ያልሰለጠነ›› በሚሉት ጥቁር ህዝብ ሽንፈትን ከተከናነበ የአውሮፓዊ ሀይል የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የሚያሳዝነው ግን ጣሊያን ተባራ እንደገና ክብሩን ያገኘው ሰንደቅ በኢትዮጵያውያን ያውም የመንግስትን ስልጣን በያዘው ኢህአዴግ የደረሰበት ውርደት ነው፡፡ ለእኔ ሰንደቁን አውርደው የራሳቸውን ከሰቀሉት ጣሊያኖች በላይ ሰንደቁን ሰቅለው ‹‹ጨርቅ›› ያሉት የኢትዮጵያው አቶ መለስ ዜናዊና ኢህአዴግ ናቸው ሰንደቁን ያዋረዱት፡፡
ፋሽስት ከኢትዮጵያ ምድር ከወጣ 50 አመት በኋላ ስልጣን ላይ የወጣው ኢህአዴግ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ሰንደቁን ‹‹ጨርቅ›› ብለው ባዋረዱበት ወቅት እነ ጋና፣ ጊኒ፣ ማሊ ሌሎች ከ10 በላይ አገራት የእኛውን ሰንደቅ አላማ ወስደው ያደመቁበት ዘመን ነው፡፡ አሁንም ከእኛው ይልቅ ከእኛ የወሰዱት አገራት ሰንደቁን ትልቅ ክብር ሰጥተውታል፡፡ በወቅቱ አቶ መለስ ዜናዊ ይህን ክብረ ነክ ተግባር ሲፈጽሙ ከተቃዋሚዎች፣ ከነጻው ሚዲያ እንዲሁም ከህዝብ ውጭ ከፓርቲያቸው ምንም አይነት ግፊት አልተደረገባቸውም፡፡ በመሆኑም ለዚህ አሳፋሪ ተግባር እርሳቸውም ሆነ ፓርቲው ህዝብን ይቅርታ ሳይጠይቁ በዚሁ ሰንደቅ ስም ሲገዙ ቆይተዋል፡፡
ኢህአዴግ በ2001 ዓ/ም የሰንደቅ አላማ አዋጅን አውጥቶ ‹‹የሰንደቅ አላማ ቀን›› ማክበር ሲጀመር በርካቶች ‹‹ሰንደቁ ወድቆ ተነሳ!›› በማለት ኢህአዴግ ለሰንደቅ አላማው ክብር በመስጠት ከስህተቱ መማር እንደጀመረ እምነት ጥለው ነበር፡፡ ሆኖም ሰንደቅ አላማው አሁንም ክብር አልተሰጠውም፡፡ የሰንደቅ አላማ አዋጅም ሆነ በስሙ ‹‹የሚከበርለት በዓል›› ኢህአዴግ ሰንደቁን እንዳላዋረደ ለማሳየት እንጅ ክብሩን የሚገልጽበት አይደለም፡፡ ኢህአዴግና የቀድሞው መሪ ‹‹ጨርቅ›› ብለው ለጠሩት ሰንደቅ አላማ አዋጅ ሲያወጡም ሆነ ‹‹በዓል›› ሲያከብሩ ለቀደመው ጥፋታቸው ህዝብን ይቅርታ አልጠየቁም፡፡ የሰንደቅ አላማ አዋጅ ያወጣውና በዓል እያከበርኩ ነው የሚለው ኢህአዴግ አሁንም ቢሆን ለሰንደቁ የሚሰጠው ክብር የይስሙላህ ነው፡፡
ከመለስና ከሰንደቁ ማን ክብር አለው?
ሰንደቅ አላማውን ‹‹እራፊ›› ያሉት አቶ መለስ ከህዝብና ከተቃዋሚዎች ከደረሰባቸው ትችት ባለፈ በፓርቲያቸው ምንም አይነት ግፊት አለመደረጉ ኢህአዴግ ከሰንደቁ ይልቅ ስልጣን ሊነጥቁ፣ ሊሰጡ፣ ‹‹ሊያራግፉ›› አሊያም ሊያስሩ ለሚችሉት አቶ መለስ ክብር ሰጥቷል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በብሄር ስም የተደራጁት የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ከአገሪቱ ሰንደቅ አላማ ይልቅ ለየክልሉ ‹‹ባንዲራ›› ክብር የሚሰጡ ናቸው፡ ለዚህ ደግሞ የካሪቢያንና ሌሎች የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን የሰንደቅ አላማ ቀለማት ሲወስዱ አብዛኛዎቹ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ለክልሎቻቸው ከእኛዎቹ ቀለማት ይልቅ ቀይ ባህር፣ ሜዲትራኒያንና አትላንቲክን ተሸግረው የአረብና የምዕራባዊያንን የሰንደቅ አላማ ቀለማት መዋሳቸው ነው፡፡ የሰንደቅ አላማ አዋጅና በዓል መከበር ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ኢህአዴግ እነዚህ ራሱ ያጸደቃቸውን ህጎች ጥሶ ከሰንደቅ አላማው የአቶ መለስን ክብር አስበልጧል፡፡ ጥቂት ክስተቶችን እንመልከት፡፡
በ2004 ዓ/ም መጋቢት አጋማሽ አካባቢ ሰንደቅ አላማውን ‹‹እራፊ›› ያሉት አቶ መለስ ከኬንያና ደቡብ ሱዳን ጋር እንደ ሰንደቁ ሁሉ ‹‹ሸቀጥ›› ብለው የሚያጣጥሉት ወደብ ላይ አንድ ስምምነት አድርገው ነበር፡፡ በዚህ የለሙ ወደብን በአማራጭ ወደብነት ለመጠቀም ባደረጉት ስምምነት ድሮም የማይወዱትን ሰንደቅ አላማ ገልብጠውት ታይተዋል፡፡ በአቶ መለስና ኢህአዴግ የበላይነት የጸደቀው የኢፌደሪ ህገ መንግስት በአንቀጽ 3(1) እንዲሁም በ2001 ዓ/ም የወጣው አዋጅ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ቀለሞች አቀማመጥ ከላይ ወደ ታች አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ በተለይ በሰንደቅ አላማው አዋጅ አንቀጽ 17 መሰረት ‹‹(ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርና) ማንኛውም ዜጋ ለሰንደቅ አላማው የሚገባውን ክብር የመስጠት ሀላፊነትና ግዴታ›› አለበት በሚል ደንግጓል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 23(6) ላይ ደግሞ የሰንደቅ አላማውን ቀለማት ቅደም ተከተል ሳይጠብቅ ማውለብለብ የተከለከለ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በአንቀጽ 24(1) ላይ ይህን ህግ የተላለፈ ግለሰብ ከ3000 ሺህ ብር መዋጮና እስከ አንድ አመት ጽኑ እስራት እንደሚፈረድበት በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ኢህአዴግ በቅርቡ የሙስሊም ሰልፈኞቹን ‹‹ጥፋተኛ›› ብሎ የፈረጀው በዚህ አዋጅ ላይ ያሉትን ህጎች መዞ ነው፡፡ አቶ መለስ ላይ ግን ይህ ህግ አልሰራም፡፡
አቶ መለስ የገለበጡት አውቀው ነው በስህተት የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ በህጉም መሰረትም ቢሆን አለማወቅ በራሱ ከጥፋተኝነት ሊያድን አይችልም፡፡ ዳግመኛ እንዲያውም በራሳቸው ትዕዛዝ የወጣውን አዋጅ ጥሰው ሰንደቁን ያዋረዱት አቶ መለስ ግን 3000 ብርና የአንድ አመት እስር ይቅርና ይቅርታ አልጠዩቁም፡፡ ኢህአዴግም እርሳቸውን ወክሎ ይቅርታ አይጠየቀም፡፡ እንዲያውም አቶ መለስ ሰንደቅ አላማውን መገልበጣቸው ስህተት መሆኑን የገለጹ ኢትዮጵያውያን ላይ ‹‹ምን አገባችሁ!›› ተብለው እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ እኔው ራሴ ቋሚ ምስክር ነኝ፡፡
በወቅቱ ለአቶ መለስ ተጠሪ በሆነ ‹‹ኢንሳ›› በተባለ መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሬ እሰራ ነበር፡፡ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አቶ መለስ በፈጸሙት ነገር ተቃውሞ ማሰማት ነበረብኝና በፌስ ቡክ ገጼ ትክክል አለመሆኑን ፎቶውን አስደግፌ ሀሳቤን ገለጽኩ፡፡ ታዲያ ከሰንደቅ አላማው ይልቅ ለአቶ መለስ ክብር የሚሰጡት የመስሪያ ቤቱ አመራሮች (ኢህአዴጎች ናቸው) ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከሆኑ ድረስ ሰንደቅ አላማውን መዘቅዘቃቸው ስህተት መስሎ አይታያቸውም፡፡ በተቃራኒው እኔ ‹‹አቶ መለስ ለምን ሰንደቅ አላማውን ዘቀዘቁት?›› ብዩ መጠየቄን በህገ ወጥነት ፈረጁት፡፡ ሰንደቅ አላማውን ‹‹ጨርቅ›› ሲሉም ሆነ ሲዘቀዝቁ ምንም ያልተባሉት አቶ መለስ ላይ ጥያቄ በማንሳቴ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩን ክብር አዋርደሃል!›› በሚል ‹‹ወንጀል›› ተከስሼ ከመስሪያ ቤት ታገድኩ፡፡ ህገ መንግስቱም ሆነ አዋጁ ስለ ሰንደቅ አላማ ክብር ያስቀመጠውን ጠቅሼ መከራከሬ ‹‹በከፍተኛ ወንጀል›› ከመስሪያ ቤቱ ከመባረር አላዳነኝም፡፡
ከሟቹ መለስም ያነሰው ሰንደቅ አላማ
ለሰንደቅ አላማው ጥላቻ ያላቸው አቶ መለስ ብቻ ቢሆኑ ኖሮ አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ ኢህአዴግ ለሰንደቅ አላማው ከድሮው የተለየ ክብር በሰጠ ነበር፡፡ ሰንደቅ አላማ ከተዘቀዘቀ ከወራት በኋላ በስልጣን ዘመናቸው ሰንደቅ አላማውን ሲያዋርዱ የኖሩትና በኢህአዴግ ዘንድም ከሰንደቅ አላማው በላይ የሚከበሩት አቶ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ፡፡ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ረዥም የሀዘን ቀን መታወጁ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ሀዘን ሲባል ደግሞ አገራዊ ቀናትም ተራዝመዋል፡፡ አሊያም ተሰርዘዋል፡፡ በአዋጅ የተወሰነው የሰንደቅ አላማ ቀን ከተራዘሙት መካከል አንዱ ነው፡፡
በአዋጅ 654/2001 መሰረት የሰንደቅ አላማ በዓል በየ አመቱ መስከረም ሁለተኛ ሳምንት ላይ በአገር ደረጃ እንዲከበር ቢደነገግም ኢህአዴጎች ‹‹አይሞትም!›› ለሚሏቸው አቶ መለስ ሀዘን ሲባል ለጥቅምት ሶስተኛ ሳምንት (ሰኞ ጥቅምት 19) ተራዝሞ ‹‹ተከብሯል››፡፡ በዚህ ቀንም ቢሆን ከሰንደቅ አላማው ይልቅ ህወሓት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የአቶ መለስ 38 አመት ታሪክ በሚዘክር መልኩ ተከብሮ ውሏል፡፡ እናም ከሰንደቅ አላማው ይልቅ ተከብረው የዋሉት አቶ መለስ ነበሩ፡፡
በኢህአዴግና ሰንደቅ አላማው መካከል ያለውን ተቃርኖ ተከትሎ የሚመጣው መዘዝ ደግሞ እኔን አልለቀቀኝም፡፡ በወቅቱ ሰንደቅ አላማውን አዋርደው ምንም ያልተባሉትን አቶ መለስን ‹‹አዋርደሃል!›› በሚል ተባርሬ መሰናዘሪያ ጋዜጣ ላይ እየሰራሁ ነበር፡፡ በአቶ መለስ ሀዘን ምክንያት ተራዝሞ ሲወደሱበት ከዋሉት ‹‹የሰንደቅ አላማ ቀን›› ማግስት ማክሰኞ ጥቅምት 20/ 2005 ዓ/ም ሳምንታዊ መሰናዘሪያ ጋዜጣ ላይ ‹‹እውን ኢህአዴግ ሰንደቅ አላማውን ያከብረዋልን?›› የሚል ጽሁፍ ጽፌ ነበር፡፡ እኔ ከመስሪያ ቤት የተባረርኩበት የሰንደቅ አላማው ጉዳይ አሁን ወደ መሰናዘሪያ ዞረ፡፡ ከሰንደቅ አላማው ይልቅ ለአቶ መለስ ክብር የሚሰጠው ኢህአዴግ መሰናዘሪያ ዳግመኛ እንዳትታተም በማተሚያ ቤቶች ላይ ጫና አደረገ፡፡ እኔን ከመስሪያ ቤት ያባረረኝ ኢህአዴጋዊ የአቶ መለስ ክብር መሰናዘሪያን አሳገዳት፡፡ ይህም ከአንድም በሁለት ሶስት ህግ ስለ ሰንደቅ አላማው አስፍሮ፣ ወጭ አውጥቶና ቀን ቆርጦ ለሰንደቅ አላማው ቀን ‹‹እያከበረ›› የሚገኘው ኢህአዴግ በእውኑ ለሰንደቅ አላማው ክብር እንደማይሰጥ ያሳያል፡፡ ይህ እርምጃ ግን የተወሰደው በእኔ ብቻ አይደለም፡፡ የሰንደቅ አላማ ቀን መከበሩን ተከትሎ ኢህአዴግ በግዳጅ ‹‹በዓል አክብሩ›› ያላቸው በርካታ ወጣቶች ሰንደቅ አላማው ‹‹ጨርቅ›› መባሉን በመከራከሪያነት በማቅረባቸው መባረራቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ኢህአዴግ ጥፋቱን አምኖ ለሰንደቅ አላማው ክብር እስካልሰጠ ድረስ በቀጣይነትም ጥያቄ ያነሱ ኢትዮጵያውያን ይባረራሉ፡፡ ተቋማትም ይዘጋሉ፡፡
ኢህአዴግ ያኔ አቶ መለስ ሰንደቁን ‹‹እራፊ›› ሲሉም ሆነ ሲዘቀዝቁት ይቅርታ አልጠየቀም፡፡ ለአቶ መለስ ሲል በአዋጅ የጸደቀውን የሰንደቅ አላማ ቀን እንደፈለገው ሲያራዝም ጥፋት መስሎ አልታየውም፡፡ ታዲያ በሰንደቅ አላማው ላይ ይህን ሁሉ ጥፋት የፈጸመው ኢህአዴግ ሰንደቅ አላማው ላይ ጥፋት ፈጽመዋል በሚል በሌሎች ላይ ክስ ለመመስረት ሞራል ከየት አገኘ? ካልሆነ ህገ መንግስቱና አዋጁ ከኢህአዴግ ውጭ ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ነው የሚሰራው እንደማለት ነው፡፡
እስካሁን በዓለም የራሱን ሰንደቅ አላማ የተሳደበ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ፕሬዝዳንት አሊያም ፓርቲ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ይህ የኢህአዴግ ብቸኛ መገለጫ ነው፡፡ በተቃራኒው ሰንደቅ አላማውን ያከበረ የሚያስመስልባቸው ህጎችና አዋጆች ሰንደቅ አላማቸውን ከልብ ከሚወዱ ስርዓቶች ‹‹በመልካም ተሞክሮነት›› ቃል በቃል የተገለበጡ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል የብሪታኒያ ፓርቲዎች ለሰንደቃቸው ትልቅ ክብር ከሚሰጡት መካከል ይመደባሉ፡፡ ኢህአዴግ አጽድቆ የሚጥሰው ‹‹የሰንደቅ አላማ ቀን››ም ሆነ ‹‹አዋጅ›› ከብሪታኒያ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ሆኖም ብሪታኒያውያን ለራሳቸው ሰንደቅ አላማ ይቅርና ለሌሎቹም ክብር ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ባለፈው የለንደን ኦሎምፒክ ከሰንደቅ አላማ ጋር በተያያዘ አንድ ስህተት ተፈጽሞ ነበር፡፡ በኦሎምፒኩ ወቅት የሰሜን ኮሪያ የሴቶች የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን እየተዋወቀ እያለ ቴሊቪዥን ላይ ይታይ የነበረው ሰንደቅ አላማ የደቡብ ኮሪያ ነበር፡፡ ለዚህ ስህተትም በተለይ በሰሜን ኮሪያውያን ዘንድ የኦሎምፒኮ አዘጋጆች ብቻ ሳይሆኑ ብሪታኒያ ራሷም ተወቅሳለች፡፡ ብሪታኒያውያን ይህንን ወቀሳ የኦሎምፒኩን አዘጋጆች፣ የብሪታኒያ መሪዎች አሊያም ብሪታኒያን ‹‹ክብር አዋረደ›› ብለው መስል አልሰጡም፤ እርምጃ አልወሰዱም፡፡ ይልቁንስ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ለተፈጠረው ስህተት በዓለም አቀፍ ደረጃ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ስህተቱን የፈጸሙት የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር አልነበሩም፡፡ ሆኖም ለሌላ አገር ሰንደቅም ያላቸውን አክብሮትና የተፈጸመውን ጥፋት በይቅርታቸው አምነዋል፡፡ የብሪታኒያ ገዥዎች በራሳቸው ላይ ብቻ ሳይሆን በሌላ አገር ሰንደቅ አላማ የሚፈጸም ስህተት ላይ የመክሰስ፣ የመቃወምና የመተቸት የሞራል ልዕልና ይኖራቸዋል፡፡ ሙስሊሞቹ ሲያውለበልቡት ነበር ያለውን የተበጣጠሰ ሰንደቅ አላማንም በሰንደቅ አላማ የማያምንበት ኢህአዴግ እንዴት ጥብቅና ለመቆም ይቻለዋል?
ኢህአዴግ የሚያደርገው ከዚህም በተቃራኒ ነው፡፡ ራሱ ህግ አውጥቶ፣ አዋጅ አጸድቆ፣ በዓል ‹‹እያከበርኩ ነው›› እያለ፣ እራሱ የቀየረውን ሰንደቅ አላማ አሁንም እያወረደው ነው፡፡ ከጣሊያን ቀጥሎ ደግሞ ለረዥም አመት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እያዋረደ ይገኛል፡፡ በመሆኑም እስካሁን በተፈጸሙት ላይ ህዝብን ይቅርታ ሳይል ሌሎች ሰንደቅ አላማውን እንደማየከብሩት ለማሳጣት መሞከሩ አሁንም ከራሱ ጠባብ ቡድናዊ ጥቅም የዘለለ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሰንደቅ አላማው ከኢትዮጵያውያን አልፎ በዓለም ህዝቦች ዘንድ ዝና እና ተቀባይነትን ያተረፈው ህገ መንግስትም ሆነ አዋጅ ሳይወጣለት ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ስፍር ቁጥር የሌለው ህግ አውጥቶ እራሱ እየጣሰ ሌሎችን ለመክሰሻነት ብቻ እየተጠቀመበት ነው፡፡ መቼም ከአሁን በኋላ ሰንደቁን የሚያዋርድ የውጭ ሀይል ይበጣል ተብሎ አይገመትም፡፡ ኢህአዴግ እስካለ ድረስ ግን ሰንደቁ እንደተዋረደ የሚቀጥል ይመስላል፡፡ ከኢህአዴግ ውጭ ያሉት እንኳን ሰንደቁን ቢያዋርዱት ያዩት ከእሱው ነው፡፡ ‹‹መንግስት››ን ያህል ነገር የተቆጣጠረ ፓርቲ፣ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን መንበር የተቆናጠጠ አካል ሰንደቁን ሳያከብር ማን ሊያከብረው ይችላል? ህጉን ለማጥቂያነት ብቻ የሚጠቀምበት ኢህአዴግ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ‹‹ለሰንደቁ ክብር የላቸውም›› የሚል ፕሮፖጋንዳውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በእርግጥ ይህ የተጀመረው በሙስሊሞቹ ብቻ አይደለም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ባዘጋጀው ሰልፍ ላይም ሰልፈኞቹ ‹‹ሰንደቅ አላማውን አዋርደዋል›› ተብለው ተከሰዋል፡፡ ሰንደቅ አላማ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ምን ያህል ቦታ እንዳለው የሚያውቀው የኢህአዴግ ‹‹መንግስት›› ሰንደቁን ከማክበር ይልቅ ሌሎቹ እንደማያከብሩት በመምቻነት በስፋት እየተጠቀመበት መሆኑ ያሳየናል፡፡
ይህን ጽሁፍ ዳግመኛ ስጽፍም ሆነ ስለ ሰንደቁ ለሶስተኛ ጊዜ ሳነሳ ከሰንደቁ ይልቅ ለአቶ መለስ ክብር የሚሰጠው ኢህአዴግ የሚወስደው እርምጃ አላሳሰበኝም፡፡ በአባቶታችን ደም የተቀለመው ይህ ሰንደቅ አላማ ከስራ ከመባረርና ከመሳሰሉት ‹‹ጥቃቅን›› እንቅፋቶች በላይ በርካታ መስዋትነት ተከፍሎበታልና!
No comments:
Post a Comment