Thursday, April 4, 2013

አቶ ስብሐት ነጋ ኤርትራውያንንና ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ስብሰባ ጠሩ

መጋቢት ፳፭ (ሀያ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር የሚገኘውና በቀድሞ የህወሃት መስራችና አመራር አባል አቶ ስብሃት ነጋ የሚመራው
የኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት የፊታችን ቅዳሜ የኢትዮጵያና ኤርትራ የሕዝብ ለሕዝብ
ግንኙነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ የሚመክር ሕዝባዊ ስብሰባ በአዲስአበባ ጠራ፡፡
በትጥቅ ትግሉ ወቅት እና ወደመንግስት ስልጣን ከመጡም በኃላ በመጀመሪያዎቹ 10 ዓመታት ሃይለኛ ፍቅር ውስጥ
የነበሩት ሻዕቢያና ኢህአዴግ በድንገት የፈጠሩት አለመግባባት ተካርሮ ከ15 ዓመታት በፊት ጦርነት ካስነሳና
በሁለቱም ወገኖች ዘንድ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ካለቁ በኃላ በመንግስት ደረጃ የዚህ ዓይነቱ የውይይት መድረክ
ሲዘጋጅ ይህ የመጀመሪያ እንደሆነ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ከቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኃላ የተሾሙት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለአልጀዚራ
ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለምልልስ ኤርትራ ድረስ ሔደው ለመወያየት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን
የአሁኑ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የተባለው ከሳቸው አቋም ጋር በቀጥታ ስለመያያዙ ወይም አለመያያዙ የታወቀ ነገር
የለም፡፡
አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ከኤርትራ መንግስት ጋር በሔግ ተከራክረው በይፋ ከተሸነፉ በሃላ ኤርትራዊያን
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ጥለውት የሄዱትን ንብረት መልሰው ማግኘት እንዲችሉ መፍቀዳቸውን ተከትሎ በርካታ
ኤርትራዊያን በዕድሉ በመጠቀም ከተለያዩ ዓለማት ወደኢትዮጵያ በመሄድ የቀድሞ ንብረታቸውን አስከብረዋል፡፡
በተጨማሪም ድንበር አቋርጠው ወደኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኛ ኤርትራዊያን በአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀር በልዩ
ድጋፍ ገብተው እንዲማሩ እንደተፈቀደላቸው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ ዜናዊ መግለጻቸው ይታወሳል።
በ1990 ዓ.ም ድንገት በሁለቱ አገራት መካከል ጦርነቱ ሲቀሰቀስ በአሰብ ወደብ ላይ የሚገኝ ንብረታቸው የተወሰደባቸው ኢትዮጽያዊያን ነጋዴዎች ንብረቶች ብቻ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ይገመት ነበር፡፡ ያኮና ኢንጂነሪንግ፣ኮስ ትሬዲንግ እና የመሳሰሉ አገር በቀል ኩባንያዎች ከዘረፋው ጋር ተያይዞ በደረሰባቸው ኪሳራ ከገበያ መውጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ የኢትዮጵያዊያንን ጥቅም ሳያስጠብቁ የኤርትራዊያን እንዲጠበቅ በማደረግ ሚዛን የሳተ ውስኔ አሳልፈዋል በሚል ክፉኛ ሲተቹም እንደነበር አይዘነጋም፡፡
አቶ ስብሃት ነጋ የሚመሩት ድርጅት መጋቢት 28 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስአበባ ሒልተን ሆቴል የጠራው ስብሰባም
ፋይዳው ይህንኑ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ነው መሆኑን ምንጫችን ተናግሯል፡፡
የሁለቱ አገራት መንግስታት ዕርቀ ሰላም ባላወረዱበት ሁኔታ ያውም ገለልተኛ ባልሆነ ተቋም አማካይነት ለማምጣት
የታሰበው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ምን እንደሚመስል እነአቶ ስብሃት ያስረዱናል ያለው ምንጫችን፣ በአጠቃላይ ሒደቱ
በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተጣበቁ ጥቂት የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎችን ለመጥቀም የታስበ ይመስላል በማለት ገልጿል፡፡

No comments: