ነዋሪነታቸው ወላይታ ሶዶ የሆኑት አቶ አላሮ አላንቦ ለዝግጅት ክፍላችን ይዘው በቀረቡት ሰነድ እንደሚሉት “ከወ/ሮ አበበች ኩንቼ ጋር ተጋብተን ልጆች ወልደናል ቤት ሠርተናል፤ ንብረት አፍርተናል፡፡ ከ28 ዓመት በፊት በፍ/ቤት ተለያይተናል፡፡
በወቅቱ በጋራ ያፈራነው ንብረታችንና ቤታችንን እንድንካፈል ተወስኗል፡፡ ያፈራነውን ንብረትም ተዘርዝሯል፡፡ ይሁን እንጂ ንብረቴ ሁለት ቦታ ተከፍሎ ከሚባክን ለልጆቼ ባለበት ሁኔታ በቀድሞ ባለቤቴ እጅ እንዲቀመጥ ወሰንኩኝ ይህንኑ በጋራ ሽማግሌዎች ተስማምተን ለእሷ አስረክቤ ከቤቴ ወጣሁኝ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቤቱን ግማሹን ለት/ቤት አከራይታ ግማሹን በብቸኝነት ትጠቀምበታለች በጋራ ያፈራነው ንብረትም ቤት ውስጥ በእሷ እጅ ቀርቷል በፍላጎቴ የሰጠኋት በመሆኑ ቅሬታ የለኝም እኔ ልጆቼን ሰብስቤ በማገኛት ወርሃዊ ገቢ ልጆቼን አሳድጋለሁ፡፡ ዘመዶቼ በሚያደርጉልኝ ድጋፍ የግሰብ ቤት ተከራይቼ እኖራለሁ፡፡” በማለት ይዘረዝራሉ፡፡
አቶ አላሮ በመቀጠልም “እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ከ28 ዓመት በኃላ በፖለቲካ አመለካከቴ እኔን ለማጥቃት የፈለጉ ግለሰቦች ባቀነባበሩት ሴራ የቀድሞ ባለቤቴ በወላይታ ሶዶ ከተማ መርካቶ ክፍለ ከተማ በ900 ካሬ ሜትር ላይ የተሰራ የጋራ መኖሪያ ቤት ስለአለኝ እንዲያካፍለኝ የሚል ክስ መሠረተች፡፡ እኔም ክሱ ደርሶኝ ለፍ/ቤቱ መልስ ሰጠሁኝ፡፡ ከ28 ዓመት በፊት መለያየታችን፤ ያፈራነው ንብረት ተዘርዝሮ በሽማግሌዎች መለያየታችንን፤ በጋራ ያፈራነው መኖሪያ ቤታችን በእሷ እጅ እንደሚገኝ፤ ከዚያ በኋላ ልጆቼን በማሳደግ ማሳለፌን፤ ቤትም ንብረትም ማፍራት አለመቻሌን በስሜ የተሰራ ቤት አለመኖሩን በመግለጽ መልስ ሰጠሁኝ፡፡
ከሳሽ የሆነችው የቀድሞ ባለቤቴም በ300 ካሬ ሜትር ላይ የተሠራውን የአጎቴን ቤት የእሱ ስለሆነ ያካፍለኝ አለች፡፡ ይህ በመጀመሪያ ካቀረበችው ክስ ጋር የማይጣጣም ቤቱም የእኔ አለመሆኑንም አስረዳሁ፡፡ ጉዳዩን የሰማው አጎቴም ጣልቃ ገብ ተከራካሪ ሆኖ በመግባት ቤቱ የእኔ አለመሆኑን ገልጾ የእሱ መሆኑን የሚያሳይ ሠነዶች በመያዝ ተከራከረ፡፡ ማዘጋጃ ቤቱ የሰጠውንም የይዞታ ባቤትነት ካርታ አቀረበ፡፡ ፍ/ቤቱም ለወላይታ ሶዶ ማዘጋጃ ቤት ደብዳቤ ጽፎ በሰሜ ቤት መኖር አለመኖሩን ጠየቀ ማዘጋጃ ቤቱም ለፍ/ቤቱ በጹሑፍ በሰጠው መልስ በአቶ አላንቦ ስም ሰጪ ቤት አለመኖሩን አረጋግጠ፡፡ ክርክሩን የተመለከተው የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቱም ክሱን ውድቅ አድርጎ በነጻ አሰናበተኝ፡፡” ሲሉ ይናገራሉ፡
በመቀጠልም “የቀድሞዋ ባለቤቴ ለከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ጠይቀች::” በማለት ሂደቱን በማስረዳት ይቀጥላሉ፡፡ “ይግባኙን የተመለከተው ከፍተኛው ፍ/ቤት የሥር ፍ/ቤትን ውሳኔ በመሻር ቤቱን እንዲያስረክባት ወሰነ፡፡ የሌለኝን ቤት ከየት አምጥቼ ብዬ ብከራከር አስረክብ! አስረክብ !! ተባልኩ፡፡ እኔም በተራዬ ለጠቅላይ ፍ/ቤቱ ይግባኝ ጠየኩኝ:: የሌለኝን ቤት አስረክብ እየተባልኩ ነው ፡፡
የማንን ቤት ላስረክብ? ከየት አምጥቼ ልስጣት? ብዬ ተከራከርኩ፤ ጠቅላይ ፍ/ቤቱም የከፍተኛ ፍ/ቤቱን ፍርድ አጽድቆ አስረክብ አለኝ ፌዴራል ሰበር ችሎት ድረስ በይግባኝ ቀረብኩኝ ያላፈራሁትን ቤት ከየት ላምጣ? ማዘጋጃ ቤቱን በስሜ ምንም ቤት እንደሌለኝ እያረጋገጠ ፤አሁንም ቤቱን አስረክብ ተብሎ የመጨረሻ ፍርድ ተሰጠብኝ፡፡ አሁን በአፈጻጸም ለማዘጋጃ ቤቱና በቀበሌ መስተዳድሩ የቤቱ ግምት እንዲቀርብ ተጠየቀ፡፡ አሁንም ማዘጋጃ ቤቱ በስሙ ቤት ስለሌለ ግምት አውጥቼ ማቅረብ አልችልም ብሎ መልስ ሰጠ፡፡
ፍ/ቤቱ የአፈጻጸሙን ትዕዛዝ ቀይሮ አፈጻጸሙን ዳኛ እንዲያስፈጽም ፍ/ቤቱ አንድ ዳኛ መደበ የተመደቡት ዳኛ አሁን አስረክብ እያሉ እያሰቃዩኝ ነው፡፡
እኔ ደግሞ የሌለኝን ቤት ከየት አምጥቼ ላስረክብ? ብዬ ብጠይቅ ቤቱን ካላስረከብክ ትታሰራለህ እያሉኝ ነው፡፡ የት ሄጄ አቤት እንደምል ግራ ገብቶኛል ኸረ እባካችሁ የሚሰማ የመንግስት አካል ካለ አሳውቁልኝ፡፡ ጉዳዩን አጣርቶ መፍትሔ የሚሰጥ አካልም ካለ አስውቁልኝ:: እየተፈፀመ ያለውንም ጉድ የኢትዮጵያ ህዝብ ይወቅልኝ” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment