ግንቦት ፳፮ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-እሁድ ግንቦት25 ከፍተኛ ህዝብ የተገኘበትን የተቃውሞ ሰልፍ በተመለከተ የኢህአዴግ የጽህፈት ቤት ሀላፊ የሆኑት አቶ ሬድዋን ሁሴን ለሬዲዮ ፋና ሲናገሩ ” የሃይማኖት አክራሪነትን አጀንዳው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰማያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ጸረ ህገ መንግስታዊ እንቅስቃሴው ዛሬ በጠራው ሰልፍ ተጋልጧል ” ብለዋል።
ፓርቲው ያዘጋጀውን ሰላማዊ ሰልፍ ላልተፈለገ አላማ አውሎታል ያሉት አቶ ሬድዋን ፣ በሰልፉ በአብዛኛው የተንጸባረቀው የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ይፈቱ እየተባለ መስተጋባቱ ፥ ፓርቲው ህገ መንግስቱን በመጣስ በሃይማኖት እጁን መክተቱና በህግ የበላይነት አምናለሁ እያለ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው የተያዘባቸው ሰዎች በሁካታ ይፈቱልን ማሰኘቱ ተጠያቂ ያደርገዋል ሲሉ አክለዋል።
የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማልም እንዲሁ የአቶ ሬድዋንን ንግግር የሚያጠናከር አስተያየት ለኢቲቪ ሰጥተዋል
ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ የቀረበላቸው ኢ/ር ይልቃል ጌትነት መንግስት የሚያቀርበው የሀሰት ውንጀላ ከወደፊቱ ጉዙአቸው እንደማይገታቸው ተናግረዋል **
በእለቱ ተናጋሪ የነበሩት ዶ/ር ያእቆብ ሀይለማርያም ህዝቡ ከ8 አመታት በሁዋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀዳጀው መብት መሆኑን ገልጸው፣ ህገመንግስቱን የጣሰው መንግስት እንጅ ፓርቲው ወይም እርሳቸው አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ሁለት ታዋቂ ህግ ባለሙያዎች መንግስት ያቀረበውን ውንጀላ ውድቅ አድርገውታል።
የድምጻችን ይሰማ የሙስሊም አመራሮችን የፍርድ ቤት ጉዳይ የያዙት አቶ ተማም አባቡልጉ ሙሰሊም ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ተቃውሞአቸውን የማሰማት መብት እንዳላቸው፣ ገልጸዋል። የእኛ ደንበኞች የህገመንግስት መብታቸው በመጣሱ አመለካከታቸውን በተቃውሞ ማቅረባቸው መብታቸው መሆኑን የገለጹት አቶ ተማም፣ ህገወጥ የሚሆነው ሰዎች ለምን መብታችሁን ገለጻችሁ ተብለው እንዲሸማቀቁ መደረጋቸው ነው ብለዋል።
የርእዮት አለሙ አባት አቶ አለሙ ጎቤቦ በበኩላቸው ህግ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን እንደማይከለክል እና በፍርድ ቤት ላይ የሚኖረው ተጽኖ አለመኖሩን ገልጸው መንግስት ህዝቡን ለማስፈራራት እና ሀሳቡን እንዳይገልጽ ለማድረግ የወሰደው ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል::
No comments:
Post a Comment