Thursday, June 13, 2013
8ኛውን አመት የሰኔ 1997 ሰማዕታት የምናስታውሰው የተሰውለትን ክቡር አላማ ለማሳካት ዝግጁነታችንን እየገለጽን ነው
የምርጫ 1997 ውጤት በወያኔ/ኢህአደግ መሰረቁን ተከትሎ ተቃውሞአቸውን ለማሰማት አደባባይ የወጡት ዜጎቻችን ላይ በመለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው አጋአዚ ጦር ፋሽስታዊ እርምጃ መውሰድ የጀመረበት ሰኔ 1 1997 8ኛ አመቱን ባለፈው ቅዳሜ አገባዷል።
በግፍ የተጨፈጨፉትን የሰኔ 97 ሰማዕታቶቻችንን ባሰብን ቁጥር ሁሌም በአይነ ህሊናችን የሚመላለሰው፣ አገርን ከወራሪ ጠላት ለመከላከል በሚያስችል ወታደራዊ አቅምና ዝግጅት እስከ አፍንጫው ድረስ ታጥቆ የነበረውና; በመላው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተርመሰመሰ በወገኖቻችን ላይ ያን ሁሉ የተኩስ ናዳ ሲያዘንብ የሰነበተው የአጋአዚ ጦርና በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የቴሌቪዥን መስኮቶች የተመለከትናቸው በደም የተጨመላለቁ አካላት ምስል ፤ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ከተስተጋባው የሟቾች ቤተሰቦች የድረሱልን ለቅሶና ዋይታ ጋር ተደበላልቆ ነው። “መሪያችሁን ወጥታችሁ በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ምረጡ” ብሎ የፈቀደ ሃይል ሲሸነፍ: ታንክና መተረየስ የታጠቁ አልሞ ተኳሾችን ያዘምትብናል ብሎ ያሰበ አልነበረምና ፍትህ፤ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነበት አገር ባለቤት ለመሆን ተስፋ ሰንገው ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ለማሰማት ከቤታቸው የወጡ ዳግም ላይመለሱ እስከወዲያኛው ተለዩን።
ፋሽስት ጣሊያን አገራችንን በቅኝ ግዛትነት የራሷ ለማድረግ በነበራት ህልም ለነፃነቱ ቀናዕ የሆነውን ህዝባችንን በፍርሃት ለማሽመድመድ የሩዶልፍ ግራዚያኒ ጦር የካቲት 12 ቀን 1928 በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ከፈጸመው የጭካኔ እርምጃ ፈጽሞ ባልተናነሰ አረመኔያዊነት ሰኔ 1 ቀን 1997 ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ያ አሰቃቂ ጭፍጨፋ፡ ታዳጊዎችን ከአዋቂ ፤ አዛውንትን ከጎልማሳ፤ አካለ ስንኩላንን ከጤነኛ ፤ ሴቶችን ከወንዶች መለየት ሳያስፈልግ አደባባይ የወጣውን ሁሉ “ የትግሬ ጠላትና የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች ናቸውና በሉዋቸው” የሚል ትዕዛዝ ባስተላለፉ የዘር ጥላቻ ሂሊናቸውን ባናወዛቸው ጥቂት “ከትግራይ ህዝብ አብራክ የተገኘን እንቁዎች ነን” በሚሉ ዘረኞች የተቀነባበረ እንደሆነ ታወቃአል።
መለስ ዜናዊ ፤ በረከት ስሞን ፤ ሳሞራ ይኑስና ታደሰ ወረደ ከነዚህ ቀንደኛ ዘረኞች ዋንኞቹ እንደሆኑ ሲታወቅ “የተጭበረበረው የምርጫ ድምጻችን ይመለስልን!! ፤ እንዲመሩን የመረጥናቸው ሰዎች ያስተዳድሩን !!” በማለት ጥያቄ ያነሳውን ህዝብ ለመቅጣት ሲባል የአገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች በሙሉ በአንድ ዕዝ ሰንሰለት ሥር ገብቶ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለመለስ ዜናዊ እንዲሆን ምርጫው በተካሄደበት የግንቦት 7/ 1997 ምሽት መመሪያና አዋጅ በሬዲዮና በቴሌቭዥን በራሱ በመለስ ዜናዊ ካስነገሩ ቦኋላ: እስከዛሬ ወደ አፎቱ ያለተመለሰ የጥቃት ሳንጃቸውን በህዝባችን ላይ መዘዋል።
ዘረኝነት ምን ያህል ጭካኔ ሊያመነጭ እንደሚችል ትምህረት ሰጥቶ ባለፈው የሰኔ 97 ጭፍጨፋ ሰለባ ከሆኑት መቶዎች ውስጥ፡ መርካቶ አካባቢ ይጫወትበት የነበረውን የጨርቅ ኳስ አንስቶ ለመሸሽ ጎንበስ ባለበት ተደፍቶ የቀረው የ10 አመቱ ታዳጊ ህጻን እንዲሪስ፤ ደብተሩን ተሸክሞ ከትምህረት ቤት ሲመለስ ፍልውሃ አካባቢ የተገደለው የ14 አመቱ ነብዩ አለማየሁ፤ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ፊት ለፊት ግንባሯን በጥይት ተመታ የተገደለቺው የ18 አመቷ ወጣት ሽብሬ ደሳለኝ፤ ባሌን አትውሰዱብኝ በማለታቸው ደረታቸውን በጥይት ተደብድበው የተገደሉት የ8 ልጆች እናት ወ/ሮ እቴነሽና ቀድሞ በተተኮሰ ጥይት የወደቀውን ወንድሙን አብረሃም ይልማን አስከሬን ቀና ለማድረግ ሲሞክር ጀርባውን በጥይት ተበሳስቶ የተገደለው የፈቃዱ ይልማ ወላጅ ቤተሰቦች በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ያሰሙት የድረሱልን እሮሮና ለቅሶ ዛሬም ድረስ ሂሊናችን ውስጥ እያንቃጨለ እረፍት ይነሳናል።
በተለይም ደግሞ ድንገተኛ ሞት ከረጂሙ የጥፋት አላማው ከቀጨው መለስ ዜናዊ በስተቀር የዚህ ሰቆቃ ፈጻሚዎች ዛሬም ድረስ በሰሩት ወንጀል ፍትህ ፊት ሳይቀርቡና ተገቢውን ቅጣታቸውን ሳያገኙ መቅረታቸው ያንገበግበናል፤ ይቆጨናል፤ እስከመጨረሻው የድል ቀን ድረስ ፀንተን እንድንታገላቸው ሞራላችንንና ወኔያችንን በየደቂቃው ይሰቀሰቃል።
ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በምርጫ 97 የተነጠቅነውን የህዝብ ድል ለማስመለስና ወያኔ በአገዛዝ ዘመኑ በህዝባችን ላይ ለፈጸመው ሰቆቃና አገራችን ላይ ለፈጸማቸው ወንጀሎች ህግ ፊት ቀርቦ ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ ተግቶ እየታገለና እያታገለ ያለው ለነጻነት ሲሉ ውድ ህይወታቸውን መሰዋዕት የከፈሉ ወገኖቻችን አደራና የህዝባችን የነጻነት ጥማት ከሁሉም በላይ ስለሚያሳስበው እንደሆነ ደጋግሞ ገልጾአል።
ወያኔ ሥልጣን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ የአገራችንን ሉአላዊነት ለማፍረስና የህዝባችንን አንድነት ለመናድ የሚያደርገውን እኩይነት ተቃውሞ ሲታገሉ የታሰሩ፤ የተደበደቡ፤ የተገደሉና ለአካለ ጎዶሎነት የተዳረጉት ዜጎቻችን መስዋዕትነት መና ሆኖ እንዳይቀር እንዲሁም ከሰኔ 1997 እስከ ህዳር 1998 በአጋአዚ ጦር የተጨፈጨፉ የዲሞክራሲ ለውጥ አርበኞች አጥንትና ደም እንዳይፋረደን እያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ትግሉን ከዳር ለማድረስ እየተካሄደ ያለውን የነፃነት ትግል ለማገዝ ዛሬውኑ እንዲቀላቀለን ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪዉን ለያንዳንዱ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ያቀርባል። አውራው እንደሞተበት ንብ እየተበታተነ ያለው የወያኔ ኢህአደግ አባላትና ደጋፊዎችም በጭፍጨፋ ወንጀል ተሳታፊ እስካልነበሩ ድረስ የሚመጣው ለውጥ ለነርሱም የተስፋና የነፃነት ዋስትና የሚሰጥ በመሆኑ ምንም ሳያቅማሙ የትግሉን ጎራ ዛሬውኑ እንዲቀላቀሉ ወገናዊ ጥሪውን ያስተላለፋል።
ወያኔ ላለፉት 22 አመታት በአገራችንና በህዝባችን ላይ እየፈጸመ ያለውን ሰቆቃ ማስቆም የሚቻለው ወያኔን በማስወገድ ብቻ እንደሆነ አቋም የያዘው የግንቦት 7 ንቅናቄ አመራርና መላው አባላቱ ትግሉ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆናቸውን የሚገልጹት በታላቅ ብሄራዊ ስሜትና ኩራት ነው። ለሰኔ 97 ሰማዕታትና ለቤተሰቦቻቸው ከዚህ የበለጠ ቃልኪዳን የለምና።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment